Thursday, November 17, 2016

አዳዲስ ሹማምንት ሚኒስትሮች ሊለምዱ አልቻሉም። አማካሪዎቻቸው ስኳር እስከሚላስ ነው ይለመዳል ይላሉ።


አዳዲስ ሹማምንት ሚኒስትሮች ሊለምዱ አልቻሉም። አማካሪዎቻቸው ስኳር እስከሚላስ ነው ይለመዳል ይላሉ።
ቆንጂት ስጦታው VIA  ሪፖርተር ክቡር ሚኒስትር
የአንተ ትንሽ መታሰር በቂሊንጦ፣
እኛን ያኖረናል አንበላጦ፡፡
( የኣዲስ ተሿሚዎች ሚስቶች )
Image result for ethiopian new cabinet ministers

[አዲስ የተሾሙት ክቡር ሚኒስትር ከአማካሪያቸው ጋር ቢሯቸው እያወሩ ነው]
  • እንኳን ደስ አለዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እንደዚህ አትበለኝ ባክህ?
  • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
  • ኧረ ይኼን መጠሪያ ተወው፡፡
  • የቱን መጠሪያ?
  • ይኼ ክቡር ሚኒስትር የሚለውን፡፡
  • ለምን?
  • በቃ እኔ ልለምደው አልቻልኩም፡፡
  • አይጨነቁ ይለምዱታል፡፡
  • እኔ እኮ ከምርምሩ ዘርፍ ስለመጣሁ ይኼን መጠሪያ መልመድ ከበደኝ፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ለእርስዎ እንዲያውም ሌላ መጠሪያ ነው የሚያስፈልግዎት፡፡
  • ምን የሚል?
  • ዶክተር ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ኧረ ባክህ በስሜ ጥራኝ?
  • ስነግርዎት ይለምዱታል፡፡
  • ምኑን ነው የምለምደው?
  • የበፊቱም ሚኒስትር እንዲህ ነበሩ፡፡
  • ማለት?
  • ገና ሲሾሙ ክቡር ሚኒስትር አትበሉኝ ይሉ ነበር፡፡
  • ማን በሉኝ ነበር የሚሉት?
  • ታጋይ በሉኝ ይሉ ነበር፡፡
  • ለነገሩ ታጋይ ነበሩ እኮ፡፡
  • ታዲያ የታገሉት ለአገር ሳይሆን ለራሳቸው ነበራ?
  • እንዴት?
  • ስኳር ይልሱ ነበር፡፡
  • ስኳር ያማቸዋል ነው ያልከኝ?
  • ለነገሩ የስኳር በሽተኛም ነበሩ፡፡
  • እ…
  • ግን የተጨማለቁ ነበር፡፡
  • በምን?
  • በሙስና፡፡
  • ሰምቻለሁ፡፡
  • ለማንኛውም ከስምዎት በላይ ሌላ የሚያስጨንቅ ብዙ ነገር አለ፡፡
  • እ…
  • ሙስናው፣ ኔትወርኩ፣ ብልሹ አሠራር ኧረ ስንቱ፡፡
  • እሱስ ልክ ነህ፡፡
  • እነሱ ላይ ማተኮር ነው፡፡
  • አንድ ጉዞ ነበረኝ፡፡
  • መንፈሳዊ ጉዞ ነው?
  • ኧረ ወደ ውጭ ለመሄድ፡፡
  • ከአገር ውጭ?
  • አዎ፡፡ ምነው?
  • አስፈቅደዋል?
  • ማንን?
  • አለቃዎትን ነዋ፡፡
  • የግል ጉዞ እኮ ነው፡፡
  • ቢሆንም ፈቃድ ማግኘት አለብዎት፡፡
  • ለግል ጉዳይም?
  • ጉዞ ለአገር ይጠቅማል ወይስ አይጠቅምም የሚለው መታየት አለበት፡፡
  • ጉዞውማ እኔን ነው የሚጠቅመው፡፡
  • ይኼን እኮ ነው ያልኩዎት፡፡
  • አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ ለማቅረብ ነው የምሄደው፡፡
  • እ…
  • በዚያው ሰዎችን እተዋወቅበታለሁ፡፡
  • የሚቻል አይመስለኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ብዙ ሰውም እተዋወቅበታለሁ እኮ ነው ያልኩህ?
  • ለምን በስልክ አይተዋወቋቸውም?
  • የስልክ አበሌ እኮ 300 ብር ነው፡፡
  • በቫይበር ወይም በዋትስአፕ ይደውሏ?
  • ኢንተርኔት መቼ ይሠራል?
  • ወጣ ብለው ይሞክሯ፡፡
  • ከአገር ነው?
  • ከአዲስ አበባ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ለምሳ ቤት ሲገቡ ሚስታቸውን አገኟቸው]
  • እሺ ሥራ እንዴት ነው?
  • ባክሽ ያስፈራል፡፡
  • ምኑ ነው የሚያስፈራው?
  • ሁሉ ነገር፡፡
  • ማለት?
  • በቃ አብዛኛው ሌባና ሙሰኛ ነው፡፡
  • እና ሥራውን አልወደድከውም?
  • እንደዚያ ማለቴ አይደለም፡፡
  • እስቲ የወደድካቸውን ነገሮች ንገረኝ?
  • መኪናዬን በጣም ወድጃታለሁ፡፡
  • እውነት?
  • በቃ በሾፌርም ስለምሄድ ነው መሰለኝ በጣም ተመችታኛለች፡፡
  • ሌላስ?
  • ያው አሁን ያለኝ ክብር ሌላ ነው፡፡
  • ማለት?
  • ሁሉም ክቡር ሚኒስትር ክቡር ሚኒስትር ሲለኝ ነው የምውለው፡፡
  • እሺ ሌላስ?
  • ያው እንግዲህ የተሰጠንን አዲሱ ቤታችንን በጣም ወድጄዋለሁ፡፡
  • ስማ አሁን ማስተዋል አለብህ፡፡
  • ምን ላስተውል?
  • እነዚህ ነገሮች ከአንተ ጋር ላይቀጥሉ ይችላሉ፡፡
  • ማለት?
  • ጊዜያዊ ነገሮች ናቸው፡፡
  • ምን እያልሽ ነው?
  • ዘለቄታዊ ልታደርጋቸው ይገባል፡፡
  • ሴትዮ ምን ለማለት ፈልገሽ ነው?
  • ተረቱን በደንብ ታውቀዋለህ፡፡
  • የቱን ተረት?
  • ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል የሚለውን፡፡
  • አንቺ ጤና ያለሽ አትመስይኝም፡፡
  • በጣም ጤነኛ ነኝ፡፡
  • ሙሰኛ ሁን ነው የምትይኝ?
  • አልወጣኝም፡፡
  • እና ምን እያልሽ ነው?
  • ዕድሉን ተጠቀምበት፡፡
  • እ…
  • ተረቱን ነው የነገርኩህ፡፡
  • እኔ ተረቱን ቀይሬዋለሁ፡፡
  • ምን ብለህ?
  • ሲሾም ያልሠራ ሲሻር ይቆጨዋል ብዬ፡፡
  • ሰውዬ ተረት ኪስ አይገባም፡፡
  • ምን አልሽ?
  • የወደፊቱን አስብ፡፡
  • የወደፊቱንማ የማታስቢ አንቺ ነሽ፡፡
  • የወደፊቱን ካሰብክማ ያልኩህን ታደርጋለህ፡፡
  • ያልሽኝንማ ባደርግ የወደፊቴ ቂሊንጦ ነው፡፡
  • የአንተ ትንሽ መታሰር በቂሊንጦ፣ እኛን ያኖረናል አንበላጦ፡፡
  • አንቺ በጣም ደፋር ነሽ፡፡
  • ነገርኩህ ክቡር ሚኒስትር አስብበት፡፡
  • ምኑን ነው የማስብበት?
  • በጊዜ መመረቅ አለብህ፡፡
  • ከምን?
  • ከክቡር ሚኒስትርነት፡፡
  • ወደ ምንድን ነው የምመረቀው?
  • ወደ ክቡር ኢንቨስተር!
[የክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ የሥራ ባልደረባ ደወሉላቸው]

No comments:

Post a Comment