Friday, August 19, 2016

መንግስታችን የሚሞገትለት ልማታዊ ነውን? ግርማ በቀለ

መንግስታችን የሚሞገትለት ልማታዊ ነውን? ግርማ በቀለ
በሰሞኑ ከብዙ ጸሃፊዎች በተለይም የህወኃት ደጋፊዎችና ንኪኪዎች ህገመንግስቱን ማክበርና መገዛት ያለብን የጀመርነው ልማት እንዳይደናቀፍ፣ ሰላማዊ ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ እንደሆነ ያስረዳሉ፣ ትንታኔም ያቀርባሉ፡፡ ግን ያልተመለከቱት ወይም መመልከት ያልፈለጉት ልማቱ ላይ የሚነሳውን የፍትሃዊነት፣ የነጻ ውድድር ዕድልና ተወዳዳሪነት፣ ፍትሃዊ ልማት ሲሆን በተቃራኒው በሁሉም ዘርፍ ፖለቲካ አድሎኣዊነትና የዘር ወገናዊነት እንዳለው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ይህም በየቱም መስክ ለማደግና ስኬታማ ለመሆን ለህወኃት ቅርብ መሆንን እንደሚጠይቅ፣ መነሻውም የዘር ፖለቲካውና የህወኃት አድሎኣዊ የልማት ፖሊሲ መሆኑን ይህንንም ህዝብ ገና ከጅምሩ ‹‹ ትግራይ እስክትለማ ሌላው አገር ይድማ ›› በማለት በአካሄዱ ላይ ያለውን ጥርጣሬ መግለጹን ሊያስታውሱ አይፈልጉም፡፡ በኑሮ ውድነት የሚሰቃየው ህዝብ ጥቂት ባለጊዜዎች በበሉት እንዲያገሳ ፣ ከቤቱ ላልደረሰውና በኑሮው ላላጣጣመው/ላላገኘው ልማት ዘብ እንዲቆም ይሰብካሉ፡፡ ይህ ምጸት፣ሲበዛም ድፍረት ነው፡፡ እነርሱ እሰረቁና እየዘረፉ ያለጠያቂ የሚንደላቀቁበት ሰላም ህዝብ በየማዕዘናቱ በጥይት ግንባሩ ሲበረቀስ፣ አካለጎዶሎ ሲሆን ሲታሰርና ሲሰደድ እንዳይመለከቱ ጋርዶኣቸዋል፤ ከህጻናት እስከ አረጋዊን የሚሰቃዩበትን እውነታ ሰላም ነው ብለን አታሞ እንድንደልቅና ስለልማታችን ስንል ለቀጣይነቱ ከጎናቸው እንድንቆም ይሰብካሉ፡፡ ይህ መታወር ፣ ሲያልፍም ንቀት ነው፡፡ በተጨባጭ ያለው ‹መንግስታችን› ልማታዊና በህገ መንግስቱ መሰረት ሁሉን በእኩልነት እያስተናገደ ነውን? ብለን እንድንጠይቅ ያስገድዳል፡፡ ተመሳሳዮችን በሺዎች የሚቆጠሩ ትተን ለማሳያነት የሚከተሉትን በኢትዮጵያዊያን ባለራዕዮች ተጀምረው በህወኃት መንግስት የቀጥታና ተዘዋዋሪ ጣልቃገብነት የከሸፉ የልማት ፕሮጄክቶችን ከየዘርፉ በጥቅል እንመልከት፡፡
  • 1. ትምህርት፡- ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ፤ በአገራችን የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ፈር ቀዳጅና በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ስኬትን ያስመዘገበው የዩኒቲ ዩኒቨርስቲ መስራችና ፕሬዝዳንት ዛሬ የት ናቸው? ዩኒቨርስቲውን እንዴትና ለማን አስተላለፉ? ከአገራችን አልፈው ለአፍሪካ የሚዳረስ ራዕይ ሰንቀውና ተቀባይነት ማግኘታቸውን በሰማን ማግስት ለምንና እንዴት ለስደት እንደበቁ፣ ለምን ወደ ተቃውሞ ጎራው እንደተቀላቀሉ ከራሳቸው አንደበት የሰማነው ይህን የህወኃት መንግስት ‹ልማታዊ› እንድንለው ወይስ ህወኃትና የህወኃት ባለሟሎች ካልገቡ- ካልተጠቀሙበትና ካልተቆጣጠሩትና ካልዘረፉበት የምን ልማት የሚል አድሎኣዊና ዘረኛ የልማት ፀር እንድንል ያስገድዳል ? ይህን መጠየቅ በራሱ ፀረ-ልማት ፀረ-ሰላምና ፣ ሲያልፍም ‹‹ሽብርተኛ›› የሚያስብል ስርኣት አይቀጥል ማለት ስለመንግስታችን ልማታዊነት ምን ይነግረናል? በዚሁ ዘርፍ በተመሳሳይ በቅርቡ በኩዊንስ ኮሌጅ የደረሰውን እየሰማን ነው፡፡ 2. አግሮ-ኢንዱስትሪ፡ – ሕብር ስኳር አክሲዮን ማኅበር፤
    ከመንግስት ለ10 ስኳር ፕሮጄክቶች በተመደበ 77 ቢሊዮን ብር አንድም ፋብሪካ ወደ ምርት ባልገባበት በስኳር ማምረት ተስፋ የተጣለበት ሕብር በማንና ለምን ተደናቀፈ ስንል የመከላከያው ሜቴክና የትግሬዎቹ እነወዲ አስመራ ግልጽ ዓይን ያወጣ የአየር ባየር ዘረፋና ፣ የመስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂኒሪንግ ( 25 ሚሊየን ብር) ምንተፋ ፣800 ሚሊን ብር አድራሻው የጠፋበት እውነታ በቂ መልስ ይሰጣል ፡፡ የአገር ልማት በእነ ወዲ አስመራ /ነፍስ ይማር/ ደላላነት፣ በሜቴክና መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂኒሪንግ ዘራፊነት የሚመራ ልማት የት ያደርሰናል ?
    3. ኢንዱስትሪ ፡- ግሪን ስታር የምግብ ኩባንያ፤
    ይህ በአሜሪካ የ16 ዓመታት ልምድ ያለው ኩባንያ በአገራችን ‹ ጉድ ፉድ › የሚል ምርት አምርቶና ለኤክስፖርት ገበያ ማቅረብ ከጀመረበት ለምን አገር ለቆ ወጣ ስንል መስራቹ የሚሰጡን መልስ ያስረዳናል፡፡ ከመንግስት ባለሥልጣናት ወሳኝ ሰዎችን ባለመያዙ ስለመሆኑ ‹‹..ደህና ሰው ሼር ብታስገቡ/ ወ/ሮ አዜብን ብታስገቡ ነው ጥቆማው…›› ይህ ሁሉ ችግር አይገጥማችሁም ተብሎ መመከሩን ነው፡፡ ስለ አጉዋ በሚሰበክበት ፣ የህወኃት አባላትና ደጋፊዎች አየር ባየር በሺዎች ሄክታር በሚወስዱበት አገር በአሻጥርና በመርህ በመመራቱ ብቻ 200 ሄክታር ተከልክሎ ከአገር እንዲወጣ መደረጉ ‹የልማታዊ መንግስታችን› አበርክቶ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየን የመንግስትን ልማታዊነት ወይስ የህወኃት ዘረኞችን ጥቅም ያላስከበረ ልማት ሊሳካ ያለመቻሉን ? 4. ትራንስፖርት ፡- ሆላንድ ካር ለምንና እንዴት ከሸፈ ?
    በአገራችን መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ በመትከል ፈር ቀዳጅ የነበረው 690 የቤት አውቶሞቢሎች፣ ‹‹አሃዱ›› የሚባል የከተማ አውቶቡስ አምርቶ ለገበያ ያቀረበ፣ ምርጥ የአፍሪካ ኩባንያ ተብሎ በ-አፍሪካን ግሮውዝ ኢንስትቲዩት ተሸላሚ የነበረ ኩባንያ ከገበያ እንዲወጣ / መስራቹ ከአገር እንዲባረሩ ተደርጎ በወጡበት ማግስት መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂኒሪንግ ተመሳሳይ ምርት ወደማምረት እንዲገባ ተደርጓል፡፡ ለዚህም በጨዋታው የህወኃት ወሳኝ ሰው ‹ተሰላፊ› ያለመሆኑ ነው፡፡
    የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፡- አክሰስና አያት ሪል ስቴትስ – እነ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን የሄዱበት የስኬት መንገድና የተጫወቱበት ደንቃራውን አፈራርሶ ሁሉንም የሚያስችል ሜዳ ‹ጠፍቶባቸው›፣ የልማትና ቢዝነስ ዕውቀትና ክህሎት ‹አንሶኣቸው› ለእስራት የተዳረጉት ግን የሪል ስቴት ፈር ቀዳጅ የሆኑት አቶ አያሌውና በተለያበፈጠራና ዕውቀት የታገዙ የልማት ሥራዎች የሚታወቁት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ — ነገ ፀሃይ ስትወጣ ምን ይነግሩን ይሆን ?
    በሌላ በኩል ትናንት የት እንደነበሩ የማናውቃቸው የህወኃት ባለሥልጣናትና የድንገቴ ባለሃብት የህወኃት ሰዎችን ብዛትና ስርጭት ዘርዝረን አንጨርስም፤በቀጥታና በተዘዋዋሪ አልሚነት/ተጠቃሚነት ‹የመሃሉን ጨርሰው› ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ፣ ደቡብ ኦሞ ሁሉ ደርሰዋል ፡፡ አገሪቱን ለአስርተ ዓመታት ያገለገሉ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላትና የቀድሞ የደርግ ባለሥልጣናት የትም ተጥለው ባሉበትና ያሉበት በማይታወቅበት ትናንት ባዶ እጃቸውን ከጫካ ገብተው ‹ተባረሩ› የተባሉ ጀኔራሎችና በጡረታ የተገለሉ የህወኃት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ግን ባለኢንዱስትሪ ኢንቨስተሮች፣ በመቶ ሺህ የሚከራይ ህንጻ ፣… ባለቤት ሆነዋል፡፡ እንዲያው ስለአገር ልማት ከአንጀት እንነጋገር ከተባለ በሙስና (እኔ ቃሉን መሸፈኛ አድርጌ ስለምወስደው) በሌብነትና ዘረፋ የቀድሞውን ‹ባለራእይ መሪ› ጨምሮ በህወኃት ሰዎች እጅ የገባው የግለሰቦችና የኢፌርት ሃብት፣ ዛሬ እንደገድልና ድል የሚወራላቸውን ለዘረፋ የታጩ ስንት ህዳሴ ግድብ፣ ስንት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፣ ስንት ኪሎ ሜትር አስፋልት መንገድ፣ ስንት የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ስንት …. ይሰራልን ነበር ብላችሁ አስቡ፡፡ እውነቱን በግልጽ እንነጋገር ካልን ይህ የአዲስ አበባ -ፊንፍኔ ዙሪያ የጋራ ማስተር ፕላን ፕሮጀክት በኦሮሚያ ያስነሳው ተቃውሞ ከዚህ አስተሳሰብ የተለየ አይደለም ፣ በአሁኑ ተጨባጭ ሁኔታ በሌሎች ክልሎችም ከዚህ የተለየ አስተሳሰብ ይኖራል ብዬ አልገምትም ፡፡
    ለአገራቸው ትልቅ ራዕይ ይዘው ፣ብዙ ተጉዘው ጉዞኣቸው በስደት እንዲጠናቀቅ የተገደዱት የህብር ስኳር አክሲዮን መስራችና ዋና ስራአስኪያጅ አቶ ምንአላቸው ስማቸው እንዳሉት አገሪቱ ‹‹ ፓርላማው ስለሜቴክ ሰምቶ ምንም እርምጃ በማይወስድበት የካዛንቺስ መንግስት እየተመራች ነው ›› በሚባልበት እውነታ ውስጥ ስለአገር ልማትና ልማታዊ መንግስት መስበክ እስከየት ይወስደናል? ልማቱን ለማስቀጠል ህገመንግስቱን ማክበርና መጠበቅ አለብን ስንል በዚሁ በተለመደው መንገድ ከሆነ አያስኬድም፣ አይሰራም፡፡ ከዚህ ውጪ ስለልማት የምንነጋገረው ስለድንገቴ ዘራፊ ባለሃብት የህወኃት ሰዎች ( ከሌላ ዘር ያሉትን ጨምሮ ባለሥልጣናት፣ ደላሎች፣ አቀባባዮች… ) ስለኢፌርት ድርጅቶች ( በአጭር ጊዜ ከ 798 ሚሊዮን ብር ካፒታል ተነስተው ሰባ አንድ እጥፍ አድገው 57 ቢሊዮን ብር ስለደረሱትና ከአገራዊ ባለሃብቶች/ኢንቨስተሮች በአንደኛ ደረጃ የሚገኝና የልማቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርካች መሆኑ በአቦይ ስብሃት በኩራት የሚነገረን) ‹ልማት› ከሆነ መነጋገር ይቻላል፡፡ ሌላው አገራዊ የልማት ጅምርማ እናንተ እንኳ/ህወኃት/ የደርግን እንዳስቀጠለው/ እንዳላቃጠለው (እንዲያውም የደርግን ዕቅድ የራሱ አድርጎ እያቀረበ እንንደሚመጻደቀው ) የሚመጣው መንግስትም ሥራው ነው፣ ያውም የዕለት ተዕለት የፕሮፖጋንዳ ማደንቆሪያ ሳያደርገው የቀጠርነው ይህን እንዲሰራ መሆኑን ነግረነው በየጊዜው እየገመገምነው ቀጥ- ለጥ ብሎ የሚሰራ የህዝብ አገልጋይ ተጠያቂ መንግስት፡፡ እንደሜቴክ ተከሶ እያለ ክሱን እንዲሰማ የቀረበለትን የተወካዮች ም/ቤት (ዳኛውን) በምስክርነት እያቀረበ ስለልማታዊነቱና ገድሉ በመስክ ላይ ዶክመንቴሪ የሚያሳየን ሳይሆን ካላገለገለ የምንከሰው፣ የምናባርረው/የምናወርደው ፡፡ መንግስት ስለተለወጠ ለአገር ልማት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ቀርቶ የተወጠኑ ዕቅዶችም በውጤታማ አመራርና በተጠያቂነት መርህ ተጠናክረው ይቀጥላሉ እንጂ አይጨናገፉምና ማስፈራሪያ ሆነው ሊቀርቡ አይገባም ፡፡
    ዛሬ ላይ ጥያቄው እነዚህና ሌሎችም የልማት ጅምሮችና ዕቅዶች በትርምስና በግርግር ለረጅም ጊዜ እንዳይስተጓጎሉ፣ በተረጋጋና ሰላማዊ ሁኔታ ለማስቀጠል ምን ማድረግ አለብን ሲሆን መልስና መፍትሄው ይህን የህወኃት ዘረኛ የጠባቦች ቡድን ማስገደድና ወደ ብሄራዊ ውይይትና ዕርቅ መድረክ በማምጣት የማሪያም በር መስጠት፣ ያሊያም አልመጣም ካለ ‹በቃህ› ብሎ ማስወገድ እንጂ ህገመንግስት ማክበር፣ ልማት ማስቀጠል በሚል ቀለም ቀብተን ማስቀጠልና ዘረኛ አገዛዙንና አድሎኣዊነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ለሌላ 25 የጥፋት ዘመን ዕድል እንዲያገኝ ማማከርና ጥብቅና መቆም አይደለም ፡፡
    ስለዚህ በምሁራዊ ትንታኔና በዘርፉ ተሞክሮ አለን የሚሉ የህወኃት ጥቅም ተጋሪዎች ለህወኃትም ሆነ ለራሳቸው የሚጠቅመው እውነቱን ተቀብለው ወደዘላቂና አስተማማኝ ሰላማዊ መፍትሄ መምጣት እንጂ የተለመደው የማጭበርበርና ጊዜ መግዢያ ማስፈራራትና የቅልበሳ ምክርና ሙከራ አያዋጣም ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከህዝብ ጋር በሰላምና ፍቅር የሚኖሩትን ተጋሩ በማስፈራራት ከየከተማውና ዩኒቨርሲቲው ወደትግራይ በመጫን ሲያልፍም ጉዳት/እርምጃ በመውሰድ ከህዝብ ጋር ለማጋጨት የሚደረገው ሙከራ ለጥቂት የህወኃት ዘረኞች የእፎይታ ጊዜ ለማግኘት ያገለግል ይሆናል እንጂ በምንም መልኩ ከዘላቂ መፍትሄ አያደርስም ፡፡
    ለራሳችሁም ለትግራይ ህዝብም የምታስቡ ከሆነ የያዛችሁት መንገድ የትግራይ ህዝብንና ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ቀጣይ ግንኙነት ችግር ውስጥ ሊከት ይችላልና ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ ፣ የትግራይ ተወላጆችን ከህወኃት ጋር አስተሳስሮ የእነርሱ/ህወኃቶች መመከቻ/ መደበቂያ እንዳያደርጉ መምከርና ለዚህም ህዝብን ማስተባበርና ማታገል የወቅቱ ሥራችሁ ሊሆን ይገባል ፡፡ የመጨረሻው ሰዓት የአርቆ አሳቢዎች፣ የዘር ጥላቻ ፖለቲካ ድልድያችሁ መሰበሩንና የእስከዛሬው ድካም ፍሬ ያለማፍራቱን ያረጋገጥን ፣ መቼም ለጥላቻ ፖለቲካ ቦታ የማንሰጥ ኢትዮጵያዊያን ማሳሰቢያ ነው፡፡
    ይህ የዝርዝር ምልክታዬ መንደርደሪያ ነው፡፡ ከዝርዝሩ ጋር በቅርብ ጊዜ በቸር ያገናኘን ፡፡

No comments:

Post a Comment