[ክቡር ሚኒስትሩን ሾፌራቸው ከቤታቸው እየወሰዳቸው ነው]
  • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
  • ምን ሆንክ?
  • እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
  • ምንድን ነው የምትለው?
  • ራስዎትን ተመልክተውታል?
  • ሁሌም ራሴን እንደተመለከትኩ ነው፡፡
  • ታዲያ እንዴት እንዲህ ያደርጋሉ?
  • እኔ ምንም አላደረኩም፡፡
  • ሸሚዝዎትን አይተውታል?
  • ምን ሆነ ሸሚዜ?
  • ታኝኮ የተተፋ ነው እኮ የሚመስለው፡፡
  • ምን አልክ አንተ?
  • ለጨዋታ ብዬ ነው፡፡
  • ከእኔ ጋር የምን ጨዋታ ነው?
  • ይቅርታ አልተተኮሰም ለማለት ነው፡፡
  • እና በምኔ ልተኩሰው?
  • ኧረ ክቡር ሚኒስትር ሠራተኛዋ ምን ሠርታ ትበላለች? እሷ ትተኩሰው እንጂ፡፡
  • እኮ እሷስ በምኗ ትተኩሰው?
  • እንዴ በካውያ ነዋ?
  • መብራት ከጠፋ እኮ ሰነባበተ፡፡
  • ምን?
  • ይኸው ሦስት ቀን ሞላን፡፡
  • እየቀለዱ ነው ክቡር ሚኒስትር?
  • የምን ቀልድ ነው?
  • ሚኒስትር እኮ ነዎት፡፡
  • ብሆንስ ታዲያ?
  • ብዙ የገባዎት አልመሰለኝም፡፡
  • ምኑ ነው ያልገባኝ?
  • ሚኒስትርነት፡፡
  • ምን ማለትህ ነው?
  • ክቡር ሚኒስትር አንድ ነገር ልንገርዎት?
  • ምንድን ነው የምትነግረኝ?
  • የቀድሞው አለቃዬን ያውቋቸዋል?
  • የተነሱት ሚኒስትር?
  • የተሾሙት በሉኝ እንጂ፣ ኢሕአዴግ መቼ ማንሳት ያውቃል?
  • እ…
  • ሲጀመር የእሳቸው ቤት መብራት ጠፍቶ አያውቅም፡፡
  • እሺ፡፡
  • ቢጠፋም ፋብሪካ የሚያንቀሳቅስ ጀነሬተር ቤታቸው አለ፡፡
  • ምን?
  • ምን ይኼ ብቻ?
  • ሌላ ምን አለ?
  • ከጥበቃቸው ጋር ሁሌ እንደተጣላን ነበር፡፡
  • ለምን?
  • እሱ ራሱ ዴኤስቲቪ ክፍሉ ተገጥሞለታል፡፡
  • እ…
  • በቃ ሁሌ ኳስ እያየ በር እንኳን አይከፍትልኝም፡፡
  • ለምን እንደተባረሩ ገባኝ፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ለምን እንደተሾሙ ገባኝ ማለትዎ ነው?
  • እ…
  • እሳቸው ቤት ቁርስ የበላሁ ዕለት ቀኑን ሙሉ ምግብ አልበላም ነበር፡፡
  • ለምን?
  • ቁርሱ ራሱ ድግስ በሉት፡፡
  • አስገራሚ ነው፡፡
  • እርስዎም ራሱ አስገራሚ ነዎት፡፡
  • እንዴት?
  • መብራት ጠፍቷል ሲሉኝ ነዋ፡፡
  • ምን ላድርግ?
  • እኔ ግን አንድ ምክር ልምከርዎት፡፡
  • ምንድን ነው?
  • በአግባቡ ይጠቀሙበት፡፡
  • ምኑን?
  • ሹመትዎን!
[ክቡር ሚኒስትሩ የቦርድ ሊቀመንበር ከሆኑበት አንድ የልማት ድርጅት ኃላፊ ጋር እየተወያዩ ነው]
  • ክቡር ሚኒስትር ስለተገናኘን ደስ ብሎኛል፡፡
  • ሥራ አይደለ እንዴ ምን ችግር አለው?
  • የቀድሞውን ሚኒስትር ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡
  • ለምን?
  • በቃ ራሳቸውን የሚጠቅማቸው ነገር ከሌለ ወደዚህ ዝር ማለት አይፈልጉም፡፡
  • ምን ታደርገዋለህ?
  • ለነገሩ ምን ያድርጉ?
  • እንዴት?
  • እስር ቤት የሚገባቸው ሰውዬ ሹመት ነው የጠበቃቸው፡፡
  • እ…
  • ለማንኛውም ስለጨረታው እናውራ ብዬ ነው፡፡
  • እሺ ምን ዓይነት ጨረታ ነው የሚወጣው?
  • ሁለት ዓይነት ጨረታ ማውጣት እንችላለን፡፡
  • ምንና ምን ዓይነት?
  • ግልጽ ወይም ዝግ ጨረታ፡፡
  • አሁን የትኛውን ዓይነት ጨረታ እናውጣ ታዲያ?
  • እኔ ግልጽ ጨረታ ቢወጣ ባይ ነኝ፡፡
  • ለምን?
  • ዝግ ጨረታው ለሙስና በጣም ተጋላጭ ነው፡፡
  • እንዴት?
  • ያው ለዝግ ጨረታው የሚመረጡት ሰዎች አደገኛ ሙሰኞች ናቸው፡፡
  • ስለዚህ ግልጽ ጨረታ ይደረጋ?
  • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ዓለም አቀፍ ተቋማት ብቻ ይሳተፉ ወይስ የአገር ውስጦቹም ይኑሩበት?
  • የአገር አቀፎቹም ቢኖሩ መልካም ነው፡፡
  • አቅም አላቸው ግን?
  • እሱን በውድድሩ ያሳዩ፡፡
  • በቃ እንደዛው ይደረግ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ሲገቡ አማካሪያቸውን አገኙት]
  • ሪፖርቱን እየሠራህ ነው?
  • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን ያህል ገጽ ሠራህ?
  • ገና ሁለተኛ ገጽ ላይ ነኝ፡፡
  • ምን?
  • ሥራ ስለሚበዛብኝ ነው እኮ፡፡
  • የ50 ገጽ ሪፖርት እንደምፈልግ ታውቃለህ አይደል?
  • ምን ችግር አለው? ከቀድሞው ሪፖርት ኮፒ ፔስት ማድረግ ነው፡፡
  • እ…
  • ከፈለጉም ከኢንተርኔት ኮፒ ማድረግ እችላለሁ፡፡
  • ስማ ለሚኒስትሮች የሚቀርብ ሪፖርት እኮ ነው፡፡
  • ምን ችግር አለው?
  • አንተ በዚህ አቅምህ እንዴት ነው ከእኔ ጋር የምትሠራው?
  • እኔ የምልዎት ጠዋት የት ሄደው ነበር ግን?
  • የቦርድ ሊቀመንበር የሆንኩበት የልማት ድርጅት ስለሚያወጣው ጨረታ ለመነጋገር እዛ ነበርኩ፡፡
  • አልሰሙም እንዴ?
  • ምኑን?
  • ጨረታው መሰረዙን?
  • እ…
  • ጨረታው እኮ የበርካታ ባለሥልጣናትን ቀልብ ስቧል፡፡
  • እና?
  • ተሰረዘ፡፡
  • እንዴት?
  • በአንድ የስልክ ጥሪ!
[አንድ ነባር ሚኒስትር ለክቡር ሚኒስትሩ ስልክ ደወሉላቸው]
  • ተመስገን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን ተገኘ?
  • ስልክዎት ሠራ ብዬ ነዋ፡፡
  • እምቢ ብሎ ነበር አይደል?
  • በተደጋጋሚ ነበር የሞከርኩልዎት፡፡
  • ውጭ ነበርኩ፡፡
  • እሱማ ሰምቻለሁ ግን…
  • ምነው?
  • ማለት ገና ከመሾምዎት…
  • ምን?
  • ጉዞ አበዙ፡፡
  • ለሥራ እኮ ነው የምሄደው፡፡
  • ቢሆንም በየሳምንቱ የውጭ ጉዞ እንዴት ነው?
  • በሪሰርቸርነቴ አይደለም እኮ እየሄድኩ ያለሁት፡፡
  • እሱማ ይገባኛል፡፡
  • አገር ወክዬ እኮ ነው የምሄደው፡፡
  • ያው ዓይን ውስጥ እንዳይገቡ ብዬ ነው፡፡
  • ማለት?
  • የሚባለው እኮ ሌላ ነው፡፡
  • ምንድን ነው የሚባለው?
  • ከአየር ላይ ነው እየመሩት ያለው እየተባለ ነው፡፡
  • ምኑን?
  • መሥሪያ ቤቱን፡፡
  • ወሬኞች በላቸው፡፡
  • ሌላም ነገር ተብለዋል፡፡
  • ሌላ ምን?
  • ክቡር ካፒቴን!
[ክቡር ሚኒስትር ቢሮ አንድ የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኛ ገባ]
  • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ሰላም እንዴት ነህ?
  • ጥሩ ሰው መሆንዎትን ሰምቻለሁ፡፡
  • አመሰግናለሁ፡፡
  • በርካታ ለውጦች ያመጣሉ ብዬ አስባለሁ፡፡
  • ምንድን ነው የምትሠራው?
  • ጠቅላላ አገልግሎት ላይ ነው የምሠራው፡፡
  • ብዙ ዓመት ሠራህ?
  • ጡረታ ለመውጣት አምስት ዓመት ነው የቀረኝ፡፡
  • ቆይተሃላ?
  • መሥሪያ ቤቱን በሚገባ አውቀዋለሁ፡፡
  • እስቲ ንገረኝ?
  • ሕይወቴን የነጠቀኝ መሥሪያ ቤት ነው፡፡
  • እንዴት?
  • የቀድሞው ሚኒስትር ግፈኛ ነበሩ፡፡
  • ማለት?
  • ሁሌም ባዶ ተስፋ ይሰጡኝ ነበር፡፡
  • የምን ባዶ ተስፋ?
  • ይኸው ይኼን ያህል አገልግዬ የኮንዶሚኒየም ቤት እንኳን የለኝም፡፡
  • እሺ፡፡
  • እሳቸው ግን ሁሌም የማያደርጉትን ነገር እንደሚያደርጉልኝ ያወሩልኝ ነበር፡፡
  • ምን ታደርገዋለህ?
  • ለራሳቸው ግን ቤት ሳይሆን ቤተ መንግሥት ነው የገነቡት፡፡
  • ካልኖሩበት ምን ይጠቅማል ብለህ ነው?
  • እኔ የመጣሁት እንደሳቸው እንዳይሆኑ ለመምከር ነው፡፡
  • እንደሳቸው ምን እንዳልሆን?
  • ክቡር ሙሰኛ!
[አንድ ደላላ ክቡር ሚኒስትር ቢሮ ገባ]
  • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን ፈልገህ መጣህ?
  • ጉዳይ አለኝ፡፡
  • የምን ጉዳይ?
  • በርዎት ክፍት መስሎኝ፡፡
  • ለአንተ ግን ክፍት አይደለም፡፡
  • ረሱት እንዴ?
  • ምኑን?
  • የሰጡትን መግለጫ፡፡
  • የምን መግለጫ?
  • ለሁሉም ኢትዮጵያዊ በሬ ክፍት ነው ብለው ተናግረው ነበር፡፡
  • እሱማ ክፍት ነው፡፡
  • ታዲያ እኔ ላይ ለምን ይዘጉታል?
  • ስማ ከሙሰኞች ጋር መሥራት አልፈልግም፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ቢሰሙኝ ጥሩ ነው፡፡
  • ምንድን ነው የምሰማው?
  • የምሰጥዎትን ምክር፡፡
  • ምን?
  • አብረን እንብላ፡፡
  • ውጣ ከዚህ፡፡
  • ምን አጠፋሁ?
  • ውጣልኝ፡፡
  • በሬ ክፍት ነው ብለው?
  • ለአንተ መከፈት ያለበት ሌላ በር ነው፡፡
  • የምን በር?
  • የእስር ቤት!