Monday, November 14, 2016

የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና የንግድ ባለሙያዎች በአዲሱ ሹም ሽር ዙሪያ


ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በተቀሰቀሰው ታይቶ የማይታወቅ ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ በአጠቃላይ ወደ አንድ ሺ የሚጠጉ ዜጎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በብዙ ሺዎች የሚገመቱ በእስር ላይ እንደሚገኙ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሪፖርት ይጠቁማል፡፡ የሟቾች ቁጥር ተጋንኗል የሚለው መንግስት በበኩሉ፤የጸጥታ ሃይሎችን ጨምሮ ከ500 በላይ ሰዎች መሞታቸውን አልካደም፡፡ በተቃውሞው በርካታ የመንግስትና የግል ባለሃብቶች
ንብረትም እንደተቃጠለና እንደወደመ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ይሄን የፖለቲካ ቀውስ ተከትሎ ነው በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት፤የከፍተኛ ባለስልጣናትን ሹም ሽር የሚያካትት “ጥልቅ ተሃድሶ” በማድረግ የህዝቡን ጥያቄዎች እንደሚመልስ በ2008 መጠናቀቂያ ላይ ቃል የገባው፡፡ በዚህ መሃል በኦሮሞ ባህላዊ የምስጋና ቀን “እሬቻ” በዓል ላይ በተከሰተው አስደንጋጭ የበርካታ ዜጎች ህልፈት ሳቢያ
ህዝባዊ ቁጣ ተቀሰቀሰ፡፡ በቀጣዮቹ ቀናትም በተለይ የውጭ ባለሃብቶችን ክፉኛ ያስደነገጠ ውድመትና ዘረፋ በፋብሪካዎቻቸው፣በእርሻቸው፣በአጠቃላይ በንብረቶቻቸው ላይ ተፈጸመ፡፡ ይሄን ተከትሎም የዛሬ ሦስት ሳምንት መንግስት አገሪቱን ለማረጋጋትና የህዝቦችን ሰላም ለማስጠበቅ በሚል ለ6 ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁን አስታወቀ፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በግንቦት 200ገ ምርጫ ማግስት ራሳቸው ያቋቋሙትን የሚኒስትሮች ካቢኔት በመበተን፣ከወትሮው በተለየ መንገድ
በምሁራን የተዋቀረ አዲስ ካቢኔ የመሰረቱ ሲሆን 9 ሚኒስትሮች ብቻ ባሉበት ሲቀሩ 16 አዳዲስ ሚኒስትሮችን ሾመዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 5 የሚሆኑት የፓርቲ አባል አይደሉም
ተብሏል፡፡ ሹመቱ የተከናወነው በዋናነት የትምህርት ዝግጅትና ብቃትን መሰረት አድርጎ መሆኑን ለተወካዮች ም/ቤት የገለጹት ጠ/ሚኒስትሩ፤አዳዲሶቹ ሚኒስትሮች የህዝብን
ጥያቄ ለመመለስ አቅሙና ብቃቱ ያላቸው እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና የንግድ ባለሙያዎች በአዲሱ ሹም ሽር ዙሪያ አስተያየታቸውን ጠይቋቸዋል፡፡
“የካቢኔ ቡድኑን መምራት በጠ/ሚኒስትሩ ብቃት ይወሰናል”
ኢ/ር ፀደቀ ይሁኔ
ከግንባሩ ፖለቲካ ውጪ የሆነ የካቢኔ ውይይት ይኖራል ብዬ እጠብቃለሁ፡፡ ብዙዎቹ አሁን ወደ ካቢኔው የገቡ በግንባሩ ፖለቲካ ውስጥ ብዙም ተሳታፊ ያልነበሩ ስለሆኑ፣ ምናልባት አብላጫውን በመያዝ ጠ/ሚኒስትሩ ከተለመደው የፖለቲካ ድባብ ውጪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ ውይይቶች እንዲለመዱ ይረዷቸዋል ብዬ አስባለሁ። ከአዲሱ ካቢኔ ምን ውጤት ይገኛል የሚለውን አሁን መተንበይ አይቻልም፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ይሄን የካቢኔ ቡድን እንዴት እንደሚጠቀሙበት ማየት ያስፈልጋል። ይህ ቡድን እንዴት ይመራል የሚለው፣ የጠ/ሚኒስትሩን ብቃት ነው የሚወስነው፡፡
አሁን በካቢኔው የተካተቱ እንደነ ኢንጂነር ስለሺ፣ ኢ/ር አይሻ፣ ዶ/ር ነገሪ ዓይነት ሰዎች ያላቸው ብቃት፣ ካቢኔው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በደንብ ውይይት እንዲያደርግ ያግዛል፡፡ እነዚህን የመሰሉ ሰዎች መግባታቸው፣ በካቢኔ ደረጃ ለውይይት የሚቀርበውን አጀንዳም ከፍ የሚያደርገው ይመስለኛል፡፡ እኔ መንግስት ምሁራኖችን ለካቢኔው ሊያሳትፍ ይችላል የሚል ግምት ነበረኝ፤ ነገር ግን ምሁራኑ የዚህን ያህል ፍቃደኛ ይሆናል ብዬ አልጠበቅሁም ነበር፡፡
የእነዚህ ሰዎች ፍቃደኛ መሆን ትልቅ ነገር ነው፡፡ በተለይ አሁን የፖለቲካ ትኩሳቱ ባየለበት ሰዓት ፈተናው ስለሚበዛ፣ እነዚህ ሰዎች እሺ ላይሉ ይችላሉ የሚል ግምት ነበረኝ፡፡ ነገር ግን እሺ በማለታቸው ተደንቄያለሁ። መንግስት በካቢኔው እንዲካተቱ በመጠየቁ ብዙም አልተደነቅሁም፡፡
==================================
“የተለየ ሀሳብ ያላቸው ቢካተቱ ጥሩ ነበር”
አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ (የግል ቢዝነስ መሪ)
አዲስ የተሾሙትን የካቢኔ አባላት እምብዛም አላውቃቸውም፡፡ ስለዚህ ብዙ አስተያየት መስጠት አልችልም፡፡ ነገር ግን የመንግስት አካላት እነዚህን ሰዎች በደንብ ያውቋቸዋል፡፡ በደንብ  መርምረው፣ ተጨንቀው ተጠበው መርጠዋቸዋል፡፡
ነገር ግን አሁንም ያልተለወጠ አንድ ባህል አለ። በስራው ዓለም ከመንግስት ውጪ የተፈተኑ ሰዎች አላየንም፡፡ አንድ ሀገር በምሁራንና በፖለቲከኞች ስብጥር ብቻ ምናልባትም በታጋዮች —– (በነሱ ስብስብና በነሱ ልምድ ብቻ) ለምን እንድትመራ ይደረጋል? ምናልባት የሚፈለጉት የጥያቄዎቹ መልሶች የሚገኙት እነሱ ጋ ብቻ ይሆን? ኢህአዴግ በሀሳብ የሚሞግቱትንም ሆነ የተለየ ሀሳብ አለን የሚሉትን እያስገባ አብሮ መስራት ቢለመድ ሸጋ ይመስለኛል፡፡ እኔ ከሹመኞቹ የበለጠ በጣም የሳበኝ፣ ጠ/ሚኒስትሩ በተወካዮች ም/ቤት ንግግራቸው፣ የምርጫ ህግ ሥርዓት መሻሻልን በተመለከተ ደህና አድርገው የገለጹት ጉዳይ ነው።
“አሸናፊው ሁሉንም ነገር ጠቅልሎ የመውሰድ ነገር አለውና እንደገና ልንፈትሸው የሚገባ ነው፤ 51 በመቶ የምርጫ ውጤት ያገኘ መቶ በመቶውን ይውሰደው፤ የሚለው እንደገና ሊታይ ይገባዋል” ብለዋል።
49 በመቶው በምን ይወከል የሚለው አሳስቧቸውም፣ ይሄን እንዴት እናስተካክለው – ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ስለዚህ ወደፊት ከተሸናፊዎችም የፓርላማ ተወካዮች ይኖራሉ ማለት ነው። የሚደግፍና የሚቃወም የፓርላማ አባላት ስብጥር ይኖራል ማለት ነው፡፡ ግን እስከ መጪው ምርጫስ፣ እንዴት ይሁን? የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ ይሄን ለማስተካከል የኢህአዴግ አባል ያልሆኑ፣ የተለየ ሀሳብ ሊያፈልቁ የሚችሉ ሌሎች ሰዎችም በካቢኔው ቢካተቱ ጥሩ ነበር፡፡ እንደኔ አንዳንድ ነገሮች ትንሽ ለወጥ ቢሉ ደስ ይለኛል፡፡፡ ግን አሁን የተደረገውንም ቢሆን በመጥፎ አላየውም፡፡

No comments:

Post a Comment