Friday, August 26, 2016

በአማራው ክልል ያለው መለስተኛ ጦርነት ሳይባባስ መፍትሄ ይፈለግ

 
ግርማ ካሳ

በአማራው ክልል ያለው መለስተኛ ጦርነት ሳይባባስ መፍትሄ ይፈለግ –  ግርማ ካሳ
– በሰሜን ጎንደር ዞን 145 ወታደሮች ተገድለዋል
– ከአዘዞ ካምፕብቻ 143 ወታደሮች ካምፑን ጥለው እስከነ ትጥቃችው ጠፍተዋል
ህወሃት ለሰላም በሮቹን በሙሉ ስለዘጋ፣ በሰላም የሚታገሉ፣ እንደ አንድነት ያሉ ፓርቲዎችን አግዶ፣ እንደ አንዱዋለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን ኦልባና ለሌሳ …ያሉ ሰላማዊ የፖለቲካ መሪዎችን አስሮ፣ ምርጫ መቶ በመቶ አሸነፍኩ ብሎ፣ ዜጎች ወደ ማይፈለጉት መስመር ፊታቸውን እንዲያዞሩ ገፋፍቷቸዋል።የሰላም በር ሲዘጋ የአመጽ በር ተከፍቷል። በአሁኑ ወቅት ምንም መሸፋፈን አያስፈለግም፤ በተለይም በአማራው ክልል በአሁኑ ጊዜ መለስተኛ ጦርነት ነው ያለው።
አንዳንዶች የሕዝቡን ተቃዉሞ እንደ ቀላል ይቆጥሩታል። ከሚገባውም በላይ ሕወሃትን አጎዝፈው ይመለከታሉ። ምናልባት ሕወሃቶችም ራሳችው፣ ለብሄራዊ እርቅ እስከ አሁን ድረስ በራቸውን የዘጉት፣ ለራሳቸው ከፍተኛ ግምት ስለሰጡና ህዝቡንም ስለናቁት ይሆናል ብዬ አስባለሁ።
እርግጥ ነው የህወሃት ሰራዊት መሳሪያ የታጠቀ ሃይል ነው። ያኔ ደርግ እንደነበረው ማለት ነው። ግን የመሳሪያ ብዛት በራሱ የሚፈይደው ነገር አይኖርም። መሳሪያና ትጥቅ አስፈላጊነቱ እንደተጠበቀ፣ ጦርነት የሚደረግበት አካባቢ ሁኔታ፣ የወታደሮች ሞራልና ስሜት፣ የስለላ መረጃ የመሳሰሉትን የየራሳችው ትልቅ አስተዋጾ አላቸው። እንደ ደርግ በአፍሪካ የታጠቀ ሰራዊት አልነበረም። ወደ 500 ሺህ የሚሆን ወታደር ነበር። በመሳሪያና በወታደር ብዛት ቢሆን ደርግ አይሸነፍም ነበር። ያ ጦር ግን የተሸነፈው አንደኛ ወታደሩ ስለተሰላቸና ሻእቢያና ወያኔም በቀጥታ ቅድመ መረጃዎች ያገኙ ስለነበረ ነው። ወያኔና ሻእቢያ ደርግን ያሽነፉት ተዋግተው ሳይሆን በሳቦታጅ ነበር። አሁን ያለው የሕወሃት ሰራዊትም ከደርግ ሰራዊት በምንም አይለየም፡
ሕወሃቶች አንደኛ በአማራው ክልል የታጠቁ ሃይላት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴዎች የማወቅ እድል የላቸዉም። ያ ብቻ አይደለም፡ እነማን እንደሆኑም አያውቅም።
ሁለተኛ በኮንቮይ ከአዲስ አበባ ይሁን ከመቀሌ ወታደሮች መንቀሳቀስ ሲጀምሩ በቀላሉ መረጃዎች ይወጣሉ። የአማራው ክልል መሬቶችም አስቸጋሪ እንደመሆናቸው በወታደራዊ ኮንቮዩ ላይ ጥቃቶችን በመፈጸም ወይንም መንገዶችን በመዝጋት የጦሩን እንቅስቃሴ መግታት ወይንም ማጓተት ቀላል ነው የሚሆነው።
ሶስተኛ መሬቱን የማያውቅ ወታደር፣ ከባባድ መሳሪያ ቢሸከምም ፣ ጉድጓድ ሸንተረሩን ከሚያውቅ የአካባቢው ታጣቂ ጋር መፋለሙ ለርሱ አስቸጋሪ ነው። ባዙቃዉን ተሸክሞ ወደ ላይ ሲመለከት፣ በስር ከዋሻ ብቅ ብሎ አንዱ ይጠለዋል።
አራተኛ አሁን ያለው ሰራዊት በስሜት የሚዋጋ ሰራዊት አይደለም። የሚለግም፣ በሕዝቡ ላይ መተኮስ የማይፈለግ፣ እያጉረመረመ ያለ ሰራዊት ነው። በአለቆቹ እየተሰደበ፣ የዘር ልዩነት እየተደረገበት፣ እድገትና የዉጭ ስልጠና ለአንድ ብሄረሰብ ተወላጆች ብቻ ስለሚሰጠት የተማረረ ሰራዊት ነው። እንዲህ አይነት ሰራዊት ተዋግቶ ድል ማድረግ አይደለም፣ አንድ እርምጃ መራመድ አይችልም።
አምስተኛ ቀውስና አለመረጋጋት የተፈጠረባቸው ቦታዎች አድማሳቸው በጣም የሰፋ ነው። ድፍን ሰሜን እና ደቡብ ጎንደር ( ጎንደር ከተማ፣ ዳባት፣ ደባርቅ፣ አምባ ጊዮርጊስ፣ አዘዞ፣ ማክስኚት፣ ጎርጎራ፣ አርማጭሆ፣ ዳንሻ፣ ደብረ ታቦር፣ ጋይንት፣ አዲስ ዘመን፣ አዘዞ፣ ጭዋሂት፣ ሐሙሲት፣ ሳቆጥራ፣ አለፋ፣ አይንጋ፣ ሳንጃ፣ ሙሴ ባንድ፣ ቆላ ደባ….) በምእራብ ጎጃም ዞን ( ፍኖት ሰላም፣ ማንኩሳ፣ ቡሬ፣ ጅጋና እንዳለ የዳሞት አወራጃ )፣ ምስራቅ ጎጃም ዞን ( ደብረ ማርቆስ፣ አባይ በረሃ ፣ በደጀን አርጎ ወደ ሞጣ ከዚያ ባህር ዳር በሚወስደው መንገድ በአይንጋ) ፣ በባህር ዳር ከተማ እና በጢስ አባይ ከተማ፣ በሰሜን ወሎ ሸዋ (መቄት፣ ቆቦ፣ ማጀቴ ….)፣ በአጠቃላይ በመላው የአማራ ክልል ማለት ይቻላል እንቅስቃሴና ተቃዉሞ አለ። በስንቱ ቦታ ወታደር፣ ከዚህ እዚያ እያመላለሱ ይችላሉ ? እንደ ደሴ ፣ ደብረ ብርሃን፣ ወልዲያ፣ ኮምቦልቻ፣ ሸዋ ሮቢት ባሉ ቦታዎች ህዝቡ ተቃዉሞ ለማሰማት ተዘጋጅቷል። በነዚህ ከተሞች ከፍተኛ የወታደር ክምችት አለ። ህዝቡ እንዳይወጣ ለማፈን እየተጠባበቀ ያለ። ወታደሮቹ ወደ ሌላ ቦታ ከተንቀሳቀሱ ሸዋና ወሎ እንደ ፍም እሳት መቀጣጠሉ አይቀሬ ነው።
እስከ አሁን በተደረገው መለስተኛ ጦርነት፣ ሕወሃቶች ኮሎኔል ደመቀ ዘዉዱን አፍነው ለመወሰድ ብዙ ጊዜ ሞክረው አልተሳካላቸውም። ከሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም ጀመሮ እስከ አሁን በሰሜን ጎንደር ዞን ብቻ (ጎጃምን እና ደቡብ ጎንደር ዞንን ሳይጨምር) ቢያንስ 145 ወታደሮች ሕይወታቸው ጠፍቷል።
በጎንደር ከተማ አሥራ ስድስት የፌዴራል ፖሊስ፣ አንድ የመከላከያ ሰራዊት፣ አንድ ሚሊሺያ፣ ስምንት ልዩ ኃይል የተገደሉ ሲሆን በአዘዞ ሶስት፣ በአይንጋ አሥራ ሶስት፣ በአምባ ጊዮርጊስ ሶስት ፣ ቆላድባና አዘዞ መሃል ላይ (ከገበሬ ማህበር ጋር በተደረገ ጦርነት) ዘጠኝ ፣ በሙሴ ባንድ ዘጠና አንድ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ተገድለዋል።
በአጠቃላይ 143 ወታደሮች። (ይህ መረጃ የተገኘው በሰሜን ጎንደር በጸጥታና ደህነነት እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት አመራር አባላትን ባካተተ ስብስባ ከቀረበ ሪፖርት ነው)
አንድ መቶ አርባ አምስት ወታደሮች መገደላቸው፣ የሕወሃት ጦር ያለበትን ከፍተኛ አጣብቂኝ አንዱን ገጸታ ብቻ ነው የሚያሳየው። ትጥቃቸውን እየያዙ ሰራዊቱን ትተው፣ ህዝቡን ከቀድሞ አለቆቻቸው ለመጠበቅ የሕዝቡን ትግል የተቀላቀሉም ጥቂት አይደሉም። አዘዞ ከሚገኘው የጦር ካምፕ ብቻ ከሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም ጀመሮ፣ ትላንት 13 የሰራዊቱን አባል ያካተተ አንድ ጋንታን ጨመሮ፣ አንድ መቶ አርባ አንድ ወታደሮች ካምፑን ጥለው ሄደዋል። ጠፍተዋል።
የህዝብን መብት በሃይልና በጠመንጃ ማፈን አይቻልም። ህዝብ ቆርጧል። የሕወሃትን መንግስት በፊትም አልመረጥኩም፣ አሁንም እኔን አይወክልም። ይሄን መንግስት የምሸከምበት ትከሻ ከአሁን በኋላ የለኝም ብሏል።ይህ ህዝብ አንገቱን ከዚህ በኋላ አይደፋም። የዚህን ህዝብ ጥያቄ ከመስማትና ከማክበር ዉጭ ሌላ አማራጭ የለም። የዚህ ሕዝብ ጥያቄ ፍትህ፣ ሰላም፣ ልማት፣ እኩልነት፣ አንድነት ፣ ዲሞክራሲ ነው።
በመሆኑ የሕወሃት መንግስት ያለዉን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት በማስገባት፣ ነገሮች የበለጠ ወደ ከፋ ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት፣ ነገሮችን በማርገብ፣ ራሱን ለብሄራዊ እርቅ እንዲያዘጋጅ አሳስባለሁ። በአፋጣኝ የሚከተሉት ቢደረጉም ይጠቅማሉ ብዬ አስባለሁ፡
1. የሕሊና እስረኞች በሙሉ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ይፈቱ
2. የሽግግር መንግስት ወይንም ካቢኔው አገር ቤት ያሉ ተቃዋሚዎችን ያካተተ( መድረክ፣ ሰማያዊ፣ መኢአድ. የቀድሞ አንድነትና ኢዴፓ) የአንድነት መንግስት ይቋቋም (ጦርነት ወይንም ችግር ሲፈጠር ብዙ ጊዜ እስራኤሎች የፓርቲ ልዩነቶቻቸው ወደ ጎን አድርገው ለአገራቸው ደህነንት ሲሉ የአንድነት መንግስት ይመሰርታሉ) ከ እስራኤሎች ትምህርት ይወሰድ። ከፓርቲ ይልቅ የአገር ሰላምና ደህንነት ይቅደም።
3. አሁን ያለውን የፌዴራል አወቃቀር የሚመረመር ገለልተኛ ኮሚሽን ይቋቋም። ይሄ በዘር ላይ የተመሰረተው ፌዴራል አወቃቀር ነዉና አሁን ወዳለነብት ቀዉስ ዉስጥ የከተተን።
4. ፖሊሲ፣ ፍርድ ቤት፣ ምርጫ ቦርድ፣ የህዝብ ቆጠራ ጽ/ቤት፣ የመከላከያ ሰራዊት፣ ሜዲያው ነጻና ገለልተኛ የሚሆንበት ሁኔታ እንዲፈጠር የሚረዳ ተቃዋሚዎችና ባለሞያተኞችን ያካተተ ኮሚሽን ይቋቋም።
5. ለሁለት አመት በኋላ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ይደረግ።

No comments:

Post a Comment