Sunday, November 20, 2016

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊነሣ ይችላል ተባለ አውሮፓ ህብረት በሚዲያና በሞባይል ኢንተርኔት ላይ ጥያቄ አቅርቧል


‹‹ከታሠሩት 70 በመቶ ያህሉ ተለቀዋል››
አውሮፓ ህብረት በሚዲያና በሞባይል ኢንተርኔት ላይ ጥያቄ አቅርቧል
ከ11 ሺህ በላይ ሰዎች የታሠሩበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሃገሪቱን ሰላምና ፀጥታ ወደ ነበረበት እየመለሠ በመሆኑ ሊነሣ እንደሚችል ጠቅላይ ሚኒስቴር ሃይለ ማርያም ደሣለን ገለፁ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከውጭ ሃገራት አምባሳደሮችና የውጭ ተቋማት ተወካዮች ጋር ሰሞኑን በሃገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ በሰጡት ገለፃ በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በ‹‹ሁከት›› ተሳትፈው ከነበሩት መካከል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ትምህርት ተሠጥቷቸው ምህረት ተደርጎላቸዋል ብለዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ ባለፈው ሣምንት ከ11 ሺህ በላይ ሰዎች መታሠራቸውን አስታውቆ የነበረ ሲሆን ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በርካታ አባሎቻቸው መታሠራቸውንና ታሣሪዎች ያሉበት ሁኔታ እንደማያውቁ መግለፃቸው ይታወሳል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ አዲስ አድማስ የጠየቃቸው የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ መሃመድ ሰዒድ፤ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲታወጅ ቅድመ ሁኔታዎች መቀመጣቸውንና ችግሮች ደረጃ በደረጃ ሲቃለሉ ማስተካከያዎች እንደሚደረጉ በግልፅ መቀመጡን ጠቁመው ቀደም ሲልም ዲፕሎማቶች ከአዲስ አበባ 40 ኪ. ሜትር ራዲየስ ውጪ ለሚመለከተው አካል ሳያሳውቁ እንዳይንቀሳቀሱ የሚለው እገዳ ተብሎ የነበረው መነሣቱን ጠቅሰው ሌሎች መሻሻሎችም እየተገመገሙ እንዲነሳ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የአንድ ወር ግምገማው ሲታይ፣ በርካታ መሻሻሎች መታየታቸውን አቶ መሃመድ አብራርተዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሀገሪቱን ሰላም ለመመለስ፣ የኢንቨስተሮችን ዋስትና ለማስጠበቅና የቱሪስቶችን ደህንነት ለማረጋገጥ የታወጀ መሆኑን በመጠቆም ባለፈው አንድ ወር በነዚህ ጉዳዮች ላይ መሻሻሎች መታየታቸው ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል የአውሮፓ ህብረት በመገናኛ ብዙኃን ነፃነትና በሞባይል የኢንተርኔት አገልግሎት ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርቧል፡፡
ህብረቱ በተለይ የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባና በመላ ሀገሪቱ የ3ጂ የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡ ዘመናዊ ንግድ ወደ ሀገሪቱ ለመሳብ የሚደረገውን ጥረት የውጪ ኢንቨስትመንት ፍላጎትን የሚገታ ነው ብሏል፡፡
ለመገናኛ ብዙኃን በቂ ነፃነት አለመሰጠቱንና ዜጎች ወደ ውጭ ሚዲያዎች ለማማተር መገደዳቸውን የጠቆመው ህብረቱ፤ መንግስት የህዝቡን የመረጃ ጥማትና ፍላጎት እንዲያጤን ጠይቋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም የፖለቲካ ውይይቶችንና ለችግሮች መፍትሄ ለማበጀት በተለይም የችግሮችን ምንጭ ከስሩ አጥርቶ መሻሻል ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ይገድበዋል የሚል ስጋት እንዳለው ህብረቱ አስታውቋል፡፡

No comments:

Post a Comment