በአዲሱ ካቢኔ ሹመት ዙሪያ ምን እየተባለ ነው ? ?
የህወኃት/ኢህአዴግ መንግስት ባለፈው ዓመት የሚኒስትሮች ም/ቤት ካቢኔ አባላት ሲሾም ስለ ትምህርት ዝግጅታቸው፣ ልምዳቸውና ብቃታቸው አድናቆቱን ገልጾ ሁለተኛውን የ5 ዓመት የልማትና ትራንስፎረሜሽን ዕቅድ ለማሳካት ባላቸው ቁርጠኝነት እተማመናለሁ ብሎ ካቀረባቸው ውስጥ በዓመቱ ግማሹን አራግፎ ከፍሉን በውዞ በአዳዲስ ‹የተማሩና የተመራመሩ – ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች › መተካቱን ትናንት በተለመደው ሙገሳ አጅቦ ሾሟቸዋል፡፡ ይህን ሹም ሽር- ብወዛና አዲስ ሹመት በሚመለከት የተለያዩ ወገኖች እንዲህ ገልጸውታል፡፡
1. ‹‹ ብዋዛው— ለሁሉም ቦታ ብቃት ያላቸው–አምና ሲሾሙ ያልበቁበት ቦታን ዓመቱን ባሳለፉበት ሚኒስቴር መ/ቤት ሆነው ባገኙት ልምድ ዘንድሮ ለሌላ ሚኒስትር መ/ቤት ብቁ ሆነው ተገኙ ወይስ አምና ከሚኒስትርነታቸው ጎን ለጎን ለአዲሱ ቦታቸው ሲሰለጥኑና ሲዘጋጁ ነበር? መልሱ የቱም ይሁን ፡ መለማመጃ ሆነናል ከማለት ሌላ ምን ይባላል፡፡
2. በቦታቸው የጸኑትም ቢሆኑ ልክ እንደተበወዙት ከሥልጣን ሥልጣን ሲገለበበጡ የመጡ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ ታዲያ እኚህስ ለየተመደቡበት የተለያየ ቦታ የሚያበቃቸው የተለየ ብቃት የሚያስታጥቃቸውና የተሟላ የሚያደርጋቸውን ‹ ምስጢር› የሚያውቀው ህወኃት/ኢህአዴግ ብቻ ነው፡፡ ህዝቡ በነዚህም ቢሆን እምነቱ ከሌሎቹ የተለየ ሊሆን አይችልም፡፡
3. አዲሱ ሹመት– አዲስ ተሽዋሚዎች አምና አልነበሩምን ወይስ ለቦታው ያበቃቸውን ልምድ ያካበቱት፣ ትምህርት የቀሰሙት ብቃታቸውን ያረጋገጡት ባሳለፍነው ዓመት/አምና መሆኑ ነው ? .. እንዴት ተቀለደብን፡፡
አዲሱ የ ‹ምሁራን› ካቢኔ ‹‹ ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም ›› እንዲሉ ነው እንጂ አንዳች ለውጥ ያመጣል ተብሎ አይጠበቅም፡፡››
ለምሳሌ — ‹‹በህገ መንግስትና በአዋጅ ለማንም ፖለቲካ ድርጅት ወገናዊ ሳይሆን በገለልተኝነትና ነጻነት ተግባርና ኃላፊነቱ እንዲወጣ የተወቀረው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ላለፉት 10 ዓመታት ይመራ የነበረው በፕሮፌሰር እና በዶክተር ነበር፡፡ ግን ይህ ነጻ የተባለ ተቋም ያሳየውን ሁሉም የሚያውቀው ነው፣ ከቀደሙት አቶ አሰፋ ብሩ ጊዜ ወደ ከፋ ሁኔታ ወረደ እንጂ አልተሻሻለም፡፡፡፡ ከየቱም ተቋም በበለጠ የገዢው ፓርቲ ታዛኝነቱን፣ ወገናዊነቱን ያረጋገጠ ፣ ከገዢው ፓርቲ በሚወርድለት መመሪ የሚተዳደር ….. መሆኑ ከእኛ አልፎ በዓለም ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ/ችግሩ የትምርት ደረጃ ጥያቄ — የ›ፕሮፌሰርነትና ዶክተርነት እጥረት አይደለም፣ በህገ መንግስትና በአዋጅ የተሰጠ ሃላፊነትን መሰረት ለመወጣት የሚያስችል በራስ የመተማመን ጉዳይ ነው፡፡ ይህን በራስ የመተማመን ስሜት ደግሞ ህወኃት በተለያዩ ዘዴዎች መሸርሸር ሣይሆን ጠራርጎ ወስዶታል፡፡ ›› በማለት ያስረዳሉ፡፡
በአጠቃላይ ‹‹ ይህ የተወሰደው እርምጃ በ25 ዓመት የተተከለውን ሥር የሰደደ በሽታ ሊፈውስ ይቅርና የምልክት ህመሞችንም ሊያስታግስ አይቻለውም፡፡ የታሰበው‹ የጥልቅ ተሃድሶ ›ህክምናውም ሥር ለሰደደ /ክሮኒክ/ የካንሰር በሽታ የህመም ማስታገሻ መርፌ በመውጋት ለማዳን እንደመሞከር ነው ፡፡ ድርጊቱንም ህዝቡ ያነሳው መፈክር ህወኃት ‹በቃን› ፣ የጠየቀውም ዘረኛው የአገዛዝ ሥርዓት እንዲለወጥ ሆኖ የሚሰጠው መልስ ከ15 ኣመት በፊት እንዳደረጉት ‹በጥልቅ ተሃድሶ› ከዚያው አገዛዝ ያሉትን መበወዝና ሹም -ሽር ማድረግ ሆኖ ሲቀርብ ‹‹ፍዬል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ›› ከማለት ሌላ ምን ይሉታል፡፡ ይህ ከህዝብ ንቀት የሚመነጭ እብሪት እንጂ በእውነት ለመፍትሄ ታስቦ አይደለም፣ አገዛዙ እስከዛሬ ከነበረበት አንድ ኢንች ፈቀቅ አላለም፡፡ ስለሆነም በአገርና ህዝብ ላይ ከ25 ዓመት በላይ እንዲለማመዱና እንዲቀልዱ መፍቀድ የለብንምና የተጀመረውን ‹ህወኃት በቃን› ህዝባዊ እምቢተኝነት አቀናጅቶና አጠናክሮ የመቀጠል አስፈላጊነትንና ወቅታዊነትን የበለጠ ግልጽ ከማድረግ ሌላ ምንም ያስተላለፈው የተለየ መልዕክት የለም ፣ ይህ የህዝብ ንቀት ብሶቱን ያባብሰው፣ ህዝባዊ ተቃውሞውን የበለጠ ያቀጣጥለው አንደሆን እንጂ አንዳችም የሚፈይደው የለም፡፡ አጠያያቂው የምንከፍለው ዋጋ/መስዋዕትነት መጠን እንጂ ለውጡ አይቀሬ ስለመሆኑ አንጠራጠርም ፡፡›› በማለት በአዲሱ መንግስት ካቢኔ ምስረታ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ከትግራይ ወዳጆቻቸው ያገኙትን ኃሳብ እንዲህ ይገልጹታል፡፡ ካነጋገርናቸው የትግራይ ተወላጆች ጥቂቶች አስተያየት ለመስጠት ቢቆጠቡም አብዛኞቹ ግን በድፍረትና በቁጭት መንፈስ የአዲሱን ካቢኔ ሹመት በሚመለከት ‹‹ይህ ሁሉ የሆነው በመለስ ቦታ ኃ/ማሪያም የተቀመጠ ቀን ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሪነቱ ከእጃቸው መውጣት አልነበረበትም ፡››፡ ካሉ በኋላ ‹‹ ይሄው እንግዲህ የህወኃት ታጋዮች ላለፉት 25 ዓመታት አገሪቱን በልማት፣ በዲሞክራሲ እየመራ ሠላማችን ማረጋገጡ ተዘንግቶ ሥልጣኑን እንዲያስረክብ ተጠየቀ፣ አስረከበ፡፡ ሥጋታችን እነዚህ በትግል ያልተፈተኑ ምሁራን- ፕሮፌሰሮችና ዶክተሮች ሥልጣኑ የሚያስከትለውን ኃላፊነት ሳይረዱ አገሪቱን እንዳያተራምሱና እንዳያስገነጥሉ፣ ልማታችን እንዳይደናቀፍ፣ ሰላማችን በተጀመረው ዓይነት ሁከትና ብጥብጥ ከነበረበት የደርግ ጊዜ እንዳይመለስ ነው፡፡ እነርሱ በሰላም በሚማሩበት ጊዜ ትምህርታቸውን ትተው በትግል ላይ የነበሩና የተፈተኑ ስንት ጀግና ታጋዮች ባሉበት፣ እነርሱን አግልሎ ከመንገድ ላይ ለተሰበሰቡ የጥፋት ኃይሎች / ኦሮሞዎች- ኦህዴድ/ ሥልጣኑን አስረክበናል፡፡ መሪነት በትምህርት ሳይሆን በትግል ተፈትነው የሚያገኙት ነበር፣ ለመማሩም ከድል በኋላ ነባር ታጋዮች ተምረው እነርሱ የደረሱበት ደርሰዋል፤ ችግሩ የትምህርት ሳይሆን የቅናት ነው፤ ይህ ደግሞ የነፍጠኞቹ/አማራ/ ቡድን የትናንት ጠላታቸውን ጠባቦችን /ኦሮሞዎች/ በማታለል ያለፈውን ስርዓት ለማምጣት የወጠኑት ሴራ ነው እኛ የተገፋነው፤ ሆኖም የትም አይደርሱም፡፡›› በማለት ይከራከራሉ፣ ቅሬታቸውን ይገልጻሉ ፡፡
በልሁ ማንከልክሎት ፣ ጥቅምት 30/2009 ዓ.ም.
No comments:
Post a Comment