Tuesday, August 16, 2016

የትግራይ ህዝብ ማንም ሰው እንዲገደል ትእዛዝ አላስተላለፈም = By: Asfaw Gedamu


የትግራይ ህዝብ ማንም ሰው እንዲገደል ትእዛዝ አላስተላለፈም
=============================
By: Asfaw Gedamu
==============
የትግራይ ህዝብ የኦሮሞ ይሁን የአማራ፣ የጋምቤላ ይሁን የቤንሻንጉል፣ የሱማሌ ይሁን የአፋር፣ የሃረረ ይሁን የደቡብ ተወላጅ እንዲገደል አይፈልግም….በመሆኑም ማንም ሰው እንዲገደል ለህወሓትም ሆነ ለኢህአዴግ ያስተላለፈው አንድም ትእዛዝ የለም፡፡የኢህአዴግ የፅጥታ ሃይሎች ከመግደላቸው በፊት የትግራይ ህዝብን ቢያማክሩና የህዝቡን ፍቃድ የሚያከብሩ ቢሀን ኖሮ ማንም ሰው አይገደልም ነበር፡፡ “ለምን?” ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ የትግራይ ህዝብን ያህል በተደጋጋሚ ጦርነቶች ፍዳውን የበላ ህዝብ የለም፡፡በመሆኑም፣ የትግራይ ወላጆች በጦርነት ወይም የመንግስት ወታደሮች በሚወስዱት እርምጃ የውድ ልጆቻቸው ህይወት ሲቀጠፍ የሐዘን ማቅ ለብሰው መኖርን ያውቃሉ፡፡ከዚህ ጋር በተያያዘ መክንያትም ያለአባት፣ ያለእናት ወይም ያለአባትና እናት ያደገው የትግራይ ተወላጅ ቁጥሩ በጣም ብዙ ነው፡፡ስለዚህ፣ በጦርነት መክንያት ወይም የመንግስት የፅጥታ ሐይሎች በሚወስዱት ምክንያት የሚወዱትን ማጣት ምንኛ እንደሚያሳዝንና እንደሚያሳምም ጠንቅቆ ያውቃል እና እንዲህ ያለ ነገር በሌላ ህዝብ ላይ እንዲደርስ አይፈልግም…አይፈቅድምም፡፡
ሲጀመርም ህወሓት መራሹ የኢህአዴግ ስርዓት የአምባገነኖች ስርዓት መሆኑን ከተስማማን ምን ዓይነት እርምጃዎች፣ እንዴት፣መቼና የት መውሰድ እንዳለበት ከህዝብ ጋር ሊመካከር አይችልም ማለት ነው፡፡አምባገነንነ ነዋ! በህዝብ ይሁንታ ተመስርቶ እርምጃዎች የሚወስድ ቢሆን ኖሮማ አምባገነን አይባልም ነበር… ዲሞክራሲያዊ መሆን አለበት፡፡ዲሞክራሲያዊ ከሆነ ደሞ ማንንም አይገድልም ነው፡፡ ስለሊህ፣ ይህን የአምባገነኖችና የዲሞክራሲያዊ መንግስታት ባህሪ ለይተን የምናውቅ እስከሆነ ድረስ በትግራይ ህዝብ ላይ የሚያነጣጥሩ ዘለፋዎች፣ የስም ማጥፋት ዘመጃዎችና የጥቃት እርምጃዎች መሰረት የለሽ ናቸው፡፡
የህን አይነት ዘመቻ ግን በቤተ አማራዎች፣ በኢሳት ሬድዮና ቴሌቪዥን ጣብያዎች ወዘተ. ሲሰበክ አይተናል፡፡በጎንደር ላይ በትግራይ ተወላጆች የተፈፀመ ግድያና የንብረት ወድመትም ጥላቸው ወደ ተግባር መሸጋገሩን ጠቋሚነው፡፡ የሚገርመው ደሞ በጎንደር፣ በመተመና በደባርቅ የትግራይ ተወላጆች ሕይወት በመጥፋቱ፣ ንብረት በመውደሙ እንደ ጀብድ ተቆጥሮ ሽለላና ቀረርቶ እየተነፋ መሆኑን ነው፡፡
ነገሩን በደምብ እንለጥጠው ከተባለ ደሞ በአጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት መቐለ ከተማ በእንግሊዝ አውሮፕላኖች ተደብድባለች፡፡በደርግ ዘመንም ሐውዜን(የገበያ ቀን) በአንዲት ፀሐይ በሺዎች የሚቆጠር ህዝብ ሕይወት እንደ ቅጠል እንዲረግፍ መደረጉን መቸም ቢሆን አይረሳም፡፡ ሌላም ሌላም መጠቃቀስ ይቻላል፡፡ ይህ ማለት ግን ኮ/ሌ መንግስቱና አጼ ኃይለስላሴ የኦሮሞ ወይም የአማራ ተወላጅ ስለነበሩ የአማራ ወይም የኦሮሞ ህዝብን አስፈቅደው ነው ድብደባውን የፈፀሙት ማለት አይቻልም፡፡የደርግ ሰርዓት የሐውዜን ከተማን ከመደብደቡ በፊት የኦሮሞ ወይም የአማራ ህዝብ አማክሮ ቢሆንና የህዝቡ ፍቃድ ለማክበር ዝግጁ ቢሆን ኖሮ ያ ጥቁር ጠባሳ በትግራይ ህዝብ ላይ አይፈፀምም ነበር፡፡
በመሰረቱ፣ እነዝያ መንግስታትም አምባገነኖች ስለነበሩ የህዝብ ፍላጎት ለማሟላት ዝግጁ ነበሩ ማለት አይቻልም፡፡ ስልጣናቸው ለመጠበቅ ሲሉ ማንኛውም ዓይነት እርምጃ ከመውሰድ እንደማይቆጠቡ በተግባር አስመስክሯል፡፡ የኢህአዴግ ስርዓትም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው የትግራይ ህዝብ ማንም ሰው እንዲገደል ትእዛዝ አላስተላለፈም የምለው፡፡
ስለዚህ በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠሩ የጥላቻ ዘመቻዎች፣ ዘለፋዎችና ጥቃቶች በጋራ ልናወግዛቸው ይገባል፡፡የትግራይ ህዝብ በኦሮምያና በአማራ የሚፈፀመው ግድያ አላወገዘም ስለዚህ የኢህአዴግ(ወያኔ) ደጋፊነውና ከኢህአዴግ ጋር አብሮ መጥፋት አለበት የሚል ሙግትም ውሃ አይቋጥርም፡፡
የአማራ ህዝብ የሐውዜን ድብደባን አላወገዘም! ሳምረ ሳላሳ ጊዜ ስትደበደብ ድምፁን አላሰማም! ይጭላ ከ90 ጊዜ በላይ ስትደበደብ የኦሮሞ ህዝብም ሆነ የአማራ ህዝብ አንዲት ቃል ትንፍሽ አላለም፡፡የደርግ ደጋፊ ነበር ማለት ግን አይቻልም፡፡ስርዓቱ የሚወስዳቸው እርምጃዎች የህዝቡ ስሜትና ፍላጎት ከግምት ውስጥ አያስገቡም፡፡
የትግራይ ህዝብ ጉዳይም ከዚህ ተለይቶ መታየት የለበትም፡፡ማንም ሰው እንዲሞትም ሆነ የአካል ጉዳት እንዲደርስበት አይፈልግም፡፡ሐዘኑም ሆነ ስቃዩ ከማንም በላይ ስለሚያውቀው፡፡

No comments:

Post a Comment