“ለመኖር ሥንል እንጂ ለትግሉማ እኛ ነበርን።ወደፊት እሥከሞት ለነጻነት!!!!!”
ይሄን ጦምሮ የነበረው ወጣት አወቀ አባተ ነው። ወጣት አወቀ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት የወጣቶች አመራር የነበረ በጣም ከማከበራቸውና ከማደንቃቸው የኢትዮጵያ ልጆች መካከል አንዱ ነው። አገሩን፣ ህዝቡ የሚወድ፣ ግፍ ሲሰራ ዝምታን የማይመርጥ፣ ለነጻነትን ለአገር እንድነት አንገቱን አሳልፎ የሰጠ ቆራጥ የሰላማዊ ታጋይ ነው። በእዉነትም የፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ልጅ።
ወጣት አወቀ ብዙ ጊዜ ወደ እሥር ቤት ይሄዳል። የታሰሩ እስረኞችን ቤተሰቦቻቸውን የሚጠይቅ፣ የሚረዳ፣ እንዲረዱ የሚያድርግ ፣ ከወሬ ያለፈ የተጨበጠ ትግል ያደርግ የነበረ የተከበረ ወጣት ነው። አብዛኛው “እኔ ላይ እስካልደረሰ ድረስ ምን አገባኝ” የሚል ራስ ወዳድ በሆነበት ዘመን፣ እርሱ ላይ ችግር ባይደርስም፣ እርሱ ባይነካም፣ የሌላው ሕመም፣ የሌላ ስቃይ የሚሰማው ሰው በጣም ትልቅ ሰው ነው። አወቀ እንዲህ አይነት ሰው ነው።
ከወጣት አወቀ ጋር በጣም የተግባባነው በአንድ ጉዳይ ነበር። የቀድሞ የሰሜን አሜሪካ የአንድነት ድጋፍ ማህበር ፣ የአንድነትን ፓርቲ ገዢው ፓርቲ በጉልበትና ሕግ ወጥ በሆነ መንገድ ቢያገድም፣ አገር ቤት ያለውን ትግልና ታጋዮች መደገፋችንን መቀጠል አለብን በሚል የእስረኞች ቤተሰቦችን ለመደገፍ አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ጀምሮ ነበር። በዚህ ወቅት የመኢአድ እስረኞችን ሁኔታ የሚከታተል ትጉ ወጣት ስለነበረ፣ የእስረኞች ቤተሰቦች ድጋፍ እንዲያገኙ የረዳ ሰው ነው።
ይህ እሥር ቤቶችን የሚያዘወትር ወጣት ፣ አሁን በህወሃት ታጣቂዎች ታፎኖ ወደ ወህኒ ተወስዷል።ምን ደረጃ ላይ እንዳለም አይታወቅም።
አቶ ሃይልማሪያም እና ጓዶቻቸው እንታደሳለን እያሉ ሲፎክሩ ነበር። ያው “መታደሳቸውን” እነ አወቀ አባተን በማሰር፣ የአገሪቷ ወህኒ ቤቶችን በመሙላት እያሳዩን ነው።
ሕወሃቶች አወቀን በማሰራቸው አንገቱን እናስደፋዋለን ብለው አስበው ከሆነ ተሳስተዋል። “ወደፊትም እስከሞት” እንዳለው ይህ ወንድማችን አንገቱን አይደፋም። ለርሱ ለአገርና ለሕዝብ ብሎ ወደ ወህኒ መዉረዱ ክብሩ ነው።
አወቀ አባትን ብዙ ላያወቀው ይችላል። ብዙ ያልተዘመረለት ወጣት ነው። ግን እንደ አወቀ አይነቶቹን ሳስብ ዉስጤ በደስታ ይሞላል።ኢትዮጵያ የልጆች ድሃ ሳትሆን በልጆች የተባረከች እንደሆነ ያመላክተኛል።
No comments:
Post a Comment