በአንድ ስብሰባ ላይ፣ የኦዴፍ መሪ ኦቦ ሌንጮ አሁን ያለውን የፌዴራል አወቃቀርና አሁን ያለችዋ ኦሮሚያ እንድትቀጥል የድርጅታቸው አቋም እንደሆነ ገልጸዋል። ከሶስት አመታት በፊት ዶር በያንም በኢሳት ተመሳሳይ ነገር ሲናገሩ ሰምቻለሁ። ይህ የኦዴፍ አቋም የብዙ የኦሮሞ ልሂቃን አቋም ነው። ብዙ ሊያስገርመን አይገባም። እነ ኦቦ ሌንጮ ያመኑበትን፣ አቋሞቻቸዉን ማንጸባረቃቸው ሙሉ መብታቸው ነዉና ሊያስከፋንም ሆነ ሊያከራክረን አይገባም።
ወደ ዋናው ሐሳቦቼ ዝርዝር ከመሄዴ በፊት ሶስት ነጥቦችን መጀመሪያ ግልጽ እንዳደርግ ይፈቀድልኝ።
- አንደኛው ኦሮሚያ የሚባለው ነገር የመጣው በወያኔ መሆኑ ነው። ኦነግ የፈጠረውና ወያኔ ተግባራዊ ያደረገው ካርታ ነው። ስለዚህ ምንም አይነት የታሪክም፣ የሕግም የሞራል መሰረት የለውም።
- ሁለተኛ በኦሮሚያ ኦሮሞ ያልሆኑ ወይም ኦሮምኛ የማይናገሩ እጅግ በጣም ብዙ ናቸው። የኦሮሞ ትላልቅ ከተሞችን እንኳን ብንወስድ በብዛት ኦሮምኛ የማይናገሩ የሚኖሩባቸው ናቸው።
- ሶስተኛ ብዙ የኦሮሞ ከተሞችን አዳማን፣ አሰላን ጨመሮ የተቆረቆሩት፣ የኦሮሞ ብሄረተኞች ነፍጠኛ ወይም ጎበናዉያን በሚሏቸው ነው።
አሁን ኦሮሚያ የምትባለው መቀጠል እንዳለባት እንደ ኦቦ ሌንጮ ሊከራከሩ ከላይ ለዘረዘርኳቸው ነጥቦች ያላቸውን ምላሽ ብያስረዱን ጥሩ ነበር። ኦሮሚያ በታሪክ ያልነበረች፣ ያለ ሕዝብ ፍላጎት በሕዝብ ላይ የተጫነች፣ ጸረ-ዴሞራሲያዊና ዘረኝነት አሰራር የሞላበትና ሌላውን ማህበረሰ ያገለለች ክልል ናት የሚል እምነት ነው ያለኝ። ይሄንን ለማሳየት ሌሎች መረጃዎችን ማቅረብ አያስፈልግም። አሁን ያለዉን የኦሮሚያ ሕገ መንግስት ብቻ መመልከት በቂ ይሆናል። የአቶ ጁነዲን ሳዶ ፊርማ ያለበት፣ የኦሮሚያን ሕግ መንግስት በሚከተለው ሊንክ ማግኘት ይቻላል።
በዚህ ሕግ መንግስት ሶስት ሐሳቦችን ብቻ ለጊዜው ማንሳት እፈልጋለሁ።
- ኦሮሚያ የማን ናት ?
በአንቀጽ 8 “የኦሮሞ ሕዝብ የክልሉ የበላይ ሥልጣን ባለቤት ሲሆንም የሕዝቡ የበላይነትም የሚገለጸው በሚመርጣቸው ተወካዮችና ራሱ በቀጥታ በሚያደርገው ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ነው” ይላል። ይህ ማለት በዚህ ሕገ መንግስት መሰረት አያቶቹና ቅድመ አያቶቹ አዳማ ከተወለዱ ከናዝሬት ልጅ ይልቅ፣ ኦሮሞ ስለሆነ ብቻ፣ አዳማና አካባቢው ደርሶ የማያወቅ፣ የነጆ፣ ወይም የደደር ልጅ፣ የናዝሬት/አዳማ ባለቤት ተደርጎ ነው የሚወሰደው። እንግዲህ ኦሮሚያ ማለት ይሄ ነው ? በአገራቸው ሌሎች እንደ እንግዳ የሚታዩበት ክልል።
- አማርኛ ለምን ይጠላል ?
በዚሁ በኦሮሚያ ሕግ መንግስት ላይ፣ በአንቀጽ 39፣ ኦሮሞው ” ቅርሱንና ታሪኩን የመንከባከብና የማበልጸግ እንዲሁም በቋንቋው የመጠቀም፣ ቋንቋዉን የማሳደግና ባህሉን የመግልጽ መብት አለው” ይላል። ይሄ ተገቢና ሊከበር የሚገባው መብት ነው። ሆኖም ግን የኦሮሚያ ሕግ መንግስት አፋን ኦሮሞ ለማስፋፋት አማርኛን ማጥፋት ያስፈለጋል የሚል መንፈስ ያለበት ሰነድ ነው። ብዙ የኦሮሞ ልሂቃንም አማርኛን እንደ አፋን ኦሮሞ ጠላት አድርገው ነው የሚያዩ ነው የሚመስለው። አማርኛ ከተነገረ አፋን ኦሮሞ የሚጠፋ ይመስላቸዋል። ከዚህም የተነሳ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 5 ላይ ” ኦሮምኛ የሥራ ቋንቋ ይሆናል። የሚጻፈውም በላቲን ፊደል ነው” ብለው፣ በህግ ደንግገው አማርኛ መግባቢያ እንዳይሆን ለማድረግ ሞክረዋል። በኦሮሚያ ትላልቅ ከተሞች በሚኖሩ በአብዛኞቹ የሚነገረው አማርኛ፣ ቢያንስ ከአፋን ኦሮሞ ጎን የሥራ ቋንቋ እንዲደረግ እንኳን ለማድረግ አልታሰበም።
ለምሳሌ አዳማን እንመልከት። 85% ኦሮምኛ ተናጋሪ አይደለም። አብዛኛው አማርኛ ተናጋሪ ነው። ሆኖም ለአገልግሎት ወደ ከንቲባው ጽ/ቤት፣ ወይም ፖሊስ ጣቢያ ..ሲኬድ፣ ሰራተኞቹ አማርኛ እያወሩም፣ ማመልከቻ የሚጻፈው ግን በቁቤ ነው። ለምን ከአፋን ኦሮሞ በስተቀር ምንም ነገር አይኑር ስለተባለ። ይሄ ሴንስ የማይሰጥ ነገር ነው። እንግዲህ ኦሮሚያ ማለት ይሄ ነው ? አማርኛ እንደ ጠላት የሚታይበት።
- ኦሮምኛ የማይናገር በመንግስት መሶርያ ቤት ለምን አሰራም ለምን አይመረጥም ?
የመምረጥና የመመረጥ መብት በሚል በአንቀጽ 38 ፣ ንኡስ አንቀጽ “ሀ” ላይ ” ማንኛውም የክልሉ ሕዝብ በዘር፣ በቀለም፣ በብሄረሰብ፣ በጾታ ፣ በቋንቋ ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም በሌላ አቋም ላይ የተመሰረተ ልዩነት ሳይደረግበት የሚከተሉት መብቶች ይኖሩታል” ብሎ ይደነግጋል። ይሄ ግሩም አባባል ነው። መሆንም የነበረበት ይሄው ነበር። ሆኖም በዚሁ ሕግ መንግስት በንኡስ አንቀጽ “ለ”፣ ንኡስ አንቀጽ “ሀ”ን መልሶ ይሽረዋል። “በዚህ ሕግ መንግስት አንቀጽ 33 የተጻፈው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እድሜው 18 ዓመት ሲሞላ በሕግ የመምረጥ፣ 21 አመት ሲሞላው የመመረጥ መብት አለው” ይላል። ወደ አንቀጽ 33 ስንሄድ “በክልሉ ዉስጥ ነዋሪ የሆነና የክልሉን የሥራ ቋንቋ የሚያወቅ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በማንኛውም የክልሉ መንግስታዊ ወይም ሕዝባዊ ሥራ ተመርጦ ወይም ተቀጥሮ የመስራት መብት አለው” ሲል ለመመረጥ ቅድመ ሁኔታን ያስቀምጣል። አፋን ኦሮሞ የማይችል ሰው የክልሉ መንግስት ሆነ የዞን ወረዳዎች መስሪያ ቤቶች ተቀጥሮ መስራት አይችልም ማለት ነው።፡አራት ነጥብ።
97% አፋን ኦሮሞ ተናጋርዎች በሚኖሩባቸው እንደ ቀለም ወለጋ ፣ ምእራብ ወለጋ ባሉ ዞኖች የሥራ ቋንቋ አፋን ኦሮሞ ቢሆን ችግር የለዉም። በአዳማ 85%፣ በቡራዩ 45%፣ በጂማ 60%፣ በአርሲ ዞን 20% ፣ በሰሜን ሸዋ ዞን 17%፣ በምስራቅ ወለጋ 15% ….ኦሮሞኛ አንደኛ ቋንቋቸው ያልሆኑ ዜጎች ባሉበት ቦታ፣ አፋን ኦሮሞ ብቻ የሚል የትምህርትና የሥራ ፖሊሲ፣ በአማርኛ ላይ ጥላቻ መኖሩን አመላካች ነው። ይህ አፋን ኦሮሞ ብቻ የሚለው ነገር፣ ከአፋን ኦሮሞ ጋር፣ ከኦሮሞ ፍላጎት ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም።
በኔ እምነት ኦሮሞ ማለት ኢትዮጵያ ነው። ኦሮሞነት ከአማራው፣ ከጉራጌው፣ ከሶማሌው ጋር የተሳሳሰረ ነው። አፋን ኦሮሞ፣ የገዳ ስርዓት፣ የኦሮሞ ቅርጽና ባህል የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው። ኦሮምኛ የፌዴራል ቋንቋ ሆኖ፣ በወለጋ፣ አርሲ በመሳሰሉት ብቻ ሳይሆን በወሎ፣ በጎጃም በመሳሰሉት በትምህርት ቤት እንደ ሰብጅከት ተሰጥቶ ብዙዎች እንዲናገሩት ማድረግ አስፈላጊ ነው። ኦሮሞ የሚሉትን በአንድ በኩል፣ ሌላውን በሌላ በኩል በመክፈል፣ እኛና እናንተ ማለት መቆም አለበት።ከዚህ በኋላ ያለው “እኛ” ብቻ ነው።
አሁን ያለው የዘር ፌዴራሊዝም ፈርሶ፣ በሕዝቡ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ፣ ለአስተዳደር አመች የሆነ፣ የሁሉም ዜጎች መብት በእኩልነት የሚያከበር ፌዴራል ስርዓት ያስፈልገናል። እነ ኦቦ ሌንጮ አሁን ያለው ይቀጥል ካሉ፣ ያንን ይዘው በህዝብ ፊት ቀርበው ፣ በሐሳብ አሸንፈው የሕዝብን አዎንታ ካገኙ፣ ህዝብ አሁን ያለውን ፌዴራሊዝም ከደገፈ፣ እኔ ባልስማማም የሕዝብን ፍላጎት አከብራለሁ። ሆኖም ግን የኦሮሞ ብሄረተኞች እነርሱ ያላቸዉን ሐሳብ እንደሚያቀርቡትም እኛም ያለንን ሐሳብ ማቅረባችን ሊያስከፋቸው አይገባም።
No comments:
Post a Comment