Tuesday, December 27, 2016

ግልጽ ደብዳቤ ለጀዋር መሐመድ: እየተከፈተ ያለውን የአንድነት በር ጨርሰህ ክፈተው

በአንድ ወቅት አሜሪካ ሶቬት ህብረትን ለማፈራረስ አፍጋኒስታን ውስጥ የአፍጋን ኃይሎች በሚል ወጣቶችን ከዛው መልምላ በሚሊቴሪና በፖለቲካ አሰለጠነች፡፡ ተጠቀማቸው የፈለገችውንም አደረገች፡፡ እነዚህ ወታደሮች ከጊዜ በኋላ የራሳቸውን ዓላማ ቀርፀው ከአሜሪካ ተለይተው አልቃይዳን ወለዱ፡፡ አልቃይዳም እግረ-መንገዱን የአሜሪካንን ድብቅ ፀረ-ኢስላማዊ ዓላማ ገባው፡፡ ቀጥሎም ሁለቱን የአሜሪካ የአለም ንግድ ማዕከላት ለማጥቃት ደረሰ፡፡ ይህን ተከትሎም አሜሪካ አፍጋኒስታንና ኢራንን ለማፈራረስ ምክንያት አገኘችበት፡፡ አሜሪካ ባደረሰችው ዘግናኝ በደል ብዙ የአሸባሪ ቡድኖች በዓረብ ሀገራት ፈንጥቀው ወጡ፡፡ አይሲስ፣ አይሲል፣ ታክፊሪ፣ አልቃይዳ፣..…ሁሉም ዓላማቸው ኢስላማዊ ግዛትን ለመመስረትና አሜሪካና ምዕራባዊያን በሙስሊሞች ላይ በሰሩት ግፍ፣ ባላቸው ጭፍን ጥላቻና እያደረጉ ባሉት የሥም ማጥፋት የተነሳ ነው፡፡ እነዚህ የአሸባሪ ቡድኖች በምዕራባዊያን ሀገራት ተደጋጋሚ ጥቃቶችን እየፈፀሙ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም ወደፊት አብዛኛው ሙስሊሞች ህብረት መሥርተው ፀረ-ምዕራባዊ ሆነው ቀጣይ ስጋት ሊሆኑ እንደሚችሉ የፖለቲካ ተመራማሪዎች ይተነብያሉ፡፡ ከዚህ አልፎም የከረረ የክርስትናና የእስልምና የሀይማኖት ጦርነት ይጠበቃል፡፡ አንዱ አንዱን እየወለደ….የማያበቃ የበቀል ሰንሰለትም ይሆናል፡፡
ሁለተኛ የታሪክ አጋጣሚ ላጫውትህ
በ2006 ግ.ካ. በዴንማርክ አንድ ይላንድስ ፖስተን የሚባል የጋዜጣ ድርጅት በ2014 በፈረንጆች አዲስ ዓመት ዋዜማ 12 የነብዩ መሐመድ ምስሎችን በጋዜጣው አቀረበ፡፡ በምስሎቹ ነብዩ መሣሪያ ታጥቆና አሸባሪ መስሎ የታየበት ነበር፡፡ ሌላው የኖርዌይ የጋዜጣ ድርጅት ለዴንማርኩ ጋዜጣ ድጋፍ በማሳየት ምስሎቹን በራሱ ጋዜጣ አትሞት ነበር፡፡ ይህ ተከትሎም በብዙ ዓረብ ሀገራት የሚገኙ የኖርዌይና የዴንማርክ ኢምባሲዎች ላይ ዓረቦች ጥቃት አደረሱ፡፡ አሁን ላይም ኖርዌይና ዴንማርክ በዓረቦች በጥቁር ዓይን እየታዩ ይገኛል፡፡
ሦሥተኛ የታሪክ አጋጣሚ ላጫውትህ
አንድ አሜሪካዊ ቅዱስ ቁርዓንን በይፋ ማቃጠሉን ተከትሎ በብዙ ዓረብ ሀገራት የሚገኙ የአሜሪካ ኢምባሲዎች ላይ ዓረቦች ጥቃት አደረሱ፡፡ አሜሪካ የመናገር ነፃነት ነው ብላ በህግ ሳትጠይቀው በመቅረቷ አሜሪካ ሙሉ ለሙሉ ፀረ-ኢስላማዊ ተደርጋ በሙስሊሞች መታየች ጀመረች፡፡ በኮሎራዶ ምሽት ክበብ የደረሰውም አደጋ ከዚህ የመነጨ ነው፡፡ ቀጣይ አደጋዎችም ይጠበቃሉ፡፡
ስለሀገራችን
ወደ ሀገራችን እንምጣና ደርግ በነበረው ጭፍን አምባገንነት ሁለተኛውን አምባገነንን ወለደ፡፡ ደርግ በሥልጣኑ ዘመን ለተቃዋሚዎች መፈናፈኛና አብሮ የመስራት ዕድል ቢሰጥ ኖሮ ወያኔ አይወለድም ነበር፡፡ ወያኔ ያጣውን የፖለቲካ ተሣትፎ ወደ ትጥቅ ትግል በመቀየር በጫካ ከከፈለው የመሠዋትነት ጫፍ አምባገነን ለመሆን ተዳረገ፡፡ አሁንም በህልሙ ሥልጣን ላይ እንዳለ የሚሰማው ወያኔ ሥልጣኑን ላለመልቀቅ የግፍ ጫፍ እየፈፀመ ይገኛለል፡፡ የወያኔ ግፍ ማንን ሊወልድ ይሆን???
ለ25 ዓመታት ቅጥቅጡ ወያኔ በሰራው የብሄር ለብሄር ማጥላላት ሥራ ጭፍን ፖለቲከኞች መወለዳቸው አይገርምም፡፡ ታሪክ ታሪክን አጋጣሚ አጋጣሚን ይወልዳል እንደሚባል ይሄ መከሰቱ የሚጠበቅ ነበር፡፡ ኦሮሚያን ብቸኛ የአፍሪካ ሀገርና የእስልምና ግዛት ለማድረግ ቆርጠህ መነሳትህ ከዚህ ውጥን የመነጨ ለመሆኑ መስካሪ አያስፈልገውም፡፡ በግሌ እኔ ክርስቲያንና 50% ኦሮሞና 50% አማራ ነኝ፡፡ ለእኔ ዓይነቱ ዜጋ ምን አዘጋጅተህ ነው እንዲህ ዓይነት ትግል የመረጥከው? ግብዓተ-ሲኦልን??? የኦሮሚያ ህዝብ 36.7% ፐርሰንት ከሌሎች ብሄሮች ጋር በጋብቻ መተሳሰሩ ችላ ብለህ ነው? እነዚህ ከሌሎች ብሄሮች ጋር የተዳቀሉና ዘር ማንዘራችው የተወራረደ የት እንዲገቡ ነው??? ከ50% በላዩ የኦሮሚያ ህዝብ ክርስትናና የባህል አምልኮ ተከታይ ነው፡፡ ለእነዚህስ ቦታ የለህም? ያንተ ኦሮሚያ የትኛው ነውን? Oromic Islamization ልትጠቀም ይሆን? በግሌ እስከዛሬ የተደረገው ትግል ኦሮሚያ ዕውቅና እንድታገኝ በቂ ይመስለኛል፡፡ ዛሬ ላይ ያለኦሮሞዎች የፖለቲካ ተሣትፎ ኢትዮጵያ እንደማትታሰብ በቂ ትግል መደረጉን ነው፡፡ ይሄም በአብሮነት ለመታገል የሚገፋፋ ጊዜ ላይ ስላለን ግትርነትን በመተው ሁላችንም አንድነት የማይታለም ላሉ የማሳፈሪያ አጋጣሚ የምንፈጥርበት ጊዜ ይመስለኛል፡፡
በተጨማሪ ወያኔ የሠራውን ሴራ ሁሉም ተረድቷል በሚባል ወቅት እራስን ማግለል የሚጠቅም አይመስለኝም፡፡ የኦሮሚያ ህዝብ በሚታወቀው የዋህነት ዛሬ ላይ ተነስተህ አብሮነትን እናጠናክር ብትል ህዝቡ ሙሉ ለሙሉ ፍቃደኛና በራሱ እያደረገውም ነው፡፡ ይሄንም እውነታ 50% ብሄሬ ስለሆነ አውቀዋለሁ፡፡ ያለፈ አልፏል ብለን በጋራ መታገል ይበጀናል፡፡ ጠንካራ የፖለቲካ አቅም ስላለህ ለአብሮነት ብትታገል በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉን ያማከለች ህዝባዊ ኢትዮጵያን መመስረት ይቻላል፡፡ እንደ ወንድሜ ስለማይህ ነው፡፡ እግዚአብሔር ካንተ ጋር ይሁን፡፡ ፅናቱንም ይስጥህ፡፡ ትግልህንም ይባርክልህ፡፡

No comments:

Post a Comment