ያሬድ ጥበቡ
የትግራይ ማህበረሰብ ውስጥ ለወቅቱ የኢትዮጵያ ሁኔታ ምላሽ ተደርጎ የሚታየው ብአዴን በነፍጠኞች ተይዟል፣ መሪዎች መመንጠር አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን የድርጅቱ ልሳኖች ከሰሞኑ ዘግበዋል። በመሆኑም እነ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አልሰሙ እንደሆነ በመቐለ ቤተመንግስት እየተደገሰላቸው ያለውን ፍጅት ከወዲሁ አውቀው በጀመሩት ከህዝብ ጋር የመወገን ትክክለኛ ፖሊሲ ከዚህ ከተደገሰላቸው እርድ እንዴት መዳን ይቻላቸዋል? ባለፉት 40 አመታት ህወሐትን ከቅርብም ሆነ ከሩቅ እንዳጠናት ሰው የሚከተሉትን ምክሮች መሰንዘር ይጠበቅብኝ ይመስለኛል። ከተሰነዘረባቸው አደጋ ለመዳን የብአዴን መሪዎች የሚከተሉትን እርምጃዎች በአፋጣኝ መውሰድ ይኖርባቸው ይመስለኛል።
- የክልል ምክርቤቱን ስብሰባ ጠርተው፣ ያለምክርቤቱ ጥሪ ወደክልል የገቡትን የአግአዚና ፌዴራል ፖሊስ ሀይሎች ክልሉን በአፋጣኝ ለቀው እንዲወጡ ውሳኔ ማሳለፍና፣ ይህንንም ለህዝቡ በመገናኛ ብዙሀን ማስተላለፍ
- በዚሁ የክልል ምክርቤት ስብሰባ ወቅት የመከላከያ ሰራዊቱ በሃገር ውስጥ ፓለቲካ እጁን እንዳያስገባና፣ ብቸኛ ተግባሩ ሃገሪቱን ከውጪ ጠላት መከላከል መሆኑን ግልፅ ማድረግ፣ እግረ መንገዱንም የመከላከያና ደህንነት አመራሩ የሃገሪቱን ብሄራዊ ተዋፅኦ የተከተለ እንዲሆን ጥያቄ ማቅረብ፣
- በብአዴን ውስጥ ተሰግስገው ለህወሐት የሚሰልሉ እንደ ካሳ ተክለብርሀን፣ ታደሰ ካሳ፣ አለምነው መኮንን ወዘተ የመሳሰሉትን የአመራር አባላት ከአባልነታቸው ማገድና ካስፈለገም ወደ እናት ድርጅታቸው ህወሐት እንዲመለሱ ፈቅዶ ማሰናበት
- የኢህአዴግ አመራርና አደረጃጀት የብሄረሰቦችን ተዋፅኦ የጠበቀ እንዲሆን ማድረግና፣ የህዝብ ቆጠራውን ተከትሎ፣ የኢህአዴግ አመራር 34% ኦሮሞ፣ 28% አማራ፣ 6% ትግራዋይ ወዘተ እንዲሆን ውሳኔ ማስተላለፍና ለተግባራዊነቱ መታገል
- ከአማራ ክልል የተወሰዱትን የድንበር መሬቶች ለማስመለስ መወሰንና፣ ይህንኑ ውሳኔ የሚከታተል ከተቀሙት ቀበሌዎች ነዋሪዎች፣ ምሁራንና፣ የፖለቲካ ልሂቃን የተውጣጣ ግብረሃይል ማቋቋም
- የክልሉን ፕሬዚዳንትና ሌሎች በህዛባዊ ወገንተኝነታቸው የሚታወቁ የብአዴን አመራር አባላትን ካልታሰበ የህወሐት አፈናና እገታ ሊታደግ የሚችል ጥበቃ እንዲደረግላቸው አስፈላጊው የሰው ሃይልና የፋይናንስ ምደባ እንዲረግ መወሰን። ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ፣ የክልሉን ልዩ ሃይል የጥበቃ አቅም ማጎልበት፣ አስፈላጊውን ሥልጠናና ትጥቅ እንዲያገኙ መወሰን፣
- የክልሉ ህዝብ ነቅቶ ለመብቱ ቀናኢ ሆኖ ዘብ እንዲቆምና በእለት ተእለት ህይወቱ አዛዣና ናዛዥ መሆኑ እንዲሰማው፣ ባለፉት 25 አመታት ተግባራዊ ሲደረጉ የቆዩትን ከህወሐት የተወረሱ የአፈና አሰራሮች ለማጥፋት በክልሉ ሸንጎ ላይ ለህዝቡ ቃል መግባት
- ብአዴን የሚመራው ክልል ተነጥሎ እንዳይቆምና፣ ህወሐት ሌሎቹን ክልሎች ይዞ እንዳያጠቃው፣ ሌሎቹን ክልሎችም የሚመሩት አባላት የቀድሞ የኢህዴን አባላት እንደነበሩ በማስታወስ፣ በተለይ የኦሮሚያ ክልል አስተዳዳሪዎች ለተመሳሳይ አላማ እንዲቆሙ የወንድማማችነት ግንኙነት መፍጠር፣ የትግል ህብረትን ማጠናከር
- በአንዳንድ ቦዘኔዎች ወይም በራሱ በህወሐት ሰርጎ ገቦች በትግራዋዮች ላይ የተናጠል ዘር ተኮር እርምጃ እንዳይኖር ነቅቶ መጠበቅ፣ አዝማሚያው በታየበት ሁኔታ ሁሉ እርምጃ መውሰድ፣
እነዚህንና መሰል እርምጃዎችን በመውሰድ የብአዴን አመራር የራሱን አንገት ከተሳለለት ቢላዋ ከማዳን አልፎ፣ ያለምንም ድርጅትና አመራር ጭቆና ስላስመረረው ብቻ እምቢ ለመብቴ ብሎ ለመስዋእትነት የተሰለፈውን የክልሉን ህዝብ ከእልቂት ከማዳንም አልፎ፣ ኢህአዴግ ራሱ የመፍትሄው አካል የሚሆንበትን እድል ሊከፍት ይችል ይመስለኛል።
ይህን ማድረግ አቅቶት ግን የብአዴን አመራር ካመነታ፣ ሳያታሰብ እንደ መብረቅ ብልጭ የሚለው የወያኔ ሰይፍ አናቱን ሊጨፈልቀው ይችላል። ለብአዴን መሪዎች ግልፅ ሊሆንላቸው የሚገባው ነገር፣ ወያኔ ከውልደቱ እስከዛሬም ድረስ የብዙ ድርጅቶችን አመራርን ደም እየጠጣ ያደገ የተመነደገ ድርጅት ነው።
በጥቅምት 1968 ዘገብላ በተባለ ቦታ ቲ ኤል ኤፍ የተሰኘውን የትግራይ ነፃ አውጪ ድርጅት አመራር አባላት “ኑ ድርጅታዊ ውህደት እንፈፅም” ብሎ ከተሰበሰቡ በኋላ እዚያው አፍኖ በመግደል ደም ከጠጣ ጀምሮ በደም አበላ እንደተዘፈቀ የኖረ ሀይል ነው። የብአዴን አመራርም ደም የመጨረሻው አይሆንም። እንግዲህ ግማሽ እርግዝና የለም። የክልላችሁ ህዝብ ሁኔታ ኣሳዝኗችሁ መጠነኛ ወገንተኝነት በማሳየታችሁ፣ በወያኔ የተዘጋጀላችሁ መልስ እርድ መሆኑ ይፋ ተደርጓል። ባለፉት 25 አመታት እንደታዘብኩት ወያኔ አንድ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ትግራይ ኦንላይንና አይጋ ፎረም በተባሉ አፈቀላጤዎቹ መድረክ ለፈረንጆቹ የሚሆን መረጃ መሰል ትንተና በእንግሊዘኛ ይፅፋል፣ ከዚያ በቀናት ውስጥ የማያዳግም እርምጃ ይወስዳል።
አይጋ ላይ የወጣውን የመቐለ ፅሁፍ አንብቤ ይህን ምላሽ ስፅፍ ማምሸቴ የብአዴን ወገኖቼ እጣ ስላሳሰበኝ ነው። ከህዝብ ጎን ስለቆሙ ለምን ይታረዳሉ በማለት። የብአዴን መሪዎች ዛሬ ለሚገኙበት ህዝባዊ ወገንተኝነትና በመቐለ ቤተመንግስት ለተሳለላቸው የእርድ ካራ፣ ባለፉት 25 አመታት ተስፋ ባለመቁረጥ አንድ ቀን ከህዝባችሁ ጎን እንደምትቆሙ የተመሰረታችሁበትን ህዝባዊ መሰረት እንደ ተስፋ መልህቅ በመያዝ፣ “እኔ የማውቃቸው የኢህዴን ልጆች ለጠባብ ብሄርተኝነት እጃቸውን አይሰጡም” በማለት በስደት ስመሰክርና ስከራከር ቆይቻለሁ። የጎንደር ህዝባዊ እምቢተኝነት ላይ ከወያኔ ጋር ተዳብላችሁ ሳትወገዙ፣ የናንተም ልዩ ሀይል በህዝቡ ላይ ሳይተኩስ አብራችሁ ቆማችሁ ሳይ የተሰማኝን እርካታ በቃላት የምገልፀው አይደለም። ሞትን አሸንፋችሁ እንደተነሳችሁ ያህል ነው የተሰማኝ። አሁንም የተጣለባችሁን ጋሬጣ አልፋችሁ በዓይነ ስጋ ለመተያየት ያብቃን። ከህዝቡ ጎን ቆማችሁ ሰማእት ብትሆኑም፣ ስማችሁ ከመቃብር በላይ ይውላል። ተጭበርብራችሁ ግን የወያኔ እርድ ካራ ስር እንዳትወድቁ አደራዬ ጥልቅ ነው። ከክፉ ይሰውራችሁ።
No comments:
Post a Comment