Tuesday, December 27, 2016

የሕዝብን ተጋድሎ ለማምክን የአማራው ብሔረተኛ ነኝ ባዩና የኦነጋውያን ቡድን ሕብረት – ሰርጸ ደስታ

ራሱን የአማራ ብሔረተኛ ነኝ የሚለው ቡድን ለዛሬው የአማራ ሕዝብ ተጋድሎ ዋነኛ አቀነባባሪው እኔ ነኝ ይለናል በተመሳሳይ በኦሮምያም ለአንድ አመት ገደማ ተንቀሳቅሶ የነበረውን የሕዝብ ተጋድሎ ኦነጋውያን የእኛ የትግል ሥልት ውጤት ነው ይሉናል፡፡ ሁለቱም እርስ በእርስ ሲወዳደሱ እናያለን፡፡ እንደውም አሁን አሁንማ ሰላምታ ሲሰጣጡ እንኳን እንዴት እንደሚተዋወቁና ሌላውም ኢትዮጵያዊ የእነሱን ፈለግ እንዲከተል ይመክሩናል፡፡ ለማስተዋል ይረዳ ዘንድ በቅርቡ ቤተ አማራ በተባለው የአማራ ቤሔረተኛ ነኝ የሚለው ቡድን ፌስ ቡክ ላይ አንድ አስቂኝ ነገር አነበብኩ፡፡ አንዱ የአማራ ብሔረተኛ ነኝ ባይ አንድ ሱቅ ጎራ ሲል አንድ የኦሮሞ ተወላጅ አገኘሁ ይለናል፡፡ ከየት ነህ ብዬ ጠየኩት ይለናል ከኦሮሚያ ነኝ አለኝ ይለናል፡፡ ከዚያ በአጸፋው ኦሮሞውም አነተስ አለኝ ይላል አማራ ነኝ ባዩ እኔም ከአማራ ነኝ አልኩት በዚህ እጅግ ተደሰተ ይለናል፡፡ ይሄንንም አንደ ጥሩ ምሳሌ ሌሎች አንዲከተሉት ይመክራል፡፡ የአማራ ብሔረተኛ ቡድኖች አንግዲህ እነዚህ ናቸው፡፡
በእርግጥም እነሱ ይግባባሉ አላማቸውም በወያኔ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በሕዝብ ሥነልቦና ለመዝራት  እንዲህ አይነት ድራማዎችን ለማቀናበር ሁኔታዎችን አመቻችተው አጋጣሚ የፈጠራቸውም እንደሆነ ሊነግሩን ይፈልጋሉ፡፡  ወያኔ የኦሮሞን ሕዝብ በዘረኝነት ማፍዘዝ ምን ያህል ለሕልውናዋ እንደጠቀማት አሳምራ ታውቀዋለች፡፡ በአማራው ሕዝብ ላይ እስከዛሬ ብዙ ያልተመቻቹ ነገሮች ነበሩ፡፡ የአማራው ሕዝብ ኢትዮጵያዊነት ሄዶ ሄዶ አንድ ቀን እንድሚጥላት ታውቀዋለች፡፡ ሥለዚህ የአማራን ሕዝብ እንደ ኦሮሞው ሕዝብ ከብሔራዊ ማንነቱ አስወጥቶ የባዘነ ማድረግ ነበረባት፡፡ በኦሮምያ እንደሚኖረውም ባይሆን በአማራው ክልል የሚኖረው ሕዝብ ብዝሐነት አለው፡፡ የተለያየ ሕዝብ ነው፡፡ ዛሬ በኦሮምያ ኦሮሞንና ሌላውን፣ አልፎም ሙስሊሙንና ክርስቲያኑን፣ ከዛም በታች አንዱን የክልሉን አካባቢ ሕዝብ ከሌላው እርስ በእርስ እንዳይተማመን ወያኔ ተሳካልኝ የምትለውን ሥራ ሰረታለች፡፡ ለዚህም ኦነግንና ኦነጋዊያንን ከምንም በላይ ውለታቸውን ታስባለች፡፡ በአማራው ክልል ብዙ አሰበችና ቅማንትን ከሌላው አማራ የተለየ ለማድረግ እንደሙከራ በጎንደር ያሴረችው አይነተኛ ምሳሌ ነው፡፡ ሁኔታው የፈጠረውን ፈጥሮ እንደከሸፈባት ስታውቅ ነበር የኦነጋውያንን መሰል የአማራ ብሔረተኛ ቡድን እንደሚያስፈልጋት የገባት፡፡  ኦነግን ብዙ ኦሮሞዎች ባለማወቅ እንደተከተሉት ብርግጥም ብዙ አማራዎች ይህን ቡድን የእነሱ እየመሰላቸው ድጋፋቸውን ሰጡት ወያኔም እንዳሰበቸው በአጭር ጊዜ ብዙ ሽፋን አገኘ፡፡  አሁን የአማራውን ሕዝብ ተጋድሎ በዋነኝነት የምመራው አኔው ነኝ ይለናል፡፡ ዛሬ ከወያኔ ጋር ተፋጦ የሚገኘው የአማራው ሕዝብ ግን ይሄን ቡድን አያውቀውም፡፡ የዚህ ቡድን ዋነኛ አጫፋሪዎች የፌስቡክና ሌሎች ማህበራዊ ደረ ገጽ ሚዲያዎች ናቸው፡፡ በእርግጥም ወያኔ ይህን ቡድን የፈለገችው በዋነኝነት እዚህ ላይ ትልቅ የፕሮፓጋንዳ ሥራ እንዲሰራላት ነው፡፡ በተመሳሳይ ኦነጋውያንንም እንደ ድሮው በሕዝብ መካከል ሰው በአሳቃቂ ሁኔታ በመግደል ፊልም እንዲሰሩላት ሳይሆን በማሕበራዊ ድረ ገጾችና በተለያዩ መገናኛ ብዙሐን ወሳኝ ፕሮፓጋንዳዎችን በመፍጠር ወዥንብርን መንዛት ነው፡፡ ይሄ በዚህ ዘመን አይነተኛ ስልት ሆኖ ወያኔ አግኝታዋለች በእርግጥም እንዴት እየተጠቀመችበት እንደሆነ እያየን ነው፡፡ በለንደን ኢትዮጵያን እናፈራርሳለን ያለን ተናጋሪና የተናጋሪውን ሐሳብ በመደገፍ ከፍተኛ ድጋፍ የሰጠው ታዳሚ፣ በአትላንታ የኦሮምያን ቻርተር አዘጋጃለሁ ያለን ሌላው ስብሰባዎች ቅንብር ቀጥሎም በወያኔ ሚዲያ መቅረብ፣ ሌሎች ከዚህ በፊት ኦነግ የሰራላቸውን ፊልም በማቀናበር የኢትዮጰያን ሕዝብ አሸባሪ በሚል አዋጅ እንዲታወጅበት ሰነድ ምክነያት የሚሆን ለማዘጋጀት ሲጠቀምበት አናያለን፡፡
ኦነጋውያን የበሰሉ የወያኔ አጋሮች ናቸው፡፡ ለጊዜው የአማራው ብሔረተኛ ነኝ የሚለውን ቡድን በሕዝብ ዘንድ በጥርጣሬ እንዲታይባት ወያኔ አትፈልግም፡፡  ረጅም ዕቅዷ ግን በአማራው ክልል የሚኖሩ ሕዝቦችን አንዱን ከአንዱ ለመለየት በቅማንት የሞከረችውን ሙከራ በሌላ መልክና በስፋት ለማሳካት ያዘጋጀችው ቡድን ነው፡፡  የቡድኑን ባሕሪያት አስተውሉት ደጋግሞ የአማራው ሕዝብ እንደተበደለ ይነግረናል፡፡ አንዳንዶቹ ወጣት ነን በሚል ሰበብ አማራ ተወልደን አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያዊነቱ ሲገደል ነው የምናየው፡፡ ኢትዮጵያዊነቱ የሞቱ ምክነያት እንደሆነ ብቻ እንደተረዱ ይነግሩናል፡፡ አብዛኞቹ ኑሮዋቸውም አስተዳደጋቸውም አዲስ አበቤዎች ናቸው፡፡ ቀልደኞች ናቸው፡፡ ለእነሱ ወያኔ ጉያ ሥር በወያኔ ቅኝት ስላደጉ ኢትዮጵያዊነትን መካድ ቀላል ነው፡፡ በየቦታው ግፍ እየደረሰበት ያለው የአማራው ሕዝብ ልጆች ግን ከማንም በላይ ወያኔን ለመበቀል ልዩ ልብ ያላቸውና ምን ሴራ እየተሰራባቸው እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ኢትዮጵያዊነትም ከምንም በላይ ወያኔን ሊበቀሉብት የሚያስችላቸው ጉልበት፣ በዘለቄታዊውም ያለስጋት የሚኖሩበት ፍልስፍና እንደሆነ ያውቁታል፡፡  በአርሲ አረባጉጉ፣ ሐረር በደኖ ሌሎችም ኦነግና ወያኔ በትብብር ለፈጸሙበት ግፍ የአማራውና ሌሎች ክርስቲያን ሕዝቦች ሴራውን አሳምረው ያውቁታል፡፡ የኢትዮጵያዊነታቸውን ክብር መመለስና ወያኔን ማሳፈር እንጂ ለወያኔ ሴራ እጅ አልሰጡም፡፡ በዛም ተሳክቶላቸዋል፡፡ ዛሬ በአርሲም በሉት ባሌ፣ ሐረር ያለው የሕዝብ እንቅስቃሴን እነዚህ ወገኖች ሚናውን እስካላጠራ ድረስ መሳተፍን አልፈለጉም፡፡ ብዙዎች በእነዚህ አካባቢ የተደረጉን የባለፈው ተቃውሞዎችን ለምን የአማራው ሕዝብ አልተቀላቀለም የሚል ትችት ሲያቀርቡ ነበር፡፡ አባብ ሞኝን ሁለት ጊዜ ነደፈው ይባላል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ያለው እውነታ ከሌላው ቦታ ካለው ይለያል፡፡ የአኖሌን ሐውልት ወያኔና አጋሮቿ  ሲያቆሙ ምን እያደረጉ እንደሆነ ሕዝብ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ልብ በሉ ዝርዝሩን መናገር ስለሚያስቸግር ብዙ መዝለቅ አልፈልግም፡፡ የዚያን አካባቢ እንቅስቃሴ በዋነኝነት ሲመሩት የነበሩትን አስተውሉ፡፡ የሙስሊም መንግስት በኦሮምያ ለመመስረት ሕልም ያለው ቻርተር አዘጋጀሁ የሚለን ቡድን ነው፡፡ አሁን ብዙዎች እንደሚመስላቸው በዛ አካባቢ የአማራና ኦሮሞ ልዩት የለም፡፡ ችግሩ የሙስሊሙንና የክርስቲያኑን ሕዝብ ለመለያየት ነው ከፍተኛ ጥረት የሚደረገው፡፡  በእነዚያ አካባቢዎች ክርስቲያኑ በወያኔ ሥርዓት ላይ  በተደረጉ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ሊሳትፍ ሙከራ አድርጎ ነበር፡፡ ነገሮች ግን አቅጣጫቸውን ሲቀይሩ ብዙ ጊዜ ታይቷል፡፡ ወያኔና ኦነግ ለ25 ዓመት ያዘጋጀው የሙስሊም ኦሮሞ ጽንፈኛ ቡድን ሁሉን ዓቀፍ እንዲሆን አልፈለገም፡፡ ምክነያቱም በዚህ ቀውጢ ወቅት አንድ የሆነ ሕዝብ አንድነቱ እየተጠናከር በእርግጥም ወያኔን አደጋ ላይ የሙስሊም አክራሪነት ሕለመኛ ቡድኑንም ከሕልሙ ይገታዋል፡፡  አስተውላችሁ ከሆነ ወያኔ በእነዚያ አካባቢዎች የተደረጉ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ሐይማኖታዊ ይዘት እንዲኖራቸው ብዙ ስትሰራ ነበር፡፡ ውጭ ያለው የሙስሊም አክራሪ ቡድን ደግሞ ትልቅ ፕሮፓጋንዳና ገበያ ሲሰራበት ነበር፡፡  ይህ ሆኗል፡፡ በእነዚህ አካባቢ ያሉ የሕዝብ ተቃውሞዎች ለወያኔ ብዙም አልከበዳትም ነበር፡፡ ወያኔን ያስጨነቃት የኦሮምያ ተቃውሞ አለ ቢባል የምዕራብ ኦሮምያ በተለይም የዳጬ ዘር እየተባለ የሚወገዘው ሸዋ ነው፡፡ በእርግጥም ወያኔ ሸዋን ፈርታዋለች፡፡ በሰንዳፋ ቆሻሻ መጣያ ገንብታ ሕዝብ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷት እሺ  እንድትል ተገዳለች፣ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንንም ቢሆን እንዲሁ ያስፈራት  የዚሁ አካባቢ ሕዝብ ተቃውሞ ነው፡፡ አምቦ፣ ጊንጪ ፣ ወዘተ የመሳሰሉት ወያኔ የመጥፊያዋ ምክነያት ሁሉ እንደሚሆን ሳታምን አይቀርም፡፡ ይህ ሕዝብ ለአዲስ አበባ መቅረቡ ብቻም ሳይሆን ከኦሮሞ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ዛሬም የሚንቀሳቀስ የአባቶቹ ደም የሚታወሰው እንደሆነ ወያኔ ትረዳለች፡፡ የእነ መረራና በቀለ ቡድን እንግዲህ ከዚህ ጋር በተያያዘ ነው ወያኔ ትኩረት ያደረገችበት፡፡ ለዛም ትፈራዋለች፡፡ ትንሽ ጠንከር ካለ የት ድረስ እንደሚሄድ አሳምራ ታውቀዋለች፡፡ እስከዛሬ ይህን ሕዝብ ዳጬ በሚል ጀግኖች አባቶቹን የውርደት ተምሳሌት እያደረገች ስታሸማቅቀው ኖራለች፡፡ ዛሬ ላይ በኩራት ጎበና ጀግና እንጂ ባንዳ እንዳልሆነ የሚናገሩ የዚሁና ሌሎችም አካባቢ ኦሮሞውች ብቅ እያሉ ነው፡፡ በእርግጥም ጎበናና አያሌ መሰል ጀግኖች  የኦሮሞ ሕዝብ ኩራት ናቸው፡፡ ኦሮሞ የተዋረደው እነዚህን ልዩ ተምሳሌቶቹን ባንዳ ናቸው ካሉት ጋር አዎ ናቸው ብሎ የዘመረ ዕለት ነው፡፡ እነ ተስፋዬ ገብረ አብ አና ሌሎች የወያኔ ቅጥረኞች የጻፉለትን ተከትሎ ጆግኖቹን ጣለ፣ ሰደበ፣ መጨረሻ ግን ረሱ ተዋረደ፡፡ ይህ የሆነው በታሪክ እስከ ደርግ ዘመን ድረስ የምናውቃቸው ታላላቅ ጀግኖች መፍለቂያ የሆነው የኦሮሞ ሕዝብ ነው፡፡ በብዙ የኦሮሞ ጀነራሎች የምናውቀው የኢትዮጵያ ሠራዊትም ዛሬ ምን እንደሆነ እዩት፡፡ እንዲህ ነው የሆነው፡፡ አዎ ወያኔን እነ ጎበና ያስፈሯታል፡፡ ጎበና ዛሬ የምናውቃትን ኢትዮጰያን አንድ ያደረገ፣ በምዕራብ በኩል በቦረዳ በከሬ ላይ ዘምቶ የነበረውን የሱዳን ጦር ተዋግቶ የመለሰ፣ ከዚያም በላይ ለአገር ምስረታና የልማት ፈርቀዳጅ የነበረ ነው፡፡ ለዛም ነው የሚኒሊክ ቀኝ እጅ የሚባለው፡፡ ሚኒሊክ ያለ ጎበና ዛሬ የሚያስደምሙንን ስኬቶች ባልተሳካለት ነበር፡፡ ሚኒሊክ ያለ ገበየሁ ጎራና ሌሎች አያሌ የኦሮሞ ጀግኖች አደዋን እውን ባላደረጋት ነበር፡፡ ሚኒሊክ ያለ ሐብተጊዮርጊስ ዲነግዴ የሀገር ልማትና አመራር ስኬቱ ባልሠመረለት ነበር፡፡ ወያኔዎችን አንደ እሳት የሚያቃጥላቸውና የሚያስፈራቸው ይህ ታሪክ ነው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ይህን ታሪክ እንዲክድ ነው የተደረገው፡፡ አሊያማ ማነው ከኦሮሞ ልጅ አገርን ለጠላት የሸጠ?  ማን ነው አሳፋሪ ታሪክ ያለው? በአንጻሩ የወያኔ አያቶች ወይም አባቶች እኮ ናቸው አገርን ለጠላት የሸጡት፡፡ ባንዳው ኃይለሥላሴ ጉግሳ እኮ ትግሬ እንጂ ኦሮሞ አደለም፡፡
እንግዲህ እንዲህ ያሉ በጆሮም የሰማናቸው፣ በታሪክም ያነበብናቸው፣ አልፎም እስካሁንም ብሕይወት ያሉ አባቶቻችን እውነቱን እየነገሩን ወያኔ ከአጋሯ ኦነጋውያን ጋር የኦሮሞ ማነታችንን ክብር የሆነውን ታሪክ ጥለን መካን እንድንሆን አድርጋለች ከሞላ ጎደል ተሳክቶላታል፡፡ ጎዳዩ የኦሮሞ ሕዝብ መበደልና አለመበደል ሳይሆን ከመሠረታዊ ማንነቱ ማፈናቀልና መሠረት የሌለው የባዘን እንደተፈለግ የሚዘወር ለማድረግ ነው፡፡ አሁን በአማራው ብየረተኛ ነኝ በሚለው ቡድንም እየተሰራ ያለው የዚሁ ስልት ግልባጭ በአማራው ሕዝብ ላይ ነው፡፡ አንዴ ከኢትዮጵያዊነቱ ከአፈናቀለችው ምን እንደሚሆን ታውቀዋለች፡፡ እና ኢትዮጵያዊ ነኝ የምትል እየሆነ ያለው ይሄ ነው፡፡ የአማራን ሕዝብ በደል ከአዲስ አበቤ አደጎቹ የወያን ማደጎዎች በላይ ዝርዝሩን የምናውቅ ብዙ አለን፡፡ ማንም እየተነሳ የራሱን ሕልም የሚያሳካበት ሕዝብ ልንሆን አይገባም፡፡ አሁን እየተደረገ ያለው የአማራው ተጋድሎ በቀጥታ ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን ከምንም በላይ በሚቀድምባቸው የአማራው ልጆች እንጂ የወያኔ ማደጎ በሆነው ብሔረተኛው ቡድን አደለም፡፡ ከላይ የኦሮሞውን ሕዝብ ብዙ ለመዘርዘር የፈለኩት እውነታውን ለሕዝብ ለማስረዳት እንዲመቸኝ ነው፡፡ እንዴት የራሱን አኩሪ ታሪክ ሲጥል አቅም እንዳጣ፡፡ እንዴት ከኢትዮጵያዊነቱ ራሱን ሲያሳንስ መጫወቻ እንደሆነ፡፡ እንዴት ዛሬ ያለብት ሁኔታ ላይ እንደደረሰ፡፡ እንደ እውነቱ የኦሮሞውም ሕዝብ ከአማራው ሕዝብ ባልተናነሰ አልቋል፡፡ ኦነጋውያን በሞቁ የአውሮፓና አሜሪካ ከተሞች እየኖሩ ሥንት የሕዝብ ልጅ ኦነግ ነህ በሚል እንደታረደ ቤቱ ይቁጠረው፡፡  እላለሁ የአማራው ብሔረተኛ ቡድን ነኝ የሚለው የኦነግ ግልባጭ በአማራው ክልል ነው፡፡
በአለፈው ኢትዮጵያዊነትን ከአማራው ሕዝብ አእምሮ የማጥፋት ዘመቻ አዲሱ የወያኔ ስልት በሚል በጻፍኩት ጽሁፌ አንድ አስተያየት ሰጭ የአማራው ብሔረተኛ ቡድንን ለመከላከል በሚመስል መልስ ሰጥቷል፡፡ ከቅንነት ከሆነ አመሰግናለሁ፡፡ ብሄረተኛው ቡድኑ ከአሳመኗቸው አንዱ ከሆንክ ቀስ ብለህ አስተውለው፡፡ ከሴራው ተዋናዮች አንዱ ከሆንክ ግን ሥራህ ስለሆነ አልመክርህም፡፡ የግንቦት 7ን በጥልቀት እንድተችልህም የፈለግህ ይመስላል፡፡ እንደእውነቱ ስለግንቦት ሰባት እኔም ያለኝ እውቅት ውሱን ነው፡፡ ከድርጊቱ ግን ከአደገኛ ቡድኖች እንደአንዱ እንዳይሆን እፈራለሁ፡፡ ወደፊት ላገኝ የምችለው መረጃ ካለ የደረስኩበትን አካፍላለሁ፡፡  አንድ እውነት ግን ለብዙዎች የተከሰተላቸው መሠለኝ ግንቦት 7 ተብዬው በወሬ እንጂ ምድር ላይ የትም እንደሌለ፡፡ እየዋሸም እንደሆነ፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ከሴረኞች እንደ አንዱ ነው ወይስ ሊሳካለት ያልቻለ ግን ቢችል ለመታገል ፍላጎት ያለው የሚለው ግልጽ አይደለም ለእኔ፡፡ ከሴረኞቹ አንዱ ሊሆን እንማይችል ማረጋገጫ የለም ይልቁንም ከሴረኞቹ አንዱ ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬ የሚያጭሩ ነገሮች አሉ፡፡ የአርባምንጩ ጥቃት፣ ሕዝብ ከዳር እዳር ተቃውሞውን እያሰማ አንድም ቦታ ሊሳተፍ አለመቻሉ፣ አሁንም በአማራው ክልል ሌሎች የሚያደርጉትን ተጋድሎ የእኔ የሚል ገበያ ለመፍጠር እየሞከረ ሊሆን እንደሚችል፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የወያኔን ጥፋት የማይፈልገውን ሻቢያን ለትግሉ አጋዥ ማድረጉ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአንዳርጋቸው ጽጌ የተያዘበት ሂደት ሁኔታ ግንቦት ሰባትን ከሴረኞቹ እንደ አንዱ የወያኔ አጋር ያስጠረጥረዋል፡፡ ወያኔና ሻቢያ በአንድ ቤተሰብ የሚመሩ ሁለት ቡድን እንደሆነ አትዘንጉ፡፡ ግንቦት 7 ይሄን አያውቅም? ወይስ ……?  ከዛ ይልቅ በቀለለ በሱዳን የተሻለ እድል ነበር፡፡ ሱዳን የወያኔ ወዳጅ ነው ከሚለው ሻቢያ የወያኔ ጠላት ነው የሚለው አያሳምንም፡፡ በሕገወጥም በሌላም መልኩ ቢሆን በሱዳን በኩል ብዙ እድሎች አሉ፡፡ ያልተረጋጋውን የደቡብ ሱዳንን ጨምሮ በመጠቀም፡፡ ያም ባይሆን ግን ትግሉን የአጎራባች አገር ሳያስፈልገው ከውስጥ ሊያጧጡፈው የሚችልበት ሌሎች እድሎች እንዳሉ ይሰማኛል፡፡ ሻቢያ ግን በየትኛውም መስፈርት አጋር ሊሆን የሚችል አደለም፡፡
እግዚአብሔር አገራችንን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይጠብቅ!
አሜን!
ሰርጸ ደስታ

No comments:

Post a Comment