ቤተ ክርስቲያን አባቶች ዕርቀ ሰላም እና የዘመናችን ፖለቲ
መግቢያ
በሀገራችን የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ ግርግር የሁልጊዜ ተጠቂ የሆነችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት መከራ በመቀበል ኖራለች። የሩቁን ትተን የቅርቡን እንኳን ብናነሳ በኢጣልያ ወረራ ወቅት ስለሀገር ሉዓላዊነት የመሰከሩና ህዝቡ ለወራሪው እንዳይገዛ ያወገዙ ሁለት ብጹዓን ኣባቶች (ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ እና ብፁዕ አቡነ ሚካኤል) በመትረየስ ጥይት ተደብደበው ተገደሉ። እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ መነኮሳትና ካህናት በየገዳማቱና አድባራቱ በግፍ ተጨፈጨፉ። በ1966ቱ አብዮት ማግሥት ፓትርያርኳ በግፍ እና በአረመኔያዊ ጭካኔ በሲባጎ ታንቀው በደርግ ኮማንዶዎች ተገደሉ።
የዛሬ 25 ዓመት ገደማ በትረ ሥልጣኑን የተቆጣጠረው ወያኔ በስልታዊ መንገድ በቀሰቀሰው “የቤተ ክህነት ነውጥ” የቤተ ክርስቲያኗ 4ኛ ፓትርያርክ ከመንበራቸው እንዲወርዱ አድርጎ ታሪክ ይቅር የማይለው በደል በቤተ ክርስቲያኒቷ ላይ ፈጸመ። በዚሁ የወያኔ ጣልቃ ገብነት የቤተ ክርስቲያን አባቶች በአንዲት እምነት እያመኑ እና የቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ጠላት ማን እንደሆነ ልባቸው እያወቀው “ሕጋዊ እኛ ነን፣ እናንተ አይደላችሁም” እየተባባሉ መለያየት ጀመሩ። የሚገርመው “ሕጋዊ” የምትለው ቃል በሁለቱም የአባቶች ቡድን ዘንድ የምትጠቀሰው በተለያየ መንገድ ነው። 4ኛው ፖትርያርክ በሕይወት እያሉ በመንበረ ፓትርያርኩ ሌላ አይሾምበትም የሚሉት አሁን በአሜሪካና አውሮፓ የሚገኙት አባቶች የሚጠቅሱት የቤተ ክርስቲያኗን ሕግ ሲሆን፣ አዲስ አበባ ያሉት የተቀሩት አባቶች ደግሞ 4ኛው ፖትርያርክ በፖለቲካ ጫናው ከመንበራቸው መውረዳቸውን [ሳይክዱ] በተግባር ሊፈጸም የሚችለው (ወያኔ የሚፈቅደው) የሚቀጥለውን አባት መርጦ መቀጠል ብቻ እንጂ ፓትርያርኩ ይመለሱ ብለን ልንከራከር የምንችልበት አቅም አጥተን ያደረግነው ስለሆነ ሕግ እንደጣስን መቆጠር የለበትም ባይ ናቸው። (በዘመነ ደርግ የፖትርያርኩ በህይወት ያለመኖር ሳይረጋገጠ 3ኛው ፖትርያርክ እንደተሾሙት ማለት ነው።)
በዚህ ሁኔታ ፍጹም አስተዳደራዊ የነበረውና በአባቶች ውይይት በቀላሉ ሊፈታ የሚችለው ችግር በዋነኛነት በፖለቲከኞች ጫና (በሀገር ቤት በወያኔ በውጭ ሀገር ደግሞ በተቃዋሚዎች) ተካሮ በተለይም ከጥቂት ዓመታት በፊት አሜሪካ ባሉት አባቶች በተደረገ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ምክንያት ልዩነቱ ተካሮ እስከመወጋገዝ ተደረሰ። በሀገር ቤትም በአሜሪካም ያሉት አባቶች ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ሲያያዝ በመጣው የሥልጣነ ክህነት ቅብብሎሽ መሠረት በሕጋዊ መንገድ የተሾሙ በመሆናቸው (የተላለፈው ውግዘት እምብዛም ክብደት አይሰጠው) እንጂ ለመጪው ትውልድ መዘዙ ብዙ ነው። (ውግዘት ትልቅ ሃይማኖታዊ ትርጉም ያለው ጽንሰ ሐሳብ በመሆኑ)።
ይህን እንድናነሳ የሚያስገድደን ….
ሰሞኑን በአዲስ አበባ እና በአሜሪካ የተደረጉትን የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጉባኤ ሂደትና በጉባኤያቱ የወጡት መግለጫዎች ናቸው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀኖናዊ ሥርዓት መሠረት በዓመት ሁለት ጊዜ ከሚደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባዎች አንዱ ሰሞኑን ሲካሄድ ሰንብቶ መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል። አባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ብቻ በዝግ ቤት በፍጹም መንፈሳዊ ሥርዓት የሚያደርጉት ይህ ስብሰባ የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች ፍጹም መንፈሳዊ እና በመንፈስ ቅዱስ መሪነት እንዲፈጸም የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ያዛል። የቤተ ክህነቱን “ፓለቲካ” ወደ ጎን ትተን ከዚህ በላይ በተመለከተው ማዕቀፍ ብንመለከተው በሀገር ቤትም ሆነ በአሜሪካ ያሉት አባቶች በሁለት የመሰብሰቢያ ቦታዎች ሆነው ስለ ነገረ ቤተ ክርስቲያን መክረዋል ብለን ልንነሳ እንችላለን።
በሥልጣነ ክህነት ተዋረድ ለምትመራው ቤተ ክርስቲያናችን የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ወሳኝ የሆኑ ሃይማኖታዊ ጕዳዮች የሚታዩበትና በመሆኑ በፍጹም ነጻነት መከናወን አለበት። ይሁንና በሀገር ቤትም ሆነ በውጭ ሀገር ያሉት አባቶች ይህ ነጻነት እንደሌላቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። የወጡትን መግለጫዎች ይዘት በሚገባ ብንመለከታቸውም በሁለቱም ቦታዎች ያሉት አባቶች በፖለቲካ ጫና ሥር (የሀገር ቤቱ በወያኔ፥ የአሜሪካው ደግሞ በተቃዋሚው) እንዳሉ መገንዘብ አያዳግትም። ይህ ማለት ግን አባቶቻችን ስለ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች የሚወስኑት ውሳኔ ተቀባይነት የለውም ወደሚል መደምደሚያ አያደርሰንም። ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ አንስቶ የአላውያን ነገሥታትና ፖለቲካኞች ተጽእኖ የሁልጊዜም ፈተናዋ ነውና። ልዩነቱ በየዘመኑ ተጽእኖውን የሚረዱና የሚቋቋሙ፣ ለቤተ ክርስቲያን ወግነው ለወንጌል ዓላማ መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጁ አባቶች መብዛትና ማነስ ብቻ ነው።
ፓለቲካ ነክና ሌሎች አስተዳዳራዊ ጉዳዮችን የተመለከተውን ትተን “እርቀ ሰላሙን” የተመለከተውን በሁለቱም ቦታ የተሰበሰቡትን አባቶች መግለጫ ክፍል ስንመለከት አባቶቻችን ምን እየሠሩ ነው ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል። በእርግጥ በሁለቱም አባቶች መግለጫዎች ላይ አንዳቸው ሌላውን አካል የሚገልፁበት ቋንቋ (በውጭ አህጉረ ስብከት ካሉት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር (ከሀገር ቤት)፣ በቤተ ክርስቲያናችን መሰደድ ምክንያት የተፈጠረው የሰላም እጦት (አሜሪካ)) ለዘብ ያለ መሆኑ በጣም ያስመሰግናቸዋል። (ሌሎችም ይህንኑ ብንከተልና የቃላት አጠቃቀማችንን በማስተካከል ልዩነቱን ለማጥበብ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ብናደርግ መልካም ነው።)
ሆኖም ግን በየዓመቱ “የዕርቀ ሰላሙ ጥረት ይቀጥል!” የሚለው መግለጫ ጋጋታ ትርጉም የሚኖረው ከእውነተኛ ፍላጎትና ችግሩን ለመጭው ትውልድ ላለማውረስ ከመነጨ ቁርጠኝነት ሲመነጭ ብቻ ነው። ይህ ውሳኔ ከሁለቱም አባቶች ስብሰባዎች በኋላ ሁልጊዜ የሚካተት መሆኑ ያላቸውን የአንድነት ፍላጎት የሚያመለክት ቢሆንም ተግባራዊነቱ ላይ ቁርጠኝነት መጥፋቱ ጉዳዩ ከፍተኛ የፖለቲካ ጥላ ያጠላበት መሆኑን ያሳብቃል። በእርግጥም በተግባር እንደታየው ሁለቱን አባቶች ለማስታረቅ የተደረገው ጥረት ጫፍ ከደረሰ በኋላ በዋነኛነት በወያኔ ጣልቃ ገብነት ተቋርጧል። በተቃዋሚው ወገንም (በቤተ ክርስቲያኒቷ ላይ በወያኔ የደረሰው ጥቃት ዋነኛ የሥርዓቱን ሕገ ወጥነት ማሳያ ስለሆነ ችግሩ ከተፈታ ፖለቲካው ይዳከማል በሚል የተሳሳተ ስሌት) አንድነቱን በሙሉ ስሜት የመደገፍ ስሜት እንደሌለ ይታወቃል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ “የእርቀ ሰላሙ ጥረት ይቀጥል” ሲሉ የወሰኑት አባቶች (በተለይም በአሜሪካ የሚገኙት) በሌላው መሥመር የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት እንዲከናወን ቀን መቁረጣቸው በእርቀ ሰላሙ በቅርብ ጊዜ መፈፀም ተስፋ እንድንቆርጥ እየነገሩን ይመስላል። እርቀ ሰላሙን ማውረድ ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባ ነበርና። ይህ ይደረጋል የሚባለው የጳጳሳት ሹመት (በአሜሪካ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው ) በእርቀ ሰላሙ ሂደት ላይ ሌላ የተጋረጠ ፈተና መሆኑ የማይቀር ሲሆን ወደ ሌላ እልህ እንዳያጋባም ያሰጋል።
ምኞታችን
እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት እና ምእመናን ምኞት አባቶቻችን ሁሉ ከፖለቲካው ቅኝት ወጥተው የተሰጣቸውን መንፈሳዊ አደራ የፓለቲከኞችን ፊት እያዩ ሳይሆን በፍጹም መንፈሳዊ ነጻነት እንዲያከናውኑ ነው። ምክንያቱም የዘመናችን የፖለቲካ ሥራ በሰለጠኑት ሀገሮች ጭምር እንደምናየው በባህርይው ሐሰትን ከእውነት ጋር ደባልቆ መያዝን የሚጠይቅ፣ ሥጋዊ ጥቅምንና ዝናን ከኅሊና ክብር የሚያስቀደም፣ ጉልበተኞችና የዓለም ባለፀጎች ፍላጎት የሚፈፀምበት፣ የአንዱ ጥፋት እየተጋነነ ለሌላ የከፋ ጥፋት ዝግጅት የሚደረግበት፣ ግፋም ሲል ሃይማኖት የለሽነትን የሚያበረታታ ነውና። ሀገራችን ባለችበት ሁኔታ አባቶቻችን በፍፁም የኅሊና ልዕልና እንዲኖሩና ማንንም ሳይፈሩና ሳያፍሩ እንዲያስተምሩና እንዲገስጹ እንጂ የየትኛውም ፖለቲካ እጀታ እንዳይሆኑ መመኘት “ከብት ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” ቢሆንም ምኞታችን ነው። (አሁን ካሉት አባቶች አብዛኛዎቹ ይህን ማድረግ እንደሚቻል (ማለትም የትኛውንም የፖለቲካ አመለካከትም ሆነ ስልት አንደግፍም የማለት መብት እንዳላቸው) ለማመን እንኳን ይቸገራሉና)።
ይሁንና እርቀ ሰላሙ ለቤተ ክርስቲያን ወሳኝ ጉዳይ ነው። በየትኛውም ሰበብ ችግሩ ለሌላ ትውልድ መተላለፍ የለበትም። የችግሩን እውነተኛ ምንጭ እንዲህ ፍንትው ብሎ በታወቀበት ሁኔታ (ፖለቲካ እና መንደርተኝነት) የተለያዩ የማያሳምኑ ምክንያቶች እየተደረደሩ የቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚታወክበት ምክንያት የለም። እውነተኛ ሊቃውንትም በትምህርታቸው ይህንን መግለጥና የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለማስጠበቅ የተቻላቸውን ሁሉ ሊያደርጉ ይገባል። እንኳን ተከፋፍለን አንድም ሆነን የቤተ ክርስቲያንን ተልዕኮ ለመፈጸም አልቻልንምና። ስለሆነም አባቶቻችን እንዲህ እያልን እንለምናለን ። እባካችሁን! በሀገር ቤትም ሆነ ከሀገር ውጭ የምትገኙ አባቶች፥ ፖለቲከኞች በዘርና በወንዝ እየከፋፈሉት ያሉትን ሕዝብ እናንተ ደግሞ ከቁብ በማይገባ “ሃይማኖታዊ” ሰበብ በመከፋፈል መከራውን እንዳታጸኑበት በቤተ ክርስቲያን አምላክ ስም እንለምናችኋለን። ዕርቀ ሰላሙን ፈጽማችሁ ታሪክ ሳታበላሹ ብታልፉ ሰማያዊ ክብር ብቻ ሳይሆን ታሪክም በበጎነታችሁ ሲያዘክራችሁ ይኖራልና።
ከቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እና ከምእመናን ምን ይጠበቃል?
ከላይ እንደተገለጸው በዘመናችን ከሁሉ በላይ የሚያሳስበን የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት ጉዳይ ሊሆን ይገባል። በቤተ ክርስቲያናችን የተከሰተው አስተዳደራዊ ችግር ሊፈታ የሚችለው በቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና በምእመናን አንድነትና መግባባት ነው። የቤተ ክርስቲያንን ችግሮች ለመፍታት ስንሞክር መሠረታዊ የሆነውን የአንድነቱን ምሰሶ እያናጋን ችግሮች የበለጠ እንዳይወሳሰቡ በተቻለ መጠን መጠንቀቅ አለብን። የውስጥ ጉዳዮቻችን መፍትሔ የሚያገኙት፣ ዕቅበተ እምነት በአግባቡ ሊፈጸም የሚችለው ሁላችንም የእገሌ ወእገሌ ሳንባባል በአንዲት ጥምቀት ከማኅጸነ ዮርዳኖስ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከቤተ ክርስቲያን የተወለድን የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን በማመን በአንድነት በመቆም ብቻ ነው። በመሆኑም አባቶቻችን የወሰኗቸውን ውሳኔዎች አክበረን የምንኖረው አባቶቻችን የመሪነት ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የምንረዳበት ፍጹም ኦርቶዶክሳዊ የሆነ የመታዘዝ ሥነ ምግባር በመሆኑ ነው። ይህ ማለት ግን በተለያዩ የአባቶች አስተዳደር ሥር በማገልገላችን እና በመገልገላችን ሁለት የተለያየ ሃይማኖት የምንከተል አይደለንም። ስለሆነም በየአከባቢያችን ላሉት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እውነተኛ እምነታችን ይኸው መሆኑን በመግለጽ ወደ አንድነት እንዲመጡ የተቻለንን ጥረት እናድርግ። በተለይም በፖለቲካው እየተሳተፋችሁ ያላችሁ ክርስቲያኖች፥ ከክርስትና እምነታችን ጋር የማይጋጨውን የትኛውንም ፖለቲካዊ አቋም የማራመድ መብታችንን ቤተ ክርስቲያን ታከብርልናለች። ሆኖም ግን የቤተ ክርስቲያንን አንድነት እና የእርቀሰላሙን ሂደት በፖለቲካ አመለካከታችን አንጻር እያሰላን በአባቶቻችን መከከል የተከተውን ልዩነት ከማስፋት እና የተጀመረውን የእርቀ ሰላም ጥረት ከማደናቀፍ ልንቆጠብ ይገባል።
የሰላም አምላክ ሰላሙን ያድለን!
ዲባባ ዘለቀ
No comments:
Post a Comment