Monday, December 12, 2016

ታህሳስ 3 ቀን እምየ ምኒሊክ ከዚህ አለም በሞት ከተለዮ 103 ዓመት ይሆናቸዋል ፤


ታህሳስ 3 ቀን እምየ ምኒሊክ ከዚህ አለም በሞት ከተለዮ 103 ዓመት ይሆናቸዋል ፤ ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ ታህሳስ 3 ቀን 1906 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት መለያታቸው ይታወቃል።
– አጼ ምኒልክ ከመቅደላ ወጥተው ወደ አንኮበር ሊገቡ ሲሉ
የሸዋ ገዥ የነበረው አቶ በዛብህ አይገቡም ብሎ ተዋጋቸው፡፡ አጼ ምኒልክም ድል
አርገውት አንኮበር ከገቡ በኋላ ሁሉን ረስተው ለአቶ በዛብህ
ይቅርታ አደረጉለት፡፡

– አጼ ምኒልክ ከጎጃሙ ንጉሥ ተክለሃይማኖት ጋር ስለተጋጩ
እንባቦ በሚባል ቦታ ጦርነት አድርገው የምኒልክ ጦር አሸነፈ
አጼ ምኒልክም በጦርነቱ የተጎዱትን ንጉሥ ተክለሃይማኖትን
በመንከባከብ እንኳን ተረፉ እያሉ ቁስላቸውን በማከም ይቅር
ተባብለው መልካም ወዳጅ ሆኑ፡፡

– አጼ ምኒልክ ወደ ሐረርጌ ለጦርነት በሄዱ ጊዜ ራስ ጎበና
በአዲስ አበባ ሆነው መንግስት ሊገለብጡ ነበር ተበለው
ተከሰሱ በመኳንንቱም ዘንድ ጥፋተኛ ተብለው ሞት
ተፈረደባቸው፡፡
አጼ ምኒልክም የሞት ፍርዱን እንዲያፀኑ ሲጠየቁ”ጎበናን እዚህ
ለማድረስ ሰላሳ ዓመት ፈጅቶብኛል ለአንድ ቀን ጥፋቱ ብዬ
የሰላሳ ዓመት ድካሜን አላበላሽም ምሬዋለሁ እንደጥንቱ ይኑር”
ብለው ይቅርታ አደረጉ፡፡

– ጣሊያኖች በመቀሌ ጠንካራ ምሽግ ሠርተው ከባድ ውጊያ
በሚያረጉ ጊዜ ለውሃ ይጠቀሙበት የነበረውን ወንዝ የኢትዮጵያ
ሰራዊት በመቆጣጠሩ ጣሊያኖቹ በዛው በምሽጋቸው እንዳሉ
በውሃ ጥም ማለቅ ጀምሩ ፡፡አጼ ምኒልክም ሁሉንም እዛው
መጨረስ ሲችሉ ሠላሳ በርሜል ውሃ እና የሚጓጓዙበት በቆሎ
ጭምር ሰጥተዋቸው በይቅርታ ሸኟቸው፡፡

– ታላቁን የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ሰራዊት ድል ማረጉን ተከትሎ
አጼ ምኒልክ የጣሊያን ምርኮኞች ላይ መከራ ያደርሳሉ ተብሎ
ሲጠበቅ አጼ ምኒልክ ግን ሁሉን ጠብቀው አቆይተው በሠላም፣
ወደ ሀገራቸው በመላክ ይቅር ባይነትን ለዓለም አሳዩ፡፡

No comments:

Post a Comment