በትናንትናው ዕለት ሰኔ 13/08 ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ጀምሮ በኮንሶ ከተማ የሰፈረው የፌደራልና የክልሉ ልዩ ፖሊስ ኃይል ከተማዋን በመውረር ሦስት የከተማ ነዋሪዎችን አፍኖ ወዳልታወቀ ቦታ ወስዷል፡፡ ይህንኑ አፈና ተከትሎ ህዝቡ ለምንድነው የምታስገድዷቸው፣ ወዴትስ ነው የምትወስዷቸው ? ጥፋት ቢፈጽሙ እንኳ እንዲህ ያለው ኢሰብዐዊ ድርጊት ሊፈጸምባቸው አይገባም….፤ በማለት በመጠየቁና ድርጊቱን በመቃወሙ ታጣቂ ኃይሉ በህዝቡ ላይ በወሰደው የኃይል እርምጃና ድብደባ በርካቶች ለአካል ጉዳት የተዳረጉ መሆኑን የከተማው ነዋሪዎች አሳውቀዋል፡፡
በዚህ ተቃውሞ ላይ ከነበሩት ነዋሪዎች አንድ ለጊዜው ስሙ ያልተለየ ወጣት በደረሰበት ከፍተኛ ድብደባ ራሱን መሳቱንና ደብዳቢዎቹ እንደወሰዱት፣ በአሁኑ ሰዓት ያለበት ሆስፒታልም ሆነ የጤንነቱና ደህንነቱ ሁኔታ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አልታወቀም፡፡ ታፍነው የተወሰዱት የከተማው ነዋሪዎች፡- 1ኛ/ አቶ ሰለሞን ሰንጎ፤ 2ኛ/ አቶ በርሻ ከጎያ፤ 3ኛ/ አቶ ኩሴ አይሎ፣ ሲሆኑ ያሉበት ቦታና ሁኔታ እስካሁን እንደማይታወቅና ቤተሰቦቻቸውና የአካባቢው ህዝብ ስለደህንነታቸው ከፍተኛ ስጋት ውስጥ መውደቁን ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡ ምንቾቹ አክለው ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በኮንሶ ህዝብ የተነሳውን የአከላል ጥያቄ ተከትሎ በአካባቢው የፌደራልና የክልሉ ልዩ ፖሊስ ኃይል በከተማውና በከተማ መግቢዎች ሰፍሮ ሚገን በመሆኑ በኮንሶ ልዩ ወረዳ ውጥረት እንደነገሰ ነው፡፡
የትናንትናውንበህዝብና ታጣቂ ሃይሎች መካከል የተነሳውን ግችት ተከትሎ ህዝብ ከቤት እንደማይወታና ከታጣቂ ኃይሉ በቀር በከተማው የህዝብ እንቅስቃሴ እንደማይታይና የመንግስት መ/ቤቶችና ትምህርት ቤቶች ዝግ መሆናቸውን ነዋሪዎች አሳውቀዋል፡፡ አንድ ለደህንነቱ ሲል ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ የከተማዋ ነዋሪ በኮንሶ የምታየውን ሁኔታ እንዲህ በማለት ይገልጸዋል ፡፡ ‹‹በኮንሶ ሲቪል አስተዳደሩ በወታደራዊ አስተዳደር ከተተካ ወራት ተቆጥረዋል፣ የመንግስት ሹመኞችን፣ የአገር ሽማግሌዎችንና የኃይማኖት አባቶችን ጨምሮ ህዝቡ ሰብአዊ መብቱን ተገፎ ለሥቃይና እንግልት በመዳረጉ ያልተረጋጋ የጭንቀትና ሥጋት ህይወት ውስጥ ወድቋል፡፡
ኑሮን ለመምራት የሚደረገው የዕለት ተእለት እንቅስቃሴው ተቃውሷል፡፡ የማኅበራዊ አገልግሎት ተቋማት በተለይም ትምህርት ቤቶች በተረጋጋ ሁኔታ አገልግሎት መስጠት አቁመዋል ማለት ይቻላል፡፡ይህ ሁሉ የሚሆነው ህዝቡ ላነሳው ህገመንግስታዊ የመብት ጥያቄ መንግስት ተገቢ ህጋዊና አስተዳደራዊ መልስ በመስጠት ፋንታ የህዝቡን ጥያቄ በወታደራዊ ኃይል ለማፈን በመምረጡ መሆኑ ሲታሰብ የአገራችንም ሆነ ወረዳችን ሁኔታ ወዴት እያመራ ነው የሚለው አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑን በግልጽ ያሳያል፡፡ የዛሬ ህይወታችንና ቀጣይ እድላችን በእጅጉ አሳሳቢ ነው፡፡›› ካሉ በኋላ ‹‹የኢትዮጵያ ህዝብ ጩሄታችን ያድምጥ፣ ከጎናችን ይቁም ›› የሚል ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
No comments:
Post a Comment