Monday, December 12, 2016

ኢትዮጵያዊቷ ከአለማችን ምርጥ የሙዚቃ ኩባንያ መሪዎች አንዷ ሆነች


የታዋቂው ሞታውን ሪከርድስ ኩባንያ ፕሬዚዳንትና የአለማችን ትልቁ ሙዚቃ አሳታሚ ኩባንያ የዩኒቨርሳል ሚዩዚክ የኧርባን ሚዩዚክ ፕሬዚዳንት የሆነችው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኩባንያ ስራ አስኪያጅ ኢትዮጵያ ሃብተማርያም፣ በቢልቦርድ የ2016 የአለማችን ምርጥ 100 የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ስራ ስኪያጅ ሴቶች ዝርዝር ውስጥ ተካትታለች፡፡
በአለማችን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ የተሳካ ተግባራት የፈጸሙ የዘርፉ ኩባንያዎችን የሚመሩ ሴት የስራ አስፈጻሚዎችንና ማናጀሮችን እየመረጠ በየአመቱ ይፋ የሚያደርገው ቢልቦርድ፣ ሰሞኑንም ኢትዮጵያ ሃብተማርያምን ጨምሮ በአሳታሚነት፣ በአከፋፋይነትና በሌሎች ተያያዥ መስኮች የተሰማሩ ኩባንያዎችን የሚመሩ የአመቱ 100 ምርጥ ሴቶችን ዝርዝር አውጥቷል፡፡ የ37 አመት እድሜ ያላት ኢትዮጵያ ሃብተ ማርያም በምትመራቸው የሙዚቃ ኩባንያዎች አማካይነት በአመቱ ባከናወነቻቸው ተግባራት፣ ከአለማችን ምርጥ የሙዚቃ ኩባንያ መሪ ሴቶች ተርታ መሰለፏን ቢልቦርድ በድረገጹ ባስነበበው መረጃ ገልጧል፡፡
እ.ኤ.አ በ2011 የታላቁ የአለማችን የሙዚቃ ኩባንያ ሞታውን ሪከርድስ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን የተሾመችው ኢትዮጵያ፤ ስቲቪ ዎንደርን ጨምሮ ከአለማችን ታላላቅ ድምጻውያን ጋር ስኬታማ ስራዎችን በማከናወን ወደ ፕሬዚዳንትነት ማደግና በዩኒቨርሳል ሚዩዚክ ኩባንያ የኧርባን ሚዩዚክ ፕሬዚዳንት ሆና መስራት መቻሏ ተነግሯል፡፡
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2014 በዚሁ የቢልቦርድ የአለማችን ምርጥ 100 የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ሴቶች ዝርዝር ውስጥ ተካትታ እንደነበርም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

No comments:

Post a Comment