“ካብ አይገባ ድንጋይ”
ጤና ይስጥልኝ አቶ ፈቃደ ሸዋቀና ሰላምህ ይብዛ በማለት ወደ ፅሁፌ እገባለሁ ። ታዲያ አንድ በሸዋ የደረሰ ታሪክ ቀንጭቤ ልውሰድና በዚያ ልጀምር ። የአፄ ምኒልክን ወይዘሮ ባፈና ታስታውሳቸዋለህ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ። ሰትዮይቱ መጀመሪያ የምኒልክ ወዳጅ የነበሩ ቢሆንም ኋላ ላይ ግን ፍላጎታቸው ስላልተሳካ ምኒሊክን ለማስገደል ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር ታሪክ መዝግቦ አስቀምጦታል ። ሴትዮዋ ምኒሊክን እንዲገሉላቸው ሴራ ውስጥ ከከተቷቸው ሰዎች አንዱ ፤ የሚኒሊክን አልጋ ቀጥ አድርገው ከያዙት ሰዎች ዋና የሆኑትን ራስ ጎበናን ነበር ። ራስ ጎበናም በምኒልክ ጉባኤ ላይ ሽጉጥ ደብቀው ይዘው ሊገቡ ሲሉ ተያዙና ፤ ለፍርድ ቀርበው መኳንንቱ ሁሉ ጉዳዩን ሲመረምሩ የወይዘሮ ባፈና እጅ እንዳለበት ተደርሶበት ፤ መስሪያውም ምኒሊክን ለመግደል የታሰበበት መሆኑ ሲታወቅ ፤ በራስ ጎበና ላይ ፤ የተሰበሰበው ጉባኤ የሞት ፍርድ ፈረደባቸው ። ንጉስ ምኒልክም ይህን ፍርድ ማፅናት ነበረባቸው ። ካፀኑት ይፈፀማል ካላፀኑት ይሻራልና ፤ የሳቸው ውሳኔ ሲጠበቅ ፤ አፄ ምኒልክ ይህን ተናገሩ ። “ጎበናን ከልጅነቴ ከአባቴ ዘመን ጀምሮ አውቀዋለሁ ። የአባቴንም አልጋ አገልግሏል ፤ ዛሬም ቢሆን እኔን እያገለገለ የሚገኝ ታላቅ ወታደር ነው ። ለ25 አመታት የማውቀውን ጎበናን እንዲሞት ፈርጄ ፤ እሱን የመሰለ ሰው ለማግኘት ሌላ 25 አመታት እኔ ራሴስ እድሜ ይኖረኛልን ? ካሉ በኋላ ፤ ስለዚህ እንዲሞት አልፈርድበትም ” ፤ ብለው ፍርዱን ሻሩት ። ይህ የወዳጅነት ተምሳሌት ታላቅ ትምህርት ነው ለኛ ለምኒሊክ ልጆች ። እናም ወደ ዋንው ጉዳዬ ልግባ ።
አቶ ፈቃደ ሸዋቀና ይኸው የኔና ያንተም ወዳጅነት 20 አመታት ሞላው ። ሁለት ጊዜ የመኪና አደጋ አብረን ደርሶብናል ። አንዴ ባንተ ሾፌርነት ቦስተን ማሳቹሴትስ ላይ ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ በኔ ሾፌርነት ሜሪላንድ ኒው ሃምሸር አቨኑ ላይ ። በሁለቱም አጋጣሚዎች ህይወታችንን ልናጣ የምንችልበት አጋጣሚዎች ነበሩ ። ከዚያም አልፈን በተለይ በዘጠናዎቹ ማለቂያ በሳምንቱ መጨረሻ ፤ ሻይ ቡና እያልን ፤ አብረን ያላሳለፍናቸው ቀናት ትዝ አይሉኝም ። የሰዉን ልተወውና ፤ 18ኛው መንገድ ራሱ ለዚህ ምስክር ነው ። ይህን ሁሉ ማለቴ በዘመን አመጣሹ ስድብ ፤ ካንተ ጋር እስጥ አገባ ውስጥ ልገባ እንደማልፈልግ ከወዲሁ ለመግለፅ ፈልጌ ነው ። አንተን በአደባባይ ሰድቤ ፤ ለራሴም ክብር አገኛለሁ የሚል ቅዠትም የለኝም ። ሌላው እንደ አባቶቻችን ሁሉ ፤ በዘመን ያፈራሁትን አንተን የመሰለ ወዳጄን ሰድቤ አዲስ ወዳጅስ ከየት ላገኝ ይቻለኛል ?
ያም ሆኖ ግን ከፅሁፍህ ላይ አንዳንድ ነገሮችን ላንሳና ልተች ። በኤርትራ በኩል የኢትዮጵያ የአማራ ገበሬዎች ስንቅና ትጥቅ እንኳ የሚያቀብል ስለሌላቸው የኤርትራ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ፤ ከኤርትራም የተሻለ ወዳጅ የለንም ብለኻል ። የኢትዮጵያ አርበኞች በዚያ በክፉው የፋሽሽት ዘመን እንኳ ፤ የሚጠጉበት ቀርቶ ፤ አይዟችሁ የሚል መንግስት ባልነበራቸው ዘመን ፤ በአገራቸው ምድር ላይ ፤ በህዝባቸው መካከል ሆነው ታሪክ ሰርተው ነፃነታቸውን ጠብቀው ነበር ያለፉት ። ለአርበኞቹ ለነራስ አበበ አረጋይንና ለእነደጃዝማች በላይ ዘለቀ ስንቅና ትጥቅ የሆናቸው ህዝባቸውና ምድራቸው አገራቸው ነበር ። ይህም በተግባር የተፈተነ ሃቅ ነው ።
ሌላው አንተ አስተማሪ እንጂ ፤ የወታደራዊ ሳይንስ ትምህርቱ እንደሌለህ ስለማውቅ ፤ የሰጠሃቸው ወታደራዊ አስተያየቶች ከግምትነት በላይ ስለማይዘልቁ እተዋቸዋለሁ ። የኤርትራን (ሻእቢያን) ወዳጅነት በተመለከተ ፤ በጭፍን እንደአልተናገርኩ ልብህ ያውቀዋል ። በአይኔ አይቼ ፤ በተግባር ፈትኜ ፤ ለስድስት አመታት ተኩል ተመላልሼ ፤ እኔም ሆንኩኝ ሌሎች ኢትዮጵያውያን በተግባር ተፈትነውበት ያለፍነው ጉዳይ ስለሆነ ፤ ሁኔታውን ካንተ የተሻለ አውቀዋለሁ ።
እንደምታውቀው ደግሞ መመኘት አይከለከልም ፤ ብዙዎች በምኞትና በህልም ውስጥ እንደሚኖሩም አውቃለሁ ። ታዲያ እንዲሆን መመኘት ሌላ በተግባር መሬት ላይ ያለው ደግሞ ሌላ ። ስለዚህ አስተያየትህ ሁኔታውን ካለመረዳት የመነጨ ሃሳብ ነው ብየ አልፈዋለሁ ። እድሉን አግኝተህ አንዴ ሳይሆን ፤ እንደኔ ደጋግመህ ሄደህ ከሻእቢያ ጋር ቆይታ አድርገህ ፤ ምሁራዊ ግንዛቤ ይዘህ እንድትወጣ ደግሞ እመኝልኻለሁ ። አለበለዚያ ግን “ካብ አይገባ ድንጋይ” የሚባለው ተረት እንዳይደርስብህ እፈራለሁ ።
አቶ ፈቃደ ! ስሜን ሳትጠራ አስተያየትህን ብቻ ሰጥተህ ቢሆን ኖሮ ለሰጠኸው አስተያየት ይህን መልስ እንደማልፅፍልህ ከወዲሁ ልገልፅልህ እወዳለሁ ። ይህ ብቻ ሳይሆን አንተን የመሰለ የማውቀው ሰው ባይፅፈው ኖሮም መልስ አልሰጥም ነበር ።
ይህን ነበር ያልከው ። “ትላንት ማታ ባጋጣሚ ቤት ቁጭ ብዬ ፓልቶክ ላይ ያለ ውይይት ስሰማ የአማራ ሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጃለሁ የሚለው ደምስ በለጠ ኢሳያስ አማራ ስለሚጠላ እይቻለ አማርኛ አይናገርም የሚል የጠንቋይ ፖለቲካ ሲናገር ሰምቼው ሳቅኩኝ።” ይህቺን አንድ አረፍተ ነገርህን ብትን አድርጌ ላያት ፈለግኩ ። “ትላንት ማታ በአጋጣሚ ቤት ቁጭ ብየ ፓልቶክ ላይ ያለ ውይይት ስሰማ……” ብለህ ካልከው ልጀምር ። የሰማኸው በአጋጣሚ እንዳልነበረ አንተም እኔም እናውቃለን ። ለምን መሰለህ ! የፓልቶኩ አዘጋጅ ወንድማችን በፓልቶክ ስሙ “አንድነት”፤ አንተም እንግዳ ሆነህ እንደምትገባ ገልፆልኝ ነበር ። ስለዚህ በአጋጣሚ አልነበረም ስታዳምጥ የነበረው ። በምን ምክንያት እንደቀረህ ባላውቅም አንተም ከኛው ጋር ተጋባዥ እንደነበርክ አውቃለሁ ። ስለዚህ አጋጣሚ አልነበረም “………የአማራ ድምፅ ራዲዮ አዘጋጃለሁ የሚለው ደምስ በለጠ ……..” ብለኻል ።
መጀመሪያ አንድ ነገር ላስረዳ ። የፓልቶኩ ጥያቄና መልስ ሲጀመር ፤ ይህ ዛሬ የማደርገው ቃለ-መጠይቅ ከአማራ ድምፅ ራዲዮ ዝግጂት ክፍል ጋር ምንም ግንኙነት የለውም ብየ አስረድቼ ነበር የገባሁት ። ያደረኩትም እንደ አንድ ዜጋ ባለኝ መብት እንጂ ፤ በራዲዮም ስም እንዳልሆነ ካሳወቅኩ በኋላ ለምን ከራዲዮው ጋር ልታያይዘው እንደፈለክ አልገባኝም ። አማራው የራሱን ድምጽ ማግኘቱ የሚጎረውብጣቸውን ሰዎች ለማስደሰት ብለህ ከሆነ ደግሞ ምንም ልንደራቸው እንደማንችል አስረግጬ ልነግርህ እፈልጋለሁ ።
ሌላው ላስረግጥልህ የምፈልገው ፤ አዎ የአማራ ድምፅ ራዲዮ አዘጋጅ ነኝ ። ቀጥሎ ያልከው ፤ “ኢሳኢያስ አማራ ስለሚጠላ እየቻለ አማርኛ አይናገርም የሚል የጠንቋይ ፖለቲካ ሲናገር ሰምቼው ሳቅኩኝ” ፤ ነበር ። ጉዳዩን በአግባቡ አልሰማኸውም ወይም ፤ አባባሌን ገለባብጠኸዋል ። የኢሳኢያስ አማርኛ ችሎታ ፤ ከአንድ ጠያቂ እዚያው ተነስቶ ፤ ትግርኛና አረብኛ ፤ የኤርትራ ብሄራዊ ቋንቋ እንደሆኑ ተማምነን ያለቀ ጉዳይ ነበር ። ዛሬ ላይ እንደ ልማድ የተያዘው ፤ ለርካሽ እውቅና ተብሎ ፤ የሚሰራ ሸፍጥ ደግሞ የትም አያደርስም ።
እኔና አንተ በ20 አመታት ወዳጅነታችን ስለጥንቆላ አንዴ እንኳን ማውራታችንን የማስታውስበት አጋጣሚ አልነበረም ። የጠንቋይ ፖለቲካ የሚባል መኖሩንም እስከዛሬ ድረስ አላውቅም ፤ የማላውቀው ካለ ደግሞ ታላቄም አስተማሪም ነህና ካንተ ለመማር ዝግጁ ነኝ ። ይህም የጠንቋይ ፖለቲካ እንዳሳቀህም አልሸሸግክም ። ይልቅ የሚያስቀውን ልንገርህ ።
ኢሳኢያስ የኔንና ያንተን የሁለት አማሮች ንትርክ ከሰማ ፤ ሊፈጠርበት የሚችለው ስሜት ነው የሚያስቀው ።
አንድ ነገር ልበልህና ፅሁፌን ላጠቃልል ። የአማራው ህዝብ ተቆርቋሪ ነን ባዮች ያልካቸው ሰዎች ፤ አቶ ፈቃደ እንዳትሞኝ ! ባዮች እንዳይመስሉስ ትንታግ ትንታግ የሆኑ የሚሰሩትን የሚያውቁ ጠንካራ ወጣቶች ናቸው ። ታስታውስ እንደሆነ ከአንድ ወር በፊት ይመስለኛል ፤ በዚሁ ጉዳይ ላይ ከሄኖክ የሺጥላ ጋር በፌስቡክ ስትነጋገሩ የአማራው ትግል የምትሉት ወንዝ የማያሻግር ሃሳብ ነው ብለህ ነበር ። ትንታጎቹ የአማራ ልጆች ይኽውልህ ወር በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ሁኔታውን እዚህ አድርሰውት አንተም እኔም ሁላችንም ምስክር ሆነን እያየነው ነው ። በትግባር የሚያምኑ ማእበል ሱናሚ ናቸው ።
ከአራት አመታት በፊት ሞረሾች ስለአማራው መታገል ሲጀምሩ እኔም እንዳንተው ወንዝ አያሻግርም ብያቸው ነበር ። ዛሬ ግን ያፈሩትን የአማራ ወጣት ሃይልና ሁኔታው የገባው ታላላቁን ሰው ሁሉ ሳይ ልክ እንደነበሩ መገንዘብ ችያለሁ ።
አቶ ፈቃደ ሸዋቀና መቼም ወዳጆች ነንና አንዳንድ ምክር ለግሼ ልለፍ ። መሰደቤ አይቀርም ስላልክ ነው ይህን ማለቴ ። ሰው በእድሜ ሰከን ሊል በሚገባው በስተርጅናው ዘመን ፤ ጎርፍ በየጊዜው ካመጣው ጋር ሁሉ እየነጎደ ፤ ከመጡትና ጊዜው ካስጨበጨበላቸው ፖለቲከኞች ጋር ሁሉ ቅንጣት እውቅና በመፈለግ ፤ ከአላፊ አግዳሚው ጋር ፤ እንደ ተሳዳቢ የሰፈር ባልቴት ፤ ከሚላተሙ የፌስ ቡክ የመንገድ ዳር ነገረኞች እንዲሰውርህ እመኛለሁ ።
በተፈጠረው ግርግር ወዳጅነታችን ዋጋውን አያጣም ብየ እገምታለሁና መልካሙን ሁሉ ከልብ እየተመኘሁልህ በዚሁ ልሰናበትህ ። ምንጊዜም ወዳጅህ ደምስ በለጠ ።