Monday, November 14, 2016

እኔ የምለው (1) የሰሞኑ ጫጫታ ለምን ?


እኔ የምለው (1) 
 የሰሞኑ ጫጫታ ለምን ?
የመገንጠል ዓላማ ይዞ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ ቢኖር በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ክልክል ነውን ?
እንዲህ የሚያስብና የሚፈልግ ህዝብ ቢኖር በጉልበት/አፈና  እናስቀረዋለን?
— መፍትሄው  ለእንዲህ ዓይነቱ ጥያቄና ፍላጎት ‹ለምን ተነሳ› ብሎ መንጫጫትና አፈና  ወይስ በአማራና ኦሮሞ እምቢተኝነት እንደታየው አንድነትን የሚያራምድ የጋራ ተግባር፣  የዜጎችን ነጻነትና መብት ማክበር ፣በሌላ አማራጭ ኃሳብ ማሸነፍ –ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ?
አንድ /ሁለት ቡድኖች  ሎንዶን ላይ ‹‹ የኦሮሞን ነጻነት ለማረጋገጥ  ኢትዮጵያ መፈራረስ አለባት ›› —ስላሉ  ጫጫታው ተገቢ ነውን ?  የሶሻል ሚዲያውን  ይሁን  የግለሰቦች ሃሳብ ነው ብለን ብናልፈው ፣ የተደራጁ የመገናኛ ብዙሃን ይህን እስከምንና እስከመቼ  አንጠልጥለው ይቀጥላሉ ? በአገሩ ስለሁላችንም  መብትና ነጻነት፣ ስለ ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነት የ‹አማራ ደም -ደሜ ነው፣ የኮንሶ ደም- ደሜ ነው፣…›› እያሉ የሚሞቱትን በተግባራዊ የትግል ሜዳው ላይ ያሉትን የኦሮሞ ልጆች ዘንግተን ወይም ወደጎን ገፍተን አንድ -ሁለት ሰው/ ቡድን (ለዚያውም አንድን ህዝብ እወክላለሁ ያለ ፣ግን ያልተወከለ፣ ደግሞም እንወክላለን ካሉት ከሃያ አቅራቢዎች አንድ /ሁለቱ ተወካዮች ብቻ ይህን ሃሳብ ለዚያውም ጥያቄና መልስ ላይ በግል የመለሱትን ) ሎንዶን አገር ሆኖ ይህን አለ ብሎ መጮህስ ምን ይሉታል– –ለግለሰቦቹ/ቡድኖቹ የህዝብ ግንኙነት ሥራ መተግበር አይሆንምን ? ለመሆኑ በሎንዶን ኮንፈረስ ስለቀረቡት ‹ገንቢና ጠቃሚ› ሃሳቦችስ ስለምን የዚህን ያህል ሽፋን አላገኙም? የብዙዎች ተቺዎች የመረጃ ምንጭ ኢቲቪ/ፋና መሆኑስ ለህወኃት/ኢህአዴግ የድጋፍ ችሮታ አይደለምን ?
(እርግጥ ይህ አባባል ከመገንጠል አልፎ የእኔን ነጻነት/መገንጠል እውን ለማድረግ  ኢትዮጵያን/አገርን ማፍረስ አለብኝ  ብሎ መነሳቱ አግባብ ባይሆንም ፤ የቡድኑ የስትራቴጂ ጉዳይ አድርገን ብንወስደው — ያዋጣል /አያዋጣም፣ ያስኬዳል/አያስኬድም … የእነርሱ የቡድኑ አባላት ምርጫ ነው፤ አልፎም ተናጋሪውም ሆነ ቡድኑ ይህን ሃሳብ መግለጽ ማራመድ  ለምን ይከለከላል –ፈራጁ ህዝብ እስከሆነ ድረስ ?)
በሌላው  በኩል  አሃዳዊ መንግስት እመሰርታለሁ ብሎ የሚያስብና ፣ ለዚህም የማንነት/ የብሄር ብሄረሰብ ጥያቄ  የሚያነሱትን ጠራርጌ አጠፋለሁ ብሎ ቢደራጅና፣ የራሱን ዓላማ ለማስፈጸም  አፈናውን/ ጠራርጎ ማጥፋቱን   የቡድኑ ስትራቴጂ ጉዳይ አድርገን ብንወስደው — ያዋጣል /አያዋጣም፣ ያስኬዳል/አያስኬድም … የእነርሱ የቡድኑ አባላት ምርጫ ነውና ለእነርሱ እንተወው፡፡  የመጨረሻውን ፍርድ የሚሰጠው ህዝብ ነውና፡፡
የሌሎቹ  የነጻ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት አራማጆች ተግባር መሆን ያለበት ስለአንድነት መስራት፣ በተግባር ማሳየት …. ነው፤ በጋራ ጠላት ላይ ተባብሮ መቆም፡፡ በዚህ ሥርዓት የቱም ኃሣብ በየቱም ቡድን ያዋጣኛል በተባለው መንገድ ለህዝብ ይቅረብ፣ ሕዝብ ይፍረድ፡፡ በነጻ ፍትሃዊ …ተወዳዳሪነትን የሚያራምድ ዲሞክራሲያዊ  ምርጫ ፡፡ 
የሁላችን የጋራ ጠላት ጭቆና በዲሞክራሲ በተሸፈነበት ፣ የሁላችንም ነጻነትና መብት በተከበረበት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደምን አገር የማፈራረስም ሆነ የማንነት ጥያቄ የማፈን ኃሳብ ያሸንፋል ፣ እንደምን ከትልቅነት ወደ ትንሽነት፣ እንደምን ከግንድነት ወደ ቅርንጫፍነት ራስን ማውረድ፣እንደምን የህዝብን ማንነት መካድ… የህዝብ ምርጫ ይሆናል  የሚል ሥጋት  ያሳድራል ? ምርጫው የህዝብ ከሆነስ ማን እንዴት ያቆመዋል፣ ያስቀረዋል ? ለምንስ በተቃራኒው ስለብሄር ጉዳይ መስማት የለብንም የሚል ኃሳብ የሚንጸባርቁ ሃሳቦች የዚህን ያህል በአፍራሽነት ተፈርጀው ሲቀርቡ አይደመጥም ?
ለማንኛውም ማንም ኃሳቡን ይግለጽ –ህዝብ  በነጻነት ይፈረድ፡፡ የህዝብ ፍርድ የሚደመጥበት የህግ የበላይነትን የሚያከብር ሥርዓት መመስረት ላይ ትኩረት እናድርግ፣ እንረባረብ ፡፡
በቸር ያገናኘን፡፡ ጥቅምት 29/09.

No comments:

Post a Comment