Monday, November 14, 2016

አይሲኤል የተሰኘው የእስራኤል ኩባንያ ለጠፉ ንብረቶች መንግሥትን ተጠያቂ አደረገ


አይሲኤል የተሰኘው የእስራኤል ኩባንያ በኢትዮጵያ የጀመረውን ኢንቨስትመንት በማቋረጡ ምክንያት፣ በአፋር ክልል የሚገኘውን የፖታሽ ማዕድን ልማት ፕሮጀክት መንግሥት እንዲረከበው ጠየቀ፡፡
አይሲኤል ከታክስ ክፍያ ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ጋር እሰጥ እገባ ውስጥ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ኩባንያው አላና ፖታሽ የተሰኘውን የካናዳ ኩባንያን የገዛበት የካፒታል ዕድገት ግብር፣ የአላና ፖታሽ መክፈል የነበረበት ዊዝሆልዲንግና ቫት በአጠቃላይ 55 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ያላግባብ ተጠይቄያለሁ በማለት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በአፋር ክልል ዳሎል አካባቢ የጀመረውን የአንድ ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ማቋረጡን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ኩባንያው ኢንቨስትመንቱን ማቋረጡን ካስታወቀ በኋላ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የኩባንያውን የባንክ ሒሳቦችና ንብረቶቹን አግዷል፡፡ ይሁን እንጂ የኩባንያው የባንክ ሒሳቦች መታገዳቸው በሥራ ሒደቱ ላይና በንብረቶቹ ላይ የፈጠረውን አደጋ በማስረዳት የባንክ ሒሳቡ ዕግድ ተነስቶለታል፡፡
አይሲኤል ኅዳር 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ለማዕድን፣ ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ የፖታሽ ፕሮጀክቱን ሚኒስቴሩ እንዲረከበው አመልክቷል፡፡ ኩባንያው ለሚኒስቴሩ በጻፈው ደብዳቤ ዝርዝር የማስረከቢያ ሒደቱን የሚገልጽ ዕቅድ ያሰፈረ ሲሆን፣ ሚኒስቴሩ ፕሮጀክቱን ከተረከበ በኋላ የፕሮጀክት መዝጊያ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡
አይሲኤል የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የባንክ ሒሳቡን ባገደበት ወቅት ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰበት ገልጿል፡፡ የባንክ ሒሳቡ በተዘጋበት ወቅት ሠራተኞቹን መስክ ለማስወጣትና የሥራ እንቅስቃሴውን ሙሉ በሙሉ ለማቋረጥ ተገዶ እንደነበር ጠቅሶ፣ ይህም በኩባንያው ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳስከተለበት አትቷል፡፡
በመስክ የሚገኙ ማሽኖች፣ መሣሪያዎችና ሌሎች የተለያዩ የኩባንያው ንብረቶች ለዝርፊያና ለስርቆት መዳረጋቸውን የገለጸው ኩባንያው የደረሰበትን የንብረት ውድመት መጠን በማጣራት ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የባንክ ሒሳቦቹ በታገዱበት ወቅት ለሠራተኞችና ለኮንትራክተሮች ክፍያ መፈጸም ተስኖት እንደነበር ጠቁሞ፣ በዚህም ምክንያት የካሳ ጥያቄ ሊመጣበት እንደሚችልና ለዚህና ለጠፉ ንብረቶቹ ሙሉ በሙሉ መንግሥትን ተጠያቂ አድርጓል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አይሲኤል በኢትዮጵያ ቢሮ የሚሠሩ 145 ቋሚ ሠራተኞቹን ኅዳር 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በደብዳቤ ሸኝቷል፡፡ ኩባንያው ሠራተኞቹን ያሰናበተው አስፈላጊውን የአገልግሎትና የሥራ መፈለጊያ ክፍያ ሳይፈጽም መሆኑ፣ በሠራተኞቹ ዘንድ ግራ መጋባትን መፍጠሩን ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
አይሲኤል በዳሎል የፖታሽ ማዕድን ማውጫ፣ ሦስት የማዳሪያ ፋብሪካዎች ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ለመገንባት አቅዶ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ ፕሮጀክቱ ለአገሪቱ በዓመት 300 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪና ለ3,000 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተገምቶ ነበር፡፡
በአይሲኤል ደብዳቤ መሠረት ኩባንያው ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ለመሄድ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ምንጮች ይናገራሉ፡፡ መንግሥት ከወዲሁ ችግሮቹን በድርድር መፍታት ወይም የሚመጣውን ክስ ለመመከት ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡

No comments:

Post a Comment