[ክቡር ሚኒስትሩን ሾፌራቸው በጠዋት ወደ ቢሮአቸው እየወሰዳቸው ነው]
  • ሬዲዮ ክፈትልኝ ዜና ላዳምጥ፡፡
  • እሺ ክቡር ሚኒስትር (ሬዲዮው ተከፈተ)፡፡
  • ከ40/60 ቤቶች ግንባታ የተዘረፈው የአርማታ ብረት ተገኘ ነው የሚለው?
  • ብረቱን የዘረፉት 23 ተጠርጣሪዎችም ተያዙ ነው የሚለው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ብረቱ አልተገኘም?
  • ተገኝቷል ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ይኼንን አሳፋሪ ድርጊት ማን ነው የፈጸመው?
  • ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን ይዞ እየመረመራቸው ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ለመሆኑ የተዘረፈው ብረት ምን ያህል ያወጣ ነበር አሉ?
  • ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ያወጣል ነው የተባለው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • አምስት ሚሊዮን?
  • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ይኼ ሁሉ ሲሆን ኃላፊዎቹ የት ነበሩ?
  • የእነሱም ጉዳይ ይመረመራል ነው የተባለው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እኔ እኮ የሚያበሳጨኝ ይኼ ነው፡፡
  • ምኑ ክቡር ሚኒስትር?
  • ምርመራው ሁሉንም አለማካተቱ፡፡
  • እኔን የሚያበሳጨኝ ደግሞ አለ፡፡
  • ምንድነው እሱ?
  • የግልጽነትና የተጠያቂነት መጥፋት ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ለምን እንዲዚህ አልክ?
  • በሌላ አገር ቢሆን ከላይ እስከ ታች ያለ ሹም ይባረር ነበር እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ከጥልቅ ተሃድሶው በኋላ ይኼንን ጠብቅ፡፡
  • ጥልቅ  ተሃድሶውም እኮ ጊዜ እያባከነ ነው እየተባለ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ማን ነው እንደዚያ የሚለው?
  • ሕዝቡ ውስጥ በስፋት እየተባለ ያለው ይኼው ነው፡፡
  • እና አሁን ምን ይደረግ?
  • ጊዜ አይባክን ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ለምኑ?
  • ለተሃድሶውም ሆነ ለምርመራው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • አንተ መቼ ነው እንዲህ ያለ ነገር የተማርከው?
  • ይኼ ኑሮ ምን የማያስተምረው አለ ብለው ነው ክቡር ሚኒስትር?
  • ህምም. . .
[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ገብተው ጸሐፊያቸውን ጠሯት]
  • ምን አዲስ ነገር አለ?
  • አልሰሙም እንዴ?
  • ምኑን?
  • ክቡር ሚኒስትር ፊደል ካስትሮ ሞቱ እኮ?
  • ሰምቻለሁ፣ ሌላ ምን አዲስ ነገር አለ?
  • የተዘረፈው ብረት መገኘቱንስ ክቡር ሚኒስትር?
  • እሱንም ሰምቻለሁ፡፡
  • በኤርትራ በኩል የገቡ ታጣቂዎች መደምሰሳቸውንና መማረካቸውንስ?
  • ሰምቻለሁ፡፡
  • ሌላ አዲስ ነገር ምን ልንገርዎ ታዲያ ክቡር ሚኒስትር?
  • ዜና አልቆብሻል ማለት ነው?
  • ክቡር ሚኒስትር ሠራተኞች ጥያቄ እያቀረቡ ነው፡፡
  • ምን ይፈልጋሉ?
  • ክቡር ሚኒስትሩ ለምን አይተዋወቁንም እያሉ ነው፡፡
  • እሺ፡፡
  • ሌላ ደግሞ አንዳንድ ጥያቄዎች ማቅረብ ይፈልጋሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ለምሳሌ?
  • የዕድገት፣ የዝውውርና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • አንቺ ምን አስተያየት አለሽ?
  • እኔማ ይኼ ተሃድሶ እስኪያልቅ ጠብቁ ብል ማን ይስማኝ ክቡር ሚኒስትር?
  • የእነሱን ጥያቄና ተሃድሶውን ምን አገናኘው?
  • አለ አይደል ለማረጋጋት ብዬ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምንድነው የምታረጋጊው?
  • እርስዎ ሥልጣንዎ ላይ እስኪደላደሉ ብዬ ነዋ፡፡
  • የእኔ መደላደልና የእነሱ የመብት ጥያቄ ደግሞ ምን ያገናኘዋል?
  • ‹‹መጀመርያ የመቀመጫዬን›› ያለችው ዝንጀሮ እኮ ወዳ አይደለም ክቡር ሚኒስትር?
  • አሁንስ የሰለቸኝ ያረጀ ጥቅስና ተረት ነው፡፡
  • ይኼን ያህል ክቡር ሚኒስትር?
  • ለአንቺም ቢሆን አይጠቅምሽም፡፡
  • ምን ይጎዳል ብለው ነው ክቡር ሚኒስትር?
  • የሰለቸኝ ወሬ ነው፡፡
  • ወሬ ከሌለ እኮ ጥሩ አይደለም፡፡
  • ከያዝሽው ኃላፊነት ጋር አይመጣጠንም፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ከቀድሞ ጓደኞቻቸው አንዱ ደውሎላቸው እያወሩ ነው]
  • ከየት ተገኘህ እባክህ?
  • ክቡር ሚኒስትር ካለሁበት፡፡
  • በስሜ ጥራኝ፡፡
  • ፕሮቶኮሉ አይፈቅድም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ኑሮ እንዴት ነው?
  • እርስዎን ከማጣታችን ውጪ ደህና ነው፡፡
  • ይኸው አለሁ አይደል?
  • አዬዬ . . .
  • ምነው?
  • ያቺ ቢራ ፉት የምንልባት ቦታ ጭር አለች እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እንግዲህ ምን ይደረግ ትላለህ?
  • ባይሆን አንዳንዴ እቤት እየመጣን ብናውካካ ጥሩ ነበር፡፡
  • እንግዲህ ሲመች እንሞክራለን፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር አዲሱ ሹመት እንዴት ነው?
  • ከባድ ነው፡፡
  • ይኼን ያህል?
  • ከምታስበው በላይ ነው፡፡
  • ምን አጋጠመዎት?
  • ለጊዜው ዝርዝሩን ባልናገርም ትልቅ አደራና ኃላፊነት አለበት፡፡
  • እኔ እኮ አዳዲስ ወዳጆች አፍርቼ አስተዋውቀኝ ሲሉ ነው የደወልኩልዎት፡፡
  • የት አገኘሃቸው?
  • በቅርቡ ዱባይ ሄጄ ሆቴል ውስጥ በድንገት ተገናኘን፡፡
  • በድንገት?
  • አዎን በድንገት ነበር ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • የሚገርም ትውውቅ ነው እባክህ?
  • በዚያ ላይ በአገር ውስጥና በውጭ ከፍተኛ ሀብት እናንቀሳቅሳለን ብለውኛል፡፡
  • ኧረ እባክህ?
  • አንድ ቀን ቀጠሮ ቢይዙልኝ ብር ብለው ከዱባይ ይመጡ ነበር፡፡
  • አትቸኩል፡፡
  • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
  • የዘንድሮ ባለሀብት ተብዬዎች እዚያ ስትላቸው እዚህ፣ እዚህ ስትላቸው እዚያ ሲረግጡ ነው የሚገኙት፡፡
  • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
  • በቅርቡ ይገባሃል፡፡
  • ኧረ ፈታ አድርገው ይንገሩኝ?
  • ብዙዎቹ ቁጭ በሉ ናቸው፡፡
  • ማለት?
  • ዱባይ ነን ይሉህና ስታምናቸው መርካቶ ምናለሽ ተራ ይገኛሉ፡፡
  • እንዴ?
  • ኢስታንቡል ነኝ ያለህ ቦምብ ተራ ሲያተራምስ ይገኛል፡፡
  • እነዚህ እኮ እንዲህ አይደሉም ክቡር ሚኒስትር?
  • እንዳይሸውዱህ፡፡
  • በምን ይሸውዱኛል?
  • አፋቸው ጥሬ ይቆላል፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠርተውት እያወሩ ነው]
  • የተባባልነውን ጥናት ጨረስክ?
  • አዎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • የት አለ ታዲያ?
  • ተጽፎ አልቆ እየተጠረዘ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን አዲስ ነገር አገኘህ?
  • የሚገራርሙ ነገሮች አሉበት ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ለምሳሌ?
  • በግዥ፣ በጨረታ፣ በኮንትራክተር መረጣ፣ በውጭ ጉዞ አበል፣ በንብረት አያያዝና አወጋገድ፣ በበጀት አጠቃቀምና ሪፖርት አቀራረብ፣ ወዘተ የሚገርሙ ነገሮችን ያገኛሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • በአጠቃላይ ድምዳሜህ ምንድነው?
  • ካየሁት የሌብነት ተግባር  ትልቅ ትምህርት ይገኛል ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን ዓይነት ትምህርት?
  • ‹‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ›› የሚባል ምሳሌያዊ አነጋገር ያውቃሉ አይደል ክቡር ሚኒስትር?
  • ተረትህን ተውና በቀጥታ ንገረኝ፡፡
  • በአንድ በኩል የሌቦችን ቀዳዳ ለመድፈን ትልቅ ትምህርት ይሰጣል፡፡
  • በሌላ በኩልስ?
  • በሌላ በኩል ደግሞ የራስን ስትራቴጂ ለመዘርጋት በጣም ጠቃሚ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • የምን ስትራቴጂ?
  • ያው ክቡር ሚኒስትር. . .
  • ምንድነው እሱ (ተቆጡ)?
  • ኧረ አይቆጡ ክቡር ሚኒስትር?
  • ንገረኛ?
  • ‹‹ሥጋ መሬት ወድቆ አፈር ሳይዝ አይነሳም›› ይባል የለ?
  • ምን ማለት ነው?
  • መቼም እዚህ ሥልጣን ላይ ሆኖ መታማት አይቀርም ብዬ ነው ክቡር ሚኒስትር?
  • እና?
  • እናማ ዓይንን መክፈት ያስፈልጋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • የእኔ ዓይን ማን ተጨፈነ አለህ?
  • እሱን እኮ ነው የምለው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምድንነው የምትለው?
  • ኃላፊነት የሚያስገኘውን ጥቅም እንዳይዘነጉ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ገና ከአሁኑ?
  • ቻይናዎች ምን እንደሚሉ ያውቃሉ ክቡር ሚኒስትር?
  • ምን ይላሉ?
  • ‹‹የሺሕ ኪሎ ሜትር ጉዞ በዕርምጃ ይጀመራል›› ነው የሚሉት ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን አልክ አንተ?
  • ያዳመጡኝ መሰለኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ውጣልኝ!
[ክቡር ሚኒስትሩ የዕለቱን የቢሮ ውሎ ጨርሰው ምሽት ላይ ቤት ሲደርሱ ባለቤታቸው ለእራት እየጠበቁዋቸው ነበር]
  • እንዴት አመሸህ ክቡር ሚኒስትር?
  • ደህና ነኝ፡፡
  • ምነው ያኮረፍክ ትመስላለህ?
  • ይኼ አማካሪ ተብዬ አናዶኝ ነው፡፡
  • ምን አለህ?
  • ሥልጣንህን ለራስህም ተጠቀምበት ዓይነት ወሬ ሲያወራልኝ ነበር፡፡
  • ምን አልከው?
  • ተቆጥቼ ከቢሮ አባረርኩት፡፡
  • ከሥራ አባረርኩት ነው የምትለው?
  • እንደሱማ ሕጉም አይፈቅድልኝም፡፡
  • መቆጣትህም ልክ አይደለህም፡፡
  • ምን ማድረግ ነበረብኝ?
  • የሚለውን በፅሞና መስማት፡፡
  • ከዚያስ?
  • ነገሩን ማብላላት፡፡
  • ከዚያስ?
  • ከዚያማ ሁሉንም ነገር በሆድህ መያዝ፡፡
  • በሆድህ መያዝ ነው የምትይኝ?
  • አዎን!
  • እሱ ያንን ሁሉ ሲቀባጥር ዝም ብዬ መስማት አለብኝ?
  • ጥናት እኮ ነው ያቀረበልህ፡፡
  • ያጠናውና የእሱ ማብራሪያ የተለያየ ነው፡፡
  • በጥናቱ መሠረት ሁለት የተለያዩ ግኝቶችን አገኘ አይደል?
  • ልክ ነሽ፡፡
  • አንደኛው ሌሎችን ለመታገል፣ ሌላው ደግሞ ‹አድቫንቴጅ› ለማግኘት አይደል?
  • ሁለተኛውን ሐሳብ ግን ፈፅሞ አልወደድኩትም፡፡
  • አብላላው አልኩህ እኮ?
  • ተብላልቶ ምን ይገኛል?
  • የተጣራ ነገር ነዋ!
  • ለእኔ የሚታየኝ ግን የደፈረሰ ነው፡፡
  • ተረቱን አስታወስከኝ?
  • የምን ተረት አመጣሽ አንቺ ደግሞ?
  • ለአደፍራሾች የተተረተ ነዋ!
  • ምን ተብሎ?
  • ‹‹በጥባጭ ሳለ ማን ጥሩ ይጠጣል?›› ይባላል፡፡
  • ማነው በጥባጩ?
  • አደፍራሹ!
  • ምን አልሽ አንቺ?
  • የምልህ ግልጽ መሰለኝ፡፡
  • ምን ዓይነት ዘመን ላይ ደረስን እባካችሁ?
  • ዘመኑን አትውቀስ፡፡
  • ይኼንን የሞላጮች ዘመን እንዴት አልወቅስ?
  • በጣም ትገርመኛለህ፡፡
  • ምኔ ነው የሚገርምሽ?
  • ሞላጮች የምትላቸው ናቸው እኮ እየተተኮሱ ያሉት፡፡
  • እና አንቺ የሞላጮች ደጋፊ ነሽ?
  • ቆይቶ ይገባሃል፡፡
  • ምኑ ነው የሚገባኝ?
  • የሞላጮችና የከርፋፎች ጉዳይ፡፡
  • ማነው ከርፋፋ?
  • እንዲያውም ሰሞኑን የሰማሁትን ግጥም ልንገርህ፡፡
  • አሁንስ ተረት፣ ጥቅስ፣ ግጥም. . . ሰለቸኝ፡፡
  • ይልቁንስ ስማ፡፡
  • እስቲ አነብንቢው፡፡
  • ‹‹ለምን አይሰረቅ ለምን አይዘረፍ፣ የማያውቅበትን ይዞ ሲንከረፈፍ›› ተብሎልሃል፡፡
  • ለእኔ ነው የተገጠመው?
  • ለእኔ ነው ታዲያ?
  • ሆሆ . . .!