ደብረ ማርቆስ፣ ደሴ ደብረ ብርሃን፣ ወልዲያ…. የመሳሰሉትን ከተሞች ያካተተ ቢያንስ ከሃያ በላይ በሆኑ የአማራው ክልል የተለያዩ ከተሞችና የገጠር መንደሮች ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች እሁድ ነሐሴ 1 ቀን 2008 ዓ.ም ይደረጋሉ።
ህገ መንግስቱ ዜጎች ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ሙሉ መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። የሕወሃቱ ጌታቸው ረዳም በአልጃዚራ “እኛ የሕዝብ ድምጽን አናፍንም፣ ሰልፍ መዉጣት ይቻላል” ነው ያለው። ሆኖም ግን ሕወሃትበአደባባይ የሚመጻደቅበትን ሕገ መንግስት በመጣስ እነዚህ ሰለፎች ለማጨናገፍ ከፍተኛ የሆነ ዘመቻ እያደረገ ነው። “ሕገ መንግስቱ ወረቅት ብቻ” እንደተባለው። ህወሃቶች በርካታ ወጣቶችን እያፈሱ ሲሆን፣ ህዝቡን ለማስፈራራት ከፍተኛ የታጠቁ ሃይላትንም በከተሞቹ እያሰማሩ ነው።
የዜጎችን መሰረታዊ የመብት ጥያቄ ለማፈን ይሄንን ያህል ከሚዳክርና ከሚደክም፣ አገዛዙ የዜጎችን ጥያቄዎች በትንሹ እንኳን ለመመለስ ሙከራ ቢያደርግ ኖሮ አሁን ያለንበት ደረጃ ባልደረስን ነበር።
ባህር ዳርን ጨመሮ በምእራብ ጎጃም ዞን እና በሰሜን እና ደቡብ ጎንደር ዞኖች እንደ ሰደድ እሳት በስፋት የተስፋፋዉ እንቅስቃሴ ወደ ምስራቅ ጎጃም ፣ ወሎና ሸዋ ከተዛመተ አገዛዙን በጣም አስቸጋሪ ሁኔት ላይ እንደሚጠለው ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ከዚህም የተነሣ ነው “መደረግ ያለበት ሁሉ ተደርጎ ሰልፎቹ መክሸፍ አለባቸው” ከሚል ቁርጠኝነት ሐወሃቶች ደም እስኪያልባቸው ድረስ እየተንቀሳቀሱ ያሉት። ከነገ ጀመሮም ደብረ ጽዩን ኔትዎርኮች እንዲዘጉ ያደርጋልም ተብሎ ይጠበቃል።
በርካታ ሰራዊት በትላልቅ ከተሞች ቢያስገቡም፣ ወጣቶችን በብዛት ቢያስሩም፣ በሕዝቡ ዘንድ ግን ከፍተኛ መነቃቃትና ቁርጠኝነት እንዳለ ነው እየሰማን ያለነው።
የፊታችን እሁድ የሚደረጉ ሰልፎች እንደ ባህር ዳርና ጎንደር በመቶ ሺሆች የሚቆጠር ህዝብ ያሰለፉ ሰልፎች ሊሆኑ ባይችሉም፣ ከአንድ ሳምንት በላይ የፈጀዉን የአገዛዙ ማስፈራሪያና ዛቻ በመናቅ፣ ሕዝብ በብዛት ድምጹን ያሰማል ተብሎ ግን ይጠበቃል። ካሰማራቸው የታጣቁ ሃይሎች ብዛት የተነሳ፣ በትላልቅ ከተሞች አገዝዙ በሃይል ተቃዉሞዎችን ማፈን የሚችልበት ሁኔታ ቢፈጠርም፣ በገጠር ግን አስቸጋሪ ነው የሚሆነው።
በአሁኑ ወቅት በአማራዉ ክልል ያለው ተቃዉሞ፣ በኦሮሚያ ካለው፣ ወይንም ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ ከተደረጉት እንቅስቃሴዎች የተለየ ነው።
በኦሮምያ ያለው ተቃዉሞ በኦሮሚያ ያሉ እንደ አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ጂማ፣ ቢሾፍቱ፣ ሻሸመኔ፣ አሰላ ..ባሉ ትላልቅ ከተሞች የሚኖረውን ሕዝብ በነቂስ እንዲወጣ አላደረገም። በአብዛኛው በገጠርና በገጠራማ ከተሞች ነው ህዝብ በነቂስ የወጣው። እርግጥ ነው በአዲስ አበባና በአዳማ እንዲሁም በሻሸመኔ ሰልፎች ተደርገዋል። ግን ከ5 ሚሊዮን ሕዝብ 5 መቶ አካባቢ ሰው ብቻ በወጣበት ሁኔታ ሰልፉ የከተማዉን ህዝብ አቅፏል ማለት አይቻልም። አዳማ/ናዝሬት በሕዝብ ብዛት ከጎንደር እና ከባህር ዳር ትበልጣለች። በጎንደርና በባህር ዳር ከወጣው ሕዝብ ጋር ሲነጻጸር ግን በአዳማ ሕዝብ ወጥቶ ነበር ማለት አይቻልም። በጂማ፣ በአሰላ፣ በድሬዳዋ እንደዉም ተቃዉሞዎች አልተደረጉም። በአጭሩ የኦሮሞ ተቃዉሞ በኦሮሚያ ያሉ ትላልቅ ከተሞችን ያቀፈ አልነበረም። (በዚህ ረገድ የኦሮሞ ተቃዉሞ አስተባባሪዎች ክሪቲካል የሆነ ግምገማ በማድረግ ከተሞችንም ማቀፍና በብዛት ማንቅሳቀስ የሚችልበትን ሁኔታም ማጥናት አለባቸው)
በሌለ በኩል በአዲስ አበባ ብዙ ጊዜ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ደግሞ በተቃራኒው ከአዲስ አበባ አልፈው ገጠሮችን ያካተቱ አልነበሩም።
በአማራው ክልል ያለው ግን ትላልቅ ከተሞችን እና ገጠሮችን የገጠርም መንደሮችንም ነው እያንቀሳቀሰ ነው ያለው። ጎንደር ከተማና ባህር ዳር ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ወጥቷል። በደብረ ታቦር ከመቶ ሺህ ህዝብ በላይ አደባባዮችን አጥለቅልቋል። እንደ ንፋስ መዉጫ ጋይንት፣ ማክሰኚት፣ ሸዊት፣አዘዞ፣ እስቴ ….የመሳሰሉ አናሣ ከተሞችና የገጠር መንደሮችም ህዝቡ እየተነቃነቀ ነው። ከተሜው ተነስቷል።ገጠሬዉም ተነስቷል። በአማራው ክልል ያለው እንቅስቃሴ በትላልቅ ከተሞች ያለዉን ህዝብ በገጠር ካለው ህዝብ ጋር ያስስተሳሰረ ተቃዉሞ ነው።
በዚህ ምክንያት ሕወህት፣ ከተማዉን ይዞ ገጠሩን፣ ገጠሩን ይዞ ከተማዉን ነጥሎ ለመምታት የተቸገረበት ሁኔታ ነው ያለው። ለዚህም ነው እሁድ በተጠራው ሰልፍ በከተሞች ትልቅ አፈና ቢደረግም በሌሎች ቦታዎች ተቃዉሞው ሊስፋፋ ይችላል ተብሎ የሚጠበቀው።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!!!
No comments:
Post a Comment