Wednesday, June 1, 2016

ብፁዕ አባታችን ወደ ችሎት ሲሄዱ እግረ መንገድዎን ቤተ-ክርስቲያን ጎራ ይበሉ” (ያሬድ ሹመቴ)


“ብፁዕ አባታችን ወደ ችሎት ሲሄዱ እግረ መንገድዎን ቤተ-ክርስቲያን ጎራ ይበሉ”
(ያሬድ ሹመቴ)
ሰሞኑን መነጋገሪያ ከሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች መሀል የብፁዕ አባታችን አቡነ ማቲያስ የሰንደቅ ጋዜጣ አዘጋጅ ፍሬው አበበን በወንጀል ከሰው በፍትሀ ብሄር ደግሞ 100 ሺ ብር ካሳ መጠየቃቸው ጉዳይ ነው።
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት “ፓትሪያሪኩ ለኢትዮጵያ የደህንነት ስጋት፥ ለምዕመናን የድህነት ስጋት” በሚል ርዕስ የፃፈውን “የፓትርያሪኩን ክብር ያጎድፋል” ያሉትን ጽሁፍ አትመሀል በማለት ነው “ብፁዕነታቸው” ክስ የመሰረቱት።
ለብፁዕ አባታችን “ውሀ ሽቅብ ፈሰሰ” ይሉት አይነት ድፍረት ውስጥ ሆኜ መምከር ተመኘሁ።
ከአራት መቶ አመታት በፊት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸው የአፄ ፋሲል አባት የሆኑት አፄ ሱስንዮስን ዜና መዋዕል ላይ ሳነብ ያገኘሁን ሀሳብ በመጥቀስ እጀምራለሁ።
አፄ ሱስንዮስ በንግስና መንበራቸው በትረ መንግስቱን ጨብጠው ቅብዓ ንግስናው ሲቀራቸው በየቦታው የሚነሳባቸውን የዙፋን ተቀናቃኝ እየተዋጉ በማሸነፍ የጦረኛ ልባቸው ጫፍ በደረሰበት ወቅት፥ “ወረኛ” አላስቀምጥ አላቸው። እንግዲህ ሀሜተኛው እና አድመኛው ለስልጣናቸው መርጋት ትልቁ ፈተና ነው ብለው በማመናቸው አድማው ወደ በረታባቸው ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ “ክተት ሰራዊት” ብለው ጳጳሳቸውን አባ ስምዖንን አስከትለው ወደ ትግራይ ዘመቱ።
መንገዳቸውንም በዳባት፥ በደባርቅ አድርገው ሊማሊሞን ወርደው ዋልድባ ገዳም ደረሱ። እግረ መንገዳቸውንም የመናንያን አምባ ወደሆነው የዋልድባ ገዳም ዘለቁ።
መጽሀፉ ቃል በቃ እንደሚለውም “በዚያም ከባህታዊያኑና በትሕርምት (በጾም፥ በተዓቅቦ፥ በቱሩፋት ህግ፥ በአምልኮ፥ ገንዘብን ራስን ለእግዚአብሔር በመለየት፥ በመቀደስ፥ ሰውነትን ከሚገ[ነ]ባ ነገር በመከልከል) ከሚኖሩት ግሑሳን (መናኒ፥ ከአለም ስራ የተለየ ይለዋል ትርጓሜው) መነኮሳት ጋር ተገናኘ፥ እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ በተሞላ ሰላምታ እጅ ነሡት። (ለንጉስ) በሚገባ በረከትም ባረኩት።”
ለፀብ ሲገሰግሱ ጳጳስ አስከትለው የዘመቱት አፄ ሱስንዮስ “ዋልድባን አላልፍም” ብለው ከገዳሙ ዘልቀው በመግባት ሲሰነብቱ፥ በድል ብዛት ያበጠው ልባቸው በመንፈሳዊነት ጎበጠ። ትዕቢታቸውም ተነፈሰ። ከዚያም ወጥተው፥ በሽሬ አልፈው አክሱምም ሲደርሱ፥ ወረኛ ያሉትን እያስመነጠሩ መቅጣታቸውን ትተው እንደ አያት ቅድም አያቶቻቸው በአክሱም ጽዮን ስርዓተ ንግስናቸውን ቅብዓ መንግስቱን ቅርጸቱን (በሲመቱ ጊዜ የሚደረግ የፀጉር አቆራረጥ ስርዓት) አድርገው በአስከተሏቸው ጳጳስ አባ ስምዖን እጅ ንግስናቸውን ተቀበሉ።
በምድራዊው እልህ እና የአጉል አልሸነፍ ባይነት መንፈስ ይህ ሲመት አልተገኘም። እግረ መንገዳቸውን የገጠሟቸው የዋልድባ ገዳም መንፈሳዊ አባቶች የመንፈስ ጥንካሬ አውርሰው አክሱም ጽዮን ስላደረሷቸው እንጂ።
ብፁዕ አባታችን በስጋዊ የልብ እብጠት መንፈሳዊነት አይመራምና ወደ ፍርድ ቤት በሚወስደው መንገድ ካለ ገዳም ወይንም ደብር ጎራ ብለው ትንሽ ቢቆዩ መልካም ነው።
የአስታራቂነት እና የገላጋይነት ሚና ያለው “መንፈሳዊ አባትነት” ወደ ከሳሽና ወንጃይነት፥ የመቀየሩ ምስጢር ከመንፈሳዊ አስተሳሰብ እና አኗኗር የራቀ አለማዊ ህይወትን ማዘውተር ነውና ብፁዕ አባታችን ወደ ችሎት ሲሄዱ እግረ መንገድዎን ወደ ቤተ-ክርስቲያን ጎራ ይበሉ።
።።።።።
አምላካችን ሀገራችንን እና ቤተ-ክርስቲያናችንን ይጠብቅልን!!

No comments:

Post a Comment