Thursday, December 15, 2016

የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ዮናታን ተስፋዬ በእስር ላይ የሚገኙ ታዋቂ ሰዎችን ለምስክርነት ጠርቷል።


የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ዮናታን ተስፋዬ በእስር ላይ የሚገኙ ታዋቂ ሰዎችን ለምስክርነት ጠርቷል።
እስክንድር ነጋ በከፍተኛ ጥበቃ ታጅቦ ፍርድ ቤት መጥቷል።
የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት የነበረውና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ዮናታን ተስፋዬ ተከላከል በተባለበት የፀረ ሽብር አንቀፅ 6 ‘በፅሁፍ ሽብርተኝነትን ማበረታታት ወንጀል’ ህዳር 19/2009ዓ.ም ፍርድ ቤት ቀርቦ የነበረ ቢሆንም መከላከያ ምስክሮች ባለመሟላታቸው ምክንያት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶታል።
አቶ ዮናታን በመከላከያ ምስክርነት ታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት፣ በኮማንድ ፖስቱ ቁጥጥር ስር የሚገኘውና በአዋሽ አርባ የወታደሮች ካምፕ የሚገኘው የዞን፱ ጦማሪ በፍቃዱ ሀይሉ እና የኦፌኮን ምክትል ሊቀመንበርና በሽብር ወንጀል ተከሰው በቂሊንጦ እስር ቤት የሚገኘው አቶ በቀለ ገርባ ከማረሚያ ቤት በመከላከያ ምስክርነት ያስሞላ ቢሆንም ጦማሪ በፍቃዱ ሀይሉን ያሰረው አካል ሳያቀርበው ቀርቷል። አቶ እስክንር ነጋ “በፅህፈት ቤት ትፈለጋለህ ተብዬ ነው የመጣሁት፣ የፍርድ ቤት መጥሪያም አልደረሰኝም፣ ስለምመሰክርበት ጉዳይ ለማወቅና ለመዘጋጀት ጊዜ ያስፈልገኛል” ብለዋል። የአስራ ስምንት አመት ፍርደኛ የሆነው እስክንድር ነጋ ፍርድ ቤት በቀረረበት ወቅት ቁጥራቸው የበዛ ወታደሮች ያጀቡት ሲሆን በእለቱ ጉዳዩን ሲከታተሉ የነበሩት ዳኞች ይሄ ሁሉ ወታደር ፍርድ ቤት ውስጥ አያስፈልግም በማለት እንዲቀነሱ ማድረጋቸው ታውቋል።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ዮናታን ተስፋዬ በምስክርነት ካካተታቸው ውስጥ ወላጅ አባቱ አቶ ተስፋዬ ረጋሳ፣ የህግ ምሁሩ ዶር ያዕቆብ ሀ/ማርያም፣ እህቱ ገዳምነሽ ተስፋዬ፣ የቅርብ ጓደኛ ኤፍሬም ታያቸው እንዲሁም የፍልስፍና መምህር ዶር ዳኛቸው አሰፋ ይገኙበታል።
አቶ ዮናታን ለፍርድ ቤቱ ምስክሮቼን አሟልቼ እንድመጣና ተለዋጭ ቀጠሮ ያሰጠኝ ባለው መሰረት ፍርድ ቤቱ ለታህሳስ 26/27 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

No comments:

Post a Comment