Wednesday, August 31, 2016

የኢትዮጵያ ነብሮች ሲበሳጩ ያጉረመርማሉ!


ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም 
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ 
Cheetah 14አሜሪካውያን የጀግንነት በላይነት የላቸውም፣  ማለትም  የኦሎምፒክ ጀግንነት ጠቅላይነት፡፡
እ.ኤ.አ ነሐሴ 21/2016 የ26 ዓመቱ የኢትዮጵያ የረዥም ርቀት ማራቶን ሯጩ ፈይሳ ሌሊሳ በአንድ ወቅት በኦሎምፒክ ጨዋታዎች ታሪክ “የኦሎምፒክ ጨዋታዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴ መግለጫ መድረኮች ሊሆኑ አይችሉም” በማለት ይገለጽ የነበረውን ሕግ ወደ ጎን አሽቀንጥሮ በመጣል በሪዮ ኦሎምፒክ ውድድር አስደናቂ የሆነ ታሪካዊ ድርጊትን ደግሟል፡፡
እ.ኤ.አ ጥቅምት 16/1968 በሜክሲኮ ኦሎምፒክ ተደርጎ በነበረው የ200 ሜትር የአጭር ርቀት የሩጫ ውድድር ቶሚ ስሚዝ እና ጆን ካርሎስ የወርቅ እና የብር ሜዳሊያ አሸናፊዎች ሆነው ነበር፡፡ በሜዳሊያ አሰጣጥ ስነስርዓት መድረኩ ላይ አድርገውት የነበረው ታሪካዊ ድርጊት በአሁኑ ጊዜ ትልቅ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ይገኛል፡፡ የእጆቻቸውን ቡጢዎች ከፍ አድርገው ከራሳቸውበ በላይ ወደ ላይ በማንሳት የጥቁር ሕዝቦችን አይበገሬነት ምልክትነት በይፋ አሳይተዋል፡፡
ፈይሳ ከውድድሩ ማጠናቀቂያ መስመር ላይ ሲደርስ ሁለቱንም እጆቹን አጣምሮ ከእራሱ በላይ ከፍ አድርጎ በማንሳት የኢትዮጵያን ወጣቶች የአይበገሬነት የኃይል ምልክት እንቅስቃሴ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በይፋ አሳይቷል፡፡
ይህ ምልክት በዓለም ላይ የሚገኝ 3.5 ቢሊዮን ሕዝብ እንዲመለከተው የተደረገ ነበር፡፡
በዚያች ቅጽበታዊ ኩነት ፈይሳ ከያዘው እውነታ ጋር ተገናኘ፡፡ ያገኘውን የብር ሜዳሊያ ምርጫ ለዝና፣ ለዕድል እና ለታዋቂነት አውሎታል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ምንም ዓይነት የተለየ ችሎታ እንደሌለው እና እንደማንኛውም ተራ የዓለም ሕዝብ ሆኖ የመቀጠል ምርጫ ማድረግ ሲችል አርሱ ግን  የበለጠ ነገር ማድረግ ፈቀደ፡፡
ሆኖም ግን ፈይሳ የኩነቱን አጋጣሚ ለመያዝ መረጠ እና በዚህ መልኩ ተረጎመው፡፡
የኩነቱን አጋጣሚ ለመወሰን ጆሴፍ ካምፕቤል በመጽሐፋቸው እንደጻፉት እና ምዕናባዊ ገጽታን የሚላበሱ በሺዎች የሚቆጠሩ ጀግኖች እንዳሉ ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ ፈይሳም ለህይወቱ ዘላለማዊ ጀግና ሆኗል፡፡
ፈይሳ የኢትዮጵያ የጀግንነት አንጸባራቂ ገጽታ ለመሆን በቅቷል፡፡
እጆቹን ከጭንቅላቱ በላይ ከፍ በማድረግ አጣምሮ በመያዝ የውድድር ማጠናቀቂያ መስመሩን እያቋረጠ በነበረበት ጊዜ ፈይሳ የዓለምን ጀግንነት ነው ያቋረጠው፡፡
ለመሆኑ ፈይሳን ከተራ የማራቶን ውድድር ሯጭነት እንደዚህ ያለውን የጀግንነት እርምጃ ለመውሰድ እና የጀግንነት ስብዕናን እንዲላበስ ያደረገው ምክንያት ምንድን ነው?
መልሱ አየር የመተንፈስን ያህል ቀላል ነው! ሌላ ምንም ሳይሆን የአስተሳሰብ አድማሱን አእምሮውን መለወጡ ብቻ ነው፡፡
ጆርጅ በርናንድ ሻው በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፣ “ያለለውጥ ምንም ዓይነት እድገት ሊኖር አይችልም፣ እናም አእምሯቸውን መለወጥ የማይችሉ ምንም ዓይነት ለውጥ ሊያመጡ አይችሉም“ ነበር ያሉት፡፡
ፈይሳ በአሁኑ ጊዜ በሀገሩ ውስጥ ስርነቀል ለውጥ አስፈላጊ እንደሆነ በሚገባ ግንዛቤ ወስዷል፡፡ በዚያች ውሱን በሆነች የኩነት አጋጣሚ ፈይሳ በእርሱ ጨቋኞች ጫማ ስር ወድቆ እና ሁለተኛ ዜጋ ሆኖ እየተጨቆነ የእድሜ ልክ ክብር እና ሀብት እያገኘ ከመኖር ይልቅ የአንድ ሴኮንድ ነጻነት ይሻለኛል በማለት አእምሮውን ለውጧል፡፡
በሪዮ የማራቶን ውድድር ፈይሳ የውድድር ማጠናቀቂያ መስመሩን በሚያቋርጥበት ጊዜ የአትሌቲክሱን ድል አድራጊነት አይደለም ያቋረጠው፡፡ በምንም ዓይነት ይኸ አይደለም!
ሆኖም ግን ፈይሳ ፍርሀትን፣ ተስፋ የማጣት ጨለምተኝነትን፣ ሀዘንን፣ ብስጭትን፣ መጥፎ ዕድልን እና ጥርጣሬን አሽቀንጥሮ በመጣል የድፍረትን፣ የመስዋዕትነትን፣ የዓላማ ጽናት ቁርጠኝነትን፣ የአይበገሬንትን እና የተጨባጭ ተግባርን መስመር ነው በይፋ ያቋረጠው፡፡
በሩጫው የመጨረሻዎቹ ሰከንዶች ላይ ፈይሳ የጥሩምባ ጥሪ ድምጽ ሰማ፡፡
እንደ ጆሴፍ ካምፕቤል ባለ አንድ ሺ ፊት ምዕናባዊ ጀግንነት ፈይሳ ከተራው የዓለም ሕዝብ ለታላቅ ቁምነገር አድናቆትን እንዲፈጽም ጥሪ ቀረበለት፡፡
ፈይሳ ለጥሪው አውጥቶ እና አውርዶ በሚገባ አሰበበት፡፡ ለብዙ ጊዜ ሲያደርገው የነበረውን አሰበ፡፡ እንደ ካምፕቤል ጀግና ወሳኙ ጊዜ በሚመጣበት ጊዜ ፈይሳ ውሳኔ የማይሰጥ ልፍስፍስ  ወይም ደግሞ ወላዋይ አልሆነም፡፡ ቆራጥ ሆነ ።
ጥርት ባለ የእውነታ መንገድ እና በዓላማ ጽናት ላይ በመመስረት ከእራስ ወዳድነት፣ ከማን አህሎኝነት ስሜት እና ጥሩ የዓለም ህይወትን  ከመውደድ ይልቅ ማንኛውንም አደጋ በጽናት ተቋቁመው ለመልካም ነገር ለማህበረሰቡ መስዋዕትነትን ከፍለው ድልን የሚያቀዳጁ ጀግኖች መስመርን ነው ያቋረጠው፡፡
እንደ ካምፕቤል ምዕናባዊ ጀግና ማንኛውንም የጀግንነት አደጋዎች መጋፈጥ ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ ፈይሳም ለሕዝቦቹ፣ ለሀገሩ፣ ለወጣት ወገኖቹ፣ ለባለቤቱ እና ለጥቅላላው ለዘመድ አዝማዶቹ የእራሱን ህይወት በመስዋዕትነት ሰጥቷል፡፡
ግን ለምንድን ነው ይህን ያረገው!?
Cheetah 8እ.ኤ.አ በ1968 በሰሜን ካሊፎርኒያ ከሳን ጆሴ ስቴት ዩኒቨርስቲ ሁለት የኮሌጅ ተማሪዎች የእጆቻቸውን ቡጢዎች ወደ አየር ከፍ አድርገው ከራሳቸው በላይ በመያዝ በአይበገሬነት የጀግንነት መስመሩን እንደዚሁ አቋርጠዋል፡፡
ካርሎስ እድሜው 23 እና ስሚዝ ድግሞ የ24 ዓመት ወጣቶች የነበሩ ሲሆኑ የስኬት፣ የዝና፣ የዕድል እና የታዋቂነትን የወጥመድ አደጋዎች ሁሉ ያለምንም ማወላወል ፊት ለፊት ተጋፍጠዋል፡፡ በአደባባይ ተንቀዋል፣ ተወግዘዋል፣ ተዋርደዋል፣ የማስፈራሪያ ድርጊት ተፈጽሞባቸዋል፣ ተዘልፈዋል እናም የማጃጃል ድርጊት ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ከዚህም አልፎ እንዲያውም በውድድሩ አሸናፊ ሆነው ያገኟቸውን ሜዲሊያዎች ለዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴው እንዲመልሱ ተደርገዋል፡፡
ለመሆኑ እንደዚህ ያለ መስዋዕትነትን የከፈሉት ለምንድን ነው!?
የካርሎስ እና የስሚዝ ፎቶ ለጥቁር ኃያልነት ምልክት ሆኖ እንዲኖር ለመሆኑ ለዘላለም በአእምሮዬ ውስጥ ፍንትው ብሎ ይታየኛል፡፡
በአፍሪካ ቀንድ እምብርት እንደ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እኔ በግሌ በአሜሪካ የሲቪል መብቶችን እና የወጣቶችን የተቃውሞ ንቅናቄዎችን በተለይም ደግሞ በወጣት አማጺያን በ”ሕዝባዊ ሬፐብሊኮች” በካሊፎርኒያ በበርክለይ እና በኦክላንድ ይደረጉ የነበሩትን እንቅስቃሴዎች አስታውሳለሁ፡፡
ግን ለምን?
ሸክስፒር አስራሁለተኛው ሌሊት/Twelfth Night በሚለው መጽሐፋቸው እንዲህ በማለት ጽፈው ነበር፣ “ጥቂቶች ታላቆች ሆነው ተፈጥረዋል፡፡ ጥቂቶች ደግሞ በሂደት ታላቅነትን ተጎናጽፈዋል፣ ሌሎች ጥቂቶች ደግሞ በእነዚህ ታላቆች ላይ እምነቶቻቸውን ጥለዋል፡፡
ሸክስፒር ከዚህም በተጨማሪ ጥቂት ሰዎች ደግም ሁልጊዜ ተጎጂ የሆኑ ሕዝቦችን መብቶች ለማስጠበቅ ሲሉ እውነትን በመናገር ሌሎችን ሰዎች በመጨቆን ጉዳት በሚያስከትሉ ሰዎች ላይ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው እንዲያወግዙ እና እንዲጮኹ ሆነው ተፈጥረዋል የሚል ቢጨምሩበት ኖሮ እንዴት ደስ ባለኝ ነበር፡፡
በጣም የሚገርመኝ ጉዳይ ነው፡፡
የወርቅ እና የብር ሜዳሊያዎችን በእጅ ለማስገባት እንደ ነብር የሚወረወረውን የስሚዝን እና የካርሎስን የቪዲዮ ምስል እና በቀጣይነት ቀርቦላቸው የነበረውን ቃለ መጠይቅ ፈይሳ የውድድር ማጠናቀቂያ መስመሩን ቆርጦ ሲገባ እንደተደረገው ሁሉ ለብዙ ጊዜ ደጋግሜ ተመልክቸው እና አዳምጨው ነበር፡፡
ሁለቱ የኦሎምፒክ ጓደኛሞች በግዋንቲ የተሸፈኑ ሁለት ቡጢዎቻቸውን ወደ ላይ ወደ አየር ከጭንቅላታቸው በላይ ከፍ በማድረግ በሚያማምሩ ጌጣጌጦች ያሸበረቀውን ባለኮከብ የጽሑፍ ሰሌዳ ጨርቁን/ባነር በመበጠስ ውድድሩን አጠናቀዋል፡፡
ግን አወዛጋቢ የሆነው የጥቁሮች ኃይለኝነት በነበረበት ወቅት እጆቻቸውን ወደ ላይ ወደ አየር ከፍ አድርገው ያንን ምልክት ያሳዩበት ምክንያት ለምን ነበር?
ፈይሳ የውድድር ማጠናቀቂያ መስመሩን በሚያቋርጥበት ጊዜ ሁለት እጆቹን በማጣመር ከራሱ በላይ ወደ አየር ከፍ በማድረግ ያንን ምልክት ያሳየበት ምክንያት ምንድን ነው?
ካርሎስ እና ስሚዝ የዓለምን የኦሎምፒክ መድረክ አጋጣሚን በመጠቀም በአፍሪካ አሜሪካውያን ላይ እየተፈጸመ እና እያሰቃያቸው የነበረውን ዘረኝነትን፣ ድህነትን እና የሁለተኛ ደረጃ ዜግነትን በመቃወም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ ነበር፡፡
ሆኖም ግን አይበገሬው ድርጊታቸው ወደላይ ከጭንቅላታቸው በላይ በተጣመሩት ቡጢዎቻቸው ብቻ ተወስኖ አልቀረም፡፡ ሆኖም ግን በርካታ በሆኑ አፍሪካ አሜሪካውያን ላይ ዕለት በዕለት በላያቸው ላይ የሚያናጥርባቸውን አውዳሚ የሆነ ድህነት የውድድሩን ፍጻሜ ተከትሎ ሲከናወን በነበረው የሜዳሊያ አሰጣጥ ስነስርዓት ላይ ጽኑ አቋማቸውን በግልጽ አሳይተዋል፡፡ በተለይም ደግሞ ካርሎስ ቀደም ሲል ላለቁት ወይም ደግሞ ለተገደሉት  እና ደመ ከልብ ሆነው ለቀሩት ሰዎች ማንም ምንም ዓይነት ጸሎት ያላደረገላቸው እና ያላሰባቸው በመሆኑ ጥቁር ነጠብጣብ ያለበትን ከረባት አስሮ ነበር፡፡ ይህም ማለት በጀልባ በመጓዝ ላይ የነበሩ ሰዎችን በጉዞው አማካይ ርቀት ላይ ሲደርሱ በውኃው አካላ ላይ እንዳሉ ከጀልባው ወደ ባህሩ ውስጥ እንዲወረወሩ እየተደረጉ እልቂት ስለተፈጸመባቸው ሰዎች ነበር፡፡
ፈይሳም እንደዚሁ በተመሳሳይ መልኩ የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወይም ደግሞ በትክክለኛው እና ገላጭ በሆነው የባህሪ አጠራሩ መሰረት የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ዘ-ህወሀት) እየተባለ በሚጠራው ሕገወጥ የማፊያ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የግፍ አገዛዝ በወገኖቹ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ እየደረሰ ያለውን ጭቆና እና የሁለተኛ ደረጃ ዜግነትን በመቃወም እጆቹን በማጣመር ወደ ላይ ከራሱ በላይ ከፍ አድርጎ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በይፋ አሳይቷል፡፡
በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ እንደዚህ ያለውን አስደናቂ የሆነውን እርምጃ ለምን እንደወሰደ ጥያቄ በቀረበለት ጊዜ ፈይሳ እንዲህ ነበር ያለው፣ “የኢትዮጵያ መንግስት የኦሮሞ ሕዝቦችን ይገድላል፡፡ እናም መሬቶቻቸውን እና ሀብታቸውን ሁሉ ይወስዳል፡፡ ስለዚህ የኦሮሞ ሕዝብ በአሁኑ ጊዜ ድርጊቱን በመቃወም ላይ ይገኛል፣ እኔም የኦሮሞ ማህበረሰብ ተወላጅ ስለሆንኩ ድርጊቱን በመቃወም ደጋፊነቴን ለማሳየት ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ወገኖቼን በየቦታው በመግደል ላይ ይገኛል፣ እናም እኔም የኦሮሞ ጎሳ አባል ስለሆንኩ ድርጊቱን በመቃወም ከወገኖቼ ጎን መቆሜን በግልጽ ለማሳየት ነው፡፡ የእኔ ዘመዶች በእስር ቤት ውስጥ በመማቀቅ ላይ ይገኛሉ፣ ስለዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ከጠየቁ ይገደላሉ፡፡ እጆቼን ከፍ በማድረግ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያሳዬሁበት ምክንያት የኦሮሞን ተቃውሞ መደገፌን ለማሳየት ነው፡፡“
ፈይሳ የተናገረው ነገር ዋና ፍሬነገር/ ዳህራው እ.ኤ.አ በ1968 ስሚዝ እና ካርሎስ ተናግረውት ከነበረው እንዲህ ከሚለው ቃለመጠይቅ ብዙም የሚለይ አይደለም፡፡
ቃለመጠይቅ አድራጊ፡ እንደዚህ ዓይነቱን ድርጊት በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ በኦሎምፒክ ጨዋታዎች መድረክ ላይ ማሳየት ትክክለኛ ቦታው ነው ብላችሁ ታስባላችሁ?
ስሚዝ፡ እኛ አትሌቶች ነን፡፡ እኔ መምህር ነኝ ሆኖም ግን የፖለቲካ ሰው አይደለሁም፡፡ ይህንን ድርጊት የፈጸምነው የዓለም ሕዝብ በአሜሪካ በጥቁር ሕዝቦች ላይ የተንሰራፋውን ድህነት እንዲመከለተው እና ግንዛቤ እንዲወስድ በማሰብ ነው፡፡
ቃለመጠይቅ አድራጊ፡ ሜዳሊያ በማግኘት በሕዝብ ዘንድ ታዋቂነትን እና ዝናን ተጎናጽፊያለሁ ብለህ ታስባለህ ወይስ ደግሞ መስዋዕትነት ከፍያለሁ ነው የምትለው?
ካርሎስ፡ እኔ ሜዳሊያውን ምግብ ሆኖ አልበላውም፡፡ በእኔ የእድሜ የዕኩያነት ደረጃ ላይ ያሉት ታዳጊ ወጣቶችም ቢሆኑ ይህንን ሜዲሊያ አይበሉትም፡፡ ከእነዚህ ልጆች በኋላ የሚመጡት እና የሚያድጉት ልጆችም ቢሆኑ ሊበሉት አይችሉም፡፡ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ሊበሏቸው አይችሉም፡፡ ሁላችንም የምናቀርበው ጥያቄ ቢኖር የሰው ለጆች ለመሆናችን ዕኩል እድል ይሰጠን የሚል ነው፡፡ እናም አሁን እንደማየው ከሆነ ከመሰላሉ በ5 ደረጃዎች ዝቅ ብለን እንገኛለን፡፡ እናም ሁልጊዜ መሰላሉን ለመንካት በምንሞክርበት ጊዜ እግሮቻቸውን በእጆቻችን ላይ ይጭናሉ፣ እናም በመሰላሉ ወደላይ እንድንወጣ አይፈልጉም፡፡
በእርግጥ ካርሎስ እና ስሚዝ በሜዳሊያ አሰጣጥ ስነስርዓቱ ወቅት እጆቻቸውን በአይበገሬነት መንፈስ ወደ ላይ ከፍ በማድረግ ቡጢዎቻቸውን ጠበቅ በማድረግ ዘረኝነትን እና የአፍሪካ አሜሪካውያንን የሁለተኛነት ደረጃ ዜግነትን ሲቃወሙ ብቻቸውን አልነበሩም፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት የአሜሪካ ወጣቶች እና በዓለም ላይ የሚገኙ ሕዝቦች ሁሉ ከጎናቸው ነበሩ፡፡
ፈይሳ ሁለት እጆቹን በማጣመር ከጭንቅላቱ በላይ ወደ ላይ ከፍ በማድረግ የውድድር ማጠናቀቂያ መስመሩን ሲያቋርጥ ብቻውን አልነበረም፡፡ የ100 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ መንፈሳዊ ድጋፎች፣ ፍቅር እና አድናቆት ነበረው፡፡
በአየር ላይ ከፍ ብለው በምስል ይታዩ የነበሩት በግዋንት የተጠቀለሉት የካርሎስ እና የስሚዝ እጆች የአንድ ሺ ቃላት ያህል ትርጉም ሊሰጡ ይችሉ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን ለእኔ ይኸ ታሪካዊ ድርጊታቸው አንድ ቃል ብቻ ይወክላል፡እምቢተኝነት!
የእነርሱ እምቢተኝነት ጨቋኝ ለሆነው እና ለዘረኛው ስርዓት ውድቀት ጽናት ያለው እና ሰላማዊ የሆነ መገዳደርን/አይበገሬነት ይወክላል፡፡
የእነርሱ እምቢተኝነት በአሜሪካ ውስጥ ለሚደረጉ የሲቪል መብቶች ንቅናቄ እና ለብዙሀን የማንነት ትግል እና ለሙሉ የዜግነት ጥያቄ እውቅና ውክልና ይሰጣል፡፡
ስሚዝ በዚያን ጊዜ የነበረውን የእንቆቅልሽ ሁኔታ አቅሎ ባለመመልከት እንዲህ ብሎ ነበር፡ “ውድድሩን የማሸነፍ ከሆነ አሜሪካዊ እንጅ ጥቁር አሜሪካዊ አይደለሁም፡፡ ሆኖም ግን አንድ የሆነ መጥፎ ነገር ሰርቼ ከሆነ እኔን ባሪያ/Negro ነው ይላሉ፡፡ እኛ ጥቁሮች ነን፣ እናም ጥቁሮች በመሆናችን እንኮራለን፡፡ ጥቁር አሜሪካውያን በዛሬው ምሽት ምን እንደሰራን በውል ይገነዘባሉ“ ነበር ያለው፡፡
በአሜሪካ ውስጥ ጥቁር አሜሪካዊ የመሆን እና ያለመሆን የሸክስፒር ዘላለማዊ ተቃርኖ እንዲህ የሚል ነው፡ መሆን ወይም አለመሆን… ወይም ደግሞ መሆን ይችላልን… ጥቁር እስከሆነ ድረስ?
ካርሎስ እና ስሚዝ በዚያ ገጻቸው ለዓለም ሕዝብ እንዲህ በማለት ነበር ያወጁት፣ “ላመንንበት ዓላማ በጽናት እንቆማለን፡፡ በምንም ዓይነት ሁኔታ ወደኋላ አናፈገፍግም፡፡“
የውድድሩ አሸናፊ የውድድር መስመሩን ሲያቋረጥ የሚበጥሰውን ባለነጠብጣብ የኮከብ ጨርቅ/ባነር በሚበጥሱበት ጊዜ የአፍሪካ አሜሪካውያንን መንፈስ በመላበስ እንዲህ በማለት ነበር የሚዘምሩት፣ “ከዚህ አቋሜ አንዲትም ጋት ንቅንቅ አልልም“ ነበር ያሉት፡፡
ፈይሳ ሌሊሳ በካርሎስ እና በስሚዝ አስደማሚ ድርጊት እጅግ ተመስጦ እንደነበር ምንም ዓይነት ጥርጣሬ የለኝም፡፡
እንደ ካርሎስ እና ስሚዝ ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ የእርሱ ድፍረት ለሕዝቦቹ ይናገር ነበር፡፡ የእነርሱን የማጎሪያ እስር ቤቶች እና የማሰቃያ ክፍሎች እንደማይፈራቸው ፈይሳ ዘ-ህወሀት በሚገባ እንዲገነዘብ አድርጓል፡፡ ዘ-ህወሀት የእርሱን ቤተሰቦች ገሀነም እንደሚያስገባቸው በሚገባ ይገነዘባል፡፡ በእርግጥ ከገሀነም ጌቶች ከዚህ ያነሰ ሊጠበቅ አይችልም፡፡
ሆኖም ግን በዚያ ብቸኛ የእምቢተኝነት ቅርጹ ፈይሳ በኢትዮጵያ ውስጥ በዘ-ህወሀት የማፊያ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን እጅ እየተገደሉ እና እልቂት እየተፈጸመባቻው፣ በቁጥጥር ስር እየዋሉ፣ ወደ እስር ቤት የሚጋዙት እና ስይቃ እየተፈጸመባቸው ለሚገኙት ወጣት ወንድሞቹ እና እህቶቹ ፍጹም የሆነ አጋርነቱን አሳይቷል፡፡
ፈይስሳ ወደ ውድድር ማጠናቀቂያ መስመሩ እየተቃረበ በመጣ ጊዜ ለኦሎምፒክ ዝና እና የበላይነት ክብር እንዲሁም ከዚያ ጋር ተያያዞ ሊገኝ ስለሚችለው መልካም ዕድል ምንም ዓይነት ፍላጎት እንዳልነበረው ለዚያች ቅጽበት ምስክር ሊሆኑ ለሚችሉ ሰዎች ሁሉ ጉዳዩ ግልጽ ነበር፡፡
ፈይሳ የህይወቱን የማራቶንን የሩጫ ውድድር ለወገኖቹ ህይወት እና ክብር ሲል ሮጦታል፡፡
አሸንፎ ሜዳሊያ ለማግኘት ሳይሆን የእርሱን ወገኖች ከስቃይ እና ከውርደት ለማዳን ሲል የማራቶንን ሩጫ ሮጦታል፡፡
ለዚህች ለአንድ ጊዜ አልባ ለሆነች አጋጣሚ ለበርካታ ዓመታት በኮረብታዎች እና በሸለቆዎች እንደ ውኃ ቀጅ በመመላለስ ያለምንም መሰላቸት ሰልጥኗል፡፡
አፉ በዘ-ህወሀት ባይለጎም እና ባይሸበብ ኖሮ እንዲህ ብሎ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ለወገኖቹ አይናገርም ነበር፡፡
ሆኖም ግን የሚያምነበትን አቋሙን በእግሮቹ ተናግሯል፡፡ ከአፍ ይልቅ እግር እንዴት ድምጹን ከፍ አድርጎ ይናገራል እባካችሁ!
ካርሎስ እና ስሚዝም የሮጡት ለእራሳቸው ጥቅም ሲሉ ሳይሆን ለሰው ልጆች ዘር ሁሉ መብቶች መከበር ሲሉ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ በ2011 በሳን ጆሴ ስቴት ዩኒቨርስቲ እ.ኤ.አ በ1968 ካርሎስ እና ስሚዝ ፈጽመውት በነበው ታሪካዊ ድርጊት ምክንያት ለመታሰቢያነት በተገነባው ሀውልት የምረቃ ስነስርዓት በሚደረግበት ጊዜ ዶ/ር ካርሎስ እንዲህ ብለው ነበር፡
“በሚክሲኮ ሲቴ ምንም እናድርግ ምን በጣም ውድ እና እንቁ, የተከበረ፣ ቆጥቋጭ፣ አስደንጋጭ እና ገላጭ  የሆነ ነገር፣  አድርገናል፡፡ አመልካች ጣታችንን በሰዎች ላይ አልቀሰርንም፡፡ ምንም ዓይነት ግፊት አላደረግንም፡፡ ሰንደቅ ዓላማችንን በራሳችን ላይ አልጠቀለልንም ወይም ደግሞ እንደ ህጻናት የሽንት መምጠጫ ጨርቅ/ዳይፐር አላሰርንም፡፡ ክብርን በሚያዋርድ መልኩ እዚያ አልቆምንም፡፡ እዚያ የቆምነው እንዲህ ለማለት ነው፣ ‘ሰዎች ጉድ እኮ ነው፡፡ እኔ አሜሪካዊ ነኝ፡፡ የአንተ ልጅ ነኝ፡፡ ቆስያለሁ፡፡ ለእራሴ ስል አልቆሰልኩም ምክንያቱም ከአንተ ጀግኖች መካከል እኔ አንዱ ነኝ፡፡ በአሎምፒክ ላይ ነኝ፡፡ ለውድድሩ ስል ቆስያለሁ፡፡ ስለ 200 ሜትር የርቀት ሩጫ ውድድር አይደለም እያወራሁ ያለሁት፡፡ እየተናገርኩ ያለሁት ስለሰው ልጆች  ሰባዊ መብት ነው፡፡ ለዚህም ነው ሜክሲኮ ሲቲ የሄድነው’” ነበር ያለው፡፡
እጆቹን ወደ ላይ ከፍ በማድረግ ፈይሳ ዘ-ህወሀት እየተባለ በሚጠራ ወንጀለኛ የማፊያ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የኢትዮጵያ የማስመሰያ መንግስት ተብዬ ድርጅት (አሁን በቅርቡ “ኢትዮጵያ ከጭፍን የጎሳ ጥላቻ ባሻገር“ በሚል ርዕስ ያዘጋጀሁትን ትችት ይመልከቱ፡፡) በሕዝቦች ላይ እያደረሰ ያለውን ስቃይ፣ መከራ፣ የመጥፎ ነገሮቸ ሁሉ መሞከሪያነት እና ከባድ ችግር ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የህሊና ዳኝነት ለአደባባይ እንዲደርስ አድርጓል፡፡
እንደ ስሚዝ እና እንደ ካርሎስ ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ ፈይሳ የእርሱ ወገኖች፣ ልጆች፣ ቤተሰቦች እና ጎረቤቶች የብር ሜዳሊያ ሊበሉ አይችሉም በማለት ላይ ይገኛል፡፡ የብር ሜዳሊያው ክብር፣ ነጻነት እና የሰብአዊ መብቶችን አይገዛላቸውም፡፡
እንደ ስሚዝ እና ካርሎስ ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ ፈይሳ ወገኖቹ በሙሉ ዕኩል በሆነ አንድ ዓይነት እድል መስተናገድ እንዲችሉ ፈልጓል፡፡ እንደ ሁለተኛ ደረጃ ዜግነት እንዲስተናገዱ አልፈለገም፡፡ እንደ ወንጀለኞች እና አሸባሪዎች ተደርገው እንዲፈረጁ አልፈለገም፡፡ ፈይሳ የፈለገው በአምላክ አምሳል እንደተፈጠረ እንደማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር፣ አምላክ ካጎናጸፋቸው የህይወት ሙሉ ዘላለማዊ መብት፣ ነጻነት እና ደስታን ከማግኘት መብት ጋር  በሰላም እና በድሎት እንዲኖሩ ነው የሚፈልገው፡፡
ፈይሳ የእርሱ ሕዝቦች በመሰላሉ ላይ እንደማንኛውም ሰው እንዲወጡ ይፈልጋል፣ እናም በምንም ዓይነት መልኩ መሰላሉ በዘ-ህወሀት፣ በአባሎቹ እና በግብረ አበሮቹ በክልከላ በመያዝ ከላይ ከቁንጮው ላይ እግራቸውን አንፈራጥጠው በመቀመጥ ሌላው ዜጋ ለመውጣት ሙከራ በሚያደርግበት ጊዜ እየኮረኮሙ በመከልከል የኢትዮጵያን ሕዝብ መሰላል የእነርሱ ብቻ መሰላል አድርገው እንዳይቀመጡ ይፈልጋል፡፡
እ.ኤ.አ ነሐሴ 21/2016 በሪዮ የማራቶን ውድድር የሜዳሊያ አሰጣጥ ስነስርዓት ላይ ፈይሳ ሌሊሳ የኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ትውልድ (ወጣቱ ትውልድ) ማለት ምን ማለት እንደሆነ እና የኩሩ ትወልድ ዝርያ ኩሩ እንደሆነ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ እንደሚያኮራ ወይም ደግሞ እንደ ኩሩ አንበሶች የኮራ ጀግና የህብረተሰብ ክፍል መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሚገባ አሳይቷል፡፡
ሆኖም ግን ፈይሳ ለአቻ ጓደኞቹ ያስተላለፈው እንደህ የሚል ግልጽ መልዕክት ነበር፣ “በዘ-ህወሀት የማፊያ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እየተፈጸመ ያለውን የእናንተን ስቃይ፣ የመሞከሪያ ዕቃ ስለመሆናችሁ እና ስለሚያደርስባችሁ መከራ እና ስቃይ ሁሉ 3.5 ቢሊዮን ለሚሆኑ የዓለም ሕዝቦች በሚገባ ተናግሪያለሁ“ የሚል ነው፡፡
ፈይሳ ለኢትዮጵያ በግዴታ ገዥዎች በምንም ዓይነት መንገድ፣ መለኪያ እና መስፈርት ሊመጥን የማይችለውን አሸባሪ እና የማፊያ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የሆነውን እራሱን ዘ-ህወሀትን እንኳ “የኢትዮጵያ መንግስት” ብሎ ጠርቶታል፡፡
ፈይሳ እንደዚያ ዓይነቱን ደም የተጠማ የወሮበላ ዘራፊ እና የእራሱን ዜጎች ጨፍጫፊ ቡድን ስብስብ ታላቅ ቸርነትን በማሳየት በባህሪ እና በግብር ከማይገናኘው ጋር “መንግስት” ብሎ ጠርቶታል፡፡ ድንቄም መንግስት፣ መንግስት እንዳይባል የለ! የዱርዬ መንግስት እንጂ !
ዘ-ህወሀትን “መንግስት” ብሎ መጥራት ቦቅቧቃዎችን እና ፈሪ የሆኑትን ጥንብ ሲያዩ የሚያሽካኩትን ጅቦች “ኩሩ አንበሳ”ብሎ ከመመጥራት ጋር መሳ ለመሳ ነው፡፡
ማንም ቢሆን አካፋን አካፋ ብሎ መጥራት አለበት፡፡ እንደዚሁም ጅብን ጅብ ብሎ መጥራት አለበት፡፡
ዘ-ህወሀት ለዘራፊዎች በዘራፊዎች የተቋቋመ የዘራፊዎች መንግስት ነው (እ.ኤ.አ ግንቦት 2011 “ዘራፊነት፡ የአፍሪካ አምባገነኖች ከፍተኛ ደረጃ“ በሚል ርዕስ አቀርቤው የነበረውን ትችቴን ይመልከቱ፡፡)
ዘራፊዎች ምን ወርቅ ቢለብሱ ምንጊዜም ቢሆን ያው ዘራፊዎች ናቸው፡፡ ጅቦችም እንኳ ቢሆኑ ምንም እንኳን ነገር እንደገባው ሰብአዊ ፍጡር ቢሽከመከሙም (ጧ ብሎ መሳቅ) ያው ምንጊዜም ጅቦች ናቸው፡፡
አንበሶች ምንጊዜም ቢሆን ያው አንበሶች ናቸው፣ እናም ጅቦች የአንበሶቹን ማግሳት እና የአቦ ሸማኔዎችን ማጉረምረም በሚገባ ያውቃሉ፡፡
Cheetah 10ሆኖም ግን ፈይሳ በአንድ ላይ የተጠቃለለ አንበሳ እና አቦ ሸማኔ ነው፡፡
በዚያው ተመሳሳይ ቀን ፈይሳ የብር ሜዳሊያውን አሸናፊ በሆነበት ዕለት በሀገሪቱ ዋና መናገሻ በሆነችው በአዲስ አበባ ውስጥ ሊደረግ የነበረውን ሰላማዊ ተቃውሞ ለመከላከል ሲል ዘ-ህወሀት አፋኝ የደህንነት መንጋዎቹን፣ የፖሊስ ኃይሉን እና ወሮበላ ዘራፊ ወታደሮቹን በከተማይቱ አሰማርቷል፡፡
እንዴት ዓይነት በተቃርኖ የተሞላ ጊዜ ነው እባካችሁ! በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ሰላማዊ ተቃዋሚዎች በመከልከል እቤታቸው ውስጥ እንዲቀመጡ በማስገደድ ዘ-ህወሀት ሕዝቦች የእነርሱን ስራ ከመካከላቸው የእነርሱ በሆነ አንድ ሰው አማካይነት ቆንጆ በሆነ መልኩ 3.5 ቢሊዮን ሕዝብ እንዲመለከተው ሲደረግ ደስታ በተመላበት ሁኔታ ተቀምጠው ተመልክተዋል፡፡
ፈይሳ ወደ ውድድሩ ማጠናቀቀቂያ መስመር ላይ ሲያቃርብ የሚያሳየውን የቪዲዮ ምስል በምመለከትበት ጊዜ እ.ኤ.አ ሰኔ 1989 በቻይና ዋና ከተማ አንድ ግለሰብ በከተማይቱ እምብርት በታንኮቹ ፊት ተገትሮ በመቆም “በምንም ዓይነት ሁኔታ ከቆምኩባት ቦታ ንቅንቅ አልልም“ በሚል ሞገደኛ እና እልኸኛ ስሜት ዓላማውን የገለጸውን ወጣት አስታወሰኝ፡፡
ኃይለኛ በሆኑት በቻይናውያን ወታሮች እና የደህንነት ኃይሎች እብሪተኝነት በመቶዎች በሚቆጠሩ ሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ እልቂትን እየፈጸሙ ባሉበት በዚያ ቅጽበታዊ ጊዜ አንድ ትንሽ የሆነ አሞተ ቆራጥ ጀግና ሰው እምቢኝ አሻፈረኝ ካለሁባት ቦታ ጋት አልንቀሳቀስም በማለት ያሳየው ተጋድሎ የሚደነቅ እና የሚገርም ትይንት ነበር፡፡
ያ ተዋቂነትን ያልተጎናጸፈ ተራ ሰው የቻይና የጦር ማሽን/ፋብሪካ በእርሱ ላይ ምን ሊያደርስ እንደሚችል ምንም ዓይነት ፍርሀት አልነበረውም፡፡
ዘ-ህወሀት በእርሱ ላይ ሊያደርግ ስለሚችለው ሁኔታ ፈይሳ ይፈራልን?
ፈይሳ ቀጥተኛ በሆነ መልኩ በግልጽ እንዲህ በማለት ተናግሯል፣ “ባይገድሉኝ እንኳ በእስር ቤት ያማቅቁኛል፡፡ እስከ አሁን ድረስ ምንም የወሰንኩት ነገር የለም፡፡ ሆኖም ግን ምናልባትም ወደ ሌላ ሀገር የምንቀሳቀስ ይሆናል“ ነበር ያለው፡፡
የፈይሳ እናት ምንም ዓይነት ፍርሀት ሳያሳዩ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ እንዲህ ብለዋል፣ “መንግስት እየተናገረ ባለው ነገር ያምናሉን? እዚያው ባለበት ይቆይ፡፡ እዚያው እንዲቆይ ነው እኔ የምፈልገው፡፡ ደህና እንዲሆን ነው የምመኘው“ነበር ያሉት ከመጣ ደህንነቱ እንደማይጠበቅ እርግጠኛ በመሆን መንፈስ፡፡
የፈይሳ ባለቤት የእርሷ ባለቤት ምን ዓይነት ጠንካራ እንደሆነ እንደምታውቅ እንዲህ ብላለች፣ “በወቅቱ ፈርቸ ነበር፣ ሆኖም ግን ይህ ሁኔታ የሚያስደንቀኝ አይሆንም ምክንያቱም እኔ እርሱን አውቀዋለሁና፡፡ በማህበራዊ ድረ ገጾች የሰዎችን ሬሳዎች በሚያይበት ጊዜ፣ ሰዎች በቁጥጥር ስር ሲዉሉ በሚመለከትብት ጊዜ እና ሰዎች ሲደበደቡ በሚመለከትበት ጊዜ በውስጡ ይቃጠል ነበር፡፡ ስለሆነም እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ አልተደነቅሁም ነበር ምክንያቱም በውስጡ በርካታ ብስጭቶች በውስጡ ታምቀው ነበርና“  ነበር ያለችው፡፡
ፈይሳ የህወሀት ወሮበላ ዘራፊዎች እንደፈለጉ በጫማቸው ስር አድርገው የፈለጋቸውን ነገር እንዲፈጽሙበት እና በእነርሱ ስር ለመውደቅ የሚያስችል አቋም የለውም፡፡ ፈይሳ ባለው ፍጥነት ወደፊት በፍጥነት መገስገስ እንጅ በእነዚህ እርባናቢስ ቅጥር ነብሰገዳዮች እጅ ስር መውደቅን አልፈለገም፡፡
ፈይሳ በቀላል አገላለጽ ዘ-ህወሀትን ምንም ዓይነት ልብስ ሳይለብስ በሕዝብ አደባባይ ላይ ቆሞ የለበሰ መስሎት ያልለበሰ መሆኑን ሳያውቅ ራቁቱን ተገትሮ ይታይ የነበረውን የንጉስ አፈ ታሪክ በተጨባጭ አሳይቷል፡፡ ወይም ደግሞ ፈይሳ ይህንን በማድረጉ በእውኑ ዓለም በአሁኑ ጊዜ ሕዝብን እያሰቃዩ እና እየዘረፉ ያሉትን ደም መጣጮች በተጨባጭ ለዓለም ሕዝብ በሚገባ አሳይቷል፡፡
ፈይሳ በአሸናፊነቱ ስለሚያጣው የብር ሜዳሊያ እና የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ስለሚጭንበት ቅጣት የሚያሳስበው ጉዳይ ነበርን?
ለዚህ ትንሽ ክብ ቁራጭ ብረት ምንም ዓይነት ደንታ ሊኖረው አይችልም ወይም ደግሞ ከዚህ ጋር በተያያዘ ስለሚያገኘው ዝና እና መልካም ዕድል ሁሉ ደንታው እና ጉዳዩ አይደለም፡፡ መቋጫ በሌለው መልኩ የእርሱ ጭንቀት እና በበለጠ መልኩ ያሳስበው የነበረው ስለወገኖቹ ደህንነት ነበር፡፡ እንዲህ ብሎ ነበር፣ “ስለዚያ ነገር ምንም ማድረግ አልችልም [የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ/ዓኦኮ ስለሚያደርገው ነገር]፡፡ የእኔ ስሜት ይህ ነበር፡፡ በሀገሬ ውስጥ ትልቅ ችግር አለ፡፡ በሀገሬ ውስጥ ተቃውሞ ማሰማት እና በተቃውሞ መንቀሳቀስ እጅግ አደገኛ የሆነ ነገር ነው:: ዓኦኮ እነዚያን ሁለት ቁራጭ ብረቶች መውሰድ እና  እኔን መገፍተር ይችላል…የእኔ ክብር እና የሕዝቦቼ ክብር በኦሎምፒክ ገበያ ወይም ደግሞ በሌላ በማናቸውም ገበያ ቢሆን ለሽያጭ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም“ ነበር ያለው፡፡
ፈይሳን እና ቤተሰቡን እግዚአብሄር ይባርካቸው!
የኢትዮጵያ ወጣቶች ተባብረዋል በፍጹም ሊሸነፉ አይችሉም፣
እ.ኤ.አ ግንቦት 2011 “የአፍሪካ ወጣቶች ተባብረዋል በፍጹም ሊሸነፉ አይችሉም“ በሚል ርዕስ ትችት አቅርቤ ነበር፡፡
ያ ትችት ያጠነጥን የነበረው ስለሙባረክ አገዛዝ ተፈረካክሶ መውደቅ ጉዳይ እና አምባገነኖች በስልጣናቸው ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ለመቆየት ስለሚወስዱት የኃይል እርምጃ ነበር፡፡ ያ ኃይልን የመጠቀሙ እርምጃ የደካሞች ዋና መሳሪያ እንደነበር ግልጽ አድርጌ ነበር፡፡ ምንም ዓይነት መሳሪያ ያልታጠቁትን ሰላማዊ ዜጎች በመንገዶች ላይ ተኩሶ መግደል እና አካለ ጎደሎ ማድረግ የጥንካሬ ምልክት አይደለም፣ ይልቁንም በተቃራኒው የፍርሀት፣ የደካማነት እና የቦቅቧቃ ፈሪዎች ዋና መለያ ምግባር ነው ነበር ያልኩት፡፡
እ.ኤ.አ ሰኔ 2010 “ስለኢትዮጵያ ወጣቶች እውነታውን መናገር“ በሚል ርዕስ ትችት አቅርቤ ነበር፡፡ በዚያ ትችቴ በቁጣ ተሞልተው በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ ወጣቶች በጊዜ የተሞላ የስነሕዝብ ቦምብ ነው የሚል የክርክር ጭብጥ ማስረጃዬን አቅርቤ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ወጣቶች ተስፋ እያጡ የመምጣት፣ የደስታ እጦት፣ የተሳሳተ እምነት መኖር እና ለብዙ ጊዜ በቆየ የኢኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ ብርታትን ማጣት፣ የኢኮኖሚ ዕድሎች ያለመኖር እና የፖለቲካ ጭቆና ግልጽ ሆኖ እየገዘፈ መከሰቱ የማይካድ መሆኑን በማብራራት የክርክ ጭብጤን አቅርቤ ነበር፡፡ ወጣቶች ለነጻነት እና ለለውጥ ያላቸው ጥልቅ ፍላጎት በእራሱ ገላጭ ነው፡፡ ብቸኛ ሆኖ የሚቀርበው ጥያቄ ግን የሀገሪቱ ወጣቶች ለውጡን ሊያመጡት የሚችት እየጨመረ የመጣውን የኃይል እርምጃን በመጠቀም ነው ወይስ ደግሞ በሌላ ሰላማዊ በሆነ መልኩ ነው የሚለው ነው፡፡
እ.ኤ.አ ጥር 2013 “ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2013፡ የአቦ ሸማኔው ትውልድ ዓመት“ በሚል ርዕስ ለኢትዮጵያ ወጣቶች መልዕክት በማስተላለፍ ትችት አቅርቤ ነበር፡፡
በዚያ መልዕክቴ የኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ትውልድ ይፋ ባልሆነ መልኩ የውይይት መድረክ በእራሳቸው በወጣቶቹ መካከል ማድረግ እና በብሄራዊ ዕርቅ የእነርሱ ሚናዎች ምን መሆን እንዳለባቸው አስቀድመው መወሰን እንዳለባቸው ጥሪ አቅርቤ ነበር፡፡ በዚያ መልዕክቴ ወጣቶች  ከምንጊዜውም በላይ እራሳቸውን ማጠናከር እና የእራሳቸውን የፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ምህዳር መፍጠር እና አንድ በአንድ ከጎሳ፣ ኃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ጾታ፣ ክልል እና የመደብ መስመርን ሳይለይ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር መነጋገር እንደሚያስፈልግ የተማጽዕኖ ጥሪ አቅርቤ ነበር፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ለኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ወጣት ትውልድ ብዝሀነታቸውን እንደ ጥንካሬ መውሰድ እንዳለባቸው እና ብዝሀነታቸው እራሳቸውን ለመከፋፈል እና ለጥቃት ሊዳርጋቸው እንደማይገባ የተማጽኖ ጥሪ አቅርቤ ነበር፡፡
በዚያ ትችቴ ላይ የጾታ ልዩነት ክፍተትን ማስወገድ እና ሰላማዊ የእምቢተኝነት ጥረቶችን አጠናክሮ በመቀጠል የወጣት ሴቶችን ተሳትፎ ማስፋት እና ማጠናከር አስፈላጊ እንደሆነ አስምሬበት ነበር፡፡
እ.ኤ.አ ጥር 2014 “እ.ኤ.አ 2014፡ የኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው እና የጉማሬው (የቀድሞው) ትውልድ ዓመት“ በሚል ርዕስ አቅርቤው በነበረው ትችት በኢትዮጵያ ውስጥ በወጣቶች ላይ ተጋርጠው ስለሚገኙት ተግዳሮቶች በዝርዝር ጽፌ ነበር፡፡ በዚህ ትችቴ የኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ትውልድ ወጣቶች አደገኛ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ በማለት አውጀ ነበር፡፡
የ21ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ዋናው ችግር የወጣቱ ችግር ነው የሚል የክርክር ጭብጥ አቅርቤ ነበር፡፡ እንደ ዩኤስ የሕዝብ ቆጠራ ቢሮ ከ34 ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር በሶስት እጅ በመጨመር 278 ሚሊዮን እንደሚሆን እና ሀገሪቱ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት በማስመዝገብ ላይ ከሚገኙት 10 የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ከሚገኙት ሀገሮች ምድብ ውስጥ ትመደባለች የሚል ትንበያ የሰጠ መሆኑን በመጥቀስ የክርክር ጭብጤን አቅርቤ ነበር፡፡
በአሁኑ ጊዜ ወደ አንድ መቶ እና ከዚያም በላይ ሊሆን ከሚገመተው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ውስጥ ወደ 70 በመቶ የሚገመተው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከ35 ዓመት በታች እድሜ (66 ሚሊዮን) ያለው የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡
ኔልሰን ማንዴል በአንድ ወቅት እንዲህ የሚል ምልከታ አድርገው ነበር፣ “የእኛ ልጆች የእኛ ታላቅ ሀብቶች ናቸው፡፡ ልጆቹ የእኛ የወደፊት ጸጋዎች ናቸው፡፡ በእነርሱ ላይ ከሕግ አግባብ ውጭ የሚፈጸም ማንኛውም ድርጊት ሁሉ የማህበረሰባችንን የአንድነት ክር ይበጥሳል፣ እናም ሀገራችንን ያዳክማል“ ነበር ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ ወጣቶች የሀገሪቱ ታላቅ ሀብት የሆኑት እና የኢትዮጵያ የወደፊት ጸጋዎች  በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ አደጋ ላይ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሀብቶች የሆኑት ወጣቶች ፍጹም በሆነ መልኩ ተረስተዋል፣ ከሕግ አግባብ ውጭ ጭቆና ይፈጸምባቸዋል፣ ውድ የሆነው ጉልበታቸው በከንቱ እየጠፋ እና በከንቱ በመባከን ላይ ይገኛል፡፡
እንደ የአፍሪካ ሕዝቦች እና የጤና ምርምር ማዕከል/African Population and Health Research Center ዘገባ ከሆነ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ በጣም ዝቅተኛ የሆነ ጠቅላላ የትምህርት ሽፋን መጣኔ/Gross Enrollment Rate ካላቸው ሀገሮች መካከል አንዷ ናት…ዝቅተኛ የትምህርት ጥራት እና ከፍተኛ የሆነ የማቋረጥ መጣኔ እንደዚሁም ሁሉ በገጠር እና በከተማ መካከል ከፍተኛ የሆነ የጾታ ልዩነት መኖር ዋና የሀገሪቱ ችግሮች ሆነው ቀጥለዋል፡፡ እንደምንም ብለው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለመግባት በጣም የጠበቡ ዕድሎች እንዳሏቸው ወይም ደግሞ የስራ ዕድል እንደማያገኙ ዘገባው ግልጽ አድርጓል፡፡
እ.ኤ.አ በ2012 በዩኤስኤአይዲ የወጣው ዘገባ እንዲህ ይላል፣ “ኢትዮጵያ የከተማ ወጣት የስራ አጥነት የተንሰራፋባት ሀገር ናት፡፡ ይህም የስራ አጥነት መጣኔ 50 በመቶ እንደሆነ እና ከፍተኛ የሆነ የስራ አጥነት ችግር ተንሰራፍቶ እንደሚገኝ እንዲሁም 85 በመቶ የሚሆነውን ሕዝብ በሚይዘው በገጠሪቱ ኢትዮጵያም የስራ አጥነቱ ችግር በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮ ይገኛል“ ነበር ያለው፡፡
ሌላው በዓለም አቀፍ የዕድገት ማዕከል/International Growth Center እ.ኤ.አ በ2012 በወጣት ስራ አጥነት ላይ የተደረገ ጥናት የግኝት ጭብጥ እንዲህ ይላል፣ “በአሁኑ ጊዜ ያለው (እ.ኤ.አ 2010/11 – 2014/15) የ5 ዓመት የኢትዮጵያ የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ገዥው አካል የወጣቶችን ስራ አጥነት ችግር ጉዳይ በቀጥታ አላካተተም…“ ነበር ያለው፡፡ ያ ጥናት እንዲህ የሚል የጥናት ውጤት አግኝቷል፣ “እ.ኤ.አ በ2011 38 በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች አብዛኛውን ጊዜ ዝቅተኛ የጥራት ጉድለት በሚታይባቸው እና ዝቅተኛ ክፍያን በሚከፍሉ የግል ዘርፉ ውስጥ ተቀጥረው ይገኛሉ“ ነበር ያለው፡፡
በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉት ከፍተኛ ብዛት ያላቸው ወጣቶች ስራ አጥ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን መሰረታዊ የሆኑ ክህሎቶችን በተገቢው ስልጠና ያላገኙ በመሆናቸው ወደፊትም እንኳ የስራው ዕድል ቢፈጠር ተቀጥረው ለመስራት የማይችሉ ናቸው፡፡ በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኙት የስራ ዘርፎች በብቃት ወይም ደግሞ በውድድር ላይ በተመሰረተ መስፈርት መሰረት ባለሞያዎችን የሚቀጥሩ ሳይሆን በፖለቲካ የመንግስት ወገንተኝነት እምነታቸው እና በማህበራዊ ግንኙነቶች እንደዚሁም ደግሞ  የገዥው ፓርቲ አባል ለሆኑት ስራ ፈላጊዎች ብቻ ተደራሽ የሆኑ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ማንኛውም ወጣት አባልነትን የሚገልጽ ካርድ ከገዥው ፓርቲ መያዝ ትክክለኛ በሆነ የግል ጥረት ከተያዘ የዩኒቨርስቲ ዲፕሎማ በላይ ጠቃሚነት አለው፡፡ ከዚህም በላይ የገጠር ወጣቶች መሬት አልባነት ለዚህ ለተፈጠረው ቀውስ እና ወደ ከተማ ለሚደረገው ከፍተኛ የሆነ የሰው ፍልሰት፣ ስራ አጥነት እና ተስፋየለሽነት እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ ወጣቶች ላይ ተጋርጠው የሚገኙ አደጋዎች ሙሉ በሙሉ በህብረተሰቡ ውስጥ ተንሰራፍተው የሚገኙ ማህበራዊ ቀውሶች ናቸው፡፡
እ.ኤ.አ በ2010 እንደወጣው የዘ-ህወሀት ዘገባ 150 ሺ ህጻናት የጎዳና ላይ ተዳዳሪዎች ሆነዋል፣ ከእነዚህም ውስጥ 60 ሺ የሚሆኑት በሀገሪቱ ዋና መናገሻ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ ልጆቹ በመጀመሪያ ቤት አልባ የሚሆኑበት አማካይ እድሜ 10 እና 11 ዓመት እንደሆነ ተዘግቧል፡፡
ከኤች አይቪ ኤይድስ እና ከሌሎች በግብረ ስጋ ከሚተላለፉ በሽታዎች ጋር በተያያዘ መልኩ የወጣቶች የጤንነት አደጋዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመር ላይ ይገኛሉ፡፡ ምንም ዓይነት ዕድል የሌላቸው በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች አንደንዛዥ እጾችን በመውሰድ፣ አልኮልን በማዘውተር፣ በዝሙት አዳሪነት እና በሌሎች በወንጀል ድርጊቶች ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ በከተሞች አካባቢ ያለምንም ስራ እና የትምህርት ዕደል በርካታ የሆኑ ወጣቶች ስራ አጥ፣ ቤት የለሽ፣ ረዳት የለሽ እና ተስፋየለሽ ሆነው ይገኛሉ፡፡
እ.ኤ.አ በ2004 ዘ-ህወሀት ብሄራዊ የወጣቶች ፖሊሲን አወጀ፡፡ እናም ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ዘገባ መሰረት እንዲህ የሚል ግኝት ተመዝግቦ ነበር፣ “44 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ከድህነት ወልል በታች ነው፡፡ በዚህ ዓይነት የድህነት ሁኔታ ወጣቱ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቂ የሆነ የማህበረሰብ ከፍል ነው…አብዛኞቹ ስራ አጥ የሆኑት ሴት ወጣቶች የመሆናቸው ጉዳይ ደግሞ የዚህ ችግር ሰለባ የመሆናቸውን እውነታነት የበለጠ ተጨባጭ ያደርገዋል“ የሚል ነበር፡፡ ሰነዱ የፖሊሲውን ተፈጻሚነት ሲያብራራ “መንግስት፣ የመምራት፣ የማስተባበር፣ የማቀናጀት እና የአቅም ግንባታ ስራዎችን የመስራት ኃላፊነትን ይወስዳል” የሚል ነበር፡፡
ሆኖም ግን እ.ኤ.አ በ2012 በዓለም አቀፍ የዕድገት ማዕከል/International Growth Center  በወጣት ስራ አጥነት ላይ የተደረገ ጥናት የግኝት ጭብጥ እንዲህ ይላል፣ “በአሁኑ ጊዜ ያለው (እ.ኤ.አ 2010/11 – 2014/15) የ5 ዓመት የኢትዮጵያ የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ገዥው አካል የወጣቶችን ስራ አጥነት ችግር ጉዳይ በቀጥታ አላካተተም…“ የሚል ነበር፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ብሄራዊ የወጣቶች ፖሊሲ እየተባለ የሚጠራው ለዘ-ህወሀት ወጣቶችን ለይስሙላው ምርጫ መጠቀሚያነት ከመሆን ባለፈ ለወጣቱ አንዳችም የፈጠረው ፋይዳ የለም፡፡
እ.ኤ.አ በ2014 የወጣ ዘገባ አስከፊውን የገጠር ድህነት ለማምለጥ ወጣቶች እንዴት አድርገው የውስጥ ፍልሰትን እንደሚጠቀሙ ያመላክታል፡፡
ለበርካታ ዓመታት የኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ትውልድ አንድ ቀን ሊነሳ እንደሚችል እና ያችንም ቀን እንሚጠብቃት ስናገር ቆይቻለሁ፡፡ ኢትዮጵያን ከዘ-ህወሀት ጅቦች ጠብቁ፡፡
ሳስተላልፈው በቆየሁት መልካም መልዕክት ሁሉ በጣም ኩራት ይሰማኛል!
እ.ኤ.አ የካቲት 2016 “ለኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ትውልድ የጥርሙስ ውስጥ መልዕክት፡ ነጻ ሆናችሁ ተወልዳችኋል፣ ነጻ ሆናችሁ ኑሩ!“ በሚል ርዕስ ስለሚመጣው ሁኔታ እንዲህ በማለት አስጠንቅቄ ነበር፡
“የኢትዮጵያ ወጣቶች ሙሉ በሙሉ ግንዛቤው አላቸው፡፡ ጥቂት የአቦ ሸማኔው ትውልድ አባላት በንዴት እና በከፍተኛ ቁጣ በመነሳሳት በእምቢተኝነት ከዘ-ህወሀት ፊት ለፊት ይቆማሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ድምጾቻቸውን ከፍ አድርገው ያንሾካሹኩ እና ያጉረመርማሉ፡፡ የኢትዮጵያ አቦ ሸማኔዎች ደስተኞች አይደሉም” በማለት አስጠንቅቄ ነበር፡፡ ለዚህም ነው በአሁኑ ጊዜ በመላ ሀገሪቱ ውስጥ ከጅቦች ጋር ፊት ለፊት በመጋፈጥ እና በማጉረምረም ላይ የሚገኙት፡፡
እ.ኤ.አ ጥር 2016 ዘ ኢኮኖሚስት የተባለው መጽሄት ለበርካታ ዓመታት በአእምሮዬ ውስጥ ሲመላለስ የቆዬ እንዲህ የሚል አንድ ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ ጥያቄውን በሰማሁበት ጊዜ መብረቅ እንደመታው ዛፍ ድርቅ ብዬ ነበር የቀረሁት፡፡ እንዲህ የሚል ጥያቄ ነበር፣ “አትዮጵያውያን ነጻ ቢሆኑ ኖሮ የት ይደርሱ ነበር?“ ዘ ኢኮኖሚስት ለእራሱ ጥያቄ መልስም እራሱ እንዲህ በማለት ነበር የሰጠው፣ “የኢትዮጵያ መንግስት ሕዝቦች በነጻነት እንዲተነፍሱ ቢፈቅድ ክንፍ አውጥተው ሊበሩ ይችላሉ፡፡“
“ብሪሪ፣ ኢትዮጵያ ብረሪ…“ በሚል ርዕስ አዘጋጅቸው በነበረው ትችቴ የምዕናባዊ በረራዬን አከናውኘ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ መብረር የምትችል ቢሆን ኖሮ ለመሞት በባህር ላይ አይጣሉም ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሴቶች ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች በእርግጠኝነት ባሮች ለመሆን አይበሩም ነበር፡፡ በረሀዎችን በማቋረጥ ደም ለጠማቸው አሸባሪዎች የጥቃት ሰለባ አይሆኑም ነበር፡፡ ወደ ስደት አያመሩም ነበር፡፡ ለመብረር የሚችሉ ቢሆን ኖሮ እንደ አፍሪካ ዓሳ ይንሰፈፉ ነበር፡፡ ክንፎቻቸውን ወደ ሰማይ ከፍ በጣም ከፍ ያደርጉ ነበር፡፡ እንደ ድምጻዊዋ ወፍ ያዜሙም ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ወጣቶች እንዲበሩ እፈልጋለሁ፡፡
በምዕናባቸው በረራ እንዲያደርጉ እፈልጋለሁ፡፡
የእነርሱ የሆነች እና ከጎሳ ፖለቲካ፣ ከኃይማኖት ጽንፈኝነት እና ከጭፍን ጥላቻ ነጻ  የሆነች አዲስ ኢትዮጵያን እንዲያልሙ እፈልጋለሁ፡፡
በእራሷ ለእርሷ እና ለጎረቤቶቿ ሰላሟ የተጠበቀ፣ ከጭቆና እና ከወሮበላ ዘራፊዎች ነጻ የሆነች ኢትዮጵያን ለማየት እፈልጋለሁ፡፡
እያንዳንዱ የአቦ ሸማኔ ትውልድ የህንጻ ንድፍ ባለሞያ፣ ንድፍ ሰሪ፣ ፈጣሪ፣ ለኪ፣ ገንቢ እና ዜጎቿ እርስ በእርሳቸው ስለጎሳዎቻቸው ሳይሆን ስለሰብአዊ ፍጡርነታቸው፣ ስለእኩልነት ዕድሎቻቸው፣ ከሙስና፣ ከጭቆና እና ከወሮበላ ዘራፊዎች ነጻ ስለሆነች ኢትዮጵያ በአንክሮ የሚያስቡ የነጻ ኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ዜጋ እንዲሆኑ አጥብቄ እጠይቃለሁ፡፡
ኢትዮጵያን በምዕናባቸው እንዲያንጿት እፈልጋለሁ፡፡
ማሸነፍ ልብን እና አእምሮን እንጂ ሜዳሊያዎችን አይደለም፣
እኔ ሁልጊዜ ከኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ትወልድ ጠርዝ ወይም ጫፍ ላይ እንደምቆም ግልጽ አድርጊያለሁ፡፡ (እ.ኤ.አ ጥር 2013 “የአቦ ሸማኔ – ጉማሬው ትውልድ መነሰሳሳት” በሚል ርዕስ አዘጋጅቸው የነበረውን ትችቴን ይመልከቱ፡፡)
በዚያ ትችቴ ላይ በኢትዮጵያ ለነጻነት፣ ለዴሞክራሲ እና ለሰብአዊ መብጥ ጥበቃ የሚደረገው ትግል ዋናው ምስሶ እንደሆነ እና የኢትዮጵያን ሕዝቦች ልብ እና አእምሮ ለመቆጣጠር በሚደረገው ጦርነት ላይ ትልቅ ጉዳይ እንደሆነ ለኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ትውልድ በዝርዝር ገልጨ ነበር፡፡ ልብን እና አእምሮን ለመቆጣጠር በሚደረግ የጦር ሜዳ ትግል ውስጥ ጠብመንጃዎች፣ ታንኮች እና የጦር አውሮፕላኖች ዋጋቢሶች ናቸው፡፡ ይህንን ጉዳይ ታሪክ በተጨባጭ አረጋግጧል፡፡ ዩኤስ አሜሪካ በቬትናም ጦርነት ድልን አጥታለች ምክንያቱም አውዳሚ የጦር መሳሪያዎች ኃይል፣ የአየር ኃይል፣ የኒኩሌር ኃይል፣ የገንዘብ ኃይል ሳይንሳዊ ወይም ደግሞ የቴክኒክ ኃይል ስላጡ አልነበረም፡፡ ዩኤስ አሜሪካ በጦርነቱ የተሸነፈችበት ዋናው ምክንያት የቬትናማውያንን እና የአሜሪካውያንን ሕዘቦች ልቦች እና አእምሮዎች ማሸነፍ ባለመቻላቸው ነበር፡፡
ህይወት ሜዳሊያ ስለማሸነፍ ጉዳይ አይደለም፡፡
ይልቁንም ህይወት ልብን እና አእምሮን ስለማሸነፍ ጉዳይ ነው፡፡
የዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የሚያብረቀርቁ ሜዳሊያዎችን ከስሚዝ እና ከካርሎስ ቀምቶ ወስዷል፡፡  እነዚህ ሁለት ጓደኛሞች ከአራት አስርት ዓመታት በላይ ይበገሬ የሰብአዊ መብት ተሟጋችነታቸውን በተግባር አረጋግጠዋል፡፡
ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ የፈይሳን ሜዳሊያ ይወስደው ወይም አይወስደው ለመሆኑ ገና ግልጽ አይደለም፡፡
እንደ ስሚዝ እና ካርሎስ በተመሳሳይ መልኩ ፈይሳ እ.ኤ.አ በ2016 የእርሱን ሕዝቦች ልቦች እና አእምሮዎችን የተቆጣጠረውን ሜዳሊያ ብቻ አይደለም የወሰደው ሆኖም ግን በእርገጠኝነት የወሰደው በዓለም ላይ የሚገኙትን በቢሊዮኖች የሚቆጠሩትን የሌሎችን የነጻነት አፍቃሪዎች ሕዝቦች ልቦች እና አእምሮዎች ጭምር እንጅ፡፡
ፈይሳ ልክ እንደ ስሚዝ እና ካርሎስ በተመሳሳይ መልኩ ለበርካታ ጊዚያት የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች በመሆን ሲወደስ እና ሲዘከር ይኖራል፡፡
ስሚዝ፣ ካርሎስ እና ፈይሳ የፈጸሙት ድርጊት እውነተኛ የአሜሪካ መስራች አርበኞች የፈጸሙት እውነተኛ የመንፈስ እና ቃላት ድርጊት እንደሆነ አምናለሁ፡፡
ወጣቱ አሌክሳንደር ሀሚልተን (አንዱ ያሜሪካ ቆርቅዋሪ) እንዲህ በማለት ጽፎ ነበር፣ “የሰውን ባህሪ ከእራሱ በላይ አድርጎ በቆራጥነት እና በጀግንነት እንዲወጣ ሊያደርግ የሚያስችል በነጻነት ውስጥ አንድ ልዩ የሆነ የማድረግ ጉጉት አለ“ ነበር ያለው፡፡ ሀሚልተን የእንግሊዝ በሙያ ክህሎት የተካነው የጦር ኃይል በአንድ የማድረግ ጉጉት በተጠናውተው ቆራጥ እና ጀግና አማጺ ሊሸነፍ እንደሚችል ያምናል፡፡ ካርሎስ እና ስሚዝ በዝቀተኛው የህብረተሰብ ክፍል የሚገኙት የሲቪል ማህበረሰቡን መብት የማስከበር ጉጉት ያደረባቸው ጀግኖች የመብት ተሟጋቾች በአሜሪካ ውስጥ ዘረኝነትን እና ድህነትን ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ያምናሉ፡፡ ፈይሳ ለነጻነት ያለውን ጉጉት ቆራጥነት እና ጀግንነትን በተላበሰ መልኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቢሊዮኖች እንዲታይ በማድረግ ወደ ተጨባጭ ተግባር ተርጉሞታል፡፡
ወጣት ጀምስ ማዲሰን (የአሜሪካ ሕገ መንግስት መስራች አባት) አብዮታዊ በሆነ ብሄራዊ የአንድነት እና የዓላማ መንፈስን በመተግበር እንዲህ የሚል ዝናን ተጎናጽፏል፡ “የነጻነት መንፈስ እና አርበኝነት ሁሉንም የሰው ልጆችን የደስታ መጠን እና ዋጋዎች ግኡዝ ያደርጋሉ፡፡“  እንደዚሁም ሁሉ ካርሎስ እና ስሚዝ እ.ኤ.አ በ1968 እንዳደረጉት ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ የነጻነት መንፈስ እና አርበኝነት ፈይሳን እ.ኤ.አ በ2016 ግኡዝ አድርገውታል፡፡
የምክንያታዊነት ደጋፊና አምፅ አንቀሳቃሽ  የሆኑት ሳሙኤልሰን አዳምስ በአንድ ወቅት እንዲህ በማለት አስጠንቅቀው ነበር፣ “ለእውነተኛ አርበኞች ዝምታን መምረጥ አደገኛ ሁኔታ ነው“ ነበር ያሉት፡፡
እውነተኛ የአሜሪካ አርበኞች ስሚዝ እና ካርሎስ እና የኢትዮጵ አርበኛ ፈይሳ ሌሊሳ በኦሎምፒክ መድረክ ዝምታን መርጠው ነበር፣ ሆኖም ግን ወደ ላይ ከፍ ያሉት ቡጢዎቻቸው እና የተጣመሩ እጆቻቸው ስለዘርኝነት፣ ስለጎሳ ጥላቻ፣ ስለኢፍትሀዊነት እና ስለአድልኦ በርካታ ነገሮችን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵ የአቦ ሸማኔዎች ግድያ ለመጣል በማዛጋት ያጉረመርማሉ፣
“የአቦ ሸማኔ – ጉማሬ” መጽሐፍ ደራሲ የሆኑት የጋናው ኢኮኖሚስት ጆርጅ አይቴይ በአፍሪካ ውስጥ የሚታየውን የአመራር ቀውስ ለመግለጽ  የአቦ – ሸማኔን ተመሳስሎ በመውሰድ እንዲህ የሚል ምልከታ አድርገው ነበር፣ “የአፍረካ አቦ ሸማኔዎች በለውጥ የታጀቡ ጠንካሮች ናቸው፣ ምሁራዊ የአእምሮ የማድረግ ቅልጥፍና እና በተግባራዊ ውጤታማነት ላይ ልዩ የሆነ ትኩረት አላቸው፡፡ እረፍትየለሽ ትውልዶ ሊሆኑ ይችላሉ፣ ሆኖም ግን የአፍሪካ አዲስ ተስፋዎቸ ናቸው፡፡ ስለሙስና፣ ስለውጤት አልባነት፣ ስለክህሎት የለሽነት እና ስለብቃትየለሽነት ወይም ደግሞ ስለእርባናቢስ ባህሪ ትዕግስቱ ፈጽሞ የላቸውም“ ነበር ያሉት፡፡
አቦ ሸማኔ ፈይሳ ሌሊሳን ተመልከቱት!
የኢትዮጵያ ተስፋዎች የሆኑትን የኢትዮጵያውን ወጣት አቦሸማኔዎችን ተመልከቱ፡፡
ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገር እና እንደ ሕዝብ የመቀጠል የህልውና ዕድል ቢኖራቸው ያ የመኖር ህልውና ሁልጊዜ በእራሷ ወጣቶች የመፍጠር ችሎታ፣ የማይበገር የአካል፣ የአእምሮ ጥንካሬ የማሳየት ብቃት፣ ጽናት፣ መልካም ፈቃድ፣ የመፈጸም ብቃት፣ እና መስዋዕትነት በመክፈል ሁኔታ ላይ የሚወሰን ነው እላለሁ፡፡ ይኸ ሁኔታ በወጣቶች ላይ ታላቅ ሸክምን አስቀምጧል፡፡ ከባዱን ነገር ለማንሳት፣ ከባድ ስራዎችን ለመስራት እና መስዋዕትነትን በመቀበል የአንበሳውን ድርሻ (የአቦ ሸማኔውን ሳይሆን) ማድረግ አለባቸው፡፡
እንደዚሁም ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ የኢትዮጵያ ወጣቶች እንደ ወጣት መቀጠል ቢችሉ እና የመኖር ዕድል ቢኖራቸው በቀድሞው ትውልድ ለመጭው ትውልድ ንቁ እና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ በማድረግ ጥንካሬ ላይ የሚወሰን ነው፡፡
የኢትዮጵያ የጉማሬው (የቀድሞው ትውልድ) አቦ ሸማኔዎቻችን ተስፋ እንዳያጡ እና እንዳይወድቁ የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን፡፡ ይህንን ማድረግ ከቻሉ በአንጸባራቂነት እንዲወጡ እና ደግመው እና ደጋግመው እንዲያደርጉት ማስቻል አለብን፡፡
እኛ የቀድሞው ትውልድ አባላት የቱንም ያህል ጊዜ ቢፈጅም፣ ገሀነም ወይም የቱንም ያሀል በከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ ቢሆንም በማንኛውም መንገድ ከአቦ ሸማኔዎቻችን ጎን በጽናት መቆም አለብን፡፡ ከእነርሱ ጋር የውይት መድረኮችን በመክፈት መወያየት እና እነርሱን እንደምንደግፋቸው እና እንደምንወዳቸው፣ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ግንባታ ውስጥ ተሰማርተው እስካሉ ድረስ እኛ በደስታ የእነርሱ ውኃ አቀባይ እንደሆንን ልናረጋግጥላቸው ይገባል፡፡
አብዛኞቻችን እኛ የጉማሬው ትውልድ አባላት ታላላቅ ነገሮችን ለመስራት ሊያመልጡን የማይገቡ ዕድሎች በፍጹም ሊያመልጡን የማይገቡ ዕድሎች ናቸው፡፡ (ውይ እንዴት የሚያም ነገር ነው! እውነት እንዴት እንደሚጎዳ!)
ታላላቅ ነገሮችን ለእራሳችን መስራት ማለትም አይደለም፡፡ ለሌሎች ነው መስራት ያለብን፡፡ መስራት ያለብን ኃይል ለሌላቸው፣ መከላከያ ለሌላቸው፣ ለተስፋ የለሾች፣ ለመጠለያ የለሾች፣ ለሀገር አልባዎች እና ለምቾት የለሾች ነው፡፡
ከአቦ ሸማኔዎች ጎን በመቆም አቦ ሸማነኔዎቻችንን በመርዳት ይህንን ቅዱስ የሆነ አጋጣሚ እንዳናጣው ጥረት እናድርግ፡፡
የጀግና ጉዞ፣
ሺ ፊቶችን የሚጋፈጠው የጆሴፍ ካምፕቤል ጀግና በዓለም አቀፍ ደረጃ ጀግንነትን ለመስራት እና ድልን በወሳኝነት እስከመጨረሻው ለመቀዳጀት ሁሉንም ዓይነት ስቃዮች፣ መከራዎች መጋፈጥ አለበት፡፡ ማናቸውንም ፍርሀት ከሚያስከትሉ ነገሮች፣ ከሚያበሳጩ እና መከራ ከሚያስከትሉ ነገሮች ጋር ሁሉ ፊት ለፊት ይጋፈጣል፡፡ ሞትንም ሊጋፈጥ ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ጅግና በሁሉም ጉድለቶች ሳቢያ አይንበረከክም፡፡
ፈይሳም እንደዚሁ በተመሳሳይ መልኩ በእርሱ የዓለም ጀግንነት ከታላላቅ ተግዳሮቶች እና የህይወት አጋጣሚዎች ጋር መጋፈጥ አለበት፡፡
ያለምንም ጥርጥር ከእራስ መተማመን ጥርጣሬ፣ በእራስ ከማዘን፣ ከራስ ትችት፣ ከሀዘን፣ ከጥፋት፣ ከጸጸት፣ ከሀሜት፣ ከሀዘን እና ከብስጭት እራሱን ነጻ እንደሚያደረግ የሚያጠራጥር ጉዳይ አይለም፡፡
ቃላት ሊገልጹት ከሚችሉት በላይ ልጆቹን እና ባለቤቱን ሊያጣ እንደሚችል የሚያጠራጥር ጉዳይ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን እነዚህ ሁሉ ነገሮች ለእውነተኛ የሰው ልጆች ስጋ ለለበሱ ሰይጣኖች ሳይሆን ለሁሉም የሰው ልጆች መለያ ባህሪያት ናቸው፡፡
እነዚህ ነገሮች ለረዥም ርቀት ሯጩ ታላቅ ሸክም ናቸው፡፡
ሆኖም ግን ፈይሳ በማወቅ ሁሉንም የእርሱን ምቾት በመሰዋት ለልጆቹ፣ ለባለቤቱ፣ ለወላጆቹ፣ እና ለእርሱ ሕዝቦች እንደ ሰብአዊ ፍጡር ክብር እና ነጻነት አግኝተው እንዲኖሩ በማሰብ ያደረገው ጉዳይ ስለሆነ የሚጸጸትበት ነገር አይሆንም፡፡
ፈይሳ እና ሁላችንም ከእርሱ ጎን የቆምን እና በኢትዮጵያ ውስጥ ለዴሞክራሲ፣ ለነጻነት እና ለሰብአዊ መብት መከበር የማራቶን ሩጫ ለመሮጥ የተዘጋጀን ሰዎች ሁሉ በመጨረሻ የወርቅ ሜዳሊ አሸናፊዎች እንደምንሆን ምንም ዓይነት ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ማራቶን መንፈስ አይደለም፣ ስለሆነም የፍጥነት ምህዋራችንን ጠብቀን መሮጣችንን መቀጠል አለብን፡፡
የጀግኖች ጉዞ በፍጹም ቀላል አይደለም፡፡ ለዚህም ነው በዓለም ላይ እንደዚህ ያለውን ከባድ ሸክም ለመቀበል ፈቃደኛ የሆኑ በጣም ጥቂት እውነተና ጀግኖች ብቻ ያሉን፡፡
አብዛኞቻችን ለውጥን እንፈራለን፣ እናም በይበልጥም ደግሞ የእራሳችንን አእምሮ ለመለወጥ እንፈራለን፡፡ ስለሆም በፍርሀት ብርድ ልብስ ውስጥ በመወሸቅ ፍጹም በሆነ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ወድቀን እንገኛለን፡፡
እንደ ጀግና ኢትዮጵያዊ የፈይሳ ገጽታ ለሁሉም ኢትዮጵያውን እንደ ነጻነት ጠባቂ፣ ዘብ፣  የዴሞክራሲ እና ሰብአዊ መብት ተሟጋችነት ሚና እውነታነት ተተርገሟል፡፡
እንደ ካምፔል ምዕናባዊ ጀግና በተመሳሳይ መልኩ ፈይሳም ሁሉንም ነገር መስዋዕት ያደረገለትን ጉዳይ አጥብቆ በመያዝ የሁሉም ፈዋሽ መድሃኒት እና ሀብት በመያዝ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደ ሀገሩ ይመለሳል፡፡
ምናልባትም ፈይሳ ስለሰራው ቆራጥነት እና ጀግንነት ትልቅ አክብሮት ላንሰጥ እንችል ይሆናል፡፡
የእርሱ ቀደምት አባቶች ኢትዮጵያን ከውጭ ወራሪዎች፣ ከቅኝ ተገዥነት እና ከኢምፔሪያሊዝም ተጽዕኖ ለዘመናት የሀገራችንን ነጻነት ለመጠበቅ በደማቸው፣ በላባቸው እና በእንባዎቻቸው ክቡር ዋጋ የከፈሉ ሲሆን ፈይሳ ግን በእግሩ እና በእጆቹ ብቻ በመጠቀም ፈጽሞታል፡፡
ብቸኛው ልዩነት ግን ፈይሳ በሀገሩ በስልጣን ኮርቻ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው የሚገኙትን የማፊያ ወንጀለኛ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ የከፈለው መስዋዕትነት የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡
የፈይሳ እንደ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ አርበኛ ሆኖ እንደገና የመወለድ ሁኔታ የሚመጣው ሀገሩ ኢትዮጵያ  ከዘራፊዎች፣ ወሮበሎች እና ከወንጀለኞች አፈና ነጻ ከሆነችው ምድር ላይ ከቤተሰቡ ጋር እንደገና መገናኘት ሲችል ነው፡፡
ፈይሳ ወደ ሀገሩ በሚመለስበት ጊዜ እርሱን ሰላም ለማለት ሚሊዮኖች መንገዶችን ሁሉ በሰልፍ እንደሚያጣብቡ አልጠራጠርም…
አቤት ጉድ እኮ ነው፣ መላዕክቶች ወደ ሀገራቸው በሚመለሱበት ጊዜ…ሰይጣኖቹ በቀጥታ ወደ ገሀነም ይወርዳሉ፡፡
እ.ኤ.አ በ2011 ያስተላለፍኩትን መልዕክት እንደገና በ2016 ለኢትዮጵያ ወጣቶች እናገራለሁ፣
እ.ኤ.አ በ2011 እንዲህ የሚል መልካም የሆነ መልዕክት ለኢትዮጵያ ወጣቶች አስተላልፌ ነበር፡
“የኢትዮጵያ ወጣቶች ተጋርጠውባቸው ስላሉት ማናቸውም ችግሮች መፍትሄ ሊሆን የሚችል ታምራዊ ቀመር በፍጹም የለኝም፡፡ ለሁሉም ወጣት ኢትዮጵያውያን ለማስተላለፍ የምፈልገው ዋና ጉዳይ እንዲህ የሚል ቀላል ነገር ነው፡፡ ‘በፍጹም እጅ እንዳትሰጡ፣ በፍጹም!’ አእምሮዎቻችሁን ከአእምሮ ባርነት ነጻ አውጡ፡፡ የመፍጠር ኃይላችሁን አሳድጉ፡፡ እርስ በእርሳችሁ ተማሩ፣ አስተምሩ፡፡ እንደ እናት ኢትዮጵያ ልጆችነታችሁ ተባበሩ፣ እናም በጎሳ፣ በቋንቋ፣ በአካባቢያዊነት ወይም በመደብ መሰረትነት የሚከፋፍላችሁን ማንኛውንም ርዕዮት ዓለም አስወግዱ፡፡ ስለሳይንስ እና ስለማህበረሰብ ትምህርታችሁ ብቻ ሳይሆን ከዚህም በተጨማሪ ስለ ሕጋችሁ፣ ስለሕገ መንግስት እና ስለሰብአዊ መብትም አጥኑ፡፡“ 
እ.ኤ.አ በ2016 እንደገና ይህንኑ መልዕክት በድጋሜ በአስቸኳይ እንዲህ በማለት ላክሁ፡
የኢትዮጵያ የወጣት ኃይል በምንም ዓይነት መንገድ የሚቆም እንዳልሆነ በእያንዳንዱ የሰውነታችን ክፍል ይታወቃል፡፡
በፍጹም እጅ እንዳትሰጡ! በፍጹም!
እንደ እናት ኢትዮጵያ ልጅነታችሁ ሁላችሁም ተባበሩ፡፡
ዘርን፣ ቋንቋን፣ ኃይማኖትን፣ አካባቢያዊነትን ወይም ደግሞ መደብን መሰረት በማድረግ የሚመጣን ርዕዮት ዓለም ወይም ጥረት አስወግዱ፡፡
እጆቻችሁን በማጣመር ወደ ቤተሰማያት አቅጣጫ በማድረግ ጉዟችሁን ቀጥሉ፡፡ በሰላማዊ መንገድ፡፡
መላዕክት ጉዟቸውን አጠናቅቀው በሚደርሱበት ጊዜ ሰይጣኖቹ ውር ብለው እንደሚበሩ እመኑ፡፡
የእናንተ ትግል ማተኮር ያለበት ከተራው ዓለም ሕዝብ ጋር ያለመሆኑን አስታውሱ፡፡
የእናንተ ትግል በገሀነም ውስጥ ካለው ከሰይጣናዊ ኃይል ጋር ነው፡፡
የእናንተ ትግል እንደገና ህይወት ዘርቶ የጭቆና ህልውናውን ለማስቀጠል የሞት ሽረት ትግል ከሚያደርገው ከጨለማው ልዑል ሠራዊት ጋር ነው፡፡
ሆኖም ግን እናንተ አሸናፊዎች እንደምትሆኑ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ ምክንያቱም አምላክ ከእናንተ ጎን ተሰልፏልና፡፡
እመኑ!
የሀሰት ልዑሎች ይወድቃሉ፣ አፈር ትቢያም ይሆናሉ፣ እናም ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ትዘረጋለች ተብሎ በቅዱሱ መጽሐፍ ተጽፏልና፡፡
የሰላም እጆቻችሁን ለኢትዮጵያውያን ወገኖቻችሁ ዘርጉ!
እጆቻችሁን ወደ ላይ ወደ አየር ከፍ በማድረግ አጣምሩ፣ እናም ሰይጣኖች በምንም መንገድ ሊያቋርጧቸው አይችሉም፡፡
ለቅሶ ለዛሬ ማታ ብቻ ህልውና ሊኖረው ይችላል፣ ሆኖም ደስታ እና ሀሴት ከነገ ጠዋት ጀምሮ ይመጣል፡፡
አሁን የጧቱ ጊዜ ነው!
የኢትዮጵያ ወጣቶች በአንድነት ወደፊት! ጉዟችሁን በቆራጥነት እና በጽናት ቀጥሉ!
የኢትዮጵያ አቦ ሸማኔዎች ማጉረምረማችሁን የበለጠ አጠናክራችሁ ቀጥሉ!
ድል በእጆቻችሁ መዳፍ ውስጥ ነው! ድል በእጆቻችሁ መዳፍ ውስጥ ነው!
እመኑ!
የኢትዮጵያ ወጣቶች ተባብረዋል በፍጹም ሊሸነፉ አይችሉም!!!
ኃይል ለኢትዮጵያ ወጣቶች!  
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!  
ነሐሴ 25 ቀን 2008 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment