- እንቅልፍ አልተኙም እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ምን እንቅልፍ አለ?
- ለምን አልተኙም?
- ግጥሚያውን ሳይ ነዋ፡፡
- አሸነፍን ተሸነፍን?
- እኛ እኮ የለንበትም፡፡
- ከተፋላሚዎቹ አንደኞቹ እኛ አይደለን እንዴ?
- ከመቼ ጀምሮ ነው እኛ አውሮፓዊ የሆነው?
- ስለምን እያወሩ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ስለአውሮፓ ዋንጫ ነዋ፡፡
- እየቀለዱ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- የምን ቀልድ ነው?
- ያመሹት እኮ ሥራ ላይ መስሎኝ?
- በቃ በዊኬንድም አትረፉ ነው የምትሉን፡፡
- አይ ያው ዊኬንዱ የሚታረፍበት አልነበረም ብዬ ነዋ፡፡
- ዊኬንዱማ ሰላማዊ ነበር፡፡
- ሁሉን ነገር እርግፍ አድርገው ትተውታል ማለት ነው?
- ሳትራገፍ ማራገፍ አይሻልም ብለህ ነው?
- እና ምንም ወሬ አልሰሙም?
- ያው የቤተሰብ ወሬማ ሰምቻለሁ፡፡
- ኧረ ስለጦርነቱ፡፡
- ስማ ጦርነት እኮ ቆሞ አያውቅም፡፡
- የትኛው ጦርነት?
- ከድህነት ጋር የሚደረገው ጦርነት፡፡
- ምን አሉኝ?
- ከሙስናና ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር የሚደረገው ጦርነት፡፡
- ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ አሉ፡፡
- ከመልካም አስተዳደር ጋር የሚደረገው ጦርነት፡፡
- ከእነርሱ ጋ ግን ተዋግታችሁ ታውቃላችሁ?
- ሌት ተቀን ነዋ፡፡
- ታዲያ በየጊዜው ለምን እየጨመሩ ይሄዳሉ?
- አየህ አጠቃቅህ ስትራቴጂካዊ መሆን አለበት፡፡
- እንዴት ሆኖ?
- በጣም እስኪያድጉ ዝም ብለህ ትመለከታቸዋለህ፡፡
- ከዛስ?
- ከዛማ ሳያስቡት ባንዴ ትገነድሳቸዋለህ፡፡
- ግን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
- ምን ዓይነት ጥንቃቄ?
- እነሱ እንዳይገነድሷችሁ፡፡
- አንተን ራስህን መገንደስ ነበር፡፡
- ለማንኛውም እኔ የምልዎት ጦርነት ሌላ ነው፡፡
- የምን ጦርነት ነው?
- ከኤርትራ ጋር የነበረው ጦርነት?
- ምን?
- ምንም አልሰሙም?
- የምን ጦርነት ነው?
- የኢትዮጵያ ሠራዊት ከኤርትራ ሠራዊት ጋር ተጋጭቶ ነበር፡፡
- በምን ምክንያት?
- እሱን ነበር ልጠይቅዎት የነበረው፡፡
- እሱማ አይነገርም፡፡
- ለምን?
- ወታደራዊ ሚስጥርን መጠበቅ አለብህ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ዋናው ችግርዎት እኮ ይኼ ነው፡፡
- ምንድን ነው?
- የማያውቁትን ነገር እንደሚያውቁ ሲያወሩ ነዋ፡፡
- የግጭቱን ችግርማ አውቀዋለሁ፡፡
- እሺ ምንድን ነው?
- ምቀኝነት፡፡
- ምን ማለት ነው ክቡር ሚኒስትር?
- በቃ በአገራችን ዕድገት የከፋው የኤርትራው መሪ ተመቅኝቶ ነው ውጊያ የጀመረው፡፡
- አይ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በቃ ከዚህ ሌላ ምንም ምክንያት የለውም፡፡
- ድንቄም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን አልክ?
- ድንቅ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለመሆኑ ፍልሚያውን ማን አሸነፈ?
- አቻ ነው የወጣነው፡፡
- እንዴት ማለት?
- መንግሥት ተመጣጣኝ ዕርምጃ ወስጃለሁ ነው ያለው፡፡
- ለነገሩ ያን ምቀኛ መሪ ምን ማድረግ እንዳለብን አውቃለሁ፡፡
- ምን ሊያደርጉት?
- ቂጡን በሳንጃ መውጋት!
[ክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊያቸው ጋ ደወሉ]
- ምን ሆነሽ ነው ሥራ ያልመጣሽው?
- ችግር ገጥሞኝ ነው፡፡
- የምን ችግር?
- ሐዘን ላይ ነኝ፡፡
- ቻንድራ ሞተ እንዴ?
- ኧረ አልሞተም፡፡
- ታዲያ ዛራ ሞተች?
- ዘሩ ነው የሞተው፡፡
- ማነው ዘሩ?
- ጐረቤቴ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ሆኖ ነው የሞተው?
- ዱርዬዎች ነው የገደሉት፡፡
- ለምን ገደሉት?
- ማጅራት መቺዎች ናቸዋ፡፡
- ባለሀብት ነው እንዴ?
- ባለሀብት ቢሆንማ በቪ8 ነበር የሚሄደው፡፡
- ታዲያ እሱ በምንድን ነው የሚሄደው?
- በቪ11፡፡
- ቪ11 ካለውማ ከቪ8 ስለሚበልጥ ከፍተኛ ባለሀብት ነበር ማለት ነው?
- ቪ11 እኮ ማለት በሁለት እግሩ ነው የሚሄደው ለማለት ነው፡፡
- መቼም የማታመጪው ነገር የለም?
- ክቡር ሚኒስትር ይኼ የዝርፊያ ጉዳይ ግን ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡
- እንዴት ማለት?
- ይኸው ይኼኛው እኮ በ15 ቀናት ውስጥ ሁለተኛው ሞት ነው፡፡
- አንቺ ሰፈርሽ ሞቃዲሾ ነው እንዴ?
- ክቡር ሚኒስትር የሥራ አጡ ቁጥር እየጨመረ መጥቶ ማጅራት መምታት ሥራ ከሆነ ሰነባበተ፡፡
- አሁን እዚህ አገር ላይ ሥራ አጣሁ የሚል ሰው ነው የሚገርመኝ?
- ምኑ ነው የሚገርምዎት?
- አገሪቷ በፍጥነት እያደገች ባለችበት በዚህ ወቅት ገና ከቤትሽ ስትወጪ አይደል እንዴ ሥራ የሚያገኝሽ?
- አገር ቀየሩ እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ማን? እኔ?
- ታዲያ ስለየትኛው አገር ነው የሚያወሩት ብዬ ነዋ?
- እኔ ወሬ አልወድም፣ ሥራ ብቻ ነው የምወደው፡፡
- ለነገሩ ክቡር ሚኒስትር እነዚህ ማጅራት መቺዎች የእርስዎ አለቃ ለመሆን ስማቸው ላይ ሚኒስትር የሚለው ብቻ ነው የጐደላቸው፡፡
- ማን ነው ስማቸው?
- ጠቅላይ፡፡
- ወሬማ ማን ብሎሽ?
- ለማንኛውም የሚዘርፉትም ተደራጅተው ነው ተብሏል፡፡
- በምን?
- በአነስተኛና ጥቃቅን!
[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት]
- የተመደበልንን በጀት እንዴት አየኸው?
- ክቡር ሚኒስትር ከፍተኛ በጀት ነው፡፡
- ጥሩ ነዋ፡፡
- ምን ጥሩ ነው?
- እንዴት ማለት?
- ባለፈው ከተመደበልን በጀት 30 በመቶውን ብቻ ነው እኮ የተጠቀምነው፡፡
- ከባለፈው ስህተታችን ትምህርት ወስደናላ፡፡
- የባለፈው ችግራችን እኮ የአቅም ማነስ ነው፡፡
- እኮ አሁን አቅማችንን እናጠናክራለና፡፡
- አቅማችን እኮ ምንም አልተጠናከረም፡፡
- የእኔ አቅም ተጠናክሯል፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- በቅርቡ የጭስ አልባ ኢንዱስትሪውን ለመቀላቀል ወስኛለሁ፡፡
- አልገባኝም?
- በቃ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ለመሥራት አቅጃለሁ፡፡
- ምን?
- ጥራቱን የጠበቀ ሆቴል ነው የምገነባው፡፡
- ከየት አምጥተው?
- ስነግርህ? ከሚቀጥለው በጀት ዓመት ተመላሽ የምናደርገውን ገንዘብ አይኖርም፡፡
- ሌላስ?
- በግሌ ያሉኝን አምስት ቤቶችም ቢቻል ከእጥፍ ለመጨመር አስቤያለሁ፡፡
- ካልተቻለስ?
- ቢያንስ አንድ ሦስት መጨመር አለብኝ፡፡
- እ…
- ከዛም ባለፈ ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፉ መግባት አለብኝ፡፡
- ምን አሉኝ?
- መንግሥት ይኼን ሁሉ የኢንዱስትሪ ፓርክ የገነባው እኮ እኛ እንድንገባበት ነው፡፡
- ኧረ የግል ባለሀብቶች እንዲገቡበት ነው?
- እኛ አርዓያ መሆን አለብን፡፡
- እንዴት ማለት?
- በተደጋጋሚ ባለሀብቶች እንዲገቡ ተጨቃጭቀን አሻፈረኝ ስላሉ እኛ ገብተን እናሳያቸዋለን፡፡
- ለመሆኑ ገንዘቡን ከየት ነው የሚያመጡት?
- ለጋሽ አገሮች ለመንግሥት ለዘላቂ ልማት ፕሮግራሞች በጀት መድቧል፡፡
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እኔም ለፕሮጀክቶቼ ከመንግሥት በጀት እመድብላቸዋለሁ፡፡
- የእርስዎ ፕሮጀክቶች ምንድን ነው የሚባሉት?
- የሚኒስትሩ የዘላቂ ልማት ፕሮግራሞች!
[ክቡር ሚኒስትሩ በፓርቲያቸው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እየተገመገሙ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር ምን ይሻልዎታል?
- ልማት ነው የሚሻለኝ፡፡
- የእርስዎ ሌብነት እኮ አሳፋሪ ሆነ፡፡
- እኔ የሚገርመኝ እናንተ የማትሰርቁ ነው የምትመስሉት?
- የእርስዎ ግን ባሰ፡፡
- ምን ማስረጃ አላችሁ?
- ይኸው በአሥሩም ክፍለ ከተማ በስምዎት ሕንፃ አለዎት፡፡
- ቢኖረኝስ?
- በስምንት ክፍለ ከተማ ደግሞ የመኖሪያ ቤቶች አልዎት፡፡
- ብርቅ ነው ታዲያ? ማን የሌለው አለ?
- ለልማቱ ፀር እየሆኑ ነው፡፡
- ከዚህ በላይ ልማት ምን አለ?
- እርስዎ እኮ አስለሚ እንጂ አልሚ አይደሉም፡፡
- እንግዲህ ቃላት እየሰነጣጠቃችሁ አታደናግሩን፡፡
- ምን ማለት ነው?
- እኔ እስከሚገባኝ የእኔ መልማት የልማታዊ መንግሥት መገለጫ ነው፡፡
- መንግሥት የግሉ ዘርፍ በልማቱ ውስጥ እንዲሳተፍ እኮ ነው የሚፈለገው፡፡
- እኔም እኮ በግሌ ነው እያለማሁ ያለሁት፡፡
- እርስዎ ግን የመንግሥት ባለሥልጣን ነዎት፡፡
- የግል ባለሀብቱ እምቢ ሲል እኮ ነው አርዓያ መሆን አለብኝ ብዬ የተነሳሁት፡፡
- ክቡር ሚኒስትር የእርስዎ ሙስና ከመጠን ያለፈ ሆኗል፡፡
- እኮ እኔ ምን ላድርግ?
- በቃ እርስዎ ላይ ዕርምጃ መወሰድ አለበት፡፡
- ኧረ እኔ በቃ ግለ ሒስ አደርጋለሁ፡፡
- እርሱን ካደረገ ችግር የለውም፡፡
- ሙስና በቃ ሱስ ሆኖብኛል፡፡
- ከዚህ ሱስዎት መላቀቅ አለብዎት፡፡
- ይቻላል?
- በሚገባ፡፡
- እስቲ ራሳችሁ ተላቃችሁ አሳዩኝ፡፡
- ምን ዓይነት አስቸጋሪ ሰው ነዎት?
- ለመጨረሻ ጊዜ የምናገረው ነገር አለ፡፡
- ምንድን ነው እሱ?
- ሙስና ውስጤ ነው
No comments:
Post a Comment