Wednesday, August 24, 2016

ኢትዮጵያ አሁን የሚያስፈልጋት ሰላም ነው ወይስ ፍትህ ? – ፓስተር ዳንኤል ጣሰው

ኢትዮጵያ አሁን የሚያስፈልጋት ሰላም ነው ወይስ ፍትህ ? – ፓስተር ዳንኤል ጣሰው
ሀገራችን ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ ገብታለች።ምንም እንኳ በታሪካችን ብዙ መከራዎችንና የርስ በርስ ግጭቶችን ያሳለፍን ብንሆን እነዚያ አሁን መደገም አለባቸው ማለት አይደለም። እንዲያውም ካለፈው ተምረን በ21ኛው ክፍለ ዘመን ወደ ኋላ መመለስ አይገባንም። በተለይም ሀገራችን የአፍሪካ መኩሪያ እንደመሆኗ ባሁን ሰአት እየሆነ ያለው ከኛ የሚጠበቅ አይደለም።
ኢትዮጵያ ታማለች፤ፈውስ ያስፈልጋታል። ከዚህ አንፃር የሃይማኖት መሪዎች የበሽታው ሳይሆን የፈውሱ አካል መሆን ይጠበቅባቸዋል። በጥበብ የተሞሉት ዮሴፍና ዳንኤል የዓለም መንግስታትን አማክረዋል፤በጎውንም መንገድ አሳይተዋል።
ምነው በኛ ጊዜ ጠፉ? ያን ጊዜ የረዳቸው በነርሱ ያደረ የአምላክ መንፈስ ዛሬም ህያው ነው።
“የምድር ጨው የዓለም ብርሃን ሁኑ” ምን ማለት ነው? ጨውነታችን እኮ ለምድር ነው፤ለሰማይ አይደለም።
ብዙዎች “ሀገሬ በሰማይ ነው፤ይሄ ምድር ያልፋል ዋጋ የለውም” በሚል ድሆችን ከመርዳት፤ለፍትህና ለሰላም ድምጽ ከመሆን ሲሸሹ ይታያል። ቃሉ “ፍርድ ለተጓደለበት ተምዋገት” ይላል፤”ተርቤ አላበላችሁኝም፤ታስሬ አልጠየቃችሁኝም” ይላል። እኛ እስረኞች የምንጠይቀው ወይም የፍርድና የፍትህ መጓደል የሚታወቀን የኛ ዘመዶች ሲታሰሩ ብቻ ነው መሰል። እነዚያን እኮ “ከእኔ ሂዱ” ነው ያላቸው። ይሄንን ሁሉ ዘምረን፤ሰብከን፤ተሯሩጠን አገልግለን “ከእኔ ሂዱ” ከመባል ይጠብቀን። አንድ የሃይማኖት ድርጅት ለማስፋፋት እኮ አይደለም ጥሪያችን፤ይልቁንም ለሰው ልጆች ፍቅር እንድናሳይ እንጂ። የወንጌሉ ምርጥ ጥቅስ “ዓለሙን ወዷልና” አይደል የሚለው? ስብከቱ ይደርሳል መጀመርያ ፍቅር ለህዝባችን እናሳይ። አለበለዚያ “እኔ የምወደው የኔን ድርጅት አባሎች ብቻ ነው” ይመስላል።
አሜሪካዊው የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ማርቲን ሉተር ኪንግ ፤በበጎ ስራቸው የዓለም ኖቤል ተሸላሚና የክፍለ ዘመኑ ምርጥ ሰው የተባሉት ማዘር ቴሬዛ፤ባርነትን ለመጀመርያ ጊዜ ህገወጥ እንዲሆን ያስደረገው እንግሊዛዊው ዊሊያም ዊልበርፎርስ፤ደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ እንዲገረሰስ ታላቅ ሚና የተጫወቱት አርክቢሾፕ ዴዝሞንድ ቱቱ በሙሉ የ ቤ/ክ አገልጋዮች ናቸው። የዘመኑ ዮሴፎችና ዳንኤሎች። ዛሬስ ሰላምን፤ፍትህን፤እርቅን ለሀገር ለህዝብ እያመጣን ነው ወይስ ወንጀል ተፈጽሞበት በግፍ ደሙ የሚፈሰውን ምስኪን አልፈን ፍቅርና ህይወት ወደሌለው አገልግሎታችን እየተሯሯጥን ነው? አረጋግጥላችኋለሁ ጌታ “ከእኔ ሂዱ” ነው የሚለው። ለተደበደቡና ለሞቱት የሚቆሙ ደጋግ ሳምራውያን የት አሉ?
ሁላችንም እንደምናውቀው በሀገራችን ባለፉት ሳምንታት ከፍተኛ ተቃውሞ ተነስቶ ብዙዎች ሞተዋል፤ቆስለዋል፤ ታስረዋል፤ንብረትም ወድሟል። እንደዚህ አይነት ነገር ሲሆን የመጀመርያ አይደለም፤ከዓመት በፊትም በተመሳሳይ ብዙዎች ሞተዋል(በወቅቱ ተመሳሳይ ማሳሰቢያ በተደጋጋሚ አውጥተን ነበር ። በዚህ ከቀጠለ ጠ/ሚኒስትሩ እንዳሉት ሀገሪቱ ወደማያባራ ጥላቻና መተላለቅ ውስጥ ልትገባ ትችላለች።
ሰሞኑን የጉዳዩ አደገኝነት አሳስቧቸው የኢትዮጵያ ሃይማኖት መሪዎች ስለሰላም እንጸልያለን ብለው ጾም ጸሎት አውጅዋል፤መልካም ነው።እዚያ ጋ ግን መቆም የለበትም። አድልዎ የሌለበት የማስታረቅ፤የማግባባት፤የማቀራረብ ስራ መሰራት አለበት። ፍትህ ላጡ መምዋገት መጽሃፉ ያዛል። የኦርቶዶክስ፥ካቶሊክና ፕሮቴስታንት ህብረት የሆነው ጂኒቫ የሚገኘው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ግድያው ቆሞ ውይይት ባስቸኳይ እንዲጀመር አሳስቧል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን ሰለሞቱት ሰዎች አስቸኳይ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል።
በዚህ አጋጣሚ ከተቃዋሚዎችም ከፖሊሶችም ለሞቱት ቤተሰቦች መጽናናትንና ብርታትን እንመኛለን። ልናስተላልፍ የምንወደው 7 ነጥብ ያለው መልእክት እንደሚከተለው እናቀርባለን፤
1-ሰላማዊ ሰልፍ ስለወጡ ብቻ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ግድያ እንዳይፈጸም እንጠይቃለን።
2-ያልተመጣጠነ ሃይል በመጠቀም በሰልፈኞች ላይ ግድያ የፈጸሙ ወገኖች በአስቸኳይ በህግ ይጠየቁ፤ይሄንንም የሚያጣራ ገለልተኛና በሁሉም ወገኖች ተኣማኒነት ያለው አጣሪ አካል ምርመራውን ያድርግ፤
3-ከሰልፉ ጋር በተያያዘ ያላግባብ የታሰሩ እንዲሁም በተለያየ ምክንያት በወህኒ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና ጋዜጠኞች መንግስት ለሰላምና ለመግባባት ሲባል ይፍታ። የእስረኞች ሰብዓዊና ህገመንግስታዊ መብቶቻቸው ተጠብቀው ከቤተሰብና ከጠበቆቻቸው ጋር ያለምንም ተጽዕኖ ይገናኙ፤ፍርድ ቤት የመቅረብ መብታቸው ይጠበቅ፤
ፍርድ ቤቶች ከማንኛውም የፖለቲካ ተጽዕኖ ነፃ ሆነው ፍትህን ይስጡ።
4-ህዝቡ ያቀረበው የፍትህ ጥያቄ በአስቸኳይ ተገቢው ትኩረት ይሰጠው፤ጥያቄዎቹም ይመለሱ።
5-በተለያዩ ወገኖች ያለውን ቁጣ የምንረዳ ቢሆንም ከጥላቻ ንግግሮችና ከዘር ተኮር ስድቦች ከጥቃትና ከሀይል ተግባሮች ሁሉም አካል እንዲቆጠብ እናሳስባለን።እንዲህ አይነት ነገር ሀገር የሚገነባ ሳይሆን የሚያፈርስ ነው። ስሜታችንን ተቆጣጥረን የወደፊት ሀገርን አንድነትና ህልውና ማስጠበቅ መቻል አለብን። እድሉ ያለን ዛሬ ነው። አንዴ ጥላቻው ከቁጥጥር ውጭ ከሆነ መመለሻ አይኖረውም።
6-ይህ ችግር እንዳይደገምና ሀገሪቷ ወደ ለየለት ሁከት እንዳትገባ በሀገር ውስጥም በውጭም ያሉ የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በተወካዮቻቸው የሚሳተፉበት የውይይት መድረክ መንግስት ያዘጋጅ፤ይህን ውይይት የሚያመቻች ሁሉም ወገን የሚቀበለው ከሀገር ውስጥና አስፈላጊም ከሆነ ከዓለም አቀፉ ህብረተሰብ የተውጣጣ አካል ባስቸኳይ ይቋቋም። የወደፊቱም የሀገሪቱ አቅጣጫ መግባባትና በልዩነት አንድነት በሚፈጠርበት ሁኔታ ላይ ተመሳሳይ ብሄራዊ መረዳት ላይ ይደረስ።ለዚህም ያለ ማንም የፖለቲካ ተጽእኖ በተለይ የሃይማኖት መሪዎች፤የሀገር ሽማግሌዎች፤የሲቪክ ድርጅቶችና አስፈላጊ ከሆነ ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ድጋፉን ያድርግ።
7-ከዚያ በመቀጠል የሚደረገው ሀገራዊ ምርጫ ሁሉን ያሳተፈና በተቃዋሚውም በዓለም አቀፍ ደረጃም ተኣማኒነት ያለው ይሁን።
ኢትዮጵያችን ሰላምም ፍትህም ያስፈልጋታል
ሁላችንም የድርሻችንን ዛሬውኑ መወጣት እንጀምር
“በሰዎች መካከል ዕርቅና ሰላምን የሚያደርጉ የእግዚአብሔር ልጆች ስለሚባሉ ደስ ይበላቸው”
ዳንኤል ጣሰው
ከኢትዮጵያ ተነሺ አብሪ


1 comment: