የአዲስ አበባ (ሰበታ) ጂቡቲ የባቡር ሃዲድ ግንባታ ሲጀመር መስመሩ የገቢና ወጪ ንግድ ማቀላጠፍ የሚያስችል በመሆኑ በርካቶችን ያስደሰተ ፕሮጀክት ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ባለቤትነት በሁለት የቻይና ኩባንያዎች የተገነባው ይህ የባቡር መስመር በጉጉት ሲጠበቅ ቆይቶ፣ ከወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባሉበት ተመርቋል፡፡ የባቡር ፕሮጀክቱ ከመመረቁ በፊት የጀመረውን የሙከራ ጉዞ ወደ ማገባደዱ የቀረበ ቢሆንም፣ ፕሮጀክቱ ያላካተታቸው ማዕቀፎች እየተስተዋሉ በመምጣታቸው ቅሬታ እየፈጠረ መጥቷል፡፡
እነዚህ ጉድለቶች የአሪቱ ፕሮጀክቶች ፕላን የማድረግ አቅም ጥያቄ ውስጥ የከተቱ ሆነዋል፡፡ 656 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኢትዮ ጂቡቲ አዲስ የባቡር መስመር ለምን ተግባር እንደተገነባ እስከመጠየቅ የደረሱ ባለሙያዎች ብቅ እያሉም ይገኛል፡፡ ምክንያቱም አራት ያህል ማዕቀፎች ፕሮጀክቱ ሲጀመር ጀምሮ ተካተው መሄድ ሲገባቸው፣ ጭራሽ ታሳቢ ባለመደረጋቸው ግንባታው ብቻውን ኢኮኖሚውን ሊደግፍ አይችልም ከሚል አስተሳሰብ የመጣ ጥያቄ እንደሆነ እየተስተዋለ ነው፡፡
የባቡር መስመሩ ከአዲስ አበባ ተጉዞ ጂቡቲ ቢደርስም ወደ ወደቦች የሚወስዱ መስመሮች እስካሁን አልተገነቡም፡፡ በዚህ ምክንያት ደረቅ ዕቃዎች የሚራገፉባቸው ወደቦች ውስጥ ሆነ ነዳጅ የሚራገፍበት ሆራይዘን ተርሚናል ውስጥ መግባት አይችሉም፡፡
ባቡሩ በተለመደው የጭነት አሠራር ዕቃ ጭኖ ወደ አገር ውስጥ ቢመጣም፣ ለምሳሌ በአዋሽ በሚገኘው የመጠባበቂያ ነዳጅ ማከማቻ ዲፖ ውስጥ ነዳጅ ያራግፍ ቢባል እንኳ ወደ ቅጥር ጊቢው የሚወስድ ሃዲድ አልተገነባም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአገሪቱ ትልቁ የደረቅ ወደብ ባለበት ሞጆ ደረቅ ወደብ ቅጥር ግቢ የሚገባበት የባቡር መስመርም አልተዘረጋም፡፡
ከዚህ ባሻገር ባቡሮቹ በኤሌክትሪክና በነዳጅ የሚሠሩ ቢሆኑም፣ በታዳሽ ኃይል እንደምትጠቀም ስትገልጽ ለቆየችው ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም ቢሆን የባቡር መስመሩ ቢጠናቀቅም የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት አስፈላጊ የሆኑትን የመሠረት ልማቶች ገና ናቸው፡፡ በቅርብ በሒልተን አዲስ አበባ በተካሄደ ጉባዔ ላይ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የምህንድስና ግዥና ጥገና ኃላፊ አቶ የኑስ ሙሻጋ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ጂቡቲ ዋና የባቡር መስመር ከጂቡቲ የነዳጅ ወደብ ከሆነው ሆራይዘን ተርሚናልና ከአዋሽ ብሔራዊ የመጠባበቂያ ዲፖ ጋር ባለመገናኘቱ በዚህ ዓመት ነዳጅ ማመላለስ አይጀምርም፡፡
አቶ የኑስ በዚህ ጉዳይ ላይ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ ‹‹ይህ የገጠመን ትልቅ ፈተና ስለሆነ ችግሩን መፍታት ይኖርብናል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ነዳጅ ከማመላለስ ይልቅ በባቡር ቢጓጓዝ ወጪን በከፍተኛ መጠን ይቀንሳል፡፡ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ የባቡር መስመሩ ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ስለወጣበት ለግንባታ የወጣውን ብድር በወቅቱ ለመመለስ ነዳጅ በባቡር ማመላለስ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ ስለሆነም ነዳጅ በባቡር አለመማላለስ ኪሳራ የሚሆንበት አጋጣሚም አለ ይላሉ፡፡
የባቡር ሃዲዱ የሚያጓጉዛቸውን ዕቃዎች ሞጆ ደረቅ ወደብ ለማድረስ 3.5 ኪሎ ሜትር አዲስ የሃዲድ ዝርጋታ ለማካሄድ እንቅስቃሴ ገና ተጀምሯል፡፡ ይህ አስፍቶ አለማየትና በጥልቀት አለመታቀዱ ያመጣው ውጤት ነው ይላሉ ባለሙያዎች፡፡ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሕመድ ቱስ ስሞኑን እንደተናገሩት፣ የሞጆ ደረቅ ወደብን ከባቡር መስመሩ ጋር ለማገናኘት 3.5 ኪሎ ሜትር የባቡር ሃዲድ ግንባታ እየተካሄደ ነው፡፡ ‹‹በኮምቦልቻና በመቐለ ደረቅ ወደቦች ግን ተጨማሪ ወጪ ሳይወጣባቸው ከወዲሁ ከዋናው የባቡር መስመር ጋር እንዲተሳሰሩ ተደርጎ ይገነባሉ ሲሉ የኢንተርፕራይዙ የወደብና ተርሚናል ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ደሳለኝ ገብረሕይወት አክለው ተናግረዋል፡፡
በኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶች በኩል ሲታይም ይኸው የፕላን ችግር መኖሩን የሚያመለክቱ ችግሮች ይታያሉ፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከሚያካሂዳቸው ፕሮጀክቶች መካከል ጊቢ ሦስት ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ግንባታው ተጠናቆ በተለይ በ2008 ዓ.ም. አገሪቱን የድርቅ አደጋ ባጋጠማት ወቅት ሌሎች ግድቦች ውኃ መያዝ ባለመቻላቸው በወሳኝ ችግር ወቅት የደረሰ ኃይል ማመንጫ ግድብ ተብሎ ይሞካሻል፡፡
ግድቡ በአሁኑ ወቅት ተጠናቋል ማለት የሚቻልበት ደረጃ ላይ ቢደርስም፣ እያመነጨ የሚገኘው ከማምረት አቅሙ በግማሽ ያነሰ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፓወር ጄኔሬሽን ኤግዚኪዩቲቭ ኦፕሬሽን ኦፊሰር አቶ አንዳርጌ እሸቴ ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው አጭር ቆጥታ እንደገለጹት፣ የግልገል ጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጫ አሥሩም ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት ይችላሉ፡፡
‹‹ነገር ግን እየተመረተ ያለው በአምስት ተርባይኖች ነው፡፡ የተቀሩት በሪዘርቭ ተይዘዋል፤›› ሲሉ አቶ አንዳርጌ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይህ ሊሆን የቻለውም በአገሪቱ የኃይል እጥረት ባለመኖሩ ነው፤›› ሲሉ አቶ አንዳርጌ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በእርግጥ የመረጃ ምንጮች እንደሚጠቁሙት በአገሪቱ የኃይል ፍላጎት ተሟልቶ ሳይሆን የትራንስሜሽንና የሰብስቴሽን ሥራዎች ባለመሠራታቸው ነው፡፡ በርካታ ፋብሪካዎች የኃይል ፍላጎት ቢኖራቸውም ራሱን የቻለ መስመር ስላልተዘረጋላቸው የሚቸገሩም በርካታ ናቸው፡፡ በከተሞች በተለይ የኃይል መቆራረጡ መሻሻል እያሳየ ቢሆንም፣ አሁንም እዚህም እዚያም ችግሩ እንዳለ የሚታይ ነው፡፡ በዋናነት ግን በአዲስ አባ በሰፊው እየተገነቡ ያሉ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ መስተጓጎልም ሆነ፣ ዕጣ የወጣባቸው ቤቶችም ለነዋሪዎች መተላለፍ ያልቻሉት በኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግር መሆኑ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ጭምር ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ በከተማው የሚገኙ አዳዲስ የመኖሪያ ቤቶች ኤሌክትሪክ አልባ ሲሆኑ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለሥልጣናት ግን ችግሩ የእነሱ ሳይሆን ኤሌክትሪክ የሚያሠራጨው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ላይ ጣት መቀሰራቸው አልቀረም፡፡ ያም ሆኖ ግን ኤሌክትሪክ አቅርቦት አለ ቢባልም ማጠንጠኛው ኤሌክትሪኩ አለመድረሱ ነው፡፡
በቅርብ የተቋቋመው የፌዴራል የተቀናጀ የመሠረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ ንጉሤ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ይህ ችግር በሁሉም የመሠረተ ልማት ተቋማት የሚስተዋል ነው፡፡
አንድ ፕሮጀክት ሲታቀድ ስፋትና ጥልቀት ሊኖረው ይገባል፡፡ ‹‹የባቡር መስመር ለመገንባት ፈልገህ አትነሳም፣ ምንድነው የሚጓጓዘው ብለህ ትነሳለህ እንጂ›› በማለት የሚገልጹት አቶ በቀለ፣ ‹‹ሁሉም የመሠረተ ልማት ተቋማት የተናጠል ዕቅዳቸውን ለማሳካት የሚሯሯጡ በመሆኑ መሰል ችግሮች እየሰፉ መጥተዋል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መንግሥት አዲሱን የፌዴራል የተቀናጀ የመሠረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ አቋቁሟል፡፡ ይህ ኤጀንሲ ባለፈው ቅዳሜ በይፋ ሥራ የጀመረ ሲሆን፣ በተለይ ከዚህ በኋላ የሚሠሩት ግዙፍ የመሠረተ ልማት ተቋማት ወጥ በሆነ መንገድ በሚዘጋጀው ማስተር ፕላን እንዲመሩ ያደርጋል፡፡
እጅግ ችግር ያለባቸው ያልተጣጣሙ ፕሮጀክቶች በሚቋቋሙ ኮሚቴዎች እየተመሩ፣ ችግሩን እንዲያስተካክሉ መመርያ የተላለፈ ሲሆን፣ በግንባታ ሒደት ላይ ያሉት ፕሮጀክቶች ደግሞ ያላካተቱትን ጠቃሚ ግብዓት እያካተቱ ይሄዳሉ ተብሏል፡፡
መንግሥት ከ700 ቢሊዮን ብር በላይ በመመደብ የመንገድ፣ የባቡር ኔትወርክ፣ የቤቶች ልማት፣ የስኳር ልማት፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የውኃ ልማት፣ የኢነርጂ አቅርቦት የመሳሰሉ ግንባታዎችን በሰፊው በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
እነዚህን ፕሮጀክቶች በተለይ የመሠረተ ልማቶችን ዘርፍ አዲስ የተቋቋመው፣ የፌዴራል የተቀናጀ የመሠረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ፣ ሌሎቹ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የሚከናወኑ ቢሆንም፣ በማክሮ ኢኮኖሚ ደረጃ ያሉት ደግሞ በብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን የሚታዩ ናቸው፡፡
በአሁኑ ወቅት የፕላን ያለመናበብ፣ ፕሮጀክቶች በተያዙላቸው የጊዜ ገደብ አለመጠናቀቅ፣ በሁለቱም ዘርፎች እየታየ ያለ ችግር ሲሆን፣ የስኳር ልማትና የማዳበሪያው ፋብሪካ ዘርፍ የእነዚሁ ችግሮች ሰለባዎች ሆነዋል፡፡
በስኳር ዘርፉ 2.25 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስኳር ምርት፣ 304 ሺሕ ሜትር ኩብ ኢታኖል፣ 200 ሺሕ ሔክታር ሸንኮራ አገዳ ልማት በፕሮጀክት ውስጥ የተያዙ ናቸው፡፡ ፋብሪካዎቹና የሸንኮራ አገዳ ልማት በታቀደለት ጊዜ ተጣጥሞ መሄድ ባለመቻሉ የደረሱ የሸንኮራ አገዳዎች እየተወገዱም እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ በማዳበሪያ ፋብሪካዎችም እንዲሁ አምስት ዩሪያ፣ ሦስት የዳፕ ፋብሪካዎች፣ አንድ ሰልፈሪክ አሲድ ፋብሪካ፣ አንድ የከሰል ማዕድን ቁፋሮ ግንባታዎች ይገነባሉ ተብሏል፡፡ ነገር ግን የማዳበሪያ ፋብሪካዎቹ ከእነዚሁ ችግሮች ማምለጥ እንዳልቻሉ እየተነገረ ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ ፕሮጀክቶች በተያዙላቸው ጊዜ ቢጠናቀቁ፣ በትክክል በተሟላ መንገድ ቢታቀዱና አገሪቱ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የምታስመዘግብ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ግን እየተተገበረ ያለው የዚህ ተቃራኒ በመሆኑ አገሪቱን በሀብት ደረጃ ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ በሚገነቡ የመሠረተ ልማት አውታሮች አጀማመር ደስተኛ ቢሆንም፣ ፕሮጀክቶቹ እንዳማረባቸው የሚጠናቀቁ ባለመሆኑም ደስታ በሐዘን እየተቀየረም ይገኛል፡፡
No comments:
Post a Comment