Friday, December 23, 2016

ደጋግመን ብናወራ፤ ደጋግመን ብንቋሰል፤ ደጋግመን እዬዬ ብንል ለሀገራችን ጠብ የሚል ነገር የለም!


ብንገማገም ስድብ ንትርክ ዘለፋ ፍረጃ ብናበዛ ለሀገራችን ጠብ የሚል ነገር የለም! የሚያስፈልገን ልብ ነው! የሚያስፈልገን ቆራጥነት ነው! በቆራጥነት ጉዳያችንን መወያየትና ልባም መፍትሄ መስጠት ነው፡፡ “በላብ ያልፍልሃል! ተሸፋፍነህ ተኛ!” እንደሚባለው ያበሻ መድሃኒት ላቦት ብቻ መፍትሄ አይሆነንም! አውርተን አውርተን እፎይ ብሎ መተኛት ትላንትም፣ ዛሬም፣ ነገም መፍትሄ አይሆነንም! እድሜ ለቴክኖሎጂ የማህበራዊ ድረገጾች በሽ ናቸው፡፡ ሰራዊት በሙሉ ሊሰማራበት ነው።
ድሮ ችግር ሲፈጠር ለማስታረቅ ሩጫ ነበር፡፡ አሁን ለማባባስ የሚሯሯጥ ኃይል እንዳለም በግልጽ እየታየ ነው፡፡ መፍትሔ ከማስገኘት ይልቅ የበለጠ ብጥብጥ እንዲከሰት ግፊት እየበዛ ነው፡፡አንድነታችንን የሚፈታተኑ የጠባብ ጐሰኝነትና አካባቢያዊ ስሜት የተላበሱ አስተሳሰቦች እዚህም እዚያም ሲሰሙና በየካፌና በየማህበራዊ ድረገጾች መሟሟቂያ ሲሆኑ ማስተዋልም እ – እ – የሚያሰኝ ሆኗል፡፡ዘረኝነት፣ ጐሰኝነት፣ መከፋፈል፣ መራራቅ፣ ሃይማኖትን መጠቀሚያ ማድረግ፣ ከጠላት ጋር ወግኖ መሟገት፣ አገርንና የአገርን ክብር አሳልፎ መስጠትና ፖለቲካን ቢዝነስ በማድረግ ለአትራፊነት መወራጨት፣ አስፈሪ የሆነ አቋምና እንቅስቃሴ ማድረግ ከዚህ ራቅ ቢልም አሳሳቢ ነው፡፡ ሊታሰብበት እና በጋራ ልንታገለው የሚገባ ጉዳይ ነው ። 

No comments:

Post a Comment