Tuesday, December 27, 2016

የአማራውን ነባር ፀባይ አታስቀይሩ | በከፍያለው አባተ (ዶ/ር)

ዝም ከምል የሚሰማኝን ላንባቢ ላካፍል ብየ እንጂ፣ ያቀራረብና የሀሳብ አገላለጽ ልዩነት ካልሆነ በስተቀር፣ ይህ ጽሑፍ (እስካሁን ድረስ) ያልተነሳ አዲስ ሀሳብም መልእክትም የለውም። እሚያስተላልፈው ያንኑ የተለመደ የአማራን ታሪካዊ ‘በሽታ’ ነው። የሀገርና የወገን ፍቅር፣ የአንድነት ‘በሽታ’። ይህ የወገንና የሀገር ፍቅር ‘በሽታ’ በአማራው ይጠና ይሆናል ለማለት እንጂ፣ በዚህ ‘በሽታ’ የተለከፈ ስንት (በጐሳም በግለሰብም ደረጃ አማራ ያልሆነ) ኢትዮጵያዊ አለ። ይህ የሀገርና የወገን፣ የአንድነት ‘በሽታ’ ለረዥም ዘመናት አማራውን ሕዝብ ለጥቃትና ለበደል ሲያጋልጠው ኑሯል። ይህ ከዘመን ዘመን፣ ከጊዜ ጊዜ እየከረረ የመጣ፣ በአማራ ላይ ያነጣጠረ በደል፣ የአማራውን ነባር ፀባይ እንዳያስለውጠው፣ እጁን እንዲሰጥ እንዳያደርገው እሰጋለሁ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “አማራውም እንደ ሌሎቹ በጐሳ መደራጀት አለበት” የሚለውን አስተሳሰብ የሚያፋፍም (ቆስቋሽ) ኃይል እየጨመረ መጥቷል። በደል አያመጣው መዘዝ የለምና የበደል ብዛት (ብሎ ብሎ) አማራውንም ሊያጠበው ነው። ነባር ታሪካዊ ፀባዩን ሊያስቀይረው በመዳዳት ላይ ነው።

የአማራው ነባር ታሪካዊ ፀባይ (ከነፍሱ አብልጦ) ኢትዮጵያን መውደድ፣ በኢትዮጵያዊነት መመካትና መኩራት፣ ኢትዮጵያዊያንን በሀገር ልጅነት መውደድ፣ ከኢትዮጵያዊያን ጋር መጋባትና መዋለድ፣ በየትኛውም የኢትዮጵያ ምድር ሠርቶ፣ ሀብትና ንብረት አፍርቶ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር ተመሳስሎ (አብሮ) መኖር ነው። የአማራው ነባር ፀባይ ክፉና በጎውን፣ ደስታና መከራውን ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር መካፈል፣ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወገኖቹ ጋር ኢትዮጵያን በግምባር ቀደምነት ከጠላት መመከትና መከላከል ነው።
የአማራ ዋናው መለያው ለኢትዮጵያ ያለው ልዩ ፍቅርና ልዩ ተቆርቋሪነት ነው። አማራው ኢትዮጵያን ከራሱ ሕይወት አብልጦ ኢትዮጵያን የመውደድ አባዜ የተጠናወተው በመሆኑ፣ “አማራ ከሁሉ ተለይቶ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ የሚለው ለምን ነው? የዚች ሀገር ልዩ ተጠቃሚ ስለሆነ አይደለም እንዴ?” ይላሉ (በምእራባዊያን አገር አሳሾች፣ በሚሲዮናዊያንና በሀገራችን ቀንደኛ ጠላቶች እኩይ ሰበካ የተለከፉ) አንዳንድ ሰዎች። አማራው የኢትዮጵያ ልዩ ተጠቃሚ አለመሆኑን ለመረዳት ግን ወደ ሰሜን ሸዋ፣ ወደ ጐጃም፣ ወደ ጐንደርና ወደ ወሎ ብቅ ብሎ የሕዝቡን አኗኗር፣ መመልከትና ከሌሎች አካባቢዎች ጋር ማመዛዘን ይበቃል።
የአማራው የሀገር ፍቅር በኢኮኖሚና በቁሳዊ ጥቅም (ማጣት ወይም ማግኘት) አይመዘንም። የአማራው የትዮጵያዊነት ፍቅር ከቁሳዊ ጥቅም የላቀ ነው። የኑሮ ጉስቁልና፣ የልማትና ማህበራዊ አገልግሎት እጦት፣ ሌላ ሌላውም (በእውቀትም ሆነ ያለእውቀት ሲደርስበት የኖረው) በደል የአማራውን የሀገር ፍቅር ቅንጣት ታህል አይቀንሰውም። ብዙዎቻችን ምንም የሌላትን (ቁርስም፣ ምሳም የማትሰጥ) ድሀ እናታችን እንደምንወድ፣ ሕይወታችንንም ልንሰዋላት ዝግጁ እንደምንሆን ሁሉ፣ አማራው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነቱን ያን ያህል ይወዳል። ይህንን ጥልቅ የሀገር ፍቅርም በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች በተፈጠሩ ጦር ሜዳዎች ተሰልፎ በግምባር ቀደምትነት ሕይወቱን ለመስዋእትነት በማቅረብ አሳይቷል/አስመስክሯል። አማራው “ኢትዮጵያ በጠላት ተወረረች” ሲሉት ቁሳዊ ጥቅሙ ሳይሆን ሰብአዊ ክብሩ የተነካ/የተዋረደ ይመስለዋል። በዚህም የተነሳ “ያገርህ ዳር ድንበር ተደፈረ” ሲሉት ተዘጋጅቶ እንደሚጠባበቅ የሰለጠነ ጦር ምልምል፣ ያለምንም ማመንታት፣ ማቄን ጨርቄን ሳይል ወዲያውኑ ለጦርነት ይሰለፋል።
ይህ ተፈጥሯዊ/ባህላዊ የውትድርና ወኔና ጽኑ የሀገር ፍቅር፣ አማራውን ሕዝብ በኢትዮጵያ (የውጭና የውስጥ) ጠላቶች ጥርስ ውስጥ አስገብቶታል። ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛት ለማድረግ፣ የተከፋፈለችና ደካማ የሆነች ሀገር እንድትሆን የሚፈልጉ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች፣ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ይልቅ ሲያነጣጥሩና ሲረባረቡ የኖሩት በአማራው ሕዝብ ላይ ነው።
የሶሻሊዝምን ሥርአት ምንነት በቅጡ ያልተረዱት (እራሴን ጨምሮ) በርካታ (ጥራዝ ነጠቅ) ኢትዮጵያዊያን ምሁራንና ተማሪዎችም የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች ፈለግ ተከትለው፣ አማራውን ሕዝብ በጅምላ ሲኮንኑት ኑረዋል። ኩነኔውና ሰቆቃው አሁንም እንደቀጠለ ነው።በትምህርት ሳይበስሉ፣ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ (በጀሮ ጠገብነት) የሰሙትን እንደ ገደል ማሚቶ እያስተጋቡ፣ ትምህርታቸውን አቋርጠው ጫካ የገቡት ጮርቃና ለጋ የወያኔ ፋኖዎችም ያንኑ የጠላት ፈለግ በመከተል አማራውን ሕዝብ (ከነባህሉና ከነአመለካከቱ) በይፋ ሲያወግዙት ኑረዋል። አሁንም በያለበት በሰበብ ባስባቡ ቁም ስቅሉን እያወጡት፣ እያሳደዱትና እየገድሉት ነው። ጥቃቱ ከምንጊዜውም ይበልጥ ተጠናክሮ ቀጥሏል። የአማራው ቅስም እንዲሰበር፣ ያለልማዱ/ያለጠባዩ በማንነቱ እንዲያፍርና አንገቱን እንዲደፋ ፈርጀ-ብዙ የሆነ፣ የተቀነባበረ ሰፊ ዘመቻ እያካሄዱበት ነው።
ይህ የተቀነባበረ የረዥም ዘመን ዘመቻ ወደ ሀገራችን አራት ማእዘናት ተሰራጭቶ፣ ዛሬ አማራን “አይንህን ላፈር” የሚለው የሌላው ጐሳ ተራ ሕዝብ* * ጥቂት አይደለም። የተጋነነ እንዳይመስልብኝ እንጂ፣ ዛሬ በብዙ የሀገራችን አካባቢዎች የአማራ ሕዝብ የበዝባዥነት፣ የጨቋኝነት፣ የአድላዊነት፣ የትምክህተኝነት፣ የመሠሪነትና የተንኮለኛነት ቀለም ተለቅልቆ፣ ሳያውቁት እሚያወግዙት፣ ሲወድ የሚጠሉት፣ ሲቀርብ የሚሸሹት ጭራቅ ሁኗል። ይህ ሁሉ የሆነው ያለምክንያት * የሌላው ጐሳ ተራ ሕዝብ ስለአማራ ያለው ግንዛቤ የተለየ ነው። በብዙ የደቡብና ምእራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች፣ “አማራ” ማለት አማርኛ የሚናገር፣ ያካባቢው ተወላጅ ያልሆነና ያካባቢውን ቋንቋ እማይናገር፣ በንግድ፣ በውትድርና፣ በዳኝነትና በሌላም የመንግሥት ሥራ ምክንያት የመጣ፣ መጤ ማለት ነው። ይህ ሁሉ መጤ ከየትኛውም ጐሳ ተነስቶ የመጣ ሊሆን ይችላል። በተራው ሕዝብ ላይ የሚፈጽመው ግፍና በደል ግን የአማራው ጐሳ እንደፈጸመው ተቆጥሮ አማራው ይወገዝበታል፣ ይጠላበታል።
አይደለም። ለዘመናት በተካሄደበት የጥላቻ ዘመቻ ነው። ይሁን እንጂ ያ ሁሉ በደል አማራውን አላጠበበውም። እንዲያውም (በእልህም ይሁን በልማድ) ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን ያለውን ፍቅር እጥፍ ድርብ ያደረገው ይመስለኛል። ለዚህም በቅርብ ጊዜ ጎንደር ላይ ከተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ የተሻለ ማስረጃ የለም።
በቅርብ ጊዜ ጐንደር ላይ በወልቃይትና ጠገዴ የማንነት ጥያቄ የተነሳ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ፣ የመከራና የበደል ገፈታ ቀማሹ አማራ ሕዝብ ከያዛቸው መፈክሮች መካከል አንዳንዶቹ፣ · አትለያዩን፣ ቅማንትና አማራ አንድ ነው · የኦሮሞ ወንድሞቻችን ደም ደማችን ነው · በቀለ ገርባ ይፈታ የሚሉ ነበሩ። በነዚህና በሌሎችም (በማላስታውሳቸው) መፈክሮች አማካይነት አማራው በደሉንና ብሶቱን ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን በደልና ብሶት ጋር በማጣመር ኢትዮጵያዊ ጩኸቱን አሰማ። በመፈክሮቹ አማካይነት ለሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወገኖቹ ያለውን ፍቅርና ተቆርቋሪነት ገለጸ። “አትከፋፍሉን፣ አትለያዩን” የሚሉት መፈክሮች ብቻ የአማራውን የአንድነት ፍላጐትና ጥልቅ የሀገር ፍቅር ቁልጭ አርገው የሚያሳዩ ናቸው። ታዲያ ይህ ሥር የሰደደ የኢትዮጵያዊነት ፍቅር/ስሜት ይመስለኛል ከሌሎች ጐሳዎች በላቀ ሁኔታ አማራውን ሕዝብ የረዥም ጊዜ የጥቃት ሰለባ አድርጐት የሚኖረው።
በሀገር ውስጥ የሚገኘው፣ መከራ ገፊው አማራ፣ ከራሱ መብት ጋር በማጣመር ለመላ ኢትዮጵያዊያን ሰብአዊ መብት መከበር በሚጮህበትና በሚዋደቅበት ባሁኑ ወቅት፣ የባሕር ማዶ ‘ልሂቃኑ’ ግን እንደ ሌሎቹ የጐሳ ቡድኖች ሁሉ፣ “አማራም በአማራነቱ ተደራጅቶ ራሱን ከጥፋት ማዳን አለበት” እያሉ ይወተውታሉ። በሌላ አነጋገር አማራው “ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ” እያለ ማነኛውንም ኢትዮጵያዊ የሚያሳትፍ ድርጅት ለማቋቋም ከሚመኝ ይልቅ፣ የወያኔን ፈለግ ተከትሎ፣ በጠባቡ በጐሳ መደራጀት አለበት ማለት ነው። ውትወታው በጠባቡ እሚያስበውን በሰፊው እንዲያስብ በማትጋት ፈንታ፣ በሰፊው እሚያስበውን በጠባቡ እንዲያስብ የሚያደርግ ነው።
ይህ ውትወታ የወያኔን መንግሥት በመጣል ላይ ብቻ ያነጣጠረ የትግል ስልት ነው። የወያኔን መንግሥት ከመጣል ያለፈ ራእይ ግን የለውም። “የአማራ ቡድን እንዲፈጠር እናድርግና የጐሳዎች ቡድኖች ባንድ ላይ ተሰልፈን ወያኔን ከስልጣን እናስወግድ፣ ከዚያ በኋላ እንደፍጥርጥራችን” እንደማለት ይመስላል። ይህም ማለት እናፍርስና (እንደ ልማዳችን) በፍርስራሹ ላይ ጉልበት ያለው፣ በለስ የቀናው፣ የወር-ተረኛ የጐሳ ቡድን ሥልጣን ጨብጦ፣ ያንኑ አሳረኛ ኢትዮጵያዊ እንደ ወያኔ ሲያተራምስ ይቆይና፣ እድሜው ሲደርስ ለሌላ ወር-ተረኛ ይልቀቅ ማለት ነው።
በጐሳ ቡድኖች ጣምራ የሚደረግ ትግል ከዚህ የተሻለ ውጤት ሊኖረው አይችልም። የሻቢያ፣ የኦሮሞ ነፃ አውጭ ቡድንና የወያኔ ቡድን ጣምራ ትግል፣ የደርግን መንግሥት ገልብጦ ከጣለ በኋላ፣ ጉልበተኛው ወያኔ ሥልጣን ጨብጦ ኢትዮጵያዊያንን እንዳሻሮ እያመሰ መሆኑን ነው በመታዘብ ላይ ያለነው። የጐሳ ቡድን ጥርቅም ከቡድናዊ ንትርክና ሽኩቻ የተለየ ጠቃሚና ገምቢ ነገር ሊያስገኝ አይችልም።
ጉልበተኛው ወያኔም የኢትዮጵያን ሕዝብ በጐሳ ከፋፍሎ የሚያካሂደው አገዛዝ፣ ለጋራ አገራቸው አንድ ላይ ደማቸውን ያፈሰሱትንና የሚያፈስሱትን ዜጐች፣ ተጋብተውና ተዛምደው ለረዥም ጊዜ የኖሩትን ኢትዮጵያዊያን፣ በቋንቋቸውና በጐሳቸው ለይቶ በመከለሉ፣ በተፈጥሮም ሆነ ባስተዳደር የተነሳ የሚደርስባቸውን ጉዳትና በደል አብረው እንዳይወጡ አድርጓቸዋል። ደስታና መከራቸውን አብረው እንዳይካፈሉ ሁነዋል። በጋራ የዜግነት ጉዳያቸው ላይ አብረው እንዳይመክሩና እንዳይዘክሩተለያይተዋል። ለውጭ ጠላት ጣልቃ ገብነትም የተመቻቹ ሁነዋል። የሀገሪቱ ቀጣይነትም ሆነ የሕዝቦቿ አንድነት ቋፍ ላይ ነው።
ታዲያ በጐሳ ድርጅቶች የጋራ ትግል መንግሥትን መገልበጥ እንደ ወያኔ ዓይነቱን አንድ የጐሳ ቡድን ብቻ ፈላጭ ቆራጭ ያደረገ ከሆነ፣ ከየትኛው በጐ ተመክሮ ተነስተን ነው አማራው በጐሳ እንዲደራጅ የምንወተውተው? ኦሮሞው በጐሳ በመደራጀቱ ያገኘው ልዩ ጥቅም ምንድን ነው? አፋሩስ? ቤኒ ሻንጉሉስ? ደቡቡስ? ሐረሬውስ? ወ.ዘ.ተ. አንድ ወጥ በሆነ የዜግነት አመለካከት በመመራት ፈንታ፣ በጠባብና በጥቃቅን (በጐሳ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ ወ.ዘ.ተ) ቡድን የምንደራጅ ከሆነ፣ ሊፈጠር የሚችለውን የቡድን ብዛት ለማሰብ እንኳን ያዳግታል። የሚፈጠረውም ቡድን እርስ በርሱ የሚፋተግ እንጂ ለሕዝባችንና ለሀገራችን አወንታዊ ውጤት ኑሮት አያውቅም፣ ወደፊትም አይኖረውም።
ለምሳሌ ያህል በኦሮሞው ሕዝብ ስም የተፈጠረው የፓለቲካ ቡድን ስንት ነው? ትክክለኛ ቁጥሩን ባላውቀውም በርካታ መሆኑን አውቃለሁ። በሆነ አጋጣሚ ኦሮሞው ሥልጣን ቢጨብጥ የኦሮሞውን ሕዝብ እወክላለሁ የሚለው የፖለቲካ ድርጅት ሁሉ እርስ በርሱ ለመጠላለፍ ደባ የሚሸርብ ነው የሚሆነው። በደባ ሽረባው ሂደት ውስጥ የሚሰቃየው ግን የኦሮሞው ሕዝብ ነው። ኦሮሞው በጆግራፊ ክልል የሚደራጅ ቢሆን፣ የአርሲ ኦሮሞ ድርጅት፣ የቦረና ኦሮሞ ድርጅት፣ የወለጋ ኦሮሞ ድርጅት፣ የሸዋ ኦሮሞ ድርጅት፣ ወ.ዘ.ተ. እየተባለ እያንዳንዱ ድርጅት የየክልሉን ኦሮሞ እወክላለሁ በማለት አንዱ ከሌላው አካባቢ የኦሮሞ ድርጅት ጋር ሲነታረክ የሚኖር ነው የሚሆነው። በሃይማኖትም መቧደን ቢጀመር እንደዚያው ተመሳሳይ ችግር አለ። የእስካሁኑ ተመክሯችን የሚያሳየን በጠባብ በጠባቡ ከመቧደን ተጠቃሚ የሆኑት (በሕዝቡ ስም መዋጮ የሚሰበስቡት፣ በያሉበት ተንደላቀው የሚኖሩት) የቡድን መሪዎች ብቻ ናቸው። የኦሮሞም ሆነ የሌሎች ጐሳዎች ሕዝቦች ግን ከነበሩበት የኑሮ ሁኔታ ስንዝር ታህል እንኳን ፈቀቅ አላሉም። ፍትሕ አላገኙም፣ መሠረታዊ ዲሞክራቲክ መብታቸውን አላስከበሩም፣ እንዲያውም የኦሮሞም ሆነ ሌላው በጐሳ የተደራጀ ሕዝብ ከምንጊዜውም የበለጠ (ካማራው ባላነሰ ሁኔታ) ለእስራትና ለሞት ተጋልጦ ይገኛል። ስለሆነም ለአማራው ሕዝብ በጥሩ አርኣያነት የሚወሰዱ አይደሉም።
ታዲያ የሌሎቹ የጐሳ ድርጅቶች በጐ ተመክሮ ያስገኙ ይመስል አማራው በጐሳ ተደራጅቶ ራሱን እንዲከላከል የሚደረገው ግፊት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። የባሕር ማዶ የአማራ ልሂቃንም ይህንኑ ጐሰኛና ጠባብ የአማራ ድርጅት ለማቋቋም ደፋ ቀና በማለት ላይ ናቸው። ይሁን እንጂ በሰሞኑ ጉትጐታ መሠረት አማራውም እንደ ኦሮሞው በጐሳ ልደራጅ ቢል ፋይዳቢሶች በሆኑ አንስተኛ ቡድኖች መሸንሸኑ አይቀርም። የመሸንሸን ፍንጭም እየታየ ነው። የሸዋ አማራ አሊያንስ፣ የጐጃም አማራ፣ የጐንደር፣ የወሎ፣ የጐጃም አገው፣ የላስታና ሰቆጣ አገው፣ የቅማንት፣ ወ.ዘ.ተ. እያሉ ብዙ ቡድን መፍጠር ይቻላል።
አማራውን ሕዝብ ከኢትዮጵያ መለስ በጐሳ ማደራጀት፣ ነባሩን የአማራ ኢትዮጵያዊ ፀባይ በማይረባ አዲስ ቀለም ለቅልቆ እንደማበላሸት ነው። ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን መበታተን አስተዋጽኦ ማድረግ ነው። ለአማራው ሕዝብ፣ በጐሳ መደራጀት የሽንፈት ምልክት ነው። ራሱ በጐሳ ከተደራጀ በኋላ ሌሎችን የጐሳ ድርጅቶች በጠባብነት የሚወቅስበትና የሚተችበት የሞራል ብቃት እንዳይኖረው ማድረግ ነው።
ትግላችን የሚሰምረው ባንዲት ሀገር ዜግነት አንድ ላይ ስንንቀሳቀስ ነው። በጐሳ ላይ በተደራጀው ጉልበተኛ የወያኔ መንግሥት ከሸፈ እንጂ፣ የ1997ቱ የቅንጅት ትግል አስደናቂ ውጤት ያስገኘው ከጐሰኝነት ስሜት የጸዳ ስለነበረ ነው። የ1997ቱ የቅንጅት ድል ኢትዮጵያዊያን ጐሰኝነትን/ጠባብነትን እንደማይፈልጉ ያሳየ ጉልህ ማስረጃ ነው። ሰሞኑን ወያኔን ያሸበረውና “አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” እንዲያውጅ ያስገደደው (ጐሰኛ የተናጠል ድርጅት ትግል ሳይሆን) ከሰሜን እስከደቡብ፣ ኢትዮጵያዊያን ባንድ መንፈስ ገንፍለው በመውጣታቸው ነው። የወያኔ ወዳጆች የሆኑትን ምእራባዊያን ሀገሮች ሳይቀር ቀልብ ስቦ፣ ወያኔ በሕዝቡ ላይ የሚያካሂደው በደል እንዲጋለጥ፣ ወያኔ ገመናው እንዲወጣ ያደረገው የኢትዮጵያዊያን አንድነት ነው።
ስለዚህ አማራው ሳይታክት በእድሜ ተመክሯቸው፣ በእውቀታቸው፣ ባመለካከታቸውና በራእያቸው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ሊያገለግሉ ከሚችሉ፣ ከጠባብ የጐሳ ስሜት ከጸዱ ኢትዮጵያዊያን ጋር ተሰልፎ፣ ወያኔንም ሆነ ሌሎች ፀረ-አንድነት ኃይሎችን መታገል አለበት። ይህ ነው ታሪካዊውና ነባሩ የአማራ ፀባይ።
በዚህ አቋምና አመለካከት አማራው ሕዝብ ብቻውን አይደለም። የአማራውን አመለካከት ሌላውም የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚገባ ይጋራዋል። በሥልጣን ላይ የተቀመጡ ቡድኖች በሕዝብ ላይ የሚያደርሱት በደል (ቢበላለጥም) ከሞላ ጐደል አንድ ዓይነት ስለሆነ፣ የበደሉን መራራ ጽዋ የተጐነጩ ሁሉ ባንድነት ተሰልፎ ለመታገል ይፈልጋል። በጠባብ የጐሳ አመለካከት ተደራጅተው ኢፍትሃዊነትን፣ ግፍና ጭቆናን እንታገላለን የሚሉ የኢትዮጵያውያን፣ አንድነት ደንታ እማይሰጣቸው፣ የሀገራችን ህልውና እማያሳስባቸው፣ ግላዊ ወይም ቡድናዊ ጥቅም ለማግኘት ብቻ የሚራወጡ አስመሳዮች ናቸው።
“አማራው በጐሳ ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ፓርቲ አቋቁሞ መብቱን ያስከብር” እያሉ የሚወተውቱ ሁሉ የአማራ ወዳጅ አይደሉም። አማራው የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ባይሆንም በቋንቋው፣ በሃይማኖቱና ከነዚህ ጋር አብረው በሚሄዱ ባህሎቹ አማካይነት በኢትዮጵያ ውስጥ የበላይ (domኢnአnt) ሁኗል” የሚሉ ተራ ቀናተኞች/ምቀኞች ዘይንተረፍ ናቸው።
እነዚህ ተራ ቀናተኞች ሊረዱት የሚገባቸው አንድ ነገር አለ። የተለያዩ ባህሎች በተለያየ ምክንያት (በንግድ፣ በስደት፣ በጉርብትና፣ ባስተዳደር፣ ወ.ዘ.ተ.) ለረዥም ጊዜ ጐን ለጐን ሲኖሩ ይደበላለቁና የድሮ ፀባያቸውን ይለውጣሉ። ወይም አንደኛው ጐልቶ ይወጣል። ሌላው ደግሞ እየደበዘዘ ከዚያም እየጠፋ ይሄዳል። ሕዝቦች አብረው ሲኖሩ ይህ እማይቀር ነገር ነውና ከወዲሁ ልናውቀውና ልንቀበለው ይገባል። የሚጠፉት እንዳይረሱና የተናጋሪዎቹ ይትብህልም አብሮ እንዳይጠፋ ከወዲሁ በጽሑፍ እየመዘገቡ ማስቀመጥና ለትውልድ ማቆየት/ማስተላለፍ ነው።
ባጋጣሚ እሚያድገውንና እሚጐለብተውን ቋንቋ ደግሞ የጋራ ቋንቋ፣ በቋንቋው ውስጥ የታመቀውንም ባህል የጋራ ባህል አርጐ መቀበል ያስፈልጋል። ይህን ለመቀበል ስንዘጋጅ ብቻ ነው የኢትዮጵያዊያን አንድነትና የሀገራችንም ቀጣይነት አስተማማኝ እየሆነ የሚሄደው። ስለዚህ፣ አማራው ያለባሕሉ ከጥቃት በማያድን የጐሳ ፖለቲካ ከሚደራጅ ይልቅ፣ ከማንኛውም ሀገር ወዳድ በሳል ኢትዮጵያዊያን ጋር ትግሉን አቀናጅቶ የራሱንም ሆነ የሌሎችን ኢትዮጵያዊያን መብት ማስጠበቅ አለበት። በኢትዮሚዲያ ድህረ-ገጽ ላይ አንድ ጽሐፊ እንዳስነበቡን የቡድን ነገር ማቆሚያ የለውም፣ እስከ ቤተሰብ ይደርሳል ብለዋል። ይኸው ጽሐፊ በመቀጠል፣ በጐሳ ፖለቲካ ከመቧደን ይልቅ ባስተሳሰብ፣ ባመለካከትና በራእይ ተመሳሳይነት ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ እየተደራጀ ለሀገር የሚበጅ እንቅስቃሴ ቢያደርግ ይመረጣል ብለዋል። በኔ በኩል ድንቅ ሀሳብ ይመስለኛል።
እስካሁን ያላነሳሁት ያማራ ብሶት አለ። ይህም በኢትዮጵያዊነት ፍቅሩና ለሀገር አንድነት ባለው ከፍተኛ ተቆርቋሪነት የተነሳ፣ ለውጭም ለውስጥም የሀገር አንድነት ጠላቶች ጥቃት ዓይነተኛ ሰለባ ሁኗል። ራሱን ካላደራጀ የሚደርስበትን ጥቃት እንዴት ይከላከላል? እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአማራው ላይ የተቀነባበረ የረዥም ጊዜ የጥቃት ዘመቻ ሲካሄድበት፣ ከአማራውም ሆነ ከሌላው ኢትዮጵያዊ የመመከት ሙከራ ተደርጐ አያውቅም። አማራው ያላግባብ በሀሰት ሲወነጀል ለማስተባበል ተሞክሮ አያውቅም። ስለዚህ ሀሰተኛው ክስና ውንጀላ ሁሉ በአድማጭ ጆሮ እየተንቆረቆረ ገብቶ እንደውነት ሰፊ ተቀባይነት አግኝቶ ኑሯል። ባሁኑ ጊዜ ግን ሁኔታው የተለየ ነው። አማራው ሲጠቃና ሲበደል ጥቃትና በደሉን የሚያሰማለት ሞረሽን የመሰለ ኢፖለቲካዊ ድርጅት አለ።
ሞረሽ ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆንም፣ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በአማራው ሕዝብ ላይ የደረሰውንና የሚደርሰውን ቅጥ ያጣ በደል ለብዙ አድማጭ አድርሷል። በብዙ ሰዎች ዘንድ በአማራ ላይ የነበረውን የተዛባ ግንዛቤ ለማስተካከል ችሏል። ዛሬ ያለ ተጨባጭ ማስረጃ (አፉ እንዳመጣለት) በየቦታው አማራን መኮነንና ማብጠልጠል ቀንሷል። አማራም ተቆርቋሪና ተሟጋች እንዳለው እየታወቀ ስለመጣ፣ አማራን በተመለከተ ንግግር ሲጀመር ትንሽ ጥንቃቄ ማድረግ ተጀምሯል። ከዚያም አልፎ በአማራ መጠቃት እሚያዝኑና እሚቆጩ ደጋፊዎች (sympአthኢzእrs) ማየት ተጀምሯል። ይህ የሞረሽ የሥራ ውጤት ነውና ሊመሰገንና የበለጠ ተጠናክሮ እንዲንቀሳቀስ ሊደገፍ ይገባዋል። ሌሎች የሰብአዊ መብት ድርጅቶችም ካሉ ተመሳሳይ ድጋፍ ሊሰጣቸው ይገባል። ሞረሽና መሰል ድርጅቶች (ካሉ)፣ አሁንና ወደፊት በአማራው ላይ የሚከሰተውን አሉባልታ፣ አድልኦና ጥቃት እየተከታተሉ ማሰማት/ማስተጋባት ብቻ ሳይሆን፣ ሆን ተብሎ እንዲረክስና እንዲበላሽ የተደረገውን (አንዳንድ) ያማራ ታሪክ በማስረጃ እያስደገፉ ለሕዝብ ማቅረብ ያስፈልጋል። ይህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ጥላሸት የተቀባው የአማራ ታሪክ እንዲጠራ ይረዳል።
በጐሳ መደራጀት ለአብሮነት፣ ለሰላምና ለእድገት ጠንቅ ስለሆነ፣ እሚያቀራርበንና እሚያስተሳስረን፣ ቀስ በቀስም ልዩነታችን እያጠፋ በሚሄድ አደረጃጀት ተደራጅተን፣ ሁላችንም የሀገራችን የጋራ ተጠቃሚ እንድንሆን ምኞቴ ነው።

No comments:

Post a Comment