Wednesday, June 8, 2016

ባለህበት እርገጥ : ፖለቲካችን ከአዛውንቶች መጦሪያነት ተላቆ በወጣቶች የሚመራው መች ይሆን ?


ባለህበት እርገጥ : ፖለቲካችን ከአዛውንቶች መጦሪያነት ተላቆ በወጣቶች የሚመራው መች ይሆን ? By – Minilik Salsawi
በዚህ ሳምንት ከሃገር ቤቱ የፖለቲካ ኣምባ ተከታታይ የሆኑ የዜና መረጃዎች ፈልተዋል።ከመኢኣድ ኣዲስ ኣመራር ተጠፍጥፎ መሰራት ጀምሮ ከፓርቲ ወንበር ጋር በሙጫ ተጣብቀው አስከተሰፉት የመድረክ መሪዎች አስከ ኣዲስ የኣዛውንቶች ክበብ እስከሆነው ነጻነት የሚባል ኣዲስ ፓርቲ ድረስ በማህበራዊ ድህረገጽ ጀምሮ ኢሜይሎችን በመላክ ሲያጨናንቁን ሰንብተዋል:: ሁሉንም ግን ሳያቸው የኣዛውንቶች ፖለቲካ ያልሰለጠነ የቀድሞ ኣስተሳሰብ የተጠናወታቸው ሲሆኑ ይህ ያረጀ የፖለቲካ ግዞት ገዢ ብሎ ራሱን የሰየመውን ኢሕአዴግንም ይጨምራል፥ማናቸውም ፓርቲዎች በወጣቶች ስም በሽፋን ከመነገድ ውጪ ወጣቶችን ሲያሳትፉ አይታይም::ይህ ጽሁፍ በውጪ የሚገኙ ተጠላላፊ ሃይሎች ተብለው የሚጠሩ ፓርቲዎችን አና ወጣቶችን ያቀፈው ሰማያዊ ፓርቲን አይመለከትም::
መድረክ ይሁን መኢአድ አሊያም አዲሱ ነጻነት የተባሉ ፓርቲዎች እስካሁን የተጓዙበት መንገድ ምን ያህል አዋጪ ነበር? ነው? የፖለቲካ መሪዎቹስ ምን ያህል የተቀናጀ እና የተሳካ አመራር ሰጥተዋል?የሚሉ ያልተመለሱና አሊያም መልስ ያልተገኘላቸው ሳይሆን በግልጽ የታዩና ውጤት አልባ የነበሩ ሂደቶች የታዩበት ነው::ከሰማያዊ ፓርቲ ውጪ በሌሎች ፓርቲዎች ውስጥ ለይስሙላ ካልሆነ በስተቀር የወጣቶች ተሳትፎ ከዜሮ በታች ነው::መድረክ ፓርቲን ብንወስድ መሪው ላለፉት 25 አመታት በተለያየ የፖለቲካ ድርጅቶች ስም በመሪነት ደረጃ ተቀምጠው የፈየዱት ነገር ካለመኖሩም በላይ የኢሕኣዴግን ድግስ ከማጀብ በስተቀር ይህ ነው የሚባል ስራ አልሰሩም እንዲሁም የኤምባሲዎችን ደጅ ከመጽናት እና መግለጫ ከማሽጎድጎድ በቀር ይህ ነው የተባለ የፈየደው ነገር የለም::ከመድረክ ፓርቲ ውስጥ የተሳካ ስራ ሰርቷል የሚባልለት የዶክተር መራራ ኦፌኮ ብቻ መሆኑ አይካድም::
የአዛውቶች ስብስብ የሆነው ሌላው ፓርቲ ደግሞ መኢአድ ከፕሮፌሰር አስራት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ጠንካራ መዋቅር በመናድ እርስ በርስ በመሻኮት ፓርቲውን የእድር ማህበር በማድረግ ወጣት ታጋዮችን በማግለል ፓርቲውን አፈር አብልተውታል ያም አልበቃ ብሏቸው እድሜያቸው ከ70 አመት በላይ የሆኑ ባረጀ አስተሳሰብ የሚራወጡ አዛውቶችን ፓርቲው ውስጥ በማሰለፍ የድርጅቱን የትግል ሂደት ዝግምተኛ/በሽተኛ አድርገውታል:: የቀድሞ አንድነት ወጣት አመራሮችን ለማስጠጋት የማይፈልጉ አዲስ የአዛውንቶች ፓርቲ መመስረቱም ሌላው ፖለቲካን የጡረተኞች ማህበር እንደማድረግ ይቆጠራል::በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ሰማያዊ ፓርቲ ያለ ዬጣቶች አመራር ያስፈልጋል::ይህ እስካልሆነ ድረስ ፖለቲካ የጡረተኞች ማህበር እንደሆነ ትግሉም በመግለጫ ብቻ እንደተንዛዛ ይቀጥላል ስለዚህ አዛውንቶቹ እረፍት አድርገው ወጣቶቹ በበሰለ የሰለጠነ ፖለቲካ ትግሉን ሊመሩት ይገባል:: #MinilikSalsawi

No comments:

Post a Comment