Wednesday, December 28, 2016

በቤኒሻንጉል ቡለን ወረዳ በአማራ ተወላጆች ላይ ግፍና በደል እየተፈጸመ መሆኑ ተገለጸ


ኢሳት (ታህሳስ 18 ፥ 2009)
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቡለን ወረዳ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ግፍና በደል እየተፈጸመባቸው መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ።
በአካባቢው የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች እስራትና ድብደባ የሚፈጸምባቸው የጦር መሳሪያ ታዘዋውራላችሁ በሚል መሆኑን ዕማኞች ለኢሳት ተናግረዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በአማራ ክልል አጎራባች ወረዳዎች በተለይም የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ፕሮጄክቶች ባሉበት አካባቢ የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ለስርዓቱ ስጋት መሆኑን ይነገራል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች በአካባቢው የመንግስት ታጣቂዎች ተደጋጋሚ ግፍና በደል ሲደርስባቸው ቆይቷል። በዚሁም ሳቢያ በርካታ ህጻናት ሴቶችና አባወራ የአማራ ተወላጆች እስከመፈናቀል ደርሰዋል። በተለይም ከ2005 ጀምሮ እየደረሰባቸው ያለው እስራትና ድብደባ እንዲሁም መፈናቀል የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) የሚመራው የአማራ ክልል ምንም አይነት ድጋፍም ሆነ የተቃውሞ ድምጽ አላሰማም። ይልቁንም፣ የክልሉ አመራር በቅርቡ ከተከሰተው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ከህወሃት ጋር ቁርኝት ያላቸው ጥቂት የትግራይ ተወላጆች ጉዳት ደርሶባቸዋል በሚል ይቅርታ የጠየቁበት ሁኔታ መኖሩ ነው የሚታወቀው። ለእነዚሁ የትግራይ ተወላጆች የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉም አይዘነጋም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ የአማራ ተወላጆች በተለይም በቡለን ወረዳ አለምበር በቁጅና ጭራንቆ ቀበሌዎች የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ከፍተኛ ስቃይና በደል እየደረሰባቸው መሆኑን ስማቸው እንዳይጠቀስ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል። ሰብላቸውንም እየተቀሙ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደአካባቢው ነዋሪዎች ገለጻ፣ ይህንኑ ግፍና በደል የሚፈጽሙ የክልሉ የቀበሌና የወረዳ አመራሮች ታጣቂዎች ናቸው። ትዕዛዙ የሚመጣው ደግሞ ከላይ በክልሉ በኩል ካሉ አመራሮች በኩል መሆኑን የአካባቢው ምንጮች ይገልጻሉ።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በአማራ ክልሎች አጎራባች ወረዳዎች በተለይም በጣና በለስ አካባቢ የስኳር ፕሮጄክቶች ባሉበት አካባቢ ከፍተኛ ውጥረት መኖሩ ይነገራል። በዚያ ስፍራ የነጻነት ሃይሎች ስርዓቱን መታገል መጀመራቸውም ነው የሚነገረው። ይህንኑ ለማስቆም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአካባቢውን አመራሮች ሰብስበው የአካባቢው ጸጥታ ቁጥጥር እንዲደረግበት ጥብቅ መመሪያ ማስተላለፋቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በጣና በለስ ዙሪያ ስኳር ፋብሪካ ለመገንባት በሚል በህወሃት ጄኔራሎች የሚመራው የብረታብረትና ኢንጂነሪን ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የልማት አካባቢውን ተቆጣጥሮት ይገኛል። በርካታ ወጣቶችን ከትግራይ ክልል በማስወጣት አሰማርቶ የሚገኘው ሜቴክ በጃዊና አካባቢ የተፈናቀሉ አርሶ አደሮችና ነዋሪዎች ተቃውሞ እያሰሙ በመሆናቸው አካባቢው ውጥረት ውስጥ ይገኛል። በአካባቢው የነጻነት ሃይሎች ጥቃት መሰንዘር በመጀመራቸው ሁለት ታንኮች ገብተው እንዱ መቃጠሉን በቅርቡ ዕማኞች ለኢሳት መናገራቸው ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment