Monday, November 14, 2016

እያታገልኩ ነው ስላልክ ብቻ እየታገልህ አይደለም። ኄኖክ የሺጥላ


እያታገልኩ ነው ስላልክ ብቻ እየታገልህ አይደለም። ኄኖክ የሺጥላ
መረጃዎች ይደርሱናል ፥ ከባህር ዳር ፥ ከጎንደር ፥ ከ ወሎ እና ወዘተ። በየቀኑ ከ ከመላው ኢትዮጵያ ወደ ሱዳን እና ሊቢያ የሚሰደደው ወጣት ቁጥር የትዬ ለሌ ነው። ወደ ኤርትራ በርሃ ለመግባት ከሚፈልጉት እልፎች ውስጥ ሁሉም ማለት በሚቻልበት ሁኔታ በርሃ መግባት በማይችሉበት ሁኔታ ላይ ነው ያሉት። ወዳጆቻንን ( ጓደኞቻችንን ) የዚሁ ትግል አካል ለማድረግ ብዙ ጥረን ፤ ከቀድሞ አለቆቻችን የተሰጠን መልስ « ዱባይ ድረስ መምጣት ይችላሉ ወይ ?» የሚል የሚገርም ጥያቄ ነበር ። የፅሁፍ ማስረጃ አለኝ!
የኤርትራ በርሃን ማግኘት እንደ ሰማይ የራቀው በእውነት ወያኔ እንደሚሉት ቦርደሩን ጠፍንጎ ስለሚጠብቀው ነው ? ይህንንስ ለማድረግ በእውነት ያን ያህል አቅም ኖሮት ነው ? እንዴትስ ነው ሱዳን መግባት የቻለ ሰው ( አካል ) ኤርትራ መግባት ያቃተው ? ለምን ?
እኔ እስከማውቀው ድረስ ወደ ኤርትራ በርሃ ለመግባት ወስነው ከተጓዙት ( ወይም ከተጓዝነው 7 ልጆች ውስጥ ) 6ቱ ሞተዋል ( ተገለዋል ) ። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? የጎንደር ትግል ከዳር ዳር በተቀጣጠለበት ሰዓት የጎንደር ገበሬዎች ” ጥይታችን እያለቀ ነው ድረሱልን!” ሲሉ ሰሚ አጥተው እየታፈኑ እንደሆነ እየሰማን ባለንበት ሁኔታ እንዴት ያለ ጨካኝ ሰው ብትሆን ነው « የነፃነት ሃይሎች እያልህ ልትደሰኩር የምትሻ?»
እስከመቼ እየዋሸን ለመቀጠል ፥ እየቀጠፍን እና ህዝብ እያስቀጠፍን ለመኖር ወስነናል ?
እንደው ማን ይሙት ፥ ብረት አንግበናል ለሚሉ ታጋዮች ከዚህ የተሻለ ጊዜ ይኖራል ወይ ? እንደነሱማ አባባል ከሆነ የ 6 ወር ጊዜ ብቻ ስጡን ነበር ያሉት ፥ በስድስት አመታቸውም አልደረሱልንም እንጂ !
የማነፃፅረው ነባራዊ ሁኔታውን ነው ። ከሚታየው ተነስቼ ነው የምሞግታቸው! የሚጠይቅ ሰው በሌለበት ፈሪ ህዝብ መሃል በመፈጠሬ ስጋቴ እንደ ነቆራ ይታያል። እውነቱ ግን ያ አይደለም !
ለምንድን ነው ሽምቅ ውጊያ ማድረግ ያቃታቸው ሲባል ፥ እንደ መልስ የሚመልሱት ነገር « ወያኔ ያለ የሌለ ሃይሉን የኤርትራ ድንበር ላይ ስላስቀመጠ ነው » የሚል የልጅ መልስ ሊመልሱ ይፈልጋሉ ። ይህንን ለመመለስማ እኮ ጫካ መግባት አያስፈልግም ። ጫካ የምትገባው ፥ የምትደራጀው እና መሰል ወታደራዊ ዝግጅቶችን የምታደርገው ይህንን ታሳቢ አድርገህ እኮ መሰለኝ ። ወይስ ወያኔ ድንበሩን ክፍት አድርጎ አዲስ አበባ እንድንገባ ይፈቅድልናል ብለን ነው ትግል የጀመርነው ?
የመጠየቅ መብት እንዳለን የረሱትም ይመስላል ። ወንድሞቻችን ናቸው እየሞቱ ያሉት ! ስለዚህ ያገባናል ! ባንፃሩ ጥያቄያችንን የጎንዮሽ ትግል አታድርጉ ይሉናል ። ምን ማለታቸው ነው ? « ዝም በሉ አትጠይቁን !» ማለታቸው ነው ። አሁን ምንም እየሰሩ እንዳልሆነ ለወያኔ ጠፍቶት ነው የኛ ጥያቄ የጎንዮሽ ትግል የሚሆነው ?
ወደ ኤርትራ በርሃ ገብተው ከወያኔ ጋ ለመፋለም በቁርጠኝነት ቆመው እንዳይሆኑ ሆነው የተገደሉት እና የጠፉት ሰዎች ቁጥር ፥ በርሃ ያጠፉት ዘመን እና መሰል ጉዳዮች ከማን የተደበቀ ነው ? እነ ኮ/ል ታደሰ የሻዕቢያ ማዕቀብ ቢሰለቻቸው በራሳቸው መንገድ የሽምቅ ውጊያ ባደረጉ በዕለቱ በሻዕቢያ ታፍነው እንደተወሰዱ እናውቃለን ። እነ ኮ/ል ፍፁም ስለዚህ ጉዳይ ሲጠየቁ « አይ መዓዛው ጌጡን ጠይቀው » ብለው የመለሱበትን እና መዓዛው ጌጡ በፋሲል የኔ አለም ሲጠየቅ « ይህንን ነገር እኔን አትጠይቀኝ » ብሎ ሲመልስ የሚያሳየውን ዩቱብ አይተናል ( ቀድተንም አስቀምጠናል !) ። የኋላ ኋላ የኤርትራን መንግስት ለመገልበጥ ሙከራ ሲያደርግ ተደርሶበት ነው የታሰረው የሚል ገሃድ ያልወጣ ሀሜት የኛ በምንላቸው ሰዎች ይወራ እና ይነዛ ጀመር ። ያሳፍራል ! ይህ ሰው ቢያንስ ልጅ አለችው ! ለሷ ስንል እንኳ የአባቷን መድረሻ ለማወቅ አልደፈርንም ! ጨካኞች ነን!
ቲፒዲኤም 15 ሺ የሚሆን ሰራዊት አለው ይሉናል ። እንዴት ነው ታዲያ ከነዚህ ውስጥ ቢያንስ አምስቱ መተኮስ ያቃታቸው ? ጎንደር ውስጥ 10 እና 20 ሰዎች የወያኔን ሰራዊት በቀየኑ እያርበደበዱ ባሉበት ሰዓት ከ 6 ጊዜ በላይ ወታደሮቼን አስመረቅሁ የሚል ድርጅት እንዴት 2 ወታደሮቹን ከጎንደሮቹ ጎን መቆም አቃተው ?
ይህንን መጠየቅ ነውር ነው! ያስፈራል ! ብዙዎችን ያስቆጣል ! ያበሳጫል ! ይህ ማለት ግን እርር ፥ ድብን ፥ ኩርምት እና ትክን እያሉ የሚከራከሩላችሁ ሰዎች ይህ ጥያቄ በጭንቅላተው ውስጥ የለም ማለት አይደለም ! አንድ ቀን ይጠይቋችኋል። ከዚያ በፊት ሆናችሁ ተገኙ !
ምን እየሰራችሁ ነው የሚለውን የህዝቡን ጥያቄ ለማስተንፈስ ፥ የውህደት ዲስኩር አዘጋጅተው እንደ ህፃን ልጅ ሊያታልሉን ይሞክራሉ ! ዛሬም ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀርቡልናል ። አንድ ጥይት ሳይተኩሱ ወይኔ ሲወድቅ ስለሚመጣው ስርዓት ይደሰኩራሉ ! ስካር ነው ! የወጣለት ስካር!
የመጨረሻ መውጫ ቀዳዳ ያደረጉት ትግሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የሚለውን ማለሳለሻ ነው ። እውነት ነው ካልን ደሞ የኦሮሚያውን ትግል እየመሩት ያሉት እነሱ ስለመሆናቸው ይንገሩን ! የአማራ ህዝብ ተቆርቋሪ እና ተጠሪ ስለሌለው እራሱ በጎበዝ አለቆች ተደራችጅቶ የሚያደርገውን ትግል « የነፃነት ሃይሎች ትግል » በማለት ደም ለመስረቅ የሚደረገውን ነገር በዝምታ አላልፈውም ! የፋሻ መግዢያ ባጡበት ሁኔታ ትግሉን እየመራን ነው ማለት ቅሌት ነው ። የኮ/ል ደመቀ ሚስት የምትበላው አጥታ ሶፋዋን በሸጠችበት ሁኔታ ላይ ፥ በነሱ ስም 200 እና ከዚያ በላይ ሺ ዶላሮች ሰብስቦ እየታገልን ነው ማለት ምን ማለት ነው ? ማንን ነው የምትዋሹት ?
ምናልባት እስከ አፍንጫው ስለታጠቁ ፥ ትግል ማሽተት አቅቷቸው ይሆን ? ሃሳብ ነው!
አማራ ተነስ !
ኄኖክ የሺጥላ

No comments:

Post a Comment