Monday, November 14, 2016

ለመዝባሪዎች የአገር መጥፋት የፈጣን ብልፅግና ዕድል ነው


ለመዝባሪዎች የአገር መጥፋት የፈጣን ብልፅግና ዕድል ነው Addis Admass
‹‹አገር ስትለማ ቀስ በቀስ መበልፀግ ይቻላል፡፡
አገር ስትጠፋ ግን በፍጥነት መበልፀግ ይቻላል››
ጊዜና ዘመን ሲበላሽ፣ ሙስናም ጣራ ሲነካ፤ ተራው የሂሳብ ስሌት እንኳ መደራደርን ይጠይቃል። አንዳንዶች እንደሚሉት፤ ወደፊት ሰላምታም የገንዘብ ድርድር ሳያስጠይቅ አይቀርም፡፡ እያደር ሰብዕናም ቦታ ያጣል፡፡ የሁሉም ነገር መፈክር ‹‹ገንዘብ! ገንዘብ! ገንዘብ!›› ብቻ ይሆናል፡፡ እንደ ‹‹ሁለት ሲደመር ሁለት›› ሂሳብ፣ ላይ ላዩን ቀላል የሚመስለው ነገር ሁሉ ከሥሩ የሚጎተት ገንዘብ አለ፡፡ ይሄ የገንዘብ ጥያቄ፣ በሰጪና ተቀባይ መካከል የሚያልቅ ብቻ አይደለም፡፡ በየመንግስት ቢሮው የገንዘብ ጥያቄ አለ፡፡ በየግል ድርጅቱ የገንዘብ ጥያቄ መዓት ነው፡፡ በመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የገንዘብ ጥያቄ በሽ-በሽ ነው! በየተቋማቱ ገንዘብ የማይገባበት ጨዋታ የለም፡፡ ባንኩ፣ ኢንሹራንሱ፣ ስንት ህዝብ ይታደጋሉ ሲባሉ፤ የዚያው የገንዘብ ውስጠ- ወይራ አካላት ናቸው፡፡ ስለተደረሰባቸው ጥቂት ባለገንዘቦች ሲወራ፤ ያደፈጡ ዋና ዋና በዝባዦች ያመልጡና ከስዕሉ ይሠወራሉ፡፡ ዝቅተኛውና መካከለኛው ተበዝባዥ እቤት የሚልበት ቦታ ሳይኖር በየጎጆው እያለቀሰ ይኖራል፡፡ የተገመቱና የሚጠረጠሩ መዝባሪዎች በቶሎ እርምጃ ስለማይወሰድባቸው፣ ይብሱን ሲፋፉና የልብ-ልብ ሲሰማቸው ማየት የዕለት ጉዳይ ይሆናል፡፡ የነገም ሌላ ቀን ነው (Gone with the Wind ) መጽሐፍ አንደኛው ገፀ-ባህሪ ሬት በትለር፡-
‹‹አገር ስትለማ ቀስ በቀስ መበልፀግ ይቻላል፡፡
አገር ስትጠፋ ግን በፍጥነት መበልፀግ ይቻላል››
ይለናል፡፡ ስለዚህ ለመዝባሪዎች የአገር መጥፋት የፈጣን ብልፅግና ዕድል ነው እንደማለት ነው። ሙስናን በሥር-ነቀል መንገድ ማጥፋት የግድ የሚሆነው፣ አገርን ማዳን ግድ ስለሆነ ነው፡፡ እንጂ ጥቂት ግለሰቦች ሲናጥጡ ማየት ስለሚያስቀና አይደለም፡፡
የመዝባሪዎች አለመኖር የሰላም ዋስትና ነው፡፡ ሰላም የዲሞክራሲ፤ የፍትሕ፣ የእኩልነት፣ የሉዓላዊነት ዋስትና ነው፡፡ የምርጫም ዋስትና ነው፡፡ የአሜሪካን ምርጫ ስናይ በመጀመሪያ በህሊናችን የሚመጣው የሰላሙ ድባብ ነው፡፡ የምርጫ ሳጥን አይገለብጥም፡፡ ቆጠራ አይሳሳትም፡፡ ቂም- በቀል የለም፡፡ ልቅ የሆነ የፖለቲካ ክርክር ግን አለ!! ተሰዳድበውም፣ ተማምተውም፣ ተሸረዳደውም፤ ተካሰውም… በመጨረሻው ወሳኙ የህዝቡ ድምፅ መሆኑን አምነው፤ ‹‹በመመረጥህ እንኳን ደስ አለህ››… ‹‹ጥንካሬሽን አደንቃለሁ!›› ሲባባሉ ስናይ ትምህርት ልንወስድ ይገባናል፡፡ የተመረጠው ማንም ይሁን ማን፤ እንዲት አሜሪካ አለች፡፡ በወጉ መስተዳደር ያለባት! የህዝቡን ድምፅ አክብሮ፣ ህዝቡን የሚመራ ፕሬዚዳንት የተመረጠባት! ኃያል አገር ናት ብሎ ህዝቡ የሚያምንባት! እንደ ፖለቲካ ሰዎች አባባል፤ ‹‹የአሜሪካ ህዝብ፤ አሜሪካ ውቂያኖስ አቋርጣ ነፃነትንና ዲሞክራሲን ለማስከበር ስትሄድ የሚደግፍ ህዝብ ነው፡፡ ነገር ግን ወደ ምርጫ ሳጥን ለመሄድ መንገድ ማቋረጥ ወገቤን ይላል፤ ይከብደዋል!›› ያም ሆኖ እንደ ምንም መንገድ አቋርጦ ለመሄድ የቻለው ክፍለ-ህዝብ ድምፅ ይሰጣል፡፡ ድምፁም ይከበራል፡፡ ዋናው ቁም ነገር፤ ለአገር ጥሩ ሥራ ለመሥራት መኖር ያለበት ቁርጠኝነት፣ መከፈል ያለበት መስዋዕትነት መኖሩን ማስተዋል ነው፡፡ ሼክስፒር፤ ‹‹መልካም መልካሙን ሥራ! ሠይጣን ይፈር!›› (Do good and shame the devil!)
የሚለንን ከቀልባችን ሆነን ካሰብንበት፣ ታላቅ አገር- አድን መርህ የሚሆነው ለዚህ ነው!!

No comments:

Post a Comment