Sunday, December 25, 2016

በቁሉቢ ገብርኤል ይፈጸማል የተባለው “ኃይለኛ ሙስና” ተጣርቶ እርምጃ እንዲወሰድ ተጠየቀ


በቁሉቢ ገብርኤል ይፈጸማል የተባለው “ኃይለኛ ሙስና” ተጣርቶ እርምጃ እንዲወሰድ ተጠየቀ
Kulubi Gebriel
ቁሉቢ ገብርኤል
• በኹለቱ ዓመታዊ ክብረ በዓላት፣ ከ23   ሚ. ብር በላይ የስዕለት ገቢ ተሰብስቧል
• ማሠልጠኛዎች እንዲገነቡና የማኅበራዊ ልማት ተሳትፎው እንዲጠናከር ተጠይቋል
በቁሉቢ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ውስጥ፣ እየተፈጸመ ነው በሚል ከምእመናን በተደጋጋሚ የቀረበው የሙስና  አቤቱታ፣ ተጣርቶ አስፈላጊው ርምጃ እንዲወሰድ፣ የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን መስተዳደር ጽ/ቤት አሳሰበ፡፡ የመስተዳድሩ ጽ/ቤት ማሳሰቢያውን ያቀረበው፣ ባለፈው ወር መጀመሪያ ለፓትርያርኩ ቢሮ በጻፈው ደብዳቤ ነው፡፡ በዞኑ ሜታ ወረዳ ቁሉቢ ከተማ በሚገኘው የደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ውስጥ፣ “ኃይለኛ ሙስና እየተፈጸመ” መሆኑን በመጥቀስ ጉዳዩ እንዲጣራ የአጥቢያው ምእመናን ለቤተ ክርስቲያኒቱ ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ለመስተዳድሩም በግልባጭ አስታውቀው እንደነበር ጽ/ቤቱ አስታውሷል፡፡
አቤቱታውን ለማጣራት፣ ከገዳሙ አስተዳደርም ይኹን ከምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳልተደረገ፣ ከምእመናኑ በድጋሚ መረዳቱን የጠቀሰው የዞኑ መስተዳድር፤ “ለሕዝበ ክርስቲያኑ ክብር አለመስጠትን ያመለክታል፤” ሲል ተችቷል፡፡
“ጉዳዩ ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዳያመራ”፣ በገዳሙ እየተፈጸመ ነው ስለተባለው ሙስና በቤተ ክርስቲያኒቱ አመራር በተገቢው መንገድ ተጣርቶ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድና ለሕዝበ ክርስቲያኑ እንዲገለጽ የፓትርያርኩን ቢሮ ጠይቋል፡፡ ጉዳዩ፣ በመንግሥት ደረጃ የፓትርያርኩ ቢሮ እስኪጠየቅ ድረስ ቸል መባሉ፣ በእጅጉ ቅር እንዳሰኛቸው የገለጹት የአጥቢያው ምእመናን፤ በአካባቢው በገዳሙ የተከናወነ ተጠቃሽ ማኅበራዊ ልማት አለመኖሩን፤ የአገልጋዮች ደመወዝ የገቢውን ያኽል አለመሻሻሉንና
ካህናቱ ከሚያሳዩት ትጋት ውጭ መንፈሳዊ አገልግሎቱን ለማጠናከር በአስተዳደሩ የሚደረገው ጥረት እዚህ ግባ የማይባል መኾኑን አስረድተዋል፡፡በየዓመቱ ታኅሣሥ 19 እና ሐምሌ 19 ቀን ለገዳሙ በስዕለት ከሚገባው ጥሬ ገንዘብና የተለያዩ ዓይነት ንዋያተ ቅድሳት ውጭ ባሉት ወርኃዊ በዓላትም ከፍተኛ ገቢ እንደሚገኝ ምእመናኑ ይናገራሉ፡፡ የኹለቱ ዓመታዊ ክብረ በዓላት ገቢ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና በዞኑ መስተዳድር አካላት ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበትን ያኽል በሌሎቹም ወራት አለመደረጉ ለከፍተኛ ሙስና አጋልጦታል የሚሉት ምዕመናኑ፤ የጸበል ቦታው በብዙ መቶሺዎች እንዲታወቅ፣ ማረፊያዎችንና መጸዳጃዎችን ምቹ ማድረጉ እንኳ ትኩረት አልተሰጠውም፤ ሲሉ ቅሬታቸውን ይገልፃሉ፡፡የገዳሙ አስተዳዳሪ መልአከ ኃይል አባ ወልደ ጊዮርጊስ በበኩላቸው፤ የዞኑን ጥያቄ በተመለከተ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጋር
መወያየታቸውንና የተሰጠውን ምላሽም ትላንት ለመስተዳድሩ ማድረሳቸውን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል። “ጉዳዩ መታየት ያለበት በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ነው፤” ያሉት አስተዳዳሪው፣ የሙስና አቤቱታ አቅርበዋል የተባሉት ሰዎች ራሳቸው፣ በወንጀል
የሚፈለጉ መኾናቸውን ጠቅሰው፣ ለሕግ እንዲቀርቡ ጠይቀናል፤ ብለዋል፡፡
የገዳሙ ሒሳብ ሹሙ ወ/ሪት ወይንሸት ግርማም፣ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ማንነታቸውን አለመግለጻቸውን ጠቅሰው፣ አቤቱታ የቀረቡባቸውን ጥያቄዎች ከሀገረ ስብከቱ ጋር ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በአካል አቅርበን በደብዳቤ የተሰጠውን ምላሽ ደግሞ፤ አዲስ አበባ ለሚገኘው ክልላዊ ቢሮና ለዞኑ ጽ/ቤት መስጠታቸውን አስረድተዋል፡፡
“ገዳሙ፣ በገቢረ ተኣምራቱ ያለውን ታዋቂነትና የገቢ መጠኑን ያኽል፣ መንፈሳዊ አገልግሎቱን ለከተማው ምእመናን ተደራሽ በኾነ አኳኋን እንዲያስፋፋ፤ ቀድሞም የነበሩት የካህናት ማሠልጠኛና የአብነት ት/ቤቶች በተደራጀ መልኩ እንዲከፈቱ፤ እንደ ድሬዳዋና ሐረር ባሉት ከተሞች ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኙ የራስ አገዝ ግንባታዎችን በማካሔድ ማኅበረሰባዊ አገልግሎቱን የሚያጠናክርበት አቅም እንዲፈጥር” ጠቁመዋል ምዕመናኑ፡፡ ለዚኽም ገዳሙ፣ “ለረጅም ጊዜ ከቆዩት ሓላፊዎች ይልቅ፡- ሙስናን የሚጸየፉ፣ የተማሩና የነቁ አገልጋዮች” እንደሚያስፈልጉት ጠቁመዋል፡፡በዓመት ኹለት ጊዜ ለሚከበረው የቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓል፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ወደ ገዳሙ ከሚጓዙ ተሳላሚዎች፣ ከ23 ሚሊዮን 587 ሺሕ ብር በላይ በስዕለት መግባቱን የሐምሌ 19 ቀን 2007 እና የታኅሣሥ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ ይኸው ገቢ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ የበጀት ዕቅድ እየወጣለት፥ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የነገረ መለኰት ኮሌጆች፣ ለአብነት መምህራን፣ ለሰባክያነ ወንጌልና ለሠራተኞች ደመወዝ የሚከፈል ሲሆን የሙከራ ሥርጭት እያካሔደ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቴሌቭዥን ጣቢያ የ9 ሚሊዮን ብር አስተዋፅኦ ማድረጉም በሪፖርቱ ተገልጿል። በስዕለት የሚሰበሰቡትን የተለያዩ ዓይነት ንዋያተ ቅድሳት፣ ዋጋ አጥንቶና ተማኝ ኮሚቴ አቋቁሞ የሚያሰራጭ የማደራጃ መምሪያ፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የተቋቋመ ሲኾን፤ ተጨማሪ ገቢ ማስገኛ ሕንፃ ለማሠራትም ዕቅድ መያዙን በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡

No comments:

Post a Comment