Sunday, August 21, 2016

ሸገር ለምን አታምፅም? BefeQadu Z. Hailu


ሸገር ለምን አታምፅም?

ዛሬ ረፋዱ ላይ በመስቀል አደባባይ አለፍኩ። በርካታ የፌዴራል ፖሊስ መኪኖች እና መኮንኖች ቆመዋል። ለወትሮው በስፖርተኞች ውር-ውር ይደምቅ የነበረው ገጽታዋ ቆሌው ተገፎ ጭር ብላለች። ፖሊስ ከመቼውም የበለጠ ወደአደባባዩ በሚወስዱት መንገዶች ላይ በዝቶ ነበር። ቢያንስ ከአራት ኪሎ እስከ ቦሌ ይህን አይቻለሁ። ሌላው ቀርቶ ሰፈሬ መውጫ ላይ የሚቆሙት ሁለት ፖሊሶች ቁጥራቸው ወደ አምስት ማደጉን አስተውዬ ነበር። አዎ፣ ጥበቃው ከወትሮው የከረረ ነበር። ትላንት እና ከዚያ በፊት አፈሳ እንደነበርም ይታወቃል። አፈሳው በአካል የማውቀውንን ይጨምራል። ትላንት ቦሌ አካባቢ ፖሊስ ሰልፍ እንዳይወጡ ወጣቶችን ሲመክር አይቻለሁ። ማታ ላይ ወደቤቴ ስገባ በፖሊስ ከአላፊ አግዳሚው ጋር ተፈትሻለሁ። ነገር ግን ይህ ሁሉ እንደሚሆን ቀድሞ አይታወቅም ነበር? በሕወሓት/ኢሕአዴግ ባሕሪ እንኳን ጠሪው ያልታወቀ ሰልፍ፣ ፓርቲዎች “ዕውቅና ያገኙበት” ሰልፍ ሲደናቀፍ አላየንም? የሰልፍ ቦታዎችን በፖሊስ መውረር እና አስቀድሞ ተሰላፊዎችን ማፈን የነበረና የሚኖር የኢሕአዴግ ባሕሪ ነው። ስለዚህ ዛሬ (ነሐሴ 15/2008) የተጠራው ሰልፍ በፖሊስ ተደናቀፈ የሚለው ምክንያት ተቀባይነት የለውም። ባይሆን ሌላ ምክንያት እንፈልግ።
፩) መሬት ላይ የተሠራ ነገር የለም!
ጎንደር ላይ የወልቃይትን (specific) ጉዳይ ሲያስተባብሩ የነበሩ የኮሚቴ አባላት እና በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች ነበሩ። ኦሮሚያ ላይ የማስተር ፕላኑን (አሁንም specific) ጉዳይ ሲያስተባብሩ የነበሩ የቄሮ አባላት እና ሌሎችም ነበሩ። አዲስ አበባ ላይ ሰልፍ ራሱ እንደተጠራ መጀመሪያ የሰማሁት ሐሙስ ማታ ነው። እሱም አጋጣሚ ኢሳት ላይ “ሰልፉን ለማደናቀፍ ኢሕአዴግ አፈና ጀምሯል” የሚል ዜና ሲታወጅ ነው የሰማሁት። በማግስቱ ቃሊቲ የታሰሩ ወዳጆቼን ልጠይቅ ስሔድ “የእሁዱ ሰልፍ እንዴት ነው?” አሉኝ። የሰማሁትን ነገርኳቸው። ከዚያ በኋላም በአብዛኛው የሰማሁት የሆኑ ሰዎች በዚሁ ፍርሓት እንደታሰሩ ነው። ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እዚህ ያሉ እና በአገዛዙ በጣም የተበሳጩ ጥቂት፣ በጣም ጥቂት ሰዎች ከመጻፋቸው በቀር ሌሎቹ በሐሰተኛ ሥም የሚጽፉ ወይም በውጭ አገር የሚኖሩ ናቸው ዜናውን ያስተጋቡት። በኔ አተያይ፣ በሐሰተኛ ሥም የሚጽፉት (እዚህ ያሉትም ቢሆኑ) ሰልፍ አይወጡም፤ በእውነተኛ ሥም መጻፍ ሰልፍ ከመውጣት የበለጠ አያስፈራም። እነዚያ በሥማቸው የጻፉት ደግሞ ይታፈሳሉ። ስለዚህ፣ ሰልፉን የማስተባበሩ ሒደት፣ ቢያንስ እኔ እስከማውቀው ድረስ መሬት የወረደ አልነበረም። ስለዚህ ሰልፉን የሚወጣ ሰው መኖሩ ቀድሞም አጠራጣሪ ነበር።
፪) ለአዲስ አበቤ ባዳ የሆኑ አጀንዳዎች
ሌላው ጉዳይ ሕዝብ ጋር የደረሰ ቅስቀሳም ሆነ ሰልፍ የሚያስወጣ አጀንዳ አለመኖሩ ነው። የኦሮሚያ ጉዳይ፣ ጥያቄው ብዙ ቢሆንም መነሻው [አዲስ አበባን ያስፋፋል የተባለው] ማስተር ፕላን መሆኑ ራሱ አዲስ አበባን ይገፋል። ብዙኃኑ አዲስ አበቤ ገንዘብ ካገኘ ሱሉልታ ወይም ሰበታ ላይ መሬት ገዝቶ ቤት መሥራት ነው ምኞቱ። የአማራ ጥያቄም ቢሆን ለአዲስ አበቤ ሩቅ ነው። አዲስ አበቤ ከኦሮሚያም ሆነ ጎንደር ሕዝቦች በተለየ ቅይጥ (heterogeneous) ነው፤ በቋንቋና ባሕላዊ ዳራ እንዲሁም ሃይማኖት አንድ ዓይነት (homogeneous) ሕዝብ ባለመሆኑ የቡድን ጥያቄ ሊኖረው አይችልም። ስለዚህ የአዲስ አበባን ሕዝብ ሊያስተባብሩ የሚችሉት የግለሰብ መብት ጥያቄዎች ናቸው። የአዲስ አበቤን ብሶት በአጫጭር ቃላት አሽሞንሙኖ ማንቀሳቀስ የሚቻልበት ሥራ አልተሠራም። “አማራ እና ኦሮሞ ወገኖችህ ናቸው” የሚለውም በቂ አይደለም። የአዲስ አበባ ሕዝብ ብዙ ምሬቶች አሉበት፣ የብሔር ጭቆና ትርክት ግን አደባባይ አያስወጣውም። የራሱን ችግሮች ከነመፍትሔዎቹ ቁልጭ ባለ መልኩ (specifically) ይህ ነው የሚለው ይፈልጋል። በቡድን ጉዳይ፣ አዲስ አበቤ ቢቻል የብሔር ነገር ባይወራበት ይመርጣል። የኑሮ ውድነት እና በመስፋት ላይ ያለው የመደብ ልዩነት፣ የሰብኣዊ መብት ጥሰት እና የመንግሥት ተቋማት ብልሹ አሠራር ወይም ሙስና የበለጠ ያሳስቡታል። እነዚህ ላይ ብዙ አልተባለም።
፫) ሰልፉን አገር ውስጥ ያለ አካል አልጠራውም
ቅስቀሳውን በብዛት ሲያደርገው የነበረው ኢሳት ቴሌቪዥን ሲሆን፣ ኢሳት አገር ውስጥ ያለው ተዳራሽነት በጣም ውሱን ነው። እርግጥ ኢሳት የሰልፉ አስተባባሪ ሌላ እንደሆነ ቢናገርም፣ ያንን አካል (በሥም እንኳ) የሚያውቀው አልነበረም። ከዚያም በላይ፣ አዲስ አበባ ውስጥ ኢሳት በጠራው ሰልፍ ላይ የሚወጣ ወጣት አለ ብዬ አላምንም። ለዚህ አንዱና ቀላሉ ምክንያት ኢሳት የግንቦት ሰባት ልሳን ነው የሚለው ስጋት ነው። ሌላው፣ አዲስ አበቤ ሰልፍ እንዲወጣ እዚህ እንዳለ የሚያውቀው የሆነ ቡድን ሰልፉን መጥራት አለበት፤ ማለትም የሆነ የሚያውቀው ሰው ወይም ቡድን ሰልፉን አብሮት እንደሚወጣ እርግጠኛ መሆን አለበት። ስለዚህ የፈለገውን ያህል ምሬት እና ብሶት ቢኖርበትም የአዲስ አበባ ሰው ጥቂት ሆኖ ሰልፍ መውጣቱ በፖሊስ ቆመጥ ከመቀጥቀጥ በቀር የሚያተርፍለት ነገር ስላልነበር – አልወጣም። አደጋውን ለመጋፈጥ ደፍሮ እንዲወጣ ከተፈለገ አስቀድሞ የሚያውቀው፣ የሚያምነው አካል እንደሚወጣ እርግጠኛ መሆን ነበረበት ወይም ሊነገረው ይገባ ነበር። ይህ ግን አልሆነም፤ ሁሉም ሰው ‘ሌላ ሰው ይወጣ ይሆን?’ እያለ የማያውቀውን ሰው ይጠባበቅ ነበር።
እንግዲህ፣ በመንግሥት የማፈንና የማስፈራራት እርምጃ፣ እንዲሁም በተቃዋሚዎች የፍርሓትና የሽንፈት ታሪክ መብዛት መካከል ድንገት የተጠራው ሰልፍ በሰበቡ የታሰሩትን ልጆች ሕይወት አደጋ ላይ ከመጣል በቀር ያተረፈው ነገር የለም። ያልተሳኩ የሰልፍ ጥሪዎች በመጪዎቹ የሕዝብ ንቅናቄዎች ላይ የራሳቸውን የ‘አንችልም’ ተፅዕኖ ያሳርፋሉ። የተቃውሞ ሰልፍ በማንኛውም አደጋ መካከል ለመጥራት ከመወሰን በፊት፣ ‘ማንኛውንም አደጋ ተጋፍጦ ሰልፍ መውጣት ተገቢ ነው ወይ?’ ብሎ መጠየቅ ባይቻል እንኳ፣ ‘ማንኛውንም አደጋ ተጋፍጦ ሰልፍ ለመውጣት ፈቃደኛ የሆነ ሕዝብ አለ ወይ?’ ብሎ ማሰብ ያስፈልግ ነበር። ክሽፈቱ ብዙ ዋጋ ያስከፍላልና።
እንደመፍትሔ የምጠቁመው፣ መጀመሪያ ‘የአዲስ አበባ ሕዝብ ጥያቄዎች ምን፣ ምን ናቸው? የሚመለሱትስ እንዴት ነው?’ የሚለውን ማጥራት ነው። ቀጥሎ፣ ለነዚህ መልሶች መገኘት የሚሠራ/ሩ ቡድን/ቡድኖችን ማደራጀት ያስፈልጋል። በመጨረሻም፣ ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ። ያኔ፣ ሸገር፣ በጉያዋ አፍና የያዘችውን ፍም አደባባይ ትበትነዋለች ብዬ አምናለሁ። ያለዚያ ግን፣ በስሜት የሚገኝ ድል የለም።

No comments:

Post a Comment