Thursday, June 2, 2016

ሁለቱንም የስኳር ሕመሞች ሊፈውስ የሚችል መድሃኒት በኢትዮጵያ መገኘቱ ተረጋገጠ::


ዶ/ር ፋንታሁን አበበ ይባላሉ፡፡ በአፍሪካ ሜዲካል ኮሌጅ የሕክምና መምህር፣ የዶክተር ኦፍ ዴንታል ሜዲስንና ዲፓርትመንትና የምርምር ዲፓርትመንቶች ኃላፊ ናቸው፡፡ የሕክምና ትምህርት የተከታተሉት በባህርዳር ዩኒቨርሲቲና በአትላስ ሜዲካል ኮሌጅ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት በማጥናት ላይ ይገኛሉ፡፡ የ35 ዓመቱ ዶ/ር ፋንታሁን፣ ትውልዳቸው በሰሜን ሸዋ፣ ሸዋሮቢት ነው፡፡ ጥቂት የማይባሉ የምርምር ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ በስማቸው የተመዘገቡ ልዩ ልዩ ግኝቶችም አሏቸው፡፡ በቅርቡም ለስኳር ሕመም ፈውስ የሚሰጥ መድኃኒት አግኝተዋል፡፡ በምርምር ሥራዎቻቸውና ግኝቶቻቸው ዙሪያ ሻሂዳ ሁሴን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ምን ዓይነት የምርምር ሥራዎች አልዎት?
ዶ/ር ፋንታሁን፡- በርካታ የምርምር ሥራዎች እሠራለሁ፡፡ ከእነዚህም መካከል የተወሰኑት በኢትዮጵያ የአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ተመዝግበዋል፡፡ አንደኛው ምርጥ ጣዕም ካላቸው የቡና ዘሮች ለስኳር ሕመም መድኃኒት የሠራሁት ነው፡፡ ሌላው የአየር ብክለትን ለመከላከል የሚያግዝ መሣሪያ ነው፡፡ በየጊዜው የሚከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም የሚያስችል መሣሪያም ሠርቻለሁ፡፡ መሣሪያው ዝናብን በተፈለገው ርቀት ወደ አንድ ቦታ መላክ የሚያስችል ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ውኃን ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ ኢሜይል ማድረግ ያስችላል፡፡ የአየር ብክለትን የሚቆጣጠረውን መሣሪያ የሠራሁት ከዓመታት በፊት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣  በኮፐንሀገን በተዘጋጀው ኮንፈረንስ ያስተላለፉትን መልዕክት ሰምቼ ነው፡፡ በወቅቱ ችግሩን ለመከላከል መፍትሄው ላይ ማተኮር እንዳለብን ሲናገሩ ነበር፡፡ እኔም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቼ መሥራት ጀመርኩ፡፡ የሕክምና ባለሙያ እንደመሆኔም ስለአየር ባህሪ ከሰው የአካል ክፍል ጋር አገናኝቼ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ አየር ቀጥታ ግንኙነት ያለው ከሳምባ ጋር ነው፡፡ ሳምባችን የተበከለን አየር ያጣራል፡፡ ሳንባ እንዴት ነው የተበከለን አየር የሚያጣራው ብዬ መመራመር ጀመርኩ፡፡ ሳንባ የራሱ ኦሊቪዮራል ሲስተም የሚባል ሥርዓት አለው፡፡ ይህም ያልተጣራን አየር አጣርቶ ለልብ እንዲደርሰው የሚያደርግበት ሒደት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዕፀዋት እንዴት የአየር ብክለትን እንደሚከላከሉ ወደ ኋላ ተመልሼ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ፎቶ ሲንተሲስ በሚባል ሒደት ዕፀዋት የተበከለን አየር በተለይም ካርበንዳይኦክሳይድን አጣርተው ኦክስጅን ያመነጫሉ፡፡ በመሆኑም ሁለቱን የዕፀዋትና የሳምባን አየር የማጣራት አሠራር አንድ ላይ በማዋሃድ እንደ ዕፀዋትና እንደ ሳምባ የሚሠራ መሣሪያ ሠራሁ፡፡ ከፍተኛ የአየር ንብረት ለውጥ በሚስተዋልበት በዚህ ወቅት በደን ሀብታቸው ለዓለም እንደ ሳንባ ሆነው የሚያገለግሉት አፍሪካና ደቡብ አሜሪካ ናቸው፡፡ እኔም የአፍሪካን ድርሻ ለማሳየት ስል የተበከለን አየር የሚያጣራውን መሣሪያ በአፍሪካ ካርታ ቅርፅ አድርጌ ሠራሁ፡፡ መሣሪያው የተበከለን አየር አጣርቶ ኦክስጅንን ወደ ከባቢ አየር ይለቃል፡፡ ተጣርቶ የሚቀረውን  ካርበን ደግሞ ወደ ፓውደርነት (ዱቄት) ይለውጣል፡፡ ፓውደሩም ለብዙ ፋብሪካዎች የምርት ግብዓት ሆኖ ያገለግላል፡፡ መሣሪያው በየፋብሪካዎቹ ይተከላል ብዬ አስባለሁ፡፡ በተግባር ላይ እንዲውልም ለባለድርሻ አካላት ማስተዋወቅ ያስፈለጋል፡፡ ሌላው የምርምር ሥራዬ አርቴፊሻል (ሰው ሠራሽ) ዝናብ ላይ የሠራሁት ነው፡፡ አገሪቱ 98 የሚሆኑ ትልልቅና አነስተኛ ወንዞች፣ 25 ሐይቆችና ብዙ ሊሠሩ የሚችሉ የከርሰ ምድር ውኃ አላት፡፡ ይሁንና ይህንን ያህል የውኃ ሀብት ኖሮን አገራችን ብዙ ጊዜ በድርቅ ትጠቃለች፡፡ አርሶ አደሩም ይኼንን ሁሉ የውኃ ሀብት ወደ ጎን ብሎ የዝናብ ወቅቶችን ብቻ ጠብቆ ማረሱ በቴክኖሎጂ እጥረት የተፈጠረ ነው፡፡ ችግሩን የሚፈታ ሰው ሠራሽ ዝናብ ለመፍጠር ስልም፣ መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ የተለያዩ መጻሕፍትን አንብቤያለሁ፡፡ በዚህም በመጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩ የሳይንስ ዕውነታዎች መካተቱን ታዘብኩ፡፡ ሥራውን እንድጀምርም መንገድ ከፈተልኝ፡፡ በኦሪት ዘፍጥረት ሁለተኛው ምዕራፍ ቁጥር አምስት ምድር ምንም አላበቀለችም፣ እግዚአብሔርም ዝናብን አላዘነበም ነበር የሚል አገኘሁኝ፡፡ ቁጥር ስድስት ላይ ደግሞ ከምድር እንፋሎት ሆኖ ተንኖ ፎቅ እየሠራ ወደላይ ይመጣና ምድርን ያጠጣ ነበር፤ የሚል መልዕክት አገኘሁ፡፡ አሥረኛው ቁጥር ላይም ከወንዝ የወጣው እንዴት ምድርን እንደሚያጠጣ ይናገራል፡፡ ቁጥር 13 ደግሞ ኢትዮጵያ በግዮን ወንዝ እንዴት እንደተከበበች ይገልጻል፡፡ ይህንን ይዤ ስለዝናብ አፈጣጠር የሚያወራውን የጂኦግራፊ መጽሐፍ አነበብኩ፡፡ ዝናብ በሦስት ዓይነት መንገዶች በኦሮግራፊክ፣ ኮንቬንሽናልና ሳይክሎኒክ በተባሉ መንገዶች እንደሚፈጠር ተገነዘብኩ፡፡ ሁለቱም መጻሕፍት ደመና ፎቅ ሠርቶ ወደ ላይ ወጥቶ እንደገና ዝናብ ሆኖ እንደሚመለስ ያወራሉ፡፡ እኔም ባገኘሁት ዕውቀት፣ ደመና ለምን አልሠራም ብዬ ተነሳሁ፡፡ ተሳክቶልኝም ውኃ ካለበት ቦታ ላይ ደመና መፍጠር፣ እንዲሁም በተፈለገው ቦታ ላይ ዝናብ ሆኖ እንዲወርድ የሚያስችል ጥናት ሠራሁኝ፡፡ በዚህኛው ሥራም እ.ኤ.አ. በ2011 የኢትዮጵያ አዕምሮሯዊ ንብረት ጥበቃ ማኅበር ከዓለም የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ድርጅት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ ተሳተፍኩ፡፡ ሥራዬ ተመርጦልኝ ለተጨማሪ ውድድር ደቡብ ኮሪያ ተላከ፡፡ ሥራው እዚያም ስለተመረጠ፣ የደቡብ ኮሪያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቡድን፣ ከዓለም አዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ቡድንና ከኢትዮጵያ የአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ጋር በመሆን የምርምር ሥራዬን አዲስ አበባ ሒልተን እንዳቀርብ አደረጉ፡፡ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሠርተፊኬትም ተሰጠኝ፡፡ በአሁኑ ወቅት ሥራው መሬት ሊረግጥ ነው፡፡ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ቅጥራቸው ውስጥ ቦታ ሰጥተውኝና የተለያዩ  ድጋፎች አድርገው በቅርቡ ደመና ፈጥረን ዝናብ ልናዘንብ በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን፡፡ ውኃ በአየር ላይ የመላክ ሥራውም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከሠሩዋቸው ምርምሮች መካከል የስኳር በሽታ መድኃኒት አንዱ ነው፡፡  ስኳር በሽታ ምንድነው? እንዴትስ ይፈጠራል?
ዶ/ር ፋንታሁን፡- አንድ ሰው የስኳር ሕመምተኛ ነው የሚባለው፣ ቆሽት የተባለው የሰውነት ክፍል የሚያመርተውን ኢንሱሊን የተባለውን ሆርሞን ማመንጨት ሲያቅተው አልያም ደካማ ሲሆን የሚፈጠር የጤና ችግር ነው፡፡ ኢንሱሊን የተባለው ሆርሞን በሰውነታችን ውስጥ እንደ ቁልፍ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ቆሽት ሆርሞኑን ሙሉ ለሙሉ ማመንጨት ሲያቅተው ታይፕ ዋን (አንደኛው ዓይነት) የስኳር በሽታ ይከሰታል፡፡ የሚያመነጨው ሆርሞን ደካማ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ታይፕ ቱ (ሁለተኛው ዓይነት) የስኳር በሽታ ይፈጠራል፡፡ የተመገብነው ምግብ ወደ ስኳርነት ይቀየራል፡፡ ወደ ስኳርነት የተለወጠውን ምግብ ወደ ሁሉም የሰውነታችን ክፍሎች የሚያደርሰው ኢንሱሊን የተባለው ሆርሞን ነው፡፡ ይኼ ሆርሞን የለም ማለት የምንመገበው ምግብ የትም አይሄድም፡፡ ይህ ዘርፈ ብዙ የጤና ችግሮች እንዲፈጠሩ ያደርጋል፡፡ ችግሩ ከሰውነት ክብደት መጨመር፣ ከአመጋገብ ሥርዓት፣ ከጭንቀት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ካለማድረግ ተያይዞም የሚከሰት ነው፡፡ አልፎ አልፎ በዘር ይተላለፋል፡፡ በሌላ በኩልም ከምንወስዳቸው መድኃኒቶች በተለይም ለስኳር ሕመም ሲባል በሚወሰዱ መድኃኒቶች ይፈጠራል፡፡
ሪፖርተር፡- አንድ ሰው የስኳር ሕመምተኛ ነው የሚባለው የስኳር መጠኑ ስንት ሲደርስ ነው?
ዶ/ር ፋንታሁን፡- አንድን ሰው የስኳር ሕመምተኛ ነው ለማለት በደሙ ውስጥ ያለው የስኳር መጠን፣ ግሉኮስ ሜትር በተባለ የስኳር መጠን መለኪያ መሣሪያ መለካት አለበት፡፡ ማሽኑ በተቀመጠለት የስኳር ምጣኔ መሠረትም የአንድን ሰው የስኳር መጠን ውጤቱን ያሳያል፡፡ ሆኖም የስኳር ሕመም የገበያና የፖለቲካ በሽታ ሆኗል፡፡ በተለያዩ  ድርጅቶች የተቀመጠው ጤናማ የስኳር መጠን ወጥ አይደለም፡፡ ጤናማ የስኳር ልኬት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰና ከዚህ ቀደም ጤናማ የሚባለው የስኳር መጠን ሁሉ ከመጠን ያለፈ የስኳር ክምችት እንደሆነ ተደርጎ እየተቀመጠ ይገኛል፡፡ ይህም ሆነ ተብሎ የሚደረግ ሲሆን፣ የተለየ ምስጢርም አለው፡፡ ጤናማ የስኳር መጠንን የሚወስኑት  እንደ አሜሪካን ዲያቤቲክ አሶሴሽን እና ኢንተርናሽናል ዲያቤቲክ አሶሲዬሽን ያሉ ተቋማት ናቸው፡፡ የተቋማቱ አባላት ከሆኑት መካከል የፋርማሲ ባለቤቶች አማካሪ የሆኑ ሰዎች ይገኙበታል፡፡ የጤና ባለሙያዎችም ጤናማ የስኳር መጠን ይኼንን ያህል ነው ብለው ሲወስኑ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ፡፡ ይህም የጤናማ የስኳር መጠን ባነሰ መጠን በአንዴ በርካታ ሰዎች ስኳር ሕመምተኛ ስለሚባሉና የመድኃኒት ተጠቃሚዎች ቁጥር ስለሚጨምር፣ ገበያቸውን እያሰቡ ጤናማው የስኳር መጠን እንዲቀንስ ያደርጋሉ፡፡ እንደ ማሽኖቹ ሁኔታ የተለያየ የስኳር መጠን ቢቀመጥም ምግብ ያልበላ ሰው በደሙ ውስጥ የሚገኘው የስኳር መጠን በአማካይ ከ80 እስከ 120 ሚሊ ግራም ዴሲ ሊትር መሆን አለበት፡፡ ምግብ ከተባለ ደግሞ በአማካይ ከ120 እስከ 180 ሚሊ ግራም ዴሲ ሊትር መሆን ይጠበቅበታል፡፡ በቀደሙት ጊዜያት ጤናማ የስኳር መጠን ሲቀመጥ አሁን ካለው የስኳር መጠን በጣም ይበልጥ ነበር፡፡ የነበሩት ታማሚዎች ቁጥርም ከግማሽ ሚሊዮን አይበልጥም ነበር፡፡ አንድ ሰው በሰውነቱ ውስጥ ያለው የስኳር መጠኑ ስለጨመረ የስኳር ሕመምተኛ ነው ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የቅድመ ስኳር በሽታ ምልክቶች የሚባሉ በጤናማ አመጋገብና በአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚድኑ ቀላል የስኳር ዓይነቶች አሉና ነው፡፡ ነገር ግን  አንድ ሰው በቀላሉ ሊድን የሚችል የስኳር ሕመም አጋጥሞት መድኃኒት እንዲጀምር ይደረጋል፡፡ ስኳር በሽታ እንደ ገዳይ በሽታ በመፈረጁም የስኳር መጠናቸው ሲጨምር ይጨነቃሉ፡፡ በተጨነቁ ቁጥር ደግሞ የስኳር መጠናቸው ከፍ ይላል፡፡ ከዚህም ሌላ መድኃኒት (የኢንሱሊን) እንዲወስዱም ይደረጋል፡፡ ነገር ግን የሚሰጣቸው መድኃኒቶች በራሳቸው ሰዎችን የኢንሱሊን ባሪያ ለማድረግ ቀድሞ ዲዛይን የተደረጉ ናቸው፡፡ በመጀመሪያ የሚታዘዙላቸው መድኃኒቶች ለተወሰነ ጊዜ ያህል ኢንሱሊን እንዲመነጭ ያደርጋሉ፡፡ ከትንሽ ጊዜ በኋላ ግን ቆሽትን በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳል፡፡ ከዚያ በኋላ የኢንሱሊን መደበኛ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ የመድኃኒቶቹ ተግባር እግዚአብሔር የሰጠንን ቆሽት የተባለ ኢንሱሊን የሚያመርት ፋብሪካ እንዲዘጋና ሌላ አርቴፊሻል ኢንሱሉን እንድንጠቀም ማድረግ ነው፡፡ አሁን ላይ ዲያቤቲክ ዋንና ዲያቤቲክ ቱ እየዳኑ ነው፡፡ ኢንሱሊን ይወስዱ የነበሩ ሰዎችም በሌላ ሕክምና እየዳኑ ነው፡፡ ነገር ግን እድናለሁ ብሎ ወዲያው መድኃኒት ማቆም አደገኛ ነው፡፡ ምክንያቱም መድኃኒቶቹ ከሰውነት ጋር ይላመዳሉ፡፡ ይህም ድንገት ሲቋረጥ አደገኛ ይሆናል፡፡ በአሁኑ ወቅት አንዳንድ አገራቸውን የሚወዱ ባለሙያዎች ትልልቅ ሴሚናሮች እያዘጋጁ ስለስኳር ሕመም እያስተማሩ ይገኛሉ፡፡ ብዙዎቹ ሕመምተኞችም ነፃ እየወጡ ነው፡፡ እኛስ ኢትዮጵያውያን ለምን እንደዚህ አናደርግም፡፡ ይኼንን ግን አንዳንዶች ሲሰሙ ያመጡት ኢንሱሊንና ሌሎችም መድኃኒቶች እንዳይባክኑ ስለሚፈልጉ እውነታውን መስማት አይፈልጉም፡፡
ሪፖርተር፡- ጥናት ማድረግ የጀመሩት መቼ ነበር? ያገኙት የስኳር መድኃኒትስ ከምን የተሠራ ነው?
ዶ/ር ፋንታሁን፡- ጥናቱን ማድረግ ከጀመርኩኝ አሥር ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ መድኃኒቱን የሠራሁት ከሐረር፣ ከይርጋጨፌና ከሲዳማ ቡና ነው፡፡ መድኃኒቱን ለመሥራት ያነሳሳኝ ነገር ደግሞ እንደ ባለሙያ ለሕዝቡ የስኳር በሽታ መፍትሔ ለመስጠት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ስታርባክስ የተሰኘው ድርጅት ‹‹ቡና የኔ ነው›› በማለቱና በቡና አዲስ ነገር ሠርቼ የኛ መሆኑን ለማሳየት ስል ነው፡፡ ቡናችን የራሳችን መሆኑን ለማሳወቅ በውስጡ ምን ይዟል ብዬ መመራመር ጀመርኩ፡፡ ለስኳር ሕመም መድኃኒት የሚሆን ክሎሮጄኒክ የተባለ ንጥረ ነገር አገኘሁበት፡፡ ንጥረ ነገሩ በሰውነታችን ውስጥ የሚገኘውን የግሉኮስ መጠን ማመጣጠን የሚችል ነው፡፡ ቡናችን በውስጡ ሌሎችም ከ15 የሚበልጡ ንጥረ ነገሮችንም ይዟል፡፡ ይህ ንጥረ ነገር በሌላው ዓለም የሚገኙ ሳይንቲስቶች ሁሉ ለስኳር በሽታ መፍትሔ እንደሆነ ጥናት አድርገው አረጋግጠዋል፡፡ ይህንን ሳይ እኔም መመራመሬን ቀጠልኩ፡፡ ጥሩ ውጤትም አገኘሁ፡፡ ምንም እንኳን ቡና ሁሌም የምንጠቀምበት ቢሆንም በሳይንስ ለማስደገፍ ስል ግኝቱን በእንስሳት ላይ ሞከርኩ፡፡ ጥሩ ውጤትም ነበረው፡፡ ከዚያም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የምግብና የመድኃኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ላቦራቶሪ አስመርምሬ ውጤቱ ጥሩ ሆነ፡፡ ሥራዬንም አጠናክሬ ቀጠልኩ፡፡ ከዚያም ፈቃደኛ ለሆኑ የስኳር ሕመምተኞች አጠገባቸው እየቀመምኩ እሰጣቸው ጀመር፡፡ ሰዎቹም የሚገርም ለውጥ አሳዩ፡፡ የስኳር ሕመምተኞች ብቻ ሳይሆኑ ዩሪክ አሲድ (ሪህ) ያለባቸው ሁሉ ተጠቅመውት ጥሩ ለውጥ አሳዩ፡፡ ብዙዎችም ዳኑ፡፡ ከኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ከባለሥልጣኑ ባገኘሁት ፈቃድ መሠረትም በቅርቡ ገበያ ይውላል፡፡
ሪፖርተር፡- መድኃኒቱን በምን መልኩ ነው ያዘጋጁት በክኒን፣ በመርፌ ወይስ በሽሮፕ መልክ?
ዶ/ር ፋንታሁን፡- መድኃኒቱን በክኒክ ወይም በመርፌ መልክ ከማዘጋጀት ይልቅ በሽሮፕ መልኩ ቢዘጋጅ የተሻለ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ መድኃኒት በክኒን መልክ የሚዘጋጅ ከሆነ መድኃኒቱ እንዲጣበቅ የሚያደርጉ ኬሚካሎች ይገቡበታል፡፡ ይህም የመድኃኒቱን ተፈጥሯዊ ይዘት ይቀንሰዋል፡፡ በሽሮፕ መልክ ሲሆን ግን ተፈጥሯዊ ይዘቱን እንደጠበቀ ይቆያል፡፡ ለዚህም መድኃኒቱን ያዘጋጀሁት በሽሮፕ መልክ ነው፡፡ ይህንንም ተጠቅመው የዳኑ ጥቂት አይደሉም፡፡
ሪፖርተር፡- መድኃኒቱን አግኝተዋል፡፡ ነገር ግን በስፋት አምርቶ ለሕዝቡ ተደራሽ ለማድረግ በዚህ ሥራ የተሰማሩ የውጭ ድርጅቶች ጋር ይሄዳሉ፡፡ በዚሁ መልኩ ከተዘጋጀ ደግሞ የመድኃኒቱ ዋጋ ውድ ሊሆን ይችላል፡፡ ለሕዝቡም ተደራሽ አይሆንም፡፡ ይህ እንዳይሆን ምን አስበዋል?
ዶ/ር ፋንታሁን፡-  እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ መድኃኒቱ የተገኘውም ከኢትዮጵያ ቡና ነው፡፡ የኛ ቡና ከሌላው ይለያል፡፡ የራሱ የሆነ ጣዕም፣ የተለየ ንጥረ ነገርም ይዟል፡፡ መድኃኒቱም ሙሉ በሙሉ እዚሁ መመረት ይገባዋል፡፡ ነገር ግን እኔ ብቻዬን ይህንን ማድረግ አልችልም፡፡ በጎ ፈቃደኛ የሆኑ አብረውኝ መሥራት የሚፈልጉ ሰዎች ሊኖሩ ግድ ይላል፡፡  እኔ ተመራማሪ እንደመሆኔ ለችግሮች መፍትሔ ማምጣት ሥራዬ ነው፡፡ አብሮኝ የሚሠራ ከተገኘ የመድኃኒቱን አሠራር አሳይቼው እኔ ወደ ሌላ ጥናቶቼ መግባት እፈልጋለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ይኼንን ለማድረግ አገሪቱ በቂ ቴክኖሎጂ አላት?
ዶ/ር ፋንታሁን፡- የምንም ነገር መጀመሪያ ትንሽ ነገር ነው፡፡ እኔም በትንሽ ነገር ጀምሬ መሥራት እፈልጋለሁ፡፡ አቅም ያላቸው ሰዎችም አሉ፡፡ ከእነሱ ጋር ብሠራ ደግሞ የተሻለ ይሆናል፡፡ አሁን ባለኝ አቅምም በተወሰነ መልኩ ማዳረስ የምችልበትን ነገር ማቋቋም ችያለሁ፡፡ ነገር ግን ሁሉንም ለማዳረስ የሰዎች፣ የተቋማትና የአገር ድጋፍ ያስፈልገኛል፡፡ እኛው ለእኛው መረዳዳት አለብን፡፡ ያደጉት አገሮች ይረዱናል የሚለው ነገር የማይታሰብ ነው፡፡ እኔ ሥራዬን ለአገር ማስረከብ እፈልጋለሁ፡፡ አገሪቱ ከኔ የተሻሉ በርካታ ባለሙያዎች አሏት፡፡ እነሱ እዚህ ላይ ቢሠሩ ደግሞ መድኃኒቱን ይበልጥ ማዘመን ይቻላል፡፡ የቡና ባለቤትነታችንን  አረጋገጥን፣ የሕዝቡን የጤናው ችግር መፍታት፣ ሜድ ኢን ኢትዮጵያ ተብሎም መድኃኒታችንን ኤክስፖርት ማድረግ እንችላለን፡፡
ሪፖርተር፡- የስኳር በሽታ ላይ ለመሥራት ምን አነሳሳዎት?
ዶ/ር ፋንታሁን፡- የስኳር በሽታ ላይ ለመሥራት የፈለግኩት ኢንተርን (ጀማሪ) ሐኪም ሆኜ በተለያዩ ሆስፒታሎች የመሥራት ዕድሉ ባጋጠመኝ ጊዜ ነው፡፡ በወቅቱ  በዚያ ጊዜ የስኳር በሽታ ከጥርስና ከዓይን ሕምም ጋር ተያይዞ ሰዎችን ችግር ውስጥ እየከተታቸው መሆኑን ታዝቤ ነበር፡፡ በአንድ ወቅትም አንድ ልጁ በስኳር በሽታ የምትሰቃይ አባት ሲያለቅስ አየሁ፡፡ በጣም ነበር ያዘንኩት፡፡ ልጅቷ ሕፃን ነበረች፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ አንድ ልጁ ነበረች፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ስኳር ላይ መሥራት አለብኝ ብዬ ተነሳሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ጥናቱን ሲያካሄዱ ምን ዓይነት ችግር አጋጠመዎት?
ዶ/ር ፋንታሁን፡- የተለያዩ ቁሳቁሶችን ከማግኘት ጀምሮ ሌሎች ከፍተኛ ችግሮች ገጥመውኛል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሥራዎች የገንዘበ ድጋፍ ይፈልጋሉ፡፡  እኔ ግን የገንዘብ ድጋፍ አልነበረኝም፡፡ ጥናቱን ለማካሄድ የራሴን ገቢ ብቻ ነበር የምጠቀመው፡፡ ሠርቼ የማገኘውን ሁሉ ጥናቱ ላይ ነው የማውለው፡፡ ምንም ንብረት አላፈራሁም፡፡ መኪና እንኳን የለኝም፡፡ በእግሬ ነው የምንቀሳቀሰው፡፡ የተመቸ የምሠራበት ቦታም አልነበረኝም፡፡ አብሮኝ የሚሠራ ሰውም አልነበረም፡፡ አቅሙ ያላቸውን ባለሙያዎች አብረን እንድንሠራ ጠይቄ ነበር፡፡ ፈቃደኛ የሆኑ ግን አልነበሩም፡፡ ሥራው መልክ ከያዘ በኋላ ግን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሠራተኞች እንዲሁም ሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናትን አናግሬ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርጉልኝ ቃል ገብተዋል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ዋ! ትሠራና ብለው ያስፈራሩኝም አሉ፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ውስጥ የአዕምሮ ንብረት ጥበቃ መብት ተሰጥትዎታል፡፡ በውጭ አገሮች ያለውን እንዴት እያደረጉ ነው?
ዶ/ር ፋንታሁን፡- እኔ እንደ ግለሰብ አትሠራም እየተባልኩኝ ሠርቻለሁ፡፡ አሁን ሥራው ከእኔ አልፎ በአገር ደረጃ ደርሷል፡፡ በቀጣይ ያለው ነገር እንደ አገር የኢትዮጵያ ድርሻ ነው፡፡ የኛ ከሆኑት ጤፋችንና ቡናችን ተወስደውብናል፡፡ ይህም እንዳይወሰድብን የኔ ነው ብሎ ቀድሞ ይፋ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ቀድሞ ይፋ ከተደረገ በኋላም ልክ እንደ ቡናና ጤፉ እንዳይወሰድብን  ጥንቃቄ ያሻዋል፡፡ እኔም የባለቤትነት ጥያቄዬን ለዓለም አቀፉ የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ድርጅች ልኬ ነበር፡፡ ነገር ግን እስካሁን ምላሽ አልተሰጠኝም፡፡ አፋጣኝ ምላሽ ለማግኘት የተገኘውን መድኃኒትም ማዳበር ያስፈልጋል፡፡ ካልዳበረና ይህንኑ ይዘን የባለቤትነት ጥያቄ ብናነሳ እንነጠቃለን፡፡
ሪፖርተር፡- ያገኙት መድኃኒት ሁሉቱንም ዓይነት የስኳር ሕመሞች ይፈውሳል? ወደፊትስ ምን ለማድረግ አስበዋል?
ዶ/ር ፋንታሁን፡- መድኃኒት ያገኘሁት ሁለቱንም የስኳር ሕመሞች ይፈውሳል፡፡ ወደፊት ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ የስኳር ሕሙማን መታከሚያ ማዕከል የመክፈት ሐሳቡ አለኝ፡፡ ማኅበረሰቡንም ስለ ስኳር ሕመም ማስተማርና ነፃ ማድረግ፣ የስኳር መድኃኒት ፋብሪካ መገንባትና ወደ ሌሎች አገሮች ኤክስፖርት ማድረግ (መላክ) እፈልጋለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment