Thursday, August 11, 2016

ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ፍርድ ቤት አልቀርብም አለ


ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ፍርድ ቤት አልቀርብም አለ
· አቶ በርከትን አቶ አዲሱ ለገሠ የወልቃይትን ጥያቄ ለመፍታት ቃል ገቡ
· የዐማራ ወጣቶች በገፍ እየታሰሩና ወደ ብር ሸለቆ እየተወሰዱ ነው
· ከአብደራፊ ከተማ በሕዝቡ መከላከያ ሠራዊት ለቆ ወጥቷል፤ አማ ታርጋ ያላቸው መኪኖች ከማይካድራ እንዳያልፉ ተከልክለዋል
· ወያኔን የሚያወግዙ መፈክሮች በአገዛዙ ታትመው ባሕር ዳር ገብተዋል
· በቀጣይ እሁድ በብዙ የዐማራ ከተሞች የተጋድሎ ሰልፎች ይኖራሉ
አብደራፊ፤ በአብደራፊ ከተማ ሰፍሮ የነበረው የመከላከያ ሠራዊት በሕዝቡ እምቢተኝነት ከተማውን ዛሬ ለቆ መውጣቱን ለማወቅ ችለናል፡፡ ከትግራይ ክልል በኩል ወደ ምዕራብ አርማጭሆ ከገባውን የመከላከያ ሠራዊት ጋር የአርማጭሆ ዐማሮች ተፋጠው መሰንበታቸው የሚታወስ ሲሆን በሕዝቡ እምቢተኛነት የመከላከያ ሠራዊት ከተማውን ለቆ ወጥቷል፡፡
በሌላ ዜና የዐማራ ታርጋ (አማ) ያላቸው መኪናዎች በትግራይ ክልል ፖሊስ በተቋቋመ ኬላ ከማይካድራ በኋላ እንዳያልፉ ተከልክለዋል፡፡ ኬላዎቹ የተቋቋሙት ማይካድራ ከተማና የወያኔ እርሻ አጠገብ ሲሆን ወደ ኹመራ (ዳንሻ) የሚገቡና የሚወጡ መኪናዎች ላይ ከፍተኛ ፍተሻ እንዳለም ለማወቅ ችለናል፡፡
ጎንደር፤ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቀረ፡፡ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ትእዛዝ የተሰጠ ቢሆን ‹‹ፍርድ ቤት ይቀርባል እያለችሁ ሕዝቤን በጥይት እየጨረሳችሁት ነው፤ ምንም የሠራሁት ወንጀል ስለሌለ እንዲሁ አሰናብቱኝ እንጅ ፍርድ ቤት አልቀርብም›› በማለታቸው ኮሎኔሉ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቀርቷል፡፡ ፍርድ ቤት አካባቢ ፖሊሶች የሚጠባበቀውን ሰው ለመበተን ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡
አቶ አዲሱ ለገሠና አቶ በረከት ስምዖን ትናንት ያደረጉት ስብሰባ ፍሬ አልባ ብሎም ተመሳሳይ ስብሰባ ባሕር ዳር ያደርጋሉ ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም ዛሬም ጎንደር እንደዋሉ ለማወቅ ችለናል፡፡ ዛሬ በጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲቫ ጽ/ቤት ባደረጉት ስብሰባ የወልቃይት ጠገዴን ጉዳይ በአስቸኳይ መፍትሔ እንደሚሰጡበት እንዲሁም የታሰሩ የኮሚቴ አባላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚፈቱ ቃል ገብተዋል፡፡ ሆኖም በስብሰባው የተሳተፉ ዐማሮች ‹‹እስካሁን ድረስ ብዙ ጊዜ ቃል ገብታችሁ ቃላችሁን በልታችኋል፤ ስለዚህ ልናምናችሁ አንችልም፤ ሆኖም በተሎ መልስ ብትሰጡን አገሪቱ እያጋጠማት ያለውን ቀውስ መቀነስ ትችሉ ነበር፡፡ እኛ ግን መልስ እስኪሰጠን ድረስ መቼም ቢሆን ትግላችን አናቆምም›› የሚል ሐሳብ ተንጸባርቋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ እስከ ዛሬ ድረስ በጎንደር ከተማ የንግድም ሆነ ማናቸውም ዓይነት እንቅስቃሴ እንደሌለ ነው የሚናገሩት፡፡ በተለይ ፒያሳና አራዳ የተባሉት የከተማ አካባቢዎች ጭር ብለው ይታዩ እንደነበር የመረጃ ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
ባሕር ዳር፤ በባሕር ዳር ከተማ ዛሬ ሰላማዊ ሰልፉን ለማድረግ ሲያስተባብሩ የነበሩ ወጣቶችን በማፈን አገዛዙ አስቀርቶታል፡፡ በባሕር ዳር የመንግሥት ሠራተኞችና ነጋዴዎች ሥራ እንዳልጀመሩ ለማወቅ ችለናል፡፡ የመንግሥት መሥሪያ ቤት መኪናዎች በግዴታ በከተማው እንዲንቀሳቀሱ እየተደረገ የተረጋጋ ለማስመሰልም ጥረት ሲደረግ ውሏል፡፡
ዘግየት ብሎ በደረሰን መረጃ ደግሞ ወያኔን የሚያወግዙ በርካታ መጠን ያላቸው ባነሮች ተዘጋጅተው ባሕር ዳር ከተማ መግባታቸውን አውቀናል፡፡ እነዚህ ባነሮች ዋናው ዓላማቸው በጸረ ሰላም ኃይሎች አሳበው የዐማራውን ተጋድሎ መንገድ ማሳት መሆኑን ነው መረጃዎቻችን የሚጠቁሙት፡፡ ስለሆነም መላው የባሕር ዳር ዐማራ ይህን ተንኮል እንዲገነዘበው የመረጃ ምንጮቻችን አሳስበዋል፡፡
አጠቃላይ ዐማራው፤ በጎንደር፣ በጎጃም፣ በወሎና በሸዋ አካባቢዎች በርካታ ወጣቶች እየታፈሱ ወደ ብርሸለቆ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያ መወሰዳቸው እየተሰማ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በጎንደር ከተማ (ቀበሌ 18፣09፣ 12)፣ በደብረታቦር፣ በወረታ፣ አዲስ ዘመን፣ በባሕር ዳር (ቀበሌ 11፣ 10፣ 7፣ 13)፣ በደብረ ማርቆስ (ቀበሌ 7)፣ በወልድያ፣ ሐይቅ፣ ደሴና ደብረ ብርሃን ከተሞች በርካታ ወጣቶች መታሰራቸውን ለማወቅ ችለናል፡፡
ከጎንደርና ከባሕር ዳር የታሰሩ ወጣቶች ወደ ብር ሸለቆ የተወሰዱ ሲሆን በሌሎች አካባቢዎች ግን ገና እንደሚወስዷቸው ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት፡፡ ብርሸለቆ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያ ብዙ ዐማሮች እየተወሰዱ ቶርቸር የሚደረጉበት ቦታም ነው፡፡ የ1997 ምርጫን ተከትሎ በርካታ ወጣቶች እዚሁ ቦታ መሰቃየታቸው የሚታወስ ነው፡፡ ከተለያዪ ቦታዎች የበርካታ የታሰሩ ሰዎች ፎቶ ግራፎችና ምስሎች ደርሰውናል፡፡ በብዙዎቹ አካባቢዎች ማረጋገጥ እንደቻልነው የሚወሰደው እርምጃ የሥርዓቱን ጨካኝነት አጥብቆ ያስገነዘባቸውና ለበለጠ ተጋድሎ ያነሳሳቸው መሆኑን ነው የገለጹልን፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በፍተ ሰላም በቀጣይ ሳምንት መጨረሻ የሚደረገውን የተጋድሎ ሰልፍ ለማደናቀፍ አቶ ብናል አንዷለም በፍተሰላም ከተማ ዳሞት ሆቴል መሽገው እንደሚገኙ ለማወቅ ችለናል፡፡ አቶ ብናልፍ አንዷለም የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ሲሆኑ ከአገዛዙ ጎን ሆኑን በርካታ ዐማሮችን እንዳሰቃዩ ይታወቃል፡፡
የዐማራ ተጋድሎ ያሸንፋል!!
Muluken Tesfaw

No comments:

Post a Comment