[የክቡር ሚኒስትሩ ሾፌር ፌስቡክ እያያ ይስቃል]
- አንተ ሰውዬ አበድክ እንዴ?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ብቻህን ምን ያስገለፍጥሃል?
- ፌስቡክ እያየሁ ነው፡፡
- እንዴ መቼ ተለቀቀ?
- ደግሞ ማንን አስራችሁ ነበር?
- ፌስቡክን ማን ለቀቀው?
- ለነገሩ ፌስቡክ ራሱ ታስሮ ነበር ለካ፡፡
- እኮ ማን ለቀቀው?
- ትንሽ ቆየ እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምኑ ነው የቆየው?
- ፌስቡክ ከተለቀቀ፡፡
- ማነው ልቀቁ ያላቸው?
- በነካ እጃችሁ ግን ሌሎቹንም ብትለቁ መልካም ነው፡፡
- እነማንን?
- በየጊዜው የምታጉሯቸውን ነዋ፡፡
- ምን አልክ?
- ግን ፌስቡክ ራሱ እንደ መብራትና ውኃ ልታደርጉት ነው ማለት ነው?
- እንዴት ማለት?
- በፈረቃ ነዋ፡፡
- በፈረቃ ሳይሆን በጨረቃ ነው፡፡
- እንዴት በጨረቃ?
- ማታ ማታ ብቻ ነዋ የሚለቀቀው፡፡
- እሷንም አታሳጣን ብንል ይሻላል፡፡
- ለመሆኑ ምንድን ነው የሚያስቅህ?
- እንኩ ይመልከቱት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የማነው ቦርጫም በእናትህ?
- አዩት ዓሳ ነባሪውን?
- የምን ዓሳ ነባሪ ነው?
- ቅፅል ስሙ ነው፡፡
- ይኼ ነው ያስገለፈጠህ?
- እህሳ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ይኼ ያስለቅሳል እንጂ ምኑ ያስቃል?
- ኢትዮጵያን ወክሎ ተወዳድሮ ነው እኮ፡፡
- በምን?
- በዋና፡፡
- በዚህ ቦርጭ?
- አይገርምዎትም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እና እንዴት ሆነ?
- አዋረደን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ግን ሲታይ ልማታዊ ይመስላል፡፡
- እንዴት ማለት?
- ቦርጩ የአገሪቷን ልማት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡
- ምን አሉኝ?
- አታየውም እንዴ ቦርጩ ላይ የ11 በመቶ ዕድገቱን?
- ይኼ የሚያሳየውማ ዕድገቱን ሳይሆን ውድቀቱን ነው፡፡
- ስማ ሁሌ የመፍትሔ ሰው ነው መሆን ያለብህ፡፡
- ምን ማለት ነው?
- ይኼ ሰውዬ ኦሊምፒክ የላክነው ሆን ብለን ነው፡፡
- ለምን ተላከ?
- ለአገር ገጽታ ግንባታ፡፡
- ይኼ ገጽታችንን ያፈርሰዋል እንጂ እንዴት ይገነባዋል?
- ኢትዮጵያ ዓለም ላይ የምትታወቀው በረሃብና በድርቅ ነው፡፡
- እሱማ ልክ ነው፡፡
- እና ፈረንጆቹ በልተን ጠግበን የምናድር አይመስላቸውማ፡፡
- አሁንም እኮ በልተው የጠገቡት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
- ፖለቲካህን እዛው፡፡
- እውነቴን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለማንኛውም እንደዚህ ዓይነት ቦርጫም ኢትዮጵያዊ ሲያዩ ፈረንጆቹ አመለካከታቸው ይቀየራል፡፡
- እንዴት ይቀየራል?
- ጠግበን እንደምናድር ያውቃሉ፡፡
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር ኦሎምፒኩን የተሳተፈው እኮ አባቱ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ስለሆኑ ነው ይባላል?
- ታዲያ ቢሆኑ ምን አለበት?
- እ . . .
- አሁን የእኔ ዘመዶች ሁሉም የመንግሥት ባለሥልጣናት ናቸው፡፡
- እሱስ ልክ ነው፡፡
- ከባለሥልጣኖቹ ውጪ ነጋዴዎች ናቸው፡፡
- ለነገሩ አገሪቷ በእጃችሁ ናት፡፡
- ከእጃችን ልትወጣ አትችልም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ግን እንደዚህ እስከ መቼ ይቀጥላል?
- ምን ማለት ነው?
- በየቀበሌው ራሱ ሲኬድ ሁሉም በወንዝ ነው የተደራጀው፡፡
- ኧረ አንተስ ወንዝ ይዞህ ይሂድ፡፡
- ምን አደረኩ ክቡር ሚኒስትር?
- ወሬ ታበዛለህ፡፡
- አገራችን ተዋረደች እያልኩዎት እኮ ነው፡፡
- ገጽታ ግንባታ ነው አልኩህ?
- ታዲያ ሰውዬው ዋናተኛ መባል የለበትማ፡፡
- ምን ይባል ታዲያ?
- በላተኛ!
[ለክቡር ሚኒስትሩ ከውጭ ስልክ ተደወለላቸው]
- ምን እያደረጋችሁ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- እያደግን ነዋ፡፡
- ኧረ ይኼ ያሳፍራል፡፡
- ምኑ ነው የሚያሳፍረው?
- እየሠራችሁት ያለው ነገር፡፡
- አገራችንን ማሳደጋችን ነው የሚያሳፍረው?
- እንደዚህ እየቀለዳችሁ ግን እስከ መቼ ነው የምትቀጥሉት?
- ገና እየጀመርን አይደል እንዴ?
- ቀልዱን ነው?
- ምን ይላል ይኼ?
- ክቡር ሚኒስትር ይህቺ የተከበረች አገር እያዋረዳችኋት ነው?
- እያከበራችኋት ነው ማለትህ ነው?
- ይኸው አንገታችንን አቀርቅረን እንድንሄድ አደረጋችሁን፡፡
- ስማ አቀርቅረህ መሄድህ እኮ ጥሩ ነው፡፡
- ምን እያሉ ነው?
- እንቅፋት እንዳይመታህ ነዋ፡፡
- ኧረ ይኼ ማላገጥ ይቅር ክቡር ሚኒስትር?
- የምን ማላገጥ ነው?
- ኦሊምፒክ የላካችሁት ሰውዬ ምንድን ነው?
- የቱ ሰውዬ?
- ዓሳ ነባሪው ነዋ፡፡
- ሆን ብለን ነው የላክነው፡፡
- ምን?
- ለአገር ገጽታ ግንባታ ነው፡፡
- ይኼ የአገር ገጽታን ያበላሻል እንጂ ምን ይገነባል?
- አየህ ፈረንጆች የሚያውቁን በድርቅና በረሃብ ነው፡፡
- አሁንስ ቢሆን ከእሱ መቼ ተላቀቅን?
- ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት ቦርጫም ዋናተኛ ትልክና አገሪቱ ውስጥ ጥጋብ መኖሩን ታሳያለህ፡፡
- ግን እንደዚህ እየቀለዳችሁ የምትዘልቁ ይመስላችኋል?
- ምን እያልክ ነው?
- በዚህ ጉዳይ በዓለም ደረጃ አገራችን ነው የተዋረደችው፡፡
- ለምንድን ነው የተዋረደችው?
- ለነገሩ እናንተ ራሳችሁ አዋራጆች ናችሁ፡፡
- ምን አድርገን?
- ስንት ዓለም አቀፍ ውሎችና ውሳኔዎችን በሚገባ ማንበብና መረዳት አቅቷችሁ፣ አዋርዳችሁን የለ እንዴ?
- ምን ትዘባርቃለህ?
- እናንተ ፖለቲከኞቻችን ከዋናተኛው አትሻሉም፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- እናንተም ከሌሎች የምዕራባውያን አገሮች ሚኒስትሮች ጋር ብትወዳደሩ እንደምታዋርዱ እርግጥ ነው፡፡
- ሰውዬ አደብህን ግዛ፡፡
- ለነገሩ እንደነገርኩዎ ከዚህ በፊትም አዋርዳችሁን ታውቃላችሁ፡፡
- ምን ይላል ይኼ?
- አሁን ዋናተኛው ምን እየተባለ እንደሆነ ያውቃሉ አይደል?
- ምን ተባለ?
- ሮቤል ዘ ዌል፡፡
- እ . . .
- እኔ ደግሞ ለእርስዎ ስም አውጥቼልዎታለሁ፡፡
- ምን ልትለኝ?
- ሚኒስትሩ ዘ ዌል!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከአማካሪያቸው ጋር እያወሩ ነው]
- የተናደዱ ይመስላሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አንዱ እኮ ሰድቦኝ ነው፡፡
- ለምንድን ነው የሰደበዎት?
- በዚህ በዋናተኛው የተነሳ ነዋ፡፡
- ታዲያ እርስዎ ምን አደረጉ?
- ፖለቲከኞቻችንም ያው ናችሁ ብሎ ነዋ፡፡
- ምን ብሎ ሰደበዎት?
- ሚኒስትሩ ዘ ዌል፡፡
- ኪኪኪ . . .
- ምን ያስገለፍጥሃል?
- ስድቡ አስቆኝ ነው፡፡
- ወይኔ፡፡
- ወያኔ ነው ያሉኝ?
- ምን ትቀባጥራለህ?
- ግን ተዋረድን እኮ፡፡
- በምንድን ነው የተዋረድነው?
- በኦሊምፒክ ነዋ፡፡
- እንዴት ሆኖ?
- ይኸው በወንዶች አሥር ሺሕ ሜትር አሸነፈን እኮ፡፡
- ማን ነው ያሸነፈን፡፡
- ሞ ፋራህ ነዋ፡፡
- ኃይሌ የት ሄዶ?
- ክቡር ሚኒስትር እርሱ ውድድር ካቆመ ቆየ እኮ፡፡
- ቀነኒሳስ?
- እሱም የመመረጫ ውድድሩ ላይ አቋርጦ ወጣ፡፡
- ታዲያ ማን ነበር የተሳተፈው?
- አይ ክቡር ሚኒስትር በደንብ አላቃቸውም፡፡
- እና ምንድን ነው ችግራቸው?
- ያው በወንዶች እንደ ድሮ ማሸነፍ ተስኖናል፡፡
- ለምንድን ነው ማሸነፍ የተሳነን?
- እኔን’ጃ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለመሆኑ ሯጮቻችን ልማታዊ ናቸው?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በምን አወቅህ?
- ሁሉም እኮ ሕንፃ እየገነቡ ነው፡፡
- አየህ ውስጣቸው ግን ልማታዊ ላይሆን ይችላል፡፡
- ምን እያሉ ነው?
- ለመሆኑ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ተጠምቀዋል?
- እነሱ እኮ ፖለቲከኞች ሳይሆኑ ሯጮች ናቸው፡፡
- አየህ ችግሩ ይኼ ነው፡፡
- የምኑ ችግር?
- የማያሸንፉት ለዛ ነው፡፡
- እንዴት ሆኖ?
- አብዮታዊ ዴሞክራሲ ማለት ሌላ ትርጉሙ አሸናፊ ማለት ነው፡፡
- በለው፡፡
- እኛ በፓርላማ መቶ ፐርሰንት ያሸነፍነው ለዛ ነው፡፡
- ይኼ እኮ ታይቶ የማይታወቅ ነው፡፡
- አየህ አትሌቶቻችንም ታይቶ የማይታወቅ ድል እንዲያገኙ መጠመቅ አለባቸው፡፡
- በምን?
- በአብዮታዊ ዴሞክራሲ!
[ክቡር ሚኒስትሩን የውጭ ጋዜጠኛ ኢንተርቪው ሊያደርጋቸው ቢሯቸው ገባ]
- ይህንን ቃለ መጠየቅ ለማድረግ ስለተስማሙ አመሰግናለሁ፡፡
- እኛ የምንደብቀው ነገር ስለሌለ ችግር የለውም፡፡
- ጥያቄዬን መጀመር እችላለሁ?
- ቀጥል፡፡
- በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሕዝቡ ድምፁን እያሰማ ነው፡፡
- እንግዲህ አገራችን እያስመዘገበችው ባለው ዕድገት ሕዝቡ ደስተኛ ስለሆነ በየቦታው የደስታ ድምፅ ሊሰማ ይችላል፡፡
- አልገባዎትም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምኑ ነው ያልገባኝ?
- ሕዝቡ በተለያዩ አካባቢዎች የተቃውሞ ድምፅ እያሰማ ነው?
- እንዳልኩህ አገሪቱ 11 በመቶ እያደገች ስለሆነ ሕዝብ የእልልታ ድምፅ በየቦታው ያሰማል፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኔ ሕዝብ ስለሚያሰማው ተቃውሞ ነው የምጠይቀዎት?
- በመስኮት እንደምትመለከተው ይኼ ሁሉ የሕንፃ ጫካ የልማቱ መገለጫ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር የተግባባን አይመስለኝም፡፡
- እንዴት እንግባባለን?
- የጠየኩዎትን ጥያቄ ለምን አይመልሱልኝም?
- መለስኩልህ እኮ፡፡
- ምን ብለው?
- እያደግን ነው፡፡
- አሁን የሕዝብ ችግር እየገባኝ ነው፡፡
- ምንድን ነው?
- የሚያዳምጠው የለም!
No comments:
Post a Comment