Saturday, August 27, 2016

ምዕራብ በለሳ ወረዳ በሕዝብ ቁጥጥር ሥር ውሏል፤የዐማራ ሕዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተጋድሎውን ተቀላቅሏል


የቋሪት ዐማሮች አስደናቂ ገድል ፈጸሙ፣ የዐማራ ሕዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተጋድሎውን ተቀላቅሏል
• ምዕራብ በለሳ ወረዳ በሕዝብ ቁጥጥር ሥር ውሏል፤ ገበሬው ወደ ወልቃይት ለመዝመት የጎበዝ አለቆችን እየጠየቀ ነው
• በጃቢ ጠናን ከ10 በላይ ቀበሌዎች የዐማራ ተጋድሎ ተቀጣጥሏል
• በባሕር ዳርና በደብረታቦር ከነሃሴ 22 እስከ 24 የቤት ውስጥ አድማ ይደረጋል፤ በደብረ ታቦር መንግሥት ፈርሷል እየተባለ ነው
ደንበጫ/ የጨረቃ፤ በደንበጫ ወረዳ በደንበጫ፣ በየጨረቃና በሌሎች ከተሞችም የዐማራ ተጋድሎ ዛሬ ቀጥሎ ውሏል፡፡ ‹‹ወልቃይት የዐማራ ነው፤ የወያኔ ኑሮ ይለያል ዘንድሮ፣ ኮሎኔል ደመቀና የወልቃይት ጠገዴ የዐማራ ማንነት አቅራቢ ኮሚቴዎች በአስቸኳይ ይፈቱ፣ ዐማራነት ወንጀል አይደለም…›› የሚሉ መፈክሮች ሲሰሙ ውለዋል፡፡ የዐማራ ተጋድለ ጠዋት 2፡30 የተጀመረ ሲሆን ይህ ዝግጅት እስከተጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ ተጋድሎው መቀጠሉን ሰምተናል፡፡ የደንበጫና የጨረቃ ከተማ የዐማራ ተጋድሎ ሰላማዊ በሆነ መልኩ ተጀምሮ መጠናቀቁንም ሰምተናል፡፡ ከቦታው መረጃውን ያቀበሉን ሰዎች እንደሚሉት ምንም ዓይነት ንብረት እንዳይወድም የጎበዝ አለቆች ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል ብለዋል፡፡ የወረዳዋ ካቢኔዎች ከተማዎቹን ለቀው የጠፉ ሲሆን እስከ ምሽት ድረስም የወያኔ ባንዲራ ያለባቸው ቢሮዎች ባባቶቻችን ደም የተመሠረተችው ሰንደቅ ዓላማ ተተክታለች፡፡ በደበንበጫ ከተማ ከ30 ሺህ በላይ ዐማሮች የተጋድሎ ሰልፉን ተቀላቅለውታል፡፡
እንደመረጃ አቀባዮቻችን ከሆነ በደንበጫ ማንኛውም የወያኔ ኃይል ምንም ዓይነት ጣልቃ እንዲገባ አልተፈቀደለትም፤ ፖሊስና ምኒሻም ከሕዝብ ጋር ቆሟል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አንድ የወያኔ ባንዳ የነበረ ከደንበጫ ከተማ ወጣ ብሎ ያለ የኪዳነ ምሕረት አካባቢ ቀበሌ ሊቀ መንበር ቤት ብቻ ተሰብሯል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ከሰአት በኋላ መጠነኛ ተኩስ ቢኖርም በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት የለም፡፡ ሆኖም ምሽቱን ወጣቶችን የሚያስሩ ነገ እንደምናስፈታቸው እርግጠኞች ነን ብለውናል፡፡
የአማኑኤል ከተማም የዐማራ ተጋድሎ እንዳለ የሰማን ቢሆንም በቂ መረጃ ማሰባሰብ አልቻልንም፡፡
ጃቢ ጠናን/ ብር ሸለቆ፤ በጃቢጠናን ወረዳ ያሉ አብዛኛዎቹ የገጠር ቀበሌዎች ለዐማራ ተጋድሎ ሰልፍ ወጥተዋል፡፡ ዛሬ በብር ሸለቆ ከተማ የተጀመረው የዐማራ ተጋድሎ እርግብ፤ ወይንማ ወርቅማ፣ አዲስ ዓለም እና ሌሎች ከዐሥር የሚልቁ የገጠር ቀበሌዎች ላይ ተጋድሎው ተፋፍሞ ውሏል፡፡ ጃቢ ጠናን ወረዳ አብዛኛው በዐማራ ሕዝብ በራሱ ቁጥጥር ሥር መዋሉን ነው ለማወቅ የቻልነው፡፡ በሁሉም የዐማራ አካባቢዎች እንዳለው ሁሉ በጃቢ ጠናን የገጠር ቀበሌዎችም የዐማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ሲስተጋቡ ውለዋል፡፡ የብርሸለቆ ከተማ የወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያው አካባቢ ቢሆንም የጎጃምን ገበሬ የደፈረ ሠራዊት ግን እንዳልነበረ ለማወቅ ችለናል፡፡ ከብር ሸለቆ ከተማ በስልክ ያናገርናቸው ሰዎች እንደሚገልጹት አንዳንድ ተላላኪ ባንዳዎች ሰልፍ ያስተባብራሉ የሚባሉ ሰዎችን መዝግበው ለወታደሮች መስጠታቸውን ገልጸው የእኛን ጎበዝ አለቆች እንወስዳለን ብሎ የሚመጣ ማንኛውም ኃይል ከእኛ ነጥቆ ከወሰዳቸውማ ምንኑን የበላይ ዘለቀ ልጆች ሆንን ሲሉ በስሜት ተናግረዋል፡፡
ቡሬ፣ በቡሬ ከተማ ትናንት የተጀመረው የዐማራ ተጋድሎ ዛሬም ቀጥሎ መዋሉን ሰምተናል፡፡ እስከ እኩለ ቀን ድረስ ወጣቶች የዐማራን ሕዝብ ጥያቄዎች ሲያሰሙ ውለዋል፡፡ እኩለ ቀን አካባቢ የተወሰነ የጥይት ድምጽ ቢኖርም በሕይወት ላይ የደረሰ ጥፋት እንደሌለ ሰምተናል፡፡
ቋሪት፤ የቋሪት ዐማሮች አስደናቂ ገደል ፈጸሙ፡፡ በቋሪት ወረዳ የገበዘ ማርያም እና የገነት አቦ ከተማ ነዋዎች ዛሬም የዐማራ ተጋድሎን ለሦስተኛ ቀን ቀጥለው የዋሉ ሲሆን ማንኛውም የወረዳዋ እንቅስቃሴ በሕዝቡ ቁጥጥር ሥር እንደዋለ ነው፡፡ የቋሪት ዐማሮች ሌላው የፈጸሙት ገደል የወያኔ ተላላኪ ቅጥረኛ ካቢኔዎችንና የወረዳውን አስተዳዳሪ በመያዝ የወያኔን ባንዲራ ካቢኔዎቹ በየመሥሪያ ቤታቸው አውርደው የአባቶቻችን ሰንደቅ ዓላማ እንዲሰቅሉ ተገደዋል፡፡ የንግድ ባንክ ሥራ አስኪያጅም ተገዶ የወያኔን ባንዲራ በማውረድ ሰንደቅ ዓላማችን ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ሰቅሏል፡፡
ገዥው መንግሥት ያሰማራቸውን የጸጥታ አካላት በሙሉ ከከተማዋ አባረው አስወጥተዋል፡፡ ከፖሊስ ጣቢያው ፊት ለፊት ባለው አደባባይ ላይ ጉድጓድ ተቆፍሮ የሰንደቅ ዓላማ መስቀያ እንጨት ተተከለ፡፡ ከዚያም በታላቅ ደስታና እልልታ የአባቶቻችን ደም ያለባት ሰንደቃችን ተውለበለበች፡፡ ማንም ጀግና የሆነ ከቋሪት ምድር ያችን ሰንደቅ የሚያወርድ የለም ተብሏል፡፡
በቋሪት ዛሬ በዋለው ሰልፍ ወጣቶች የዐማራን የተጋድሎ ጥያቄዎች ሲያስተጋቡ ጎልማሳዎች ደግሞ ከፍተኛ ትጥቅ እና ጥይት በመያዝ በፉከራና በሽለላ የአርበኝነት ዘመንን ሲያወድሱ ውለዋል፡፡ ፖሊሶችም ተገደው ጥይይት እንዲተኩሱ ይደረግ ነበር፡፡ ሆኖም አሁን ላይ ምንም ዓይነት የመንግሥት ተወካይ በወረዳው እንደሌለ ነው የተነገረው፡፡
አዴት፤ የይልማና ዴንሳዋ መናገሻ አዴት ከተማ ውጥረት ላይ መሆኗን ሰምተናል፡፡ የዐማራ ተጋድሎ ይቀሰቀሳል በሚል ስጋት ገበሬዎች ወደ አዴት ከተማ እንዳይገቡ መከልከላቸውን ከአካባቢው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ የጎንች ቆለላ ወረዳም እንዳዴት ሁሉ ገበሬዎች ወደ ከተማ እንዳይቡ መደረገቸው ታውቋል፡፡
ባሕር ዳር/ደብረ ታበር፤ ባሕር ዳር እና ደብረ ታቦር ከተሞች ከነገ ነሃሴ 22 እስከ 25 ቀን 2008 ዓ.ም. የቤት ውስጥ አድማ ይደረጋል፡፡ በባሕር ዳር ለአገዛዙ የሚያግዙ የባጃጅ ተሸከርካሪዎች ታርጋ ቁጥር ተለይቷል፡፡ ስለሆንም ከነገ ጀምሮ ማናቸውም ሥራ እና እንቅስቃሴ ዝግ የሚሆን ሲሆን ይህን ህግ ተላልፎ የሚገኝ ሰው የዐማራ ሕዝብ ጠላት እንደሆነ ይቆጠራል ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል በደብረ ታቦር ከተማ ከነገ ጀምሮ ለ3 ቀን የሚቆይ የቤት ውስጥ አድማ የሚኖር ሲሆን አድማውን የሚተላለፉ ግለሰቦችንና ቡድኖች የሚቀጣ የጎበዝ አለቃ ቡድን ተቋቁሟል፡፡ በደብረ ታቦርና በፋርጣ አካባቢዎች ‹‹መንግሥት ፈርሷል›› በመባሉ የአካባቢ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ሕግ ማስጠበቅ ባለመቻላቸው የጎበዝ አለቆች ሕግ እያስከበሩ እንደሆነ ገልጸውልናል፡፡ ዛሬ ማምሻውን የስርዓቱ ቅጥረኛ ባለሥልጣናት ነገ አገልግሎት መስጫ ተቋማት እንዳይዘጉ የሚሉ ማስታዎቂያዊችን ሲለጥፉ ውለዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የጎንደር ከተማ የቤት ውስጥ አድማ ዛሬም ተጠናክሮ መቀጠሉን ሰምተናል፡፡
አርባያ፤ ሰሜን ጎንደር ዞን የምዕራብ በለሳ ወረዳ ያገኘነው መረጃ አጃኢብ አስብሎናል፡፡ በምዕራብ አርባያ ወረዳ መንግሥት ፈርሷል፡፡ የአርባያ ከተማና የምዕራብ በለሳ ዐማሮች ዛሬ ተጋድሏቸውን የተቀላቀሉ ሲሆን ‹‹በወታደር አንገዛም፣ ሥርዓቱ አያስፈልገንም፣ የአንድ ብሔር የበላይነት ከዚህ በኋላ አይኖርም፤ ወልቃይት የዐማራ ነው ..›› የመሳሰሉ ጥያቄዎች ሲስተጋቡ ውለዋል፡፡
በከተማዋ በመለስ ስም የተሰየመው ትምህርት ቤት ስሙ ተቀይሮ በአጼ ቴዎድሮስ ስም ተሰይሟል፡፡ የምዕራብ አርባያ ወረዳ የዐማራን ተጋድሎ ለመደፍጠጥ የ2.4 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ 144 ቡችሌ የሚባሉ የአገዛዙ ባሪያ ወታደሮችን አሰልጥኖ ነበር፡፡ ሆኖም እነዚህን ቡችሌዎች ከከተማዋ ጠራርጎ አስወጥቶ አካባቢው ሙሉ በሙሉ በሕዝብ ቁጥጥር ስር ሆኗል፡፡
ዛሬ ምሽቱን ከቦታው የገኘናቸው ሰዎች እንደሚሉት ‹‹በእኛ አገር መንግስት ፈርሷል፤ ራሳችን በራሳችን ነው የምናስተዳድረው›› ብለውናል፡፡ ገበሬው ግብር ለማንም ከዚህ በኋላ ላለመክፈል ያቀደ ሲሆን እርሻችን ጨርሰን ወደ ወልቃይት እንድንዘምት የጎበዝ አለቆች ምሩን እያሉ እንደሆነ ነው የሰማነው፡፡
የመከላከያ ሠራዊት አልመጣም ወይ ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ ‹‹መከላከያ እንዲመጣ በናፍቆት እየጠበቅን ነው፤ የመሳሪያ ችግራችን በምርኮ እናማላ ነበር›› ሲሉ በወኔ ተናግረዋል፡፡ በአርበኝነት ዘመን አባት አርበኞቻችን መሳሪያ የሚያገኙት ከባንዳዎችና ከጠላት ላይ በመማረክ መሆኑን ጭምር ነው ያስረዱን፡፡ ትናንት ምሽት አንድ ቅጥረኛ ቡችሌ ከመገደሉ ውጭ ምንም ዓይነት በሰውም ሆነ በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት የለም ብለዋል፡፡ ሕብረተሰቡም ለሕዝብ ንብረቶች ጥበቃ እንደሚያደርግ ጭምር ገልጸዋል፡፡
የዐማራ ተጋድሎ ያሸንፋል//
ይህ ሁሉ የመጨረሻው መጀመሪያ ነው!!

No comments:

Post a Comment