Tuesday, June 28, 2016

ለኢትዮጵያ ክሊንተን ወይስ ትራምፕ?

  

ዘንድሮ አሜሪካዊያን አስጨናቂ የምርጫ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል። ለኢትዮጵያዊያን አሜሪካዊያን ደግሞ አጣብቂኙ የከፋ ነው።
ሂላሪ ክሊንተን ከህወሓት አገዛዝ ጋር ያላት ቁርኝት እያጠናከረች ነው። እንዲያውም ህወሓት የሚገዛትን ኢትዮጵያን የባሏ፣ የኦባማና የእሷ የአፍሪካ ፓሊሲ ስኬት ምሳሌ ለማድረግ የቆረጠች ይመስላል፤ ለዚህም ህወሓት ከሚያደርገው ያላነሰ የገጽታ ግንባታ ሥራ መሥራት ጀምራለች።
ትራምፕ የማይታወቅ “አውሬ” ነው። ስለ ትራምፕ የኢትዮጵያ ፓሊሲ መገመት ከባድ ነው፤ በጠቅላላው አይታወቅም ቢባል ይሻላል።
የፓለቲካ አማራጮችን “ለአገራችን የቱ ይበጃል?” በሚል መመዘኛ መወሰን ይኖርብናል። ህወሓትን የሚያጠናክሩ ነገሮች ሁሉ አገራችንን የሚጎዱ ናቸው።
ኢትዮጵያዊያን-አሜሪካዊያን በተቀረው የምርጫ ጊዜ ውስጥ ሊሰሯቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ ብዬ አምናለሁ። (1) የትራምፕን ባህርይ በማየት “ሊመረጥ አይችልም” የሚል የዋህነት ማስወገድና ከሱ ጋርም መደራደር እንደሚገባ ማመን፤ (2) የኢትዮጵያዊያን ድምጽ ተሰባስቦ ከሁለቱም ተፎካካሪዎች ጋር መደራደሪያ ማድረግ (3) ሁለቱንም ተወዳዳሪዎች በህወሓት አገዛዝ ላይ ስለሚኖራቸው የፓሊሲ አቋም እና ስለሚወስዱት እርምጃ በግልጽ ማወቅ፤ እና (4) ለትግላችን የሚበጅ ፓሊሲ ላቀረበ ተወዳዳሪ በጋራ ድምጽ ለመስጠት ጥረት ማድረግ።
ለእኛ ትልቁ ጉዳያችን የአገራችን ደህንነት ነው፤ የአገራችን ትልቁ የደህንነት አደጋ ደግሞ ህወሓት ነው። በተደራጀ ሁኔታ ከተንቀሳቀስን በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የሚደረገው የአሜሪካ ምርጫ ለአገራችን ጥቅም የሚሰጥ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል።

No comments:

Post a Comment