Wednesday, August 17, 2016

ሽረተ ፅልማሞት በሲሳይ ዘለቀ


ከህይወት ዘመን ታሪኮቼ ሁሉ ለልጄ የማወርሰው ታላቁ የህይወቴ ማስታወሻ የሆነው ይህ ታሪኬ ተፈጥሮኣዊው ማንነቴን የተቀበልኩበት የዚህ ክረምት ገጠመኜ ነው፤ ለልጄም ብቻ ሳይሆን ለወገኖቼም ጭምር! 2008 ዓ.ም ክረምት!
በሲሳይ ዘለቀ


ከ ሁለት ወር በፊት….
ሲጥርና ሲግር የዋለው አብዛኛው የአዲስ አበባ ህዝብ ወደቤቱ መግቢያ ሰዓት በመድረሱ የተነሳ እንደተለመደው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን ፈጣጥሞ ወደየመስመሩ እየተጣደፈ ነው፡፡ እኔም ሜክሲኮ አካባቢ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር አብረን ምሳ በልተን ዘና ስንል ከዋልን በኋላ ወደ 11፡00 ገደማ ቦሌ ሳይ ኬክ ቤት የቀጠረችኝን ሌላኛዋን ጓደኛዬ ቤቲን ለማግኘት ቡናና ሻይ ተሻግሮ የቦሌ ታክሲ ሰልፍ ላይ ነበርኩ፤ ያው የክረምት መግቢያ ወቅት በመሆኑ ካፊያ እያካፋ ሲሆን ሰማዩም ያለሰዓቱ ጠቋቁሯል፤ የእግረኛው መንገድ ላይ ህዝቤ ወዲያ ወዲህ ሲራወጥ አስፓልቱ ላይ ደግሞ ተሽከርካሪዎች ይተራመሳሉ፤ እኔ በተሰለፍኩበት በኩልም ታክሲዎች፣ ፐብሊክ ባሶች፣ የከተማ አውቶቡሶች፣ በየተራ ይመጣሉ፣ ሰው ያወርዳሉ፣ ሰው ይጭናሉ፣ ደግሞም ይሄዳሉ፡፡ በከፍታ የተንጠለጠለ መንገድ ላይ ባቡር ነኝ የሚል ባቡር መሳይ ባቡር ልክ እንደ አዲካ ሊመውዚን ጥቂት ሰዎች ጭኖ ሲጎተት ይታያል፤ እውነቱን ለመናገር ረጅም የታክሲ ሰልፍ የተሰለፍነውን ሰዎች እንቁልልጬ የሚል ይመስላል፤ እኔም ይኸው የተራዘመው የማትሪክ ፈተና እስኪደርስ ድረስ ባገኘሁት አጋጣሚ ጓደኞቼ ጋር እየተጎተትኩ አየር እቀበላለው፡፡ ይህንንም ክረምት ዩኒቨርሲቲ ከመግባቴ በፊት እንደልቤ ጓደኞቼ ጋር በመዞር፤ የተለያዩ ቦታዎች በመሄድ፤ በመዝናናት፤ ፌስቡክ መጣጥፎችን ለተከታታዮቼ በመፃፍ ለማሳለፍ ወስኛለው፡፡ ካፊያው ጠንከር እያለ ሲመጣ ጃንጥላ ለማውጣት ቦርሳዬን ስከፍተው ስልኬ እየጠራ ነበር፣ ቤቲ ነች፤ ከመዝጋቱ በፊት አነሳሁት፡-
‹ሄሎ› አልኳት
‹አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው ስልክ የማታነሽው?› ብላ ጮኸችብኝ
‹አረ አይደለም አትጩኺ በናትሽ ስላልሰማሁት ነው ቦርሳዬ ውስጥ ነበር ለዛ ነው› አልኳት ለማረጋጋት
‹ባንቺ ቤት መሸወድሽ ነው? ይሄኔ አንዱ የፌስቡክ ደንበኛሽ እየተጋተተሸ ይሆናል ኪኪኪኪኪ…› ብላ ሳቀችብኝ
‹አረ በፈጠረሽ እኔ ለራሴ ታክሲ ተሰልፌ ወረፋ ሊደርሰኝ አልቻለም…›
‹ምን? ገና ታክሲ ውስጥ አልገባሽም ሃና? ምን ሆነሻል ሰዓቱን አይተሽዋል? እኔን ጎልተሸ አንቺ እስካሁን ታክሲ አልተሳፈርሽም?›
‹አረ አትጩሂ ባክሽ ለራሴ ካፊያ እየደበደበኝ ነው በዛ ላይ ብርዱ፤ አንቺ ቢያንስ ካፌ ውስጥ ነሽ በቃ አሁን ልገባ ነው ደርሳለው ቤቲዬ› አልኳት
‹ምን ትደርሻለሽ ለራስሽ ዘመደ ብዙ ነሽ ይሄኔ አንዱ ጋር ነሽ እንጂ… ደሞ አምሽተሸ መጥተሽ እንደለመደብሽ አቃቂ ነው የምገባው ልሂድ ምናምን እንዳትዪ…›
‹አንቺ ያምሻል እንዴ? እንዴት ነው አንቺን ቀጥሬ ሌላ ሰው ጋር የምሄደው?›
‹ማን ያውቃል ትዝ ይልሻል አንዴ ስልክሽን አጥፍተሸ ጉድ የሰራሽኝ…›
‹ውይ በቃሽ በናትሽ፣ ይቅርታ ጠይቄሽ ታረቅን አይደል አሁን እሱን ማንሳት ምን ይጠቅምሻል? አሁን ለማንኛውም ታክሲ ውስጥ ልገባ ነው ቤቲ መጣው፤ ቻውቻው፤›
ብዬ ስልኩን ዘግቼ ወደቦርሳዬ ላስገባው ስል ባላሰብኩት ቅፅበት ከየት አቅጣጫ እንደመጣ ያላየሁት ጎረምሳ እጄን በኀይል መትቶኝ ስልኬን ከመውደቁ በፊት ቀልቦት እግሬ አውጪኝ ብሎ በገነት ሆቴል አቅጣጫ ሲፈተለክ ጩኸቴን አቀለጥኩት! አጠገቤ የነበሩት ሁለት ወጣቶች ያዙት! ያዙት! እያሉ ጥቂት ተከተሉት፣ አስፓልቱን ተሻግሮ ቆመው የነበሩ ሁለት ፖሊሶች ከነቆመጣቸው መኪኖችን እያስቆሙ ተሻግረው ሊከተሉት ሞከሩ፤ ነገር ግን አሯሯጡ ከአቅም በላይ ሆኖባቸው ሊደርሱበት አልቻሉም፤ ተስፋ ቆርጠውም ወደኔ ተመለሱ፤
‹ከማነው የወሰደው?› በማለት አንደኛው ፖሊስ ጠየቀኝ፤
‹ከኔ ነው፤ከኔ› ትንፋሼ ቁርጥ ቁርጥ እያለ
‹ሞባይል ብቻ ነው የወሰደብሽ? ወይስ ሌላም ነገር አለ?› ሁለተኛው ፖሊስ ጠየቀ፤
‹አዎ ሞባይል ብቻ ነው…›
‹በቃ ጣብያ እንሂድና ቃልሽን ስጪ›
ብዙ ሰዎች ከበውኝ ነበር ለካ ድንጋጤዬ ለቆኝ ከመሃላቸው ስወጣ ነው የታወቀኝ፤ አንዳንዶቹ አይዞሽ ተረጋጊ እያሉ ሊያረጋጉኝ ሞከሩ፤ ዳር ላይ ቆመው የተፈጠረውን ነገር ሁሉ በአርምሞ ይመለከቱ የነበሩ አንድ ልብሰ-አካላቸው የተጎሳቆሉ ደካማ አዛውንት ግን ጠጋ አሉኝና በደከመ ድምፃቸው ‹ልጄ! ልጄ ግዴለም እግዚአብሔር ሁሉን ነገር ያለምክንያት አይከውንም፤ ሁሉም ነገር ለበጎ ነውና ተዪው! አዎ እርግፍ አርገሽ ተዪው! አንቺም በሰላም እንደወጣሽ በሰላም ግቢ፤ ከአካልሽ የቆረሰው፣ ከልቦናሽ የሰወረው አንዳች የለም፤ ኋላስ ቢሆን ሰው ሰርቶ የሰጠሽን ሰው ወሰደው እንጂ…› ብለው ከመጨረሳቸው በፊት ‹ምን ሆነዋል እርስዎ ደግሞ! ለበጎ ነው ይሉኛል እንዴ? እስከዚህም ነጥቆኝ እንጂ ሰጥቶኝ እኮ አልሄደም!› አልኳቸው በቁጣ፤ ‹ተይ እንጂ አንቺ አባትሽ ይሆናሉ እኮ…› አንዷ ሴትዮ ቀጠለች፤ ፖሊሶቹም ‹ነይ በቃ እንሂድ› ሲሉ የታክሲ አስከባሪውም ‹በቃ ተበተኑ! ተበተኑ! ዳይ ሼባው በቃ ላሽ በል፤ ምክርህ አይነፋም› ሲል ጥቂቶቹ እየተሳሳቁ ሄዱ፤ የአዛውንቱ ሰውዬ አይን ግን እስከተወሰነ መንገድ በስስት ሲከተለኝ እመለከት ነበር፤ ነገር ግን ለምን እንደሚመለከቱኝ ፈፅሞ አልገባኝም፣ እኔም ቦታ ሳልሰጣቸው ከፖሊሶቹ ጋር ወደ ጣብያ ተጓዝን፡፡
ከፖሊሶቹ ጋር ተያይዘን እዛው አካባቢ ካለ ጣብያ ገብተን ቃሌን እና የእቴቴን ስልክ ሰጥቼ ወጣው፤ ቀኑ መሽቷል፤ ሰዓት ስጠይቅ 12፡25 ሆኗል፤ ከዚህ በኋላ ቤቲ ጋር መሄድ አልችልም ምክንያቱም አቃቂ ነው የምገባው፤ ስልክ እንዳልደውልላት ስልኳን በቃሌ አላውቀውም፤ ስለዚህ ቀጥታ ወደለገሃር ጫፍ ተጉዤ የቃሊቲን ታክሲ ለመሳፈር ወሰንኩ፡፡
ቤት እንደገባው ከፍተኛ እልህና ንዴት ተናንቆኝ ነበር፤ ከምንም ነገር በላይ እነዛ ሁሉ ስልክ ቁጥሮች፤ መልዕክቶች፤ ሁሉም ገደል ገቡ በቃ! በጣት ከሚቆጠሩ ጓደኞቼ ውጪ የማንንም ስልክ በቃሌ አላውቅም! እቴቴ ክፍሌ ድረስ መጥታ ‹ምን ሆነሻል ዛሬ ለምንድነው እራት የማትበዪው?› አለችኝ፤ ‹ተዪኝ ባክሽ እቴቴ እናንተ ብሉ እኔ ማረፍ እፈልጋለው› ብያት በሬን ዘግቼ ተኛሁ፡፡
እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ እንቅልፍ ሊወስደኝ አልቻለም፤ ተነስቼ የእናቴን ስልክ አምጥቼ ወደስልኬ ደወልኩ ‹የደወሉላቸው ደንበኛ ስልክ ለጊዜው ጥሪ አይቀበልም…› ስልኩን መለስኩትና ወደ አልጋዬ ተመለስኩ፤ እቴቴ የገዛችልኝን የግል ማስታወሻዬን አውጥቼ የገጠመኝን ልፅፍ አሰብኩና በእንደዚህ አይነት መጥፎ አጋጣሚ የሚጀምር ፅሁፍ አዲሱ የግል ማስታወሻዬ ላይ መፃፌ ስላልተዋጠልኝ ተውኩትና መልሼ ጋደም አልኩ፤ ደክሞኝ ስለነበር መብራት አጥፍቼ ለመተኛት ሞከርኩ፡፡
ከነበርኩበት ክፍል ወጥቼ በሬ ላይ ቆምኩ፤ ጨለማ በመሆኑ የተነሳ ምንም የሚታይ ነገር የለም፤ ለጥቂት ደቂቃ በተመስጦ አካባቢዬን ስመለከት ቆይቼ ፊት ለፊት በርቀት ላይ በትንሹ የምታበራ አነስተኛ ነገር ተመለከትኩ፤ ከዛ ሁሉ ድቅድቅ ጨለማ ይህች የብርሃን ቅንጣት ጎልታ ታየችኝ፤ ልቦናዬን አሰባስቤ በትኩረት ስመለከታት ወደኔ ስትቀርብ መጠኗ እየጨመረ መጣ፤ ግን ምን እንደሆነች ለማወቅ ስለጓጓው ከቆምኩበት በረንዳ ላይ ወርጄ ወደ እሷ ቀስ ብዬ መራመድ ጀመርኩ፤ ወደ እርሷ በቀረብኩ ቁጥር እያደገች መጣች፤ ብርሃኗም እየጨመረ ሲመጣ ታየኝ፤ በሂደትም ብርሃኗ አካባቢውን በብርሃን ስለሞላው ያለሁበትን ሰፈር በግልፅ ማየት ቻልኩ፤ መጨረሻው የማይታይ ቀጥ ያለ መንገድ መሃል ቆሜያለው፤ መንገዱም የተሰራው በነጭ የጠጠር ንጣፍ ሲሆን በግራና በቀኝ የተለያዩ ሕብረ ቀለማትን የሚተፋ ጭስ መሳይ አጥር ይታያል፤ ቀና ብዬ ሰማዩን ስመለከት በተለያዩ ቀለማት ስለተዋበ ልቤን ማረከኝ፤ አይኔን ወደምታበራው ነገር ስመልስ ግን ያልጠበኩት ነገር ገጠመኝ፤ አንዲት በግምት እድሜዋ የሰባት አመት ህፃን የሆነች ልጅ ነች፤ የለበሰችው የሀበሻ ቀሚስ በነፋሻው አየር በመጠኑ እየተውለበለበ እንደ እንፋሎት ያለ ብርሃን ይተፋል፤ ማንነቷን ለመለየት ወደሷ ቀስ ብዬ ለመቅረብ ሞከርኩ፤ ጀርባዋን ሰጥታኝ ቆማለች፤ ባዶ እግሯን ነች፤ ከተረከዟ ስር ደም ይፈሳል፤ መልኳ አይታይም፤ መልኳን ለማየት ከመጓጓቴ የተነሳ ወደሷ ተራመድኩ፤ ነገር ግን ስቀርባት ትሸሸኛለችና ልደርስባት አልቻልኩም፤ ቆምኩኝና ዝም ብዬ አየኋት፤ እንዲህም ብላ ተናገረችኝ፡-
(ይቀጥላል…)


No comments:

Post a Comment