Wednesday, June 1, 2016

የላቀ ምስጋና አቀርባለሁ (ሀብታሙ አያሌው)

ያለፉት ሁለት ዓመታት ለኔ ከባድ የመከራ ጊዜያት ነበሩ አሳሪዎቼ በነፍሴ ላይ ስልጣን ከማጣታቸው በቀር በሥጋዬ ላይ የስቃይ ጥግ፣ የመከራ ጫፍ የቱ እንደሆነ አሳይተውኛል፡፡ በአምባገነኖች ዘንድ ሀገር እና ወገንን መውደድ መቼም ፅድቅ ሆኖ እንደማያውቅ የሀገሬ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ሀገሬ ሞኝ እና ተላላ ሆና ለሞተላት አፈር ከድታ የገደላትን ስታበላ ስለመኖሯም ከአርበኞቻችን ታሪክ የተሸለ መገለጫ የለም፡፡ የደጃዝማች በላይ ዘለቀ ሞት የሚነግረን ይህንኑ ነው፡፡ የማይቀመስ የጀግና ክንዱ የኋሊት ታስሮ እንደ ወንበዴ የተሰቀለው ጃንሆይን አምኖ የሰላም ጥሪውን በማክበሩ ነበር፡፡ ታዲያ የማያልቅባቸው የሀገሬ ቅኔ ዘራፊዎች በበላይ ዘለቀ ሞት ቁጭታቸውን ሲገልጡ እንዲህ ይሉ ነበር፡፡
‹‹ከበላይ ዘለቀ ከተሰቀለው
ይሻላል ሽፈራው ሶማ የቀረው
ታናሽ ነው ይሉታል እጅጉ ዘለቀን
ከበላይ እኩል ነው እሱም የከፋው ቀን››
ሶስት ሺህ ዘመን ከኖርንበት የጉልበት ፖለቲካ ወጥተን አዲስ የሰለጠነ የዲሞክራሲ ምዕራፍ እንጀምር በማለት የህዝቤ እንባ ገዶኝ የሰላማዊ ትግል አርበኛ ብሆን ብዕር ይዞ የተገኘ እጄን በካቴና አስረው ወደ ወህኒ ቤት አጋዙኝ፡፡
መታሰሬ ብዙ አልገረመኝም ወትሮም ሰላማዊ ትግል ስመርጥ መታሰርን ለመታገስ ሞትንም ለመቀበል ዝግጁ ሆኜ ነው፡፡ እንደ መፅሐፍ ቅዱሱ እዮብ በየዕለቱ ነፍሴን እስክጠላ በጭንቅ እንድኖርና በቁሜ እንድሰቃይ የሚያደርግ የበቀል እርምጃ ይወስዳሉ የሚል ግምት ግን አልነበረኝም፡፡ ነገር ግን ሁሉም ነገር ከግምቴ ውጭ ሆኖ ጤንነቴ አደጋ ላይ ወደቀ፡፡ መስሏቸው እንጂ በእውነቱ ይህም ቢሆን  ከሃገሬ አይበልጥም…
በዚህ አስቸጋሪ ወቅት እንደ ትላንቱ ሁሉ ዛሬም ከጎኔ በመቆም በራሳችሁ ተነሳሽነት የኔን ጤንነት ለመመለስ ድጋፍ ላሰባሰባችሁ እና በድጋፉ ለተሳተፋችሁ ሁሉ የላቀ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡
በተለይ በማስተባበሩ ሂደት በኔ በኩል አንድም ድጋፍና ትብብር ሳላደርግ ሁሉንም በትዕግስት በራሳችሁ ለተወጣችሁት ሁሉ ምስጋና እያቀረብኩ በዚሁ አጋጣሚ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሀገር እንዳልወጣ የጣለውን እግድ ካነሳልኝ በቅርቡ ከሀገር ውጪ ህክምና እንደማደርግ እና ይህንኑም ስለጤንነቴ ከኔጋር ለተጨነቃችሁ ሁሉ በየጊዜው እንደማሳውቅ እገልጻለሁ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ

No comments:

Post a Comment