Friday, June 3, 2016

ቅዱስ ሲኖዶስ ለኹለት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ምደባ ሰጠ


በመክፈቻ ጸሎት ከተጀመረ፣ ዛሬ፣ ግንቦት 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ስምንተኛ ቀኑን ያስቆጠረው፣ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ፣ ለኹለት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ምደባ ሰጠ፡፡ ለቅዱስ ሲኖዶስ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት በዛሬው የቀትር በኋላ የምልዓተ ጉባኤው ውሎ ምደባ የተሰጣቸው፣ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ እና ብፁዕ አቡነ እንጦንስ ናቸው፡፡ በምደባው መሠረት፣ የምሥራቅ አፍሪቃ ሊቀ ጳጳስ የኾኑት ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ፣ ቀደም ሲል የነበሩበትን የደቡብ አፍሪቃ ሀገረ ስብከት ደርበው ይመራሉ፡፡ የሰሜን ምዕራብ አውሮጳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ እንጦንስ፣ የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲኾኑ መመደባቸው ታውቋል፡፡ የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት፣ የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል በመደረብ እየመሩት እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ በተመሳሳይ ኹኔታ፣ የሊቃውንት ጉባኤ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ የኾኑት የብፁዕ አቡነ እንድርያስ ጥያቄም ምልዓተ ጉባኤው የሚነጋገርበት ሲኾን፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የረዳት ሊቀ ጳጳስ ምርጫና ምደባም ለነገ አድሯል፡፡ በአኹኑ ወቅት በቅዱስ ሲኖዶስ የምልዓተ ጉባኤያት ስብሰባዎች የሚሳተፉና በሥራ ላይ የሚገኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ቁጥር ከ40 ያልበለጠ ሲኾን፤ በመንግሥት ዞናዊ መዋቅር በትይዩ ምደባ ከሚያስፈልጋቸው አጠቃላይ የአህጉረ ስብከት ቁጥር ሢሦው ተደርበው የተያዙ ናቸው፡፡ ራስን የመቻል ጥያቄ የቀረበበት የምዕራብ አርሲ ዞን – ሻሸመኔ እና በአርሲ – አሰላ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጰስ ምደባ ጉዳይ የቀረቡ ጥያቄዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ለአዲስ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ኮሚቴ መሠየምን በአጀንዳነት የያዘው ምልዓተ ጉባኤው፣ ለክፍተቱ እንደ ጊዜያዊ መፍትሔ የወሰደው ሊቃነ ጳጳሳቱን እየደረበ ማሠራትን ነው፡፡ በኹለቱ አህጉረ ስብከት ለተመደቡት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ መልካም የሥራ አእና የውጤት ዘመን እንመኝላቸዋለን፡፡
በመክፈቻ ጸሎት ከተጀመረ፣ ዛሬ፣ ግንቦት 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ስምንተኛ ቀኑን ያስቆጠረው፣ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ፣ ለኹለት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ምደባ ሰጠ፡፡ ለቅዱስ ሲኖዶስ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት በዛሬው የቀትር በኋላ የምልዓተ ጉባኤው ውሎ ምደባ የተሰጣቸው፣ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ እና…

No comments:

Post a Comment