Thursday, December 8, 2016

አቶ ሀብታሙ አያሌው ወደ ውጭ ሔዶ እንደሚታከም ገለጸ


አቶ ሀብታሙ አያሌው ወደ ውጭ ሔዶ እንደሚታከም ገለጸ – BBN –
ባለፈው አርብ ኅዳር 23 ቀን 2009 ከተከሰሰበት የሽብር ክስ በነጻ የተሰናበተው አቶ ሀብታሙ አያሌው ወደ ውጭ ሔዶ እንደሚታከም ገለጸ፡፡ የቀድሞ አንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረው አቶ ሀብታሙ፣ ሆምሮይድ በተባለ በሽታ በጽኑ ሲታመም እንደሰነበተ ይታወቃል፡፡ ውጭ ወጥቶ ለመታከም በተደጋጋሚ ለፍርድ ቤት አመልክቶ በተለያዩ ሰበቦች ማመልከቻው ውድቅ ሲደረግበት የቆየው አቶ ሀብታሙ፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ነጻ መባሉን ተከትሎ ውጭ ሔዶ ለመታከም ማቀዱን አስታውቋል፡፡
“ሁሉም ሰው እንደሚያውቀው እጅግ የተንዛዛ እና የተጓተተ ፍትህ ነው፡፡” ሲል በፍርድ ቤቱ የደረሰበትን መንገላታት የገለጸው አቶ ሀብታሙ፣ አያይዞም “በከፍተኛው ፍርድ ቤት አንድ ዓመት ከሁለት ወራት አካባቢ ፈጅቶ ነው ውሳኔ ላይ የደረሱትና በነጻ ለማሰናበት የወሰኑት፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ችሎት በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን የወጣውን እና እስካሁንም ያልተሻሻለውን የስነ ስርዓት ህግ አንቀጽ 288/5ን በተዛባ መልኩ ተርጉሞ በእስር ቆይተው ይግባኙን እንዲከታተሉ ብሎ አቃቤ ህግ ይግባኝ ሲያቀርብ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ችሎት ያንን ተቀብሎ በእስር ቤት እንድንቆይ ተደረገ፡፡” ሲል የነበረውን ሁኔታ አስታውሷል፡፡
በሀገር ውስጥ በሚደረግለት የማስታገሻ ህክምና አሁን ላይ መጠነኛ ማገገም ያሳየው አቶ ሀብታሙ በጽኑ በታመመበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውስ “በሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ ጠይቀን ከእስር ከተፈታንበት ጊዜ ጀምሮ ባለፈው አርብ ውሳኔ እስከተሰጠበት ጊዜ ድረስ የተለያዩ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች አቅርበናል፡፡ በከፍተኛውም ሆነ በጠቅላይ ፍርድ ቤት እና በሰበር ሰሚ ችሎት የተከራከርንባቸው ጉዳዮች ሲታዩና እንደዚህ ዓይነት የጤና እክል ገጥሞኝ እኔን ከእነ ቤተሰቤና መላውን የአገራችንን ህዝብ ጭንቀት ላይ ጥሎ ቆይቷል” ብሏል፡፡
አቶ ሀብታሙ አክሎም “ፍርድ ቤቱ መዝገቡን ዘግቶ በነጻ ያሰናበተኝ በመሆኑ ህክምናዬን ከአገር ውጭ ሔጄ መከታተል እችላለሁ፡፡” ብሏል፡፡ “እስካሁን ህክምና ላይ በነበርኩበት ወቅት ከፍተኛ ወጭ ጠይቆኛል፡፡›› ያለው ሀብታሙ፣ ‹‹ከዚህ በኋላም ቢሆን ከፍተኛ ወጭ እንደሚጠይቀኝ ይታወቃል፡፡ ይህንን ወጭ እኔ የቻልኩትን ያህል ከሞከርኩ በኋላ የተለያዩ ወዳጆቼ ባደረጉልኝ ድጋፍ ነው ህክምናውን የማደርገው” ሲል በሀገር ውስጥ ለሚታተሙ መገናኛ ብዙኃን ገልጿል፡፡

No comments:

Post a Comment