Thursday, November 3, 2016

ተቃዋሚዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን የካቢኔ ሹም ሽር ተቹ


ተቃዋሚዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን የካቢኔ ሹም ሽር ተቹ
የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ያደረጉትን የካቢኔ አባላት ሹም ሽርን ተችተዋል፡፡ መሰረታዊ ለውጥ እንጂ የግለሰቦች ሹም ሽር ሀገሪቱ አሁን ያለችበትን የፖለቲካ ቀውስ አይፈታም ሲሉ አዲሱን የሚኒስትሮች ሹመት አልተቀበሉትም፡፡ ህዝብ እየጠየቀ ያለው የፖሊሲ ለውጥ እንጂ የግለሰቦች መለዋወጥ ለውጥ አያመጣም ብለዋል፡፡
በዛሬው የካቢኔ ሹም ሽር ከ30 የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ውስጥ ዘጠኝ ሚኒስትሮች ባሉበት እንዲቀጥሉ ሲደረግ ሃያ አንዱ አዲስ ሚኒስትር አግኝተዋል፡፡ ከአዲሶቹ ተሿሚዎች ውስጥ አራቱ በባለፈው ካቢኔ ሌሎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ሲመሩ የነበሩ እና ወደ አዲስ ቦታ የተዘዋወሩ ናቸው፡፡ ሁለቱ ደግሞ በሚኒስቴር ዴኤታነት ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ሚኒስቴር የነበሩ እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪነት ሲሰሩ የነበሩ አንድ ባለስልጣን ደግሞ ወደ ሚኒስትርነት ቦታ ተመልሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተሿሚዎቹን በምክር ቤት አቅርበው ከማጸደቃቸው በፊት እንደተናገሩት ለሹመት ዋና መመዘኛ ያደረጉት ውጤታማነት፣ ለህዝብ ቀልጣፋ አግልግሎት መስጠት መቻል እንደዚሁም ፖሊሲ እና ስትራቴጂ የማስፈጸም ብቃትን ነው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራረሮች ግን ሹመቱ መሰረታዊውን የኢትዮጵያን ችግር እና የወቅቱን የፖለቲካ ቀውስ አይፈታም ባይ ናቸው፡፡
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና ህዝብ እየጠየቀ ያለው የፖሊሲ እና መሰረታዊ ለውጥ እንጂ የግለሰቦች ሹም ሽር አይደለም፡፡ ሊቀመንበሩ ሹም ሽሩን ገዢው ፓርቲ “ቀባብቶ በማለፍ” ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያደርገው ሲሉ ይተቹታል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ  ሊቀመንበር አቶ ይልቃል ጌትነት በበኩላቸው ገዢው ፓርቲ አዲስ ካቢኔ መስርቼያለሁ ባለ በአንድ ዓመት ውስጥ 21 ሚኒስትሮችን መለወጡ “መጀመሪያውኑ ችግር እንዳለበት ያመለክታል” ይላሉ፡፡
ዛሬ በድጋሚ በተዋቀረው ካቢኔ ውስጥ በተለያየ ዘርፍ የዶክተርነት ማዕረግ ያላቸው 14 ሚኒስትሮች እንደተካተቱ የተገለጸ ሲሆን ሁለት ፕሮፌሰሮችም ቦታ አግኝተዋል፡፡ ይህም ቢሆን የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን ቀልብ አልገዛም፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የነበሩት ዶ/ር መረራ ግን የዶክተርነት ማዕረግ ያላቸው ተሿሚዎች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ገዢውን ፓርቲ ሲያገለግሉ የነበሩ እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡ ሹመቱንም “ኋላ የነበሩትን ፊት ማምጣት” ሲሉ ይገልጹታል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲው አቶ ይልቃል የቀደመው ካቢኔ ሲጸድቅ “ማስተርስ ያላቸው እና የተማሩ” እየተባለ የትምህርት እና የትምህርት ልምዳቸው ሲነገር እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ የአሁን ሹመት “የተለየ ነገር የለውም” ባይ ናቸው፡፡ “የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ እና ጥፍንግ ያለ የማዕከላዊነት አመለካከት እስካልተለወጠ ድረስ የግለሰብ መቀየር ምንም ዓይነት ለውጥ አያመጣም” ይላሉ፡፡
ሁለቱም የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ኢትዮጵያ ያለችበት ወቅታዊ ችግር የሚፈታው በሚኒስትሮች መለዋወጥ ሳይሆን “ኢህአዴግ መሰረታዊ እና የፖሊሲ ለውጥ ሲያደርግ ነው” ይላሉ፡፡ ነጻ ምርጫ፣ ሁሉንም በእኩልነት የሚያስተናግድ ስርዓት እና እውነተኛ መድበለ ፓርቲ ስርዓት እንዲኖር ካልተፈቀደ እንደዚሁም እንደ ፍርድ ቤት እና መገናኛ ብዙሃን ያሉት ተቋማት ነጻ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ እስካልተደረገ ድረስ ለውጥ አይመጣም ባይ ናቸው፡፡

No comments:

Post a Comment