
ዋሽንግተን ዲሲ — የዘንድሮው ዓመት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና ሾልኮ በመውጣቱና የሁለት ፈተና ጥያቄዎች ከእነ መልሳቸው በማኅበራዊ ሚዲያ በመሰራጨቱ ምክንያት፤ የትምህርት ሚኒስቴር ሊሰጥ የነበርውን ፈተናው ሰርዞ ከሰኔ 27 እስከ ሰኔ 30 እንዲሰጥ መወሰኑ ይታወቃል።
በውጭ ሀገር የሚገኙ የኦሮሞ ተቃውሞ አስተባባሪዎች ፈተናው እንዲሾልክ የተደረገው በኦሮሚያ ለስድስት ወራት ከዘለቀው ተቃውሞ ጋራ በተያያዘ ተማሪዎች በአግባቡ ትምሕርታቸውን ባለመከታተላቸው ጊዜ ሊሰጣቸው ይገባል በሚል እንደሆነ ይናገራሉ።
ስለዚህ አሁንም አዲስ የወጣው የጊዜ ሰሌዳ ለዝግጅት በቂ አይደለም ይላሉ። እንዲሁም በእስልምና እምነት ተከታዮች ፆምና በዓል ላይ በመሆኑ ፈተናው ለሁለት ወር ሊራዘም ይገባል ይህ የማይደረግ ከሆነና እንደተባለው ፈተናው በሰኔ መጨረሻ የሚሰጥ ከኾነ ግን በሚወስዱት ተጨማሪ እርምጃ ለሚደርሰው ኪሳራ መንግሥት ኃላፊነቱን ይወስዳል ሲሉ ለትምህርት ሚኒስቴር በግልጽ ደብዳቤ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል።
በተጨማሪም በውጭ ሀገር የሚገኙ የድምጻችን ይሰማ የድጋፍ ግብረሃይል አባላት የትምሕርት ሚኒስቴርን ውሳኔ ተቃውመውታል። “እቅዱ የሙስሊም ተማሪዎች እና በአጠቃላይ የሙስሊሙን ህብረተሰብ ያላገናዘበ በመሆኑ በምንም መልኩ ተቀባይነት አይኖረውም።”ሲሉም መግለጫ አውጥተዋል።
No comments:
Post a Comment