Monday, August 22, 2016

ሕዝብን የሚያዳምጥ መንግሥት፤ መንግሥትን የሚያዳምጥ ሕዝብ!! ዲ/ን ዳንኤል ክብረት


ሕዝብን የሚያዳምጥ መንግሥት፤ መንግሥትን የሚያዳምጥ ሕዝብ!!
ሀገር ሰላም እንድትሆን፤ ሰላም ሆናም በብልጽና ጎዳና እንድትራመድ ከተፈለገ ሁለት ነገሮች ያስፈልጓታል፡፡ ሕዝብን የሚያዳምጥ መንግሥትና መንግሥትን የሚያዳምጥ ሕዝብ፡፡ ማዳመጥ ከመስማት ይለያል፡፡ መስማት ጆሮ ለተፈጠረለት ሁሉ የሚቻል ነው፡፡ ይህን ጽሑፍ ስናነብ እንኳን ስንትና ስንት ድምጾችን ፈልገንም ሳንፈልግም እንሰማለን፡፡ ማዳመጥ ግን ሦስት ነገሮችን ይፈልጋል፡፡ ይሁነኝ ብሎ መስማት፣ ሰምቶ ማስተዋል፣ አስተውሎም መመለስ፡፡
ሕዝብን የሚያዳምጥ መንግሥት ስንልም ይሁነኝ ብሎ ሕዝቡን የሚሰማ፣ ሰምቶ ሕዝቡ ምን እንዳለው የሚያስተውልና ከዚያም አስተውሎ መልስ የሚሰጥ መንግሥት ማለት ነው፡፡ ለሕዝብ የመናገር ነጻነት ብቻውን ምንም አያደርግለትም፡፡ የመደመጥ መብት ከሌለው በቀር፡፡ ሰሚ ከሌለ እንኳን ሕዝብ ፈጣሪ አይናገርም፡፡ ቢናገርም ጥቅም የለውም፡፡ ለዚህም ነው ሊቃውንቱ እንደሚነግሩን፤መላእክት እስኪፈጠሩ ድረስ ፈጣሪ ፍጥረታትን በአርምሞ ብቻ የፈጠረው፡፡ ለምን? ቢሉ ሰሚ ሳይኖር መናገር ምን ያደርጋል ብሎ። መላእክት ከተፈጠሩ በኋላ ግን ‹ብርሃን ይሁን› ብሎ ሲናገር እንሰማዋለን፡፡ አሁን ሰሚ ተገኝቷልና መናገር ዋጋ አለው፡፡
ሕዝብም መናገሩ ብቻ ጥቅም የለውም፡፡ የተናገረውን የሚያዳምጠው መንግሥት ያስፈልገዋል፡፡ ሕዝብ የሚያዳምጠው ሲያጣ፣ ጩኸቱን የሚያዳምጠው አጥቶ ቤቱ እንደተዘረፈበት ውሻ ‹ነባይነ ነባይነ ከመዘኢ ነባይነ ኮነ – ጩኸን ጩኸን እንዳልጮኽን ሆን› ብሎ አይቀመጥም፡፡ ራሱን በራሱ ማዳመጥ ይጀምራል፡፡
የልቤን መከፋት ሆዴ እያዳመጠ
ሊመረው ነው መሰል ነገር አላመጠ
— የሚል የቆለኛ ፉከራ አለ፡፡ ሰውዬው በልቡ መከፋቱን ለሰው ቢናገር ቢናገር የሚሰማው አጣ፡፡ እርሱ ሰሚ ሲያጣ ሆዱ ግን የልቡን መከፋት እየሰማ ይቃጠል ጀመር፡፡ በኋላም ሆዱ እየቆረጠ ሲሄድ ጊዜ ነው ይህንን የፎከረው፡፡ ሕዝብ ራሱን ማዳመጥ ሲጀምር፤ ‹ሊመረው ነው መሰል› የሚለው ፉከራ ላይ እየደረሰ ነው ማለት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የሚሆነውን ለመገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ ሕዝብን በርእዮተ ዓለም፣ በሐሳብና በአመለካከት አንድ ለማድረግ እጅግ ጽኑ ትግል፣ እጅግ ብርቱ ጥረት፣ እጅግ ብዙ ልፋት ይጠይቃል፡፡ ሕዝብን በቀላሉ የሚያስተባብረው አንድ ነገር ነው፡፡ መጠቃት ወይም መገፋት፡፡ ያን ጊዜ ወዲያ ማዶ ሆኖ አንዱ የተጣራውን፣ ወዲህ ማዶ ሆኖ ሌላው ይሰማዋል፡፡
እዚያ ማዶ ሆኖ አንድ ሰው ተጣራ
እዚህ ማዶ ሆኖ ሌላ ሰው ወይ አለው
ጎበዝ ተነቃቃ ይህ ነገር ለኛ ነው
—- ማለት የሚችለው የሚያዳምጥ መንግሥት ካለ ብቻ ነው፡፡
መንግሥት ሕዝብን ይሁነኝ ብሎ ማዳመጥ አለበት። አንዳንድ ጊዜ ሕዝብ የተናገረው ላይደርሰው ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሕዝብ ያልተናገረውን ሊሰማ ይችላል፡፡ ሕዝብ የተናገረው ለመንግሥት ካልደረሰው ወይም ሕዝብ ያልተናገረውን መንግሥት ከሰማ፣ እወደድ ባዮች ለመንግሥት የሚያስፈልገውን ትተው መንግሥት የሚፈልገውን ብቻ ይነግሩታል ማለት ነው፡፡ ሕዝብ ብዛት ብቻ አይደለም ያለው። ውጥንቅጥም ነው፡፡ በእምነት፣ በርእዮተ ዓለም፣ በመፍትሔ አቅጣጫ፣ በባህልና ቋንቋ፣ በዕውቀትና ሥልጣኔ፣ በዕድሜና ጾታ የተወነቀጠ ነው – ሕዝብ፡፡ ሕዝብን ማዳመጥ ማለት እነዚህን ሁሉ በየመልካቸው ማዳመጥ ማለት ነው፡፡ ሕዝብ ውስጥ መንግሥትን የሚወዱና የሚደግፉ፣ መንግሥትን የሚጠሉና የሚቃወሙም አሉ፡፡ ሕዝብን ማዳመጥ ማለት እነዚህን በየመልካቸው ማዳመጥ ማለት ነው፡፡
ሕዝቡ ይህንን ሲል ምን ማለቱ ነው? ለምን እንዲህ አለ? ምን ስለሠራሁ ወይም ምን ስላልሠራሁ ነው? የትኛውን ችግሬን ስፈታው የሕዝቡ ጥያቄ ይመለሳል? ብሎ ማስተዋል ነው ሕዝብን ማዳመጥ ማለት፡፡ ሕዝቡ ስላልገባው ነው? ስላልተረዳ ነው? ስላልተማረ ነው? ስላልሠለጠነ ነው? እያሉ ጠያቂውን የችግሩ መነሻ ማድረግ፣ ሕዝብን ያለመስማት ዋናው መገለጫው ነው፡፡ ‹ደንበኛ ንጉሥ ነው› እያልን ‹ሕዝብ ንጉሥ ነው› የሚለውን እንዴት መቀበል ያቅተናል? ‹ደንበኛ አይሳሳትም› እያልን ‹ሕዝብ አይሳሳትም› የሚለውን እንዴት ማመን ይሳነናል?
በደርግ ጊዜ አንድ የገጠር ሕዝብ ያምጻል፡፡ መሬት ሲከፋፈል የመሬት ኮሚቴዎች በጉቦ አስቸገሩት፡-
ከዛፍ ወደ ዛፍ ላይ ትዘላለች ጦጣ
መሬትን ያገኘ ኮሚቴን ያጠጣ
ብሎ ዘፈነ፡፡ የሰማው ግን አልነበረም፡፡ ትንሽ ቆይቶ የመንደር ምሥረታ ተባለና የኖረበትን ቀዬ ልቀቅ ተባለ፡፡
ቤቱን አፍርሱ አሉን የበላንበትን
ማፍረስስ አልጋውን ትኋን ያለበትን
ብሎ ዘፈነ፡፡ የሰማው ግን አልነበረም፡፡ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ልጆችህ ይዝመቱ ተብሎ ወታደር ተመራበት፡፡
ልጅህን አምጣ ይላል የኛ ዘመናይ
እኔ ልጄን ስወልድ አዋልዶኛል ወይ
ብሎ ገጠመ፡፡ የሰማው ግን አልነበረም። በመጨረሻም ከእንግዲህ ደርግ ጠላታችን ነው፡፡ ለጠላታችን ለደርግ አንገዛም ብሎ ተማማለ፡፡ ነገሩ እየከረረ መሄዱን የሰሙ ካድሬዎች ወረዱና ሕዝቡን ሰበሰቡት፡፡ ሲነግሩት ዋሉ፡፡ ሲሰማቸው ግን አልዋለም። ስብሰባው ሲያልቅ፤ ‹ጠላቶቻችን ይውደሙ› ብሎ ካድሬው መፈከር አሰማ፡፡ ሕዝቡም በአንድ ድምጽ እጁን አውጥቶ ‹ይውደሙ› አለ፡፡ ካድሬዎቹም ደስ ብሏቸው ስብሰባውን በመፈክር አሳርገው ሄዱ። ለአለቆቻቸው ሕዝቡን አሳምነው እንዳስፎከሩት ተናገሩ፡፡ ሕዝቡ ያለው ሌላ እነርሱ ያዳመጡት ሌላ፡፡
ሕዝብን ማዳመጥ ማለት ሕዝብ የሚለውን ለማዳመጥ መቻል ነው፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቅኔ ሕዝብ ነውና ሕዝቡን ለማዳመጥ ባለቅኔ መንግሥት ያስፈልገዋል፡፡
ሕዝብን የሚያዳምጥ መንግሥት ማዳመጡን በሚሰጠው ምላሽ ነው የሚገልጠው፡፡ ምላሹ የሚወሰነው ለማዳመጥ በሰጠው ማስተዋል ነው። የመጣው ከዚህና ከዚያ፣ ከነእንቶኔና ከነእንትና ነው ማለቱን ትቶ፣ ሕዝብ ተናግሯል ብሎ የሚያምን ከሆነ፣ያንንም ይዞ ከየዓይነቱ ሕዝብ ጋር የሚመክር ከሆነ፣ መክሮም መንግሥት የሚፈልገውን ሳይሆን ሕዝቡ የጠየቀውን የሚመልስ ከሆነ፣ ያ መንግሥት ‹ሕዝብን የሚሰማ መንግሥት› ይባላል፡፡
ሕዝብን የሚሰማ መንግሥት፣ መንግሥትን የሚሰማ ሕዝብ መፍጠር ይችላል፡፡ ሕዝብ የሚያከብረውን፣ የሚወደውንና ይሰማኛል ብሎ የሚያምነውን መንግሥት ይሰማል፡፡ መደማመጥ የጋራ ነው፡፡ ሕዝብ ፈጣሪው የሚለውን የሚሰማውኮ ፈጣሪዬ የምለውን ይሰማኛል ብሎ ስለሚያምን ነው፡፡ ፈጣሪ አይሰማኝም ካለማ ፈጣሪውን መስማት ያቆማል። ማንም የማያዳምጠውን አያዳምጥም፡፡ ፈጣሪም ‹ኑ እንዋቀስ› ያለው የሚወቀስ ነገር ኖሮት ሳይሆን ሕዝቡን እንደሚያዳምጥ ሲናገር ነው፡፡
ሕዝብ መንግሥት አያዳምጠኝም ብሎ ተስፋ ሲቆርጥ ቀስ በቀስ መንግሥትን ማዳመጥ ያቆማል፡፡ መንግሥት የመናገሪያ መሣሪያ ስላለው ብቻ ይናገራል፡፤ ሕዝብም ጆሮ ስላለው ብቻ ይሰማል፤ ግን አያዳምጥም። ነገሩን እውነት ነው ብሎ አይቀበለውም፡፡ ለእኔ ነው ብሎ ልብ አይለውም፡፡ አዳምጦም የሚፈለገውን ምላሽ አይሰጠውም፡፡
አንተ ስትናገር ያልፋል በእኔ ላይ
እኔም ስናገርህ ያልፋል ባንተ ላይ
ከንግዲህ ሆነናል ወንዝና ድንጋይ
የተባለው’ኮ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ወንዝ በድንጋይ ላይ ሲያልፍ ይጮኻል ግን ድንጋዩ አይሰማውም፡፡ ድንጋዩም ውኃው በላዩ ላይ ሲያርፍ ይጮኻል፤ ግን ወንዙ አይሰማውም፡፡
ሕዝብን የማያዳምጥ መንግሥትና እርሱ የሚፈጥረው መንግሥትን የማያዳምጥ ሕዝብ እንዲህ ናቸው፡

No comments:

Post a Comment