Thursday, June 23, 2016

ገንጣይን እየደገፉ፤ ለአገር ሉዓላዊነትና ሕልውና መቆም አይቻልም


ጎችዬ እንግዳ
ግንቦት ሰባት የሚባል በንቅናቄ ስም የተቋቋመ ድርጅት ለኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲና ነፃነትን አጎናጽፋለሁ በሚል ለአለፉት ሰባት ዓመታት ሲዋትት መቆየቱ ይታወቃል።ድርጅቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በየወቅቱ የሚያነሳቸው የትግል ስልቶች ምናባዊ ከመሆን ባለፈ እስከ አሁን የተጨበጠ ፋይዳ ያለው ውጤት አላሳየም።
በተለይም በዲያስፖራ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ሀብትና ንብረት የሆነውን ኢሳት የራዲዮና የቴለቪዥን ጣብያ ያላንዳች ይሉኝታ የግል ተጠቃሚ በመሆን ሲያካሂድ የቆየው ድርጅታዊ ፕሮፖጋንዳ ምቹ ሁኔታን ስለፈጠረለት፣ ብቸኛና ግዙፍ ደርጅት መስሎ በመታየቱ በሃገር ፍቅር ሰሜት እየተቃጠለ ነጻነት የራበው፣ ከሃገረ ውጭ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ወገናችን ድጋፉን ሲሰጥ ከረሞል።
እውነትና ንጋት እያደረ ይገለጣል እንዲሉ በየጊዜው እንደ ስልት እየለዋወጠ የሚያቀርባቸው የትግል እንቅስቃሴዎች ሁሉ የማይጨበጡ፣ የማይዳሰሱ፣ ከእውነትና ከሕይወት ጋር ያልተገናዘቡ በመሆናቸው በብዙዎቹ የድርጅቱ ድጋፍ ሰጭዎች ዘንድ ጥያቄን አጭሯል።
የዚህ ድርጅት ሊቀመንበር ዶክተር ብርሃኑ ነጋ በስልጣን ጥም  የሰከረ ባህሪውን ለማርካት፣ ከፋሽስቱ ኢሳይያስ አፈወርቂ ጉያ ያለአንዳች ተው ባየነት መሸጎጡ በድርጅቱ ውስጥ አምባገነንነት እንደሰፈን ጠቆሚ  ይመስላል። በማንኛውም ጊዜ በማንኛውም ስፍራ የእናት ጡት ነካሾችን የሚያዛምዳቸው ብቸኛው አንድነታቸውና የጋራ ባህሪያቸው ከሃዲነት፣ሃሰተኛነት፣ጨካኝነት፣የራስን ህልውናና ጥቅም ማስቀደም በመሆኑ በሁለቱ ግለሰቦች መካከል እየተካሄደ ያለው ወዳጅነት በዚሁ  ላይ የተመሰረተ ያደርገዋል።
ኢሳይያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች መልእክተኛ በመሆኑ በመሃል አገር ፋሽሸቱ  የወያኔን የቅኝ አገዛዝ መስርቶ ኢትዮጵያውያንን እያትራመሰ ያለና ኢትዮጵያንም ያለ ባሕር በር ያስቀረ ጠላት ነው። ግለሰቡ በዙርያው ከሚገኙ መንግሥታት ጋር በስምምነት የማይኖር፤በጠብ አጫሪነቱ የታወቀ ከመሆኑም በላይ በራሱ ሕዝብ ላይ በሚፈጽመው ፋሽስታዊ ተግባር ምክንያትየተነሳ በሽዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ወንድሞቻችን በየእለቱ ሀገር ለቀው የሰደዳሉ። ብዙዎችም ባህር ሰምጠው ቀርተዋል። ከፊሉም በየበርሃው  በውሃ ጥምና በርሃብ ለማለቃቸው ከዓለም ሕዝብ የተሰወረ አይደለም።
በቅርቡ በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ጉዳይ ቢሮ በሰው ዘር ማጥፋት ወንጀል (ጀኖሳይድ) ሪፖርት ቀርቦ ሁኔታው እየተጣራ ቢገኝም ውሻ በበላበት ይጮሃል እንዲሉ ግንቦት ሰባትና ኢሳት የተባሉ ድርጅቶች፤ይህ ጉዳይ ለህልውናቸው መቅሰፍት እንደሆነ በመገንዘባቸው ከኢሳያስ አፈወርቅ ጎን መቆምን መርጠዋል።
  • ትላንትና የኦሮሞ ሕዝብ በፋሽስቱ የወያኔ መንግሥት ህጻናት ሳይቀር በየአውራጎዳናው ደማቸው ሲፈስ ፒቲሽን እናስፈርም አላሉም፡
  • በወልቃይትና ጠገዴ ፤በአርማጭሆና ጠለምተ እንዲሁም በዳባት ሕዝብ ላይ ወያኔ እየፈፀመ ላለው ግፍ የሰፈነበተ እሥራት፤ ግርፋት፤ ግድያና ሰቆቃ ፒቲሽን እናስፈርም አላሉም።
  • በአዋሳ፤በጋምቤላ፤በጅጅጋ፤በወለጋና በተለያዩ አካባቢዎች ወያኔ በጅምላ ለፈፀመው ኢ-ሰብአዊ ግድያና የመብት ረገጣ ፒቲሽን እናስፈርም አላሉም።
ዛሬ ያለምንም እፍረት ለገዛ ሕዝቡ ደህንነትና ህልውና ጠንቅ የሆነውን ግለሰብ ደህንነትና ሕልውና ለመጠበቅ ሲሉ  በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እየተጣራ ያለውን ምርመራ ለማደናቀፍ ፒቲሽን ፈርሙ በሚል በብርሃኑ ነጋና ነአምን ዘለቀ እያከናወኑት የሚገኘው ዘመቻ የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ ፍጽም ጠላትነት ነው።
እነዚህ ፀረ-ኢትዮጵያ የሆኑ ግለሰቦች ፋሽስቱንና ገንጣዩን ኢሳይያስ አፈወርቂን እያወደሱና እየደገፉ ለአገር ሉዓላዊነት፤ ለዲሞክራሲና ለነፃነት ቆመናል የሚሉት አባዜ ከተረት ተረትነት አያልፍም። በመሆኑም እነዚህ የእናት ጡት ነካሾች በሚመሩት ድርጅትና የዜና ማሰራጫ ተቋም ውስጥ በሀገር ፍቅር ስሜትና በነፃነት ስም ተሰልፋችሁ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የእነዚህን ከሃዲዎች ሴራ ተገንዝባችሁ ልታወግዟቸው ይገባል። ከነዚህ ግለሰቦች ጋር ተባባሪ ሆኖ መገኘት በኤርትራ ምድር ለሀገር ነፃነትና ሉዓላዊነት ሲባል የፈሰሰውን የወንድሞቻችን ደም ረግጦ ከማለፍና ኢትዮጵያን ከመካድ ተነጥሎ ሊታይ አይችልም። ስለዚህ እነዚህ ከሃዲ ግለሰቦች በሚተጠሩት ማንኛውም ሕዝባዊ ስብሰባ ለሰባአዊነትና ለሰው ልጅ ህልውና እንቆማለን የምትሉ ሁሉ ተሳታፊ እንዳትሆኑ በኤርትራ ውስጥ በፈሰሰውና እየፈሰሰ ባለው ደም ስም እንጠይቃለን።
ጎችዬ እንግዳ
ክሊቭላንድ ኦሃዮ
ኢትዮጵያ ለዘላዓለም ትኑር!!


No comments:

Post a Comment