(ዘ-ሐበሻ) ሕዝብን ከሕዝብ ጋር በማናከስ ተወዳዳሪነት የሌለው የሕወሓት መንግስት በቤንሻንጉል ሕዝብ በማስመሰል በአማራው ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት አጠናክሮ ቀጥሏል:: በተለይ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በቡለን ወረዳ ስር ባሉት ጭላንቆ እና ባኩጂ ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖሩ አማሮች በስርዓቱ ጠመንጃ ታሸጋግራላችሁ; በአማራው ክልል እየተደረጉ ያሉትን ጦርነቶች ትደግፋላችሁ በሚል ግርፋት እና እስር እየተፈጸመባቸው መሆኑ ተዘግቧል::
በጭላንቆና ባኩጂ ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖሩት እነዚሁ አማሮች አርሶ ከመብላትና በሰላም ከመኖር ውጭ ምንም የማያውቁ ሆኖ ሳለ ሆን ተብሎ ከመሬታቸው ለማፈናቀልና ተረጋግተው እንዳይኖሩ ለማድረግ ሆን ተብሎ የሕወሃት መንግስት ባሰማራቸው የቤንሻንጉል ተወላጆች እንዲገረፉ ንብረታቸውም እንዲዘረፍ በማድረግ ላይ ነው::
በትናንትናው ዕለትና በዛሬው ዕለት ብቻ ቁጥራቸው ከ25 የሚበልጥ አማራ ናችሁ የተባሉ ወጣቶች ታስረው ወዴት እንደተወሰዱ አይታወቅም የሚሉት የዜና ምንጫችን ንብረት ዘረፋውም ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል::
በዚሁ በቤኒሻንጉል ክልል የሚኖሩ አማሮች ላይ ከዚህ ቀደም እንደሚደረገው ሁሉ ወደ መጣችሁበት ሂዱ በሚል ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑን ዘ-ሐበሻ ሰሞኑን በተደጋጋሚ መዘገቧ አይዘነጋም::
በሌላ ዜና የአማራው ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በቻግኒ ከቤንሻንጉል ባለስልጣናት ጋር ስብሰባ ላይ እንደዋለና በስብሰባው ውስጥም የሕወሓት ሰዎች ሙሉ በሙሉ ተሳትፎ እንደነበራቸው የዘ-ሐበሻ ምንጮች አስታውቀዋል:: የዚህ ስብሰባ ዓላማ ሰሞኑን በጃዊ ሕዝብ ያነሳውን ሕዝባዊ አመጽ ተከትሎ በክልሉ ይኖራል ተብሎ በተሰጋው የመሳሪያ ዝውውር ዙሪያ እንደሆነ ምንጮች አስታውቀዋል:: በቻግኒ ኢትዮጵያ ሆቴል በተደረገው በዚሁ ስብሰባ ላይ የቤንሻንጉል አስተዳደሮች በክልላቸው የመሳሪያ ዝውውር እንዳይኖር ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ከሕወሃት ሰዎች ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው የሚገልጹት ምንጮቹ በተለይም በክልሉ የሚኖሩ አማሮች ሕዝባዊ ዓመጹን እንዳይቀላቀሉት ጥብቅ ክትትል እንዲደረግባቸው ተመክሮባቸዋል::
No comments:
Post a Comment